Monday, 03 February 2020 11:23

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል 70 ሚ. ዶላር ያስፈልጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

    ግማሽ ሚሊዮን አንበጦች በየቀኑ የ2500 ሰዎችን የእለት ጉርስ እየነጠቁ ነው

            በምሥራቅ አፍሪካ አገራት የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በአጠቃላይ 70 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ኦክስፋም ያስታወቀ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት አደጋ መከላከል የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በዋናነት በኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሶማሊያ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ፣ ባለፈው ሰኔ ወር ከታየው በ5 በመቶ እጥፍ መከሰቱንና ቋሚ ሰብሎችና የግጦሽ መሬቶችን እያጠቃ መሆኑን የገለፀው ኦክስፋም፤ ይህን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የአለም መንግሥታት የ70 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያና ቡሩንዲ 25.5 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብና በእርዛት ውስጥ ይገኛሉ ያለው ሪፖርት፤ ለዚህ ችግር መባባስ ድርቅና የጎርፍ አደጋ ካስከተለው ጉዳት በተጨማሪ የአንበጣ መንጋ ወረራ ያስከተለው ችግር የላቀውን ድርሻ ይይዛል ብሏል፡፡
በእነዚህ አገራት የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ አሁንም በፍጥነት መቆጣጠር ካልተቻለ ከመጋቢት እስከ ሐምሌ ባለው የበልግ ወቅት አገራቱ የምግብ ሰብል ለማምረት እንደሚቸገሩ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2015 ጀምሮ ኢትዮጵያ በየአመቱ በድርቅ እየተጠቃች እስከ ዛሬ መቆየቷን ያወሳው ሪፖርቱ፤ ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ በአገሪቱ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ በተለይ በአማራና ትግራይ ክልሎች በሰብሎች ላይ ውድመት ማድረሱንና በአሁኑ ወቅትም በአትክልትና ፍራፍሬ ቡቃዮች ላይ ጉዳት ማድረስ መቀጠሉን አስገንዝቧል፡፡
በአንድ የአንበጣ መንጋ ውስጥ እስከ 150 ሚሊዮን የሚደርሱ አንበጣዎች እንደሚገኙ የጠቆመው የኦክስፋም ሪፖርት፤ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት አንበጣዎች በአንድ ጊዜ አንድ ቶን ያህል ይመገባሉ፣ በዚህም በአንድ ቀን 10 ዝሆኖችና፣ ግመሎች ወይም 2500 ሰዎች ሊመገቡ የሚችሉትን ያህል ይመገባሉ ብሏል፡፡ በየቀኑም ከ2 መቶ ቶን በላይ የአትክልት ቡቃያዎችን እንደሚመገቡ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡   

Read 748 times