Monday, 03 February 2020 11:23

የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

       ኮቢ ብራያንት - The Black Mamba

               “ሁሉም አሉታዊ፣ ተፅእኖ እና ፈተና ለስኬት የምነሳሳበት ዕድል ነው”
               “እኔ መሆን የምፈልገው ኮቢ ብራያንትን ብቻ ነው”
               “የምችለውን ሁሉ አድርጊያለሁ፡፡ ቀጣዩን መንገድ ደግሞ እግዚአብሔር ይመራኛል”

     • 20 ውድድር ዘመናት፤ 57,278 ደቂቃዎች፤ 1345 ጨዋታዎች 33583 ነጥቦች፤ 5 ጊዜ የ NBA ሻምፒዮን፤ 2 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎች
     • በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ ታሪክ 18 ጊዜ የምርጥ ቡድን አባል፤ 15 ጊዜ የሁልጊዜም ምርጥ ቡድን አባል እና 12 ጊዜ የሁሉጊዜም ምርጥ የተከላካይ ቡድን አባል
     • ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንዶችን ያስተዋወቀ፤ ከ680 ሚሊዮን ዶላርበላይ ገቢ ያገኘ


         ኮቢ ቢን ብራያንት በዓለማችን የቅርጫት ኳስ ስፖርት ታሪክ ከፍተኛ ተምሳሌት ለመሆን የበቃ የስኬት ምልክት ነው፡፡ በስፖርቱ ዓለም በተለይ በቅርጫት ኳስ ያስመዘገበው ውጤትና ታሪክ ከምንጊዜም ምርጦች ተርታ ያሰልፈዋል፡፡ አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ኮከብ በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓመት በሞት የተለየው ከሴት ልጁ ጋር ተሳፍሮበት የነበረው የግል ሂሊኮፕተር በካሊፎርኒየ ካለብሳስ ውስጥ ተከስክሶ ከጋየ በኋላ ነው፡፡ በአደጋው ኮቢ ብራይንት፤ የ13 ዓመቷ ሴት ልጁን ጂጂ እና ሌሎች ሰባት ተሳፋሪዎች ህይወታቸው አልፏል፡፡ የኮቢ ብራይንት ድንገተኛ ሞት መላውን ዓለም በተለይ ስፖርት አፍቃሪውን አስደንግጧል፡፡ ሳምንቱ ያለፈውም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ለእሱ በሚቀርቡ የሀዘን መግለጫዎች ነበር፡፡ ኮቢ ቢን ብራይንት በዓለም ስፖርት ታሪክ ተምሳሌት ሆኖ ለመጠቀስ የሚበቃ ጀግና ነው፡፡ የቅርጫት ኳስ ስፖርትን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጐታል፡፡ ዓለም አቀፋዊነት እንዲኖረውም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኮቢ ምርጥ ቅርጫት ኳስ ተጨዋች ብቻ አልነበረም፤ ኢንቨስተር፣ ስራ ፈጣሪ፣ ደራሲ የፊልም ፕሮዱዩሰር እና የማስታወቂያ ሞዴልም ነበር፡፡ የስፖርት አድማስ የታሪክ ማስታወሻ ይህን የዓለማችን ታላቅ የስፖርት ጀግና ከዚህ በታች በቀረቡ አጫጭር እውነታዎች እንዲህ ይዘክረዋል፡፡
“ዘ ብላክ ማምባ”፣ “ሊትል ፍላይንግ ዋርየር”፣ ኬቢ 24፣ ቪኖ፣ ሾውቦት እና ዘ ኤይትዝማን የተጠራባቸው ቅጽል ስሞቹ ናቸው፡፡  “ዘ ብላክ ማምባ” በተለይ የገነነ ቅጽል ስሙ ሲሆን፤ ይህን ስያሜ ያገኘው ከኪውንቲን ታሪንቲኖ ፊልም “ኪልቢል” መሆኑን ባንድ ወቅት ተናግሯል፡፡ በፊልሙ ላይ ማምባ ቀልጣፋና ፈጣን አዳኝ እንስሳን የሚገልጽ ነው፡፡
በተጨዋችነት ዘመኑ አማካይ ክብደቱ 96 ኪ.ግ የነበረ ሲሆን፤ ቁመቱ ደግሞ 1 ሜትር ከ98 ሴ.ሜ ነበር፡፡
በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ታሪክ ባስቆጠራቸው የቅርጫት ኳስ ጐሎች ብዛት ባስገኘው ነጥብ 3ኛ ደረጃ የሚሰጠው ሲሆን 33583 ነጥቦች በስሙ አስመዝግቧል፡፡
በቅርጫት ኳስ ሜዳ ለ57,278 ደቂቃዎች ተጫውቷል
በተጨዋችነት ዘመኑ 1345 የቅርጫት ኳስ ጨዋታዎችን ተሰልፏል፡፡
ባለ 3 ነጥብ የቅርጫት ኳስ ጐሎችን ለ1821 ጊዜያት አስቆጥሯል፡፡
ከ40 በላይ ነጥብ ያስመዘገበባቸው ግጥሚያዎች ብዛት ከ122 በላይ ናቸው፡፡   
በቅርጫት ኳስ ልዩ የሚባለው በሎስ አንጀለስ ሌኮርስ ጨዋታ ላይ የሚዘጋጀው የተመልካች መቀጫ ኮርት ሳይድ (Court side) (entsite) ከሞቱ በኋላ የነበረው የትኬት ዋጋ ከ12875 ዶላር ወደ 50ሺ ዶላር አድጓል
በኤንቤኤ - (NBA) በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ ታሪክ 18 ጊዜ የምርጥ ቡድን አባል፤ 15 ጊዜ የሁልጊዜም ምርጥ ቡድን አባል እና 12 ጊዜ የሁሉጊዜም ምርጥ የተከላካይ ቡድን አባል ሆኗል፡፡
የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሻምፒዮናን የተቀላቀለው በ17 ዓመቱ እ.ኤ.አ 1978 ላይ ነበር፡፡
አባቱ በጣሊያን ፕሮፌሽናል የቅርጫት ኳስ ተጨዋች የነበሩ ሲሆን 13 ዓመቱ ጀምሮ ለ4 ዓመታት በጣሊያን ኖሯል:: ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ ጣልያንኛ እና የስፓኒሽ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል፡፡
2 የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያዎችን ከአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ቡድን ጋር በ2008 እ.ኤ.አ በቤጂንግ እንዲሁም በ2012 እ.ኤ.አ በለንደን ኦሎምፒያዶች ተጐናፅፏል፡፡
በቅርጫት ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ከደሞዝ፣ ከተለያዩ ቦንሰች፣ ከስፖንሰርሺፕ ውሎችና እና ተያያዥ የንግድ ስራዎች ከ680 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝቷል፡፡ ይህ የገቢ መጠን በቅርጫት ኳስ ስፖርት ታሪክ በ2ኛ ደረጃ ያስቀምጠዋል፡፡  
5 ጊዜ የ NBA የሻምፒዮናነት ክብሮችን ተቀዳጅቷል፡፡
በተጨዋችነት ዘመኑ ከ20 በላይ ዓለም አቀፍ ብራንዶች እና የንግድ ምልክቶችን በማስተዋወቅ ሰርቷል፡፡ ከእነሱም መካከል ናይኪ፣ ኮካኮላ፣ ማክዶናልድ፣ ይጠቀሳሉ፡፡
በሚዲያ፣ በቴክኖሎጂ፣ በዳታ ቢዝነስ ኢንቨስት ለማድረግ በነበረው እቅድ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር በጀት ነበር የያዘው፡፡
ከሎስ አንጀለስ ሌከርስ መጫወት ሲጀምር በዓመት 3.5 ሚሊዮን ዶላር እየተከፈለው ሲሆን ከ20 ዓመታት በኋላ በዓመት የሚያገኘው ክፍያ 30 ሚሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡
ከስፖንሰርሺፕ ጋር በተያያዘ ትልቁ ክፍያውን ያገኘው ከናይኪ ጋር በፈፀመው ስምምነት ሲሆን ከ2013 እ.ኤ.አ ጀምሮ በዓመት 10ሚሊዮን ዶላር እየተከፈለው ነበር፡፡
4 እና 28 በሎስአንጀለስ ሌከርስ እየተጫወተ ባገኘው ስኬት ምክንያት ሙዚዬም የገቡ ማልያዎች ናቸው፡፡
በ2016 እ.ኤ.አ ላይ ከቅርጫት ኳስ ስፖርት ከተሰናበተ በኋላ በተለያዩ መስኮች የተሠማራበት ኢንቨስትመንት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል የሚንቀሳቀሱበት ሲሆን፤ ፊልም ሠሪ ኩባንያ፣ የአትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከላት እያስተዳደረ ነበር፡፡
ደራሲ፣ የፊልም ፕሮዲዩወሰር እና የፓድካስት ስርጭቶች አዘጋጅ ነበር፡፡
በታዋቂው የቅርጫት ኳስ ክለብ ሎስ አንጀለስ ሌከርስ እና በአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ሊግ ለ20 ውድድር ዘመናት በመጫወት ብቸኛው ነው፡፡
Body armor የተባለ የስፖርት መጠጥ አምራች ኩባንያ በ6 ሚሊዮን ዶላር መስርቶ ኮካኮላ በ200 ሚሊዮን ዶላር ድርሻውን ጨምሮለት የሚንቀሳቀስ ሆኗል፡፡
The Mamba Mentality የመጀመሪያ መጽሐፉ ሲሆን በአማዞን ገበያ ከፍተኛ ሽያጭ ያገኘ ነው፡፡ ከታዋቂው እና “ዘ አልኬሚስት”ን ከፃፈው ብራዚልያዊ ፓውሎ ኮውሌሆ ጋር የሚሠራበለት ፕሮጀክት ነበረው፡፡
Dear Basketball” በሚል የሠራው ፊልም በአኒሜሽን ዘርፍ የኦስካር ሽልማትን አሸንፏል፡፡
ከሞቱ በኋላ በስሙ የተመረቱ የተለያዩ የስፖርት ትጥቆችና ምርቶች ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፡፡ የአዲዳስ ክሬዚ 97 የተባለው ስኒከር ዋጋው በ600% ጨምሮ 1199 ዶላር ሆኗል፡፡ ፊርማውን ያኖረባቸው የሎስ አንጀለስ ሌከር 8 እና 24 ቁጥር ማሊያዎች በአማዞን 300 ዶላር እየተቸበቸቡ ነው፡፡ ለብሶ የተጫወተባቸውና ፊርማ ያኖረባቸው ማልያዎች ደግሞ ዋጋቸው 6500 ዶላር ይሆናል፡፡

Read 1279 times