Saturday, 25 January 2020 14:11

የአቶ ልደቱ ስጋቶች በቀጣዩ ምርጫ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

    አሁን እንደ አገር ያለንበት ሁኔታ ወደ ምርጫ ለመግባት አይፈቅድልንም በማለት የሚከራከሩት ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው፤ አቋምና በምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ በተደረገ የውይይት መድረክ፤ የምርጫውን የጊዜ ሰሌዳ በተመለከተ ያላቸውን አቋምና ስጋት በሰፊው ገልጸዋል፡፡ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡


            ‹‹የምርጫ ጊዜ በሕግ
 የማይታለፍ ነው›› ለምን?
ያለንበት ወቅት ድህረ ፖለቲካ ቀውስ ነው፡፡ ሁለተኛ አሁን ምርጫውን ለማስፈጸም የቦርዱ አመራር አባል ሆነው የተሾሙትም በታሪካዊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥትም፣ በሕዝብ ትግል የቆመ ነው፡፡ ይሄ አመራርና ለውጥ የመጣው ሕግ ተጥሶ ነው፡፡ የምናወራው የሕግና የሕግ ጥሰት ጉዳይ ከሆነ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት፤ ማንም  አካል በሕጋዊ መንግሥት ላይ ሕግን ተላልፎ ማመፅ አይቻልም ይላል፡፡
ማመፅ ወንጀል ነው፤ 25 ዓመት ድረስ ያሳስራል፤ ህጉ፤ ሥልጣን የሚያዘው በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ብቻ ነው ይላል። ይሄ የፖለቲካ ቀልድ እንደነበር የገባው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ሶስትና አራት አመት አደባባይ ወጥቶ፣ ትግል አድርጎ፣ በሕይወቱ ዋጋ ከፍሎ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡ ሕግ ተጥሶ የመጣ ለውጥ ነው፡፡ ህጉ የተጣሰው መጣስ ስለነበረበት ነው፡፡ አሁን የሕግ ጨዋታ ውስጥ ገብተን፣ ይሄን ምርጫ ካሳለፍነው፣ ከዚያ በኋላ ያለው መንግሥት ሕገ ወጥ ይሆናል የምንል ከሆነ፣ ለኔ የለውጥ ሂደቱን መካድ ነው:: ሕዝቡ ይሄ ለውጥ እንዲመጣና እናንተ እዚህ ቦታ እንድትቀመጡ የከፈለውንም መስዋዕትነት መርሳት ነው፡፡ ስለዚህ መጀመርያ ጥያቄው መሆን ያለበት፣ የሕግ ጥሰት ጉዳይ ሳይሆን አሁን ምርጫ ለማካሄድ ዝግጁ ነን ወይ? ነው፡፡
ከምርጫው በፊት
ሶስት ዋና ቅድመ ሁኔታዎች
በኔ አተያይ፤ አሁን ምርጫ ለማካሄድ በሦስት ምክንያቶች ዝግጁ አይደለንም፡፡ አንደኛ፤ ሕዝቡ ትግል አድርጎ ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ መዋቅራዊ ሥርዓት ለመሸጋገር የጠየቃቸው ጥያቄዎች አልተፈቱም፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በምርጫ የሚፈቱ አይደሉም። በድርድር የሚፈቱ ናቸው። በብሄራዊ መግባባት የሚፈቱ ናቸው፡። ያን ስራ አልሰራንም፡፡ በዚህ ሁኔታ ወደ ምርጫ ውስጥ መግባት ወደ ቅድመ 2010 ነው የምንገባው። ወደ ቀውስ ነው የሚመልሰን::
ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫ የማካሄድ ትልቅ ሃላፊነት ነው የተቀበለው። በመቀበሉ ብቻ አደንቀዋለሁ፡፡ በትልቅ ድፍረት ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ ይሄ ሀይል ግን በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አካሄደ ተብሎ እንዲመሰገን ነው የምፈልገው። ተገቢ ያልሆነ ጊዜ ላይ ወደ ምርጫ ገብቶ፣ ኢትዮጵያን ወደ እርስ በርስ ግጭት ወሰዳት መባል የለበትም። ስለዚህ የሕጉን ጉዳይ በደንብ እንነጋገርበት፡፡
ሕግ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስፈልገው ለሕዝብና ለአገር ደህንነት ነው። የሕዝብና የአገር ደህንነትን የሚጻረር ነገር ሲመጣ፣ ሕግም ራሱ ጥያቄ ውስጥ ይገባል፤ ይሻሻላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በተደረጉ ለውጦች በሙሉ ሕገ መንግሥቶች ነበሩ፡፡
ደርግ ሲመጣ የአፄ ሀይለ ስላሴ ሕገ መንግሥትን ቀዶ ጥሎ ነው ለውጥ ያመጣው፤ ኢህአዴግ ሲመጣ የደርግን ሕገ መንግሥት ቀዶ ጥሎ ነው ለውጥ ያመጣው::
አሁን ከእነሱ የተሻለ የፖለቲካ ሀይል ስልጣን ላይ ስላለ ተቀዶ ይጣል አላለም፤ ግን ለሀገርና ለሕዝብ ደህንነት ሲባል ሕግ ይሻሻላል፡፡ የሕግ ጉዳዩን የሞትና የሽረት ጉዳይ አድርጋችሁ አታቅርቡ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ የታገለውና መስዋዕትነት የከፈለው፣ እናንተ እዚህ ቦታ እንድትመጡ ያደረገውም የቀድሞ ሕጐችና ሥርዓቶች እንዲቀጥሉ አይደለም፤ ለውጥ እንዲመጣ ነው፡፡
ስለዚህ ምርጫው በሶስት ምክንያት መካሄድ አይቻልም፡፡ አንደኛ፤ ሰላም የለም፤ የሕግ የበላይነት የለም፡፡ ሰላምና የሕግ የበላይነት በሌለበት ሁኔታ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ሊካሄድ አይችልም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እንኳን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማድረግ ሕዝብ መቁጠር አልቻልንም፡፡ ሕዝብ መቁጠር ያጋጨናል ያጣላናል ብለን ነው’ኮ የተውነው፡፡ ታዲያ የፖለቲካ ስልጣን የሚያዝበት ምርጫስ?
ሌላው በቂ ዝግጅት የለም፡፡ መንግስት ደጋግሞ እየነገረን ያለው፤ ይሄ ግጭት መቼ እንደሚያቆም አላውቅም ነው እያለን ያለው:: በእርግጠኝነት አስቆማለሁ አላለም:: ዝግጁ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ወደ ኋላ ተመልሶ የሚሠራ ሕግ አውጥታችሁ 10ሺህ ድምጽ እንደገና እንድናሰባስብ ይጠበቃል፤ 500 አባላት ያሉት ጉባኤ ማዘጋጀት ይኖርብናል፡፡ ይሄን ጉባኤ ለማዘጋጀት እስከ 2.5 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ይሄን ሁሉ ብር ከየት ነው የምናመጣው?
የምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተ የመረጠው ነሐሴ ወርን ነው፡፡ ነሐሴ ክረምት ነው፤ ብርድ ነው፣ ገበሬው ስራ ላይ ነው፡ እንዴት ተደርጐ ነው በነሐሴ የሚካሄደው? የሕዝባችን ስነልቦናስ ለምርጫ የተዘጋጀ ነውን?

Read 4287 times