Monday, 03 February 2020 11:24

በሀረርና አካባቢያዋ ያሉ ከተሞች በአድማ ላይ ሰንብተዋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  መንግስት በምዕራብ ኦሮሚያ  በንፁሃን ዜጐች ላይ ያልተገባ እርምጃ ወስዷል በሚል በሀረር ከተማና በአካባቢዋ ባሉ አወዳይ፣ ሂርና እና ሌሎች ከተሞች ከረቡዕ ጀምሮ እስከ ትናንት በቤት ውስጥ የመዋል አድማ ሲካሄድ ሰንብቷል::
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በምዕራብ ኦሮሚያ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን የገለፀ ሲሆን መንግስት በበኩሉ፤ በአካባቢው ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ቡድን ላይ የመደምሰስ እርምጃ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በሐረር ከተማ የጀመረው የቤት ውስጥ መዋል አድማው፤ በነጋታው የቀጠለ ሲሆን በከተማዋና አቅራቢያዋ ባሉ ከተሞች የሚገኙ የንግድ መደብሮች፣ ሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዝግ ሆነው መሰንበታቸውን ምንጮች ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል፡፡
ከሐረር ወደ ድሬደዋ የሚወስደው ዋናው መንገድም በድንጋይና በእንጨት ተዘግቶ ረቡዕ እለት ከእንቅስቃሴ ተገትቶ የነበረ ቢሆንም የፀጥታ ሃይሎች ምሽት ላይ መንገዱን ማስከፈታቸው ታውቋል፡፡
የአድማው ዋነኛ ምክንያት በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ መንግስት በዜጐች ላይ ያልተገባ ጥቃት እየፈፀመ ነው፤ ጥቃቱ ይቁም በአካባቢው ያለው ኮማንድ ፖስት ይነሳ የሚል” ነው ብለዋል - ምንጮች፡፡
በምዕራብ ወለጋ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘ አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ባወጣው መግለጫ፤ በአካባቢው ያለው ሁኔታ በእጅጉ አስጨናቂ መሆኑን ገልጿል፡፡
አምነስቲ በሪፖርቱ፤ 75 ያህል ሰዎች ኦነግን ትደግፋላችሁ ተብለው በአካባቢው መታሠራቸውን ጠቁሞ፤ ይህም እስር ለሀገሪቱ የለውጥ ሂደት ስኬት ጥሩ ምልክት አለመሆኑን ገልጿል፡፡
መንግሥትም ከእንደዚህ አይነት እርምጃዎች እንዲቆጠብም ተቋሙ  አሳስቧል፡፡
መንግስት በበኩሉ፤ በምዕራብ ወለጋ በማህበረሰቡ ላይ እገታ በሚፈጽሙ የታጠቁ ቡድኖች ላይ እርምጃ መውሰዱን፣ በዚህ እርምጃም ቀላል የማይባል ሃይል መደምሰሱንና አሁንም ተበታትኖ የሚገኝ ተጨማሪ ሃይል ላይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Read 1078 times