Saturday, 25 January 2020 13:22

የዘንድሮ ምርጫ ስጋቶችና የተለዩ ገጽታዎች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

        • በምርጫው ከመንግስት የበለጠ የሚያስፈሩኝ ተቃዋሚዎች ናቸው
             • መንግስት “ተጭበርብሬያለሁ” ብሎ ክስ ሊያቀርብ ይችላል
             • ዘንድሮ ዘመድ ዘመዱን የሚመርጥበት ምርጫ ነው የሚሆነው
             • ምርጫውን የሞት ሽረት ጉዳይ ማድረግ አደጋው የከፋ ነው


              ምርጫ ቦርድ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በነሐሴ ወር እንደሚካሄድ ያስታወቀ ሲሆን አንዳንድ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የጊዜ ሰሌዳው የአገሪቱንነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው ሲሉ የምርጫ ጊዜው መራዘም እንዳለበት አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡ ብዙዎቹ ፓርቲዎች ግን በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ የተስማሙ ይመስላሉ፡፡ በምርጫ
የጊዜ ሰሌዳ መነሻነት የአዲስ አድማሱ አለማየሁ አንበሴ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኙና አክቲቪስቱ ዮናታን ተስፋዬ፤ ከዘንድሮ ምርጫ ጋር በተያያዘ ያላቸውን
ስጋት፣ የነሐሴው ምርጫ የተለዩ ገጽታዎች ምን እንደሆኑ፣ የምርጫ ማግስት ውዝግቦችና የከፋ ቀውስ እንዳያስከትሉ ምን መደረግ አለበት በሚሉት ዙሪያ ሃሳባቸውንና ዕይታቸውን አጋርተዋል፡፡ እነሆ፡

                በወጣው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
በወጣው ፕሮግራም ላይ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸው ምክንያቶች አሉ፡፡ ከነሐሴ በኋላ ቢካሄድ ሕግ ይጥሳል፤ ከነሐሴ ወዲህ ለማድረግ ደግሞ በቂ ዝግጅት የለም፡፡ እንደውም በነሐሴ  መካሄዱ በራሱ ለኔ ጥድፊያ ነው የሚመስለኝ፡፡ ነገር ግን ምርጫ ቦርድ ለፕሮግራሙ መውጣት ያቀረባቸው ምክንያቶች ተገቢ ናቸው ባይ ነኝ፡፡
ለውጡ የመጣው ሕግን በመጣስ ነውና አሁንም ሕግ ከአገር ህልውና አይበልጥም፤ ስለዚህ ምርጫው የአገርን ሕልውና በማይነካ መልኩ የተዳለደለ ጊዜ ተጠብቆ ሊካሄድ ይገባል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ መከራከሪያ ላይ ላዩን ሲታይ ያስኬዳል:: ነገር ግን መንግሥት ምርጫውን ለማራዘም እንዲወስን የሚያደርገው ነባራዊ ሁኔታ አለ ወይ? የሚለውን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ሕጉን አጥሮ፣ የፖለቲካ ውሳኔ ወስኖ ምርጫውን ለማራዘም የሚያስችል የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታ አለ ወይ? ብለን መጠየቅም ይኖርብናል፡፡ እንዲሁ ዝም ብሎ መከራከሪያው ምክንያታዊ ስለሆነ ብቻ አሳማኝ ይሆናል ማለት አይቻልም:: በአሁኑ ወቅት አገሪቷ ላይ ያለው የሃይል አሰላለፍ ምን ይመስላል? እነማን ናቸው ከፍተኛ ሕዝብ አንቀሳቅሰው ምርጫው እንዲራዘምም እንዳይራዘምም የማድረግ የፖለቲካ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉት? የሚለው መታየት ያለበት ይመስለኛል፡፡ ምርጫው ሕግንም ቢሆን ሽሮ መሸጋገር አለበት የሚሉት ጥቂት ናቸው:: በስምም ይታወቃሉ፡፡ እነ አቶ ልደቱ… እነ ኢንጂነር ይልቃል ናቸው። ከእነሱ ውጪ ያለው ሀይል፤ ምርጫው እንዲካሄድ የሚፈልግ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሞ የፖለቲካ ሀይሎችና ህወሃትን የመሳሰሉት ምርጫው በጊዜው ይካሄድ እያሉ እየወተወቱ ነው፡። እነዚህ ሀይሎች ብዙ ሕዝብ እናንቀሳቅሳለን ብለው የሚያስቡ ናቸው። በአንጻሩ ምርጫው ሕግንም ቢሆን ሽሮ ይራዘም የሚሉት ደግሞ ብዙም እንቅስቃሴ የሌላቸው፣ የምርጫ ወረዳቸው በጣም ውስን የሆኑ ሃይሎች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የትኛው ድምፅ ነው የበለጠ ሊሰማ የሚችለው? የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ አብላጫው የፖለቲካ ሀይል የተስማማበት ነው ወይስ ጥቂቶች ያነሱት ጉዳይ ነው ገዥ የሚሆነው? የሚለውን በሚገባ ማጤን አለብን፡፡ በሌላ በኩል፤ መንግሥት “በአገሪቱ ሰላምና ፀጥታ የለም፤ ስለዚህ ምርጫውን አራዝማለሁ” ሲል አልሰማነውም፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ሲታዩ፤ ምርጫው ሕግን ጥሶ ከሚራዘም ይልቅ አሁን በተያዘለት ጊዜ ቢካሄድ ነው ውጤቱና ይዞት የሚመጣው ችግር በእጅጉ ሊቀንስ የሚችለው፡፡ የምርጫውን ጊዜ ሕግን ጥሶ ወደፊት መግፋት የበለጠ አለመረጋጋትን ነው የሚፈጥረው፤ ምክንያቱም ውዝግቡም ግጭቱም የሚጠነሰሰው በፖለቲካው ተዋናዮች (ፓርቲዎች) ነው፡፡
ለእርስዎ ከቀጣዩ ምርጫ ጋር ተያይዞ ሊጠቀሱ የሚችሉ ዋነኛ ስጋቶች ምንድን ናቸው?
በሁለት መልክ ነው እኔ ስጋት ያለኝ፡፡ አንደኛው፤ ምርጫው ራሱ እየታየበት ያለው መንገድ ነው፡፡ በተለይም ተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ሀይሎች፤ ምርጫውን የወደፊቱን የአገሪቱን ሕልውና የሚወስን፣ የሕዝቡን ችግሮች ሁሉ ጠራርጎ የሚፈታ፣ የሞት ሽረት ጉዳይ አድርገው እያቀረቡት ነው፡፡ ይሄ በራሱ ለኔ ትልቅ ስጋት ነው፡፡ በተለይ የዲሞክራሲ ባህል ልምምድ በሌለበት ሀገር ውስጥ ቀጣዩን ምርጫ፣ የሁሉም ነገር መጨረሻ ወይም የሞት ሽረት ጉዳይ አስመስሎ ማቅረብ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ምርጫው እየታየበት ያለው መንገድ፣ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ተስፋችንን እንዳያቀጭጨውና ወደ አምባገነንነት አዙሪት እንዳይከተን እፈራለሁ፡፡ ምክንያቱም በመንግስት በኩልም ያለው ወገን ከላይ ከላይ ነው እንጂ የተቀየረው፣ ከስር ያለው ገና ብዙም አልተለወጠም፡፡ ስለዚህ ያንን ሃይል ተጠቅሞ መንግስት መልሶ አምባገነንና አፋኝ እንዳይሆን ያሰጋኛል፡፡ አሁን ያለው መንግስት ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ስልጣኔን አጣለሁ ብሎ ከሠጋ፣ ወደዚያ አይነት ችግር የማንገባበት ምክንያት የለም፡፡ ስለዚህ በተለይ በተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች በኩል ምርጫውን የመጨረሻ የህልውና ጉዳይ አድርጐ የማየትና ድምፀቱን (ቶኑን) ከልክ በላይ የማጉላት ነገር ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ሌላኛውና ሁለተኛው ስጋቴ፤ ምርጫው አሁን ባለው መንፈስ የሚካሄድ ከሆነ፣ ውጤቱን ለመቀበል በሁሉም ወገን ቁርጠኝነቱ ይኖራል ወይ? የሚለው ያሳስበኛል፡፡ ሂደቱን ሳይሆን ውጤቱን መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ኋላ ላይ የሚያመጡት ጥፋት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ዲሞክራሲ ደግሞ በባህሪው ከውጤት ይልቅ ሂደት ላይ ያተኩራል:: ሂደቱ የፉክክሩ ጤናማ ከሆነ… ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ሰዎች ተጨባብጠው የፖለቲካ ሂደቱ መቀጠል አለበት፡፡ ነገር ግን ውጤቱ ላይ ብቻ የምናተኩር ከሆነ ምርጫው ጤናማ ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ያለው ስጋቴ፤ በእነዚህ ሁለት ነገሮች ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች አሁን የጀመርነው የዲሞክራሲ ተስፋ ወደ ኋላ ተመልሶ ሊቀጭጭ የሚችልበት እድል መኖሩ ያሰጋኛል፡፡
በምርጫ ጉዳይ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ቀላል አይደለም፤ አሁን በሀገሪቱ ያለውን የመገናኛ ብዙኃን ባህርይ እንዴት ትገመግመዋለህ?
አሁን የተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፍስ ወከፍ አንድ አንድ ሚዲያ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ሁለት ሶስትም ሳይኖራቸው አይቀርም፡፡ ገዢው ፓርቲ የመንግስት ሚዲያዎችን እየተጠቀመ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በመንግስት ላይ ትንሽ ተስፋ የማደርገው፣ እንደ ሌሎቹ ነገሮችን አጉል ሊያጦዝ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሀገር የማስተዳደር፣ የሀገርን ህልውና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት:: ስለዚህ በመንግስት ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ሁከተኛ የሚሆንበት እድሉ ጠባብ ነው:: በተቃዋሚዎች በኩል ግን የተቃዋሚዎቹ ደጋፊ ወይም ጥገኛ የሆኑ ሚዲያዎች የዚያ ዓይነት የመንግስትነት ኃላፊነት የለባቸውም፡፡ ችግርም ቢፈጠር የመንግስትን ያህል ሊጠየቁ አይችሉም:: ድርብ ኃላፊነት ስለሌለባቸው ብዙም አይጨንቃቸውም:: ፓርቲዎችና ሚዲያዎች ያላቸውን የእርስ በእርስ ጥገኝነት ስንመለከት፤ በጣም ነው የሚያስፈራው፡፡ ወጣቶቻችን ደግሞ የእነዚህ መሰል ሚዲያዎች ተከታታይ ሆነዋል::  ስለዚህ በተለምዶ ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ በእነዚህ ሚዲያዎች የሚቀርቡ ሃሳብና አስተያየቶች ወጣቶቻችን ጋ ሲደርሱ እንዴት ይመነዘራሉ? የሚለው አሳሳቢ ነው፡፡ ይሄ ምናልባት በሠለጠኑት አለም ችግር ላይኖረው ይችላል፡፡ በኛ ሁኔታ ግን ጉዳዩ እጅግ አደገኛ ነው፡፡ በሠለጠኑት ሀገሮችም እኮ ሳይቀር በአንድ ሚዲያ የሚነገሩ ሀሳቦች በተለያየ መንገድ ይተረጐማሉ፡፡ ይሄን በጊዜ ከመግራት አኳያ ሃላፊነቱ የምርጫ ቦርድ ነው፡፡  በህግም ቢሆን ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ያለአግባብ የሚሠሩ ሚዲያዎችን እስከ መዝጋት የሚደርስ ህግ መዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ያንን ህግ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ማድረግ ከተቻለ በተወሰነ መልኩ ስጋቱን መቀነስ ይቻላል፤ ነገር ግን ስጋቱን ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት የሚቻልበት እድል የለም፡፡ ለምሳሌ የምርጫን ግምታዊ ውጤት አስቀድሞ መናገርን ምርጫ ቦርድ በሕግ ከልክሏል፡፡ ይሄን ሕግ ሙሉ ለሙሉ መተግበር ያስፈልጋል፡፡
የምርጫው ፉክክር ምን አይነት መልክ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
በዚህ ምርጫ ዋነኛ የፉክክር መንገድ የሚሆነው የፖለቲካ ፕሮግራም ወይም ሀሳብ ነው ብሎ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ እንደውም ይሄን ምርጫ ለመገመት አስቸጋሪ የሚያደርገው የፖለቲካ ፕሮግራምን መሠረት ያደረገ አለመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ጥርጥር በሌለው ሁኔታ ዘመድ ዘመዱን ነው የሚመርጠው:: ‹‹ብልፅግና›› በመዋሃዱ ነገሩን ሊቀይረው እንደሚችል ብዙዎች ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ይሄ ገና ብዙ ሂደትን የሚጠይቅ እንጂ በፍጥነት ውጤት የሚያመጣ አይደለም:: ካድሬዎቹ ገና ብልጽግናን እስኪረዱት ድረስ በራሱ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ስለዚህ ብልጽግና ራሱ በዚህ ምርጫ በአካባቢያዊነት፣ በተወላጅነት፣ በወንዜነት ነው ራሱን ሊያጭና ሊያስመርጥ የሚችለው፡፡ ሌላውም እንደዚያው ነው፡፡ አማራ ክልል ላይ የበለጠ የአማራነት ስሜት ያለው ማን ነው? ሲዳማ ላይ የበለጠ የሲዳማነት ስሜት ያለው ማን ነው? ትግራይ ክልል የበለጠ የትግራይነት ስሜት ያለው ማን ነው? ኦሮሚያ ላይ የበለጠ የኦሮሞነት ስሜት ያለው ማነው? በሚለው ነው የሚመራው፡፡ ለዚህ ምልክቱ ደግሞ በቅርቡ እንኳ “እኛ የጀነራል ታደሰ ብሩ ልጆች”፣ “እነ እከሌ የመለስ ልጆች”፣ “እነ እከሌ የነፍጠኛ ልጆች” መባባል ተጀምሯል፡፡ በትግራይም የኦረና ሰዎች “የሸዋ ተላላኪዎች”፣ “የብልጽግና ተላላኪዎች” እየተባሉ ነው፡፡ ከወዲሁ ፍረጃ ተጀምሯል፡፡ ስለዚህ ምርጫው በዋናነት ማንነትን የሚያጠይቅ ነው የሚሆነው ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ የሰዉም በተለየ የወጣቱ ስሜት እየተቃኘ ያለው በዚህ መንገድ ነው:: ስለዚህ በዚህኛው ምርጫ ዘመድ ዘመዱን እንጂ ሀሳብ አይደለም የሚመረጠው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የፖለቲካ ፕሮግራም አቅርቦ መመረጥ ለኛ ቅንጦት ይመስለኛል፡፡
ከምርጫው ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ችግሮች ከፍተኛ ጉዳት ሳያደርሱ፣ የአገር ህልውናንም ሳይፈታተኑ መቀነስ የሚቻለው እንዴት ነው?
በእርግጥ ችግር ሊፈጠር ሊፈጠር እንደሚችል ይጠበቃል፤ ነገር ግን ዋናው ትኩረት ሊሆን የሚገባው ችግሮች የሚያስከትሉትን ጉዳት መቀነስ ላይ ነው፡፡ መንግሥትም፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም አለማቀፍ ተቋማትም ትኩረት ማድረግ ያለባቸው፣ ጉዳቶችን መቀነስ ላይ ነው። ጉዳቶችን ለመቀነስ ደግሞ ሁሉም አካላት የሚስማሙባቸውን ቅድመ ግምቶች ማስቀመጥና መነጋገር አለባቸው። ግምታዊ ነገሮችን አስቀምጦ መነጋገር ወሳኝ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ፤ ግጭት እንደሚፈጠር፣ የሚሞቱ ሰዎች እንደሚኖሩ ጥርጥር የለውም:: ለምን ከተባለ… አሁን ላይ በምርጫ ጉዳይ በዜጎች ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ የሚፈራው መንግሥት ብቻ አይደለም፡፡ ከመንግሥትም በላይ ጉልበት እያወጡ ያሉ ሃይሎች የፖለቲካ አሉ፡፡ ወረዳዎችን፣ ቀበሌዎችን በጉልበታቸው እየዘወሩ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ምርጫውን ለማጭበርበር የማይሞክሩበት መንገድ አይታየኝም፡፡ ለምሳሌ ሲዳማ ላይ በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩት የዞን አስተዳዳሪዎች ሳይቀሩ ነው፡፡ በርካታ ሕገወጥ መታወቂያ ሲታደል ነበር፡፡ እንዲህ ያሉ ልምዶች ሲዳማ ላይ አጋጥመዋል፡፡ ይሄኛው ደግሞ አገር የሚመራበት፣ ስልጣን መያዣ ምርጫ ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ከመንግሥት በባሰ ሁኔታ እኔ የምፈራው ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችን ነው፡፡ ምርጫውን ለማጭበርበር ያለ የሌለ አቅማቸውን ይጠቀማሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ በዚህ መሃል መንግሥት ደግሞ ሀይል ስላለው ይሄን ለማስቀረት እርምጃ ሊወስድ ይችላል:: እንዲህ አይነት ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ስለዚህ ሚዲያዎች የሲቪክ ተቋማት፣ አለማቀፍ ታዛቢዎች፣ ምርጫ ቦርድ እነዚህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዝግጅት ማድረግ ይገባቸዋል:: ገና ከአሁኑ ቅድመ ጥናትና ትንበያ እያደረጉ መስራት ያስፈልጋል፡፡
ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት በምርጫ ቦርድ በኩል ምን ወሳኝ ቅድመ ዝግጅቶች መደረግ አለበት ይላሉ?
አንደኛ፤ በተለይ ከሚዲያዎችና ከፓርቲዎች ጋር ተያይዞ የወጣውን ሕግ ያለማወላወል ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ ሊጨበጥ የሚችል ሥራ ከምርጫው በፊት መስራት መቻል አለበት:: ፓርቲዎች በሚገባ እንዲነጋገሩ፣ እንዲተማመኑ ላሉ ስጋቶች መፍትሔ የሚያመጡበትን መንገድ በጋራ መድረካቸው በኩል እንዲፈጥሩ ድጋፍ ማድረግ ቢቻል የተሻለ ነው፡፡ ለምርጫው ያላቸውን የተጋነነ ግምትም ተነጋግረው በልኩ ቢያደርጉት የተሻለ ነው፡፡ ከምርጫው በኋላም የሚፈጠሩ ችግሮችን እንዴት ልንፈታ እንችላለን? የሚለውን በመነጋገርም ከወዲሁ መፍትሔ ማበጀት ይገባል፡፡ አሁን ያለውን ከልክ ያለፈ የምርጫ ድምፀት (ቶን) ማስተካከልም አስፈላጊ ነው፡፡ ከምርጫው ምን እንጠብቃለን? ምርጫው ምን ያህል ነው ህብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጠር የሚገባው? ሁሉም አካል ምርጫውን በምን መልኩ ይጠብቀው? ስለ ምርጫው  ምን ስዕል ይኖረው? የሚለውን ከወዲሁ ለክቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ ለክቶ ስንል ካለፈው የአገሪቱ የምርጫ ሂደት የተሻለ ወይስ ከሰለጠኑትና በቅተዋል ከተባሉት አገሮች ተርታ የሚስተካከል ምርጫ ነው የሚካሄደው? የሚለውን ነው ለክቶ ማስቀመጥ፡፡ ይሄን ለክቶ ማስቀመጥ በተፎካካሪዎች፣ በሕዝቡም ዘንድ ያለውን ስሜት በልኩ ያደርገዋል፤ ያቀዘቅዘዋል፡፡ መንግሥትም ለዚህ እገዛ ማድረግ አለበት፡፡
በምርጫው ማግስት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ክስተቶችን መገመት ይቻላል?
ግጭት ሊፈጠር እንደሚችል ይጠበቃል። ተጭበርብሯል የሚለው ውዝግብም አይቀርም:: የአሁኑን ምርጫ ለየት የሚያደርገው፤ መንግሥት ራሱ ‹‹ተጭበርብሬያለሁ›› ብሎ ክስ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ዕድል መኖሩ ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ ችግር ሲያጋጥም ደግሞ ወደ ፍ/ቤት የመሄዱ ልምድ ስለሌለን ችግሮች የበለጠ ሊባባሱ ይችላሉ፡፡ ነ
ገር ግን እነዚህን ችግሮች ለማቀዝቀዝ በፖለቲካ ሀይሎች መካከል ድርድር የሚኖር ይመስለኛል፡፡ በተለይ ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ጥሩ ከተወያዩ፣ ለመደራደር ክፍት የሆኑ ይመስለኛል፡፡ ይሄን ተከትሎም የሕግ ማሻሻያ እንደሚኖር እገምታለሁ፡፡ ክልሎች በተቃዋሚዎች፣ የፌደራል መንግሥት በብልጽግና ይያያዛል በሚባለው ቅድመ - ግምት እኔ ብዙም አልስማማም፡፡ የተሳሳተ ግምት ይመስለኛል፡፡ ክልሎች ላይ ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች በተቀራራቢ ድምጽ የም/ቤት ወንበር ለመያዝ ድርድር እንደሚያደርጉ እገምታለሁ፡፡ አንዳንድ ቦታዎች ላይም የማሟያ ምርጫ ሊደገም ይችላል፡፡ እንደ ወለጋ ያሉ አንዳንድ አካባቢዎች፤ ለምርጫው አስቸጋሪ እንደሚሆኑ እገምታለሁ፡፡ በአጠቃላይ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ድርድሮች ሁሉ የተለየ መልክ ያለው ድርድር ከምርጫው በኋላ እንደሚኖረን እጠብቃለሁ፡፡         

Read 3029 times