Sunday, 26 January 2020 00:00

‹‹ወደ ድል የምንሻገርበት ፈተና ስለሆነ ተስፋ እንዳትቆርጡ››

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    - መንግሥት ከጋሞ ሥርዓት ቢማር፣ አገር ለዚህ ሁሉ ቀውስ አትዳረግም ነበር
            - አገርና ሥልጣኔን የገነቡ አባቶች ሊፀለይላቸው ሲገባ እንዴት ይረገማሉ?!
            - ተማሪዎቹ ሁሉ ‹‹ሁለተኛ እጃችንን ለጥፋት አናነሳም›› ብለው ቃል ገብተዋል


             በጋሞ ባህላዊ ሥርዓት ካኦ ታደሰ ዘውዴ፤ ከዘር ሲቀባበል በመጣው የንግስና ሥርዓት 15ኛው ካኮ (ንጉስ) ናቸው፡፡ በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው ትምህርትና እውቀት የታነፁ ናቸው፡፡ በማኔጅመንትና በኢኮኖሚክስ ሁለት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፤ በህግ ትምህርትም ዲፕሎማቸውን ካገኙ በኋላ አቃቤ ህግና
ዳኛ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ለጥምቀት በዓል ወደ 60 የሚጠጋ ቁጥር ያላቸውን የጋሞ አባቶች፣ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ህብረት ተወካዮች፣ የዩኒቨርስቲው መምህራን ተወካዮችና የወጣት ተወካዮችን በመምራት፣ ‹‹የጋሞ አባቶች የሰላምና የአንድነት ጉዞ” አድርገዋል - ከአርባ ምንጭ እስከ ጎንደር፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ካኦቶ ታደሰን በጉዞውና ባከናወኗቸው የሰላምና እርቅ ሥራዎች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች፡፡ እነሆ፡-


              የጐንደር ጉዟችሁን ከማንሳቴ በፊት አንድ ጥያቄ ላስቀድም፤ በጋሞ ባህል አንድ ካኦ የሚቀየረው ምን ሲሆን ነው?
በስርዓታችን አንድ ካኦ የሚቀየረው በዋናነት እድሜውን ሲጨርስ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ስሞት የመጀመሪያ ወንድ ልጄ ይተካል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በፊት ካኦዎች የጋሞን ስርዓት ከጣሱ፣ ለምሳሌ ሴሰኛ ከሆኑና ሚስታቸውን አስቀምጠው ከወሰለቱ፣ አካለ ጐደሎነት ካለ፣ ሀሰተኛ ፍርድ ከበየኑ፣ ፍትህ ካዛቡና በጥቅም ፍርድ ከሰጡ፣ ለወገን መፍረድና ማድላት ከታየባቸው… ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡ በአማካሪዎች ይነገራቸዋል:: ምክሩን ተቀብለው ካስተካከሉ እሰየው፤ ካልሆነና በዚያው ጥፋት ከቀጠሉ አማካሪዎቹ ወይም ባህላዊ ምክር ቤቱ ካኦውን ከስራው ያግድና ያስቀምጣል፡፡ ከዚያም የካኦው ታናሽ ወንድም ወይም የደረሰ ልጅ ካለ፣ ሥርዓቱን በሞግዚትነት ይመራል፡፡ ካኦው ታግዶ ቁጭ ይልና የሰራውን ሃጢያት ተናዝዞ፣ ንስሀ ገብቶ ሲጨርስ፣ ህዝቡ ከተቀበለውና ትክክለኛ የባህሪ ለውጥ ከታየ፣ ህዝቡ እንደ አዲስ ያመጣና ቦታው ላይ ያስቀምጠዋል፤ መምራቱንም ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ የእኛ ባህላዊ ንግስና ብዙ ፈተና ያለበት፤ ብዙ ቁጥጥር የሚደረግበት፤ ልቅ ያልሆነ ትልቅ ንግስና ነው፡፡ ያልተማከለ አስተዳደር ያለበት፣ የስልጣን ተዋረድ ያለውና ለዘመናዊው አመራር ምሳሌ መሆን የሚችል ነው፡፡ መንግስትም ከጋሞ ስርዓት ጊዜ ወስዶ ቢማር፣ አገር ለዚህ ሁሉ ቀውስ አትዳረግም ነበር፡፡ ቅድም እንደነገርኩሽ፤ ከኔ በፊት 15 አያቶቼ ነግሰው አልፈዋል፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ አውሮፓዊያን እደጃችን ላይ መጥተው ድንኳን ተክለው ያጠኑ ነበረ፡፡ የእኛ አያቶች ምን እንደሚሰሩ አያውቁም፡፡ ነገር ግን አንድና ሁለት አመት ቆይተው ብዙ ነገሮችን ያጠናሉ:: ታሪካችንን፣ ባህሉን፣ የአስተዳደር ስርዓቱን ሁሉ አጥንተዋል፡፡ ይህንን ሁሉ ነገር ወስደው ዛሬ ለዓለም መልሰው እያስተማሩ ነው ያሉት:: ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ በመሆኗ፣ አሁን ዓለም ላይ የሚታየው የህንፃ ዲዛይን ከጋሞ ባህላዊ ቤት የተቀዳ ነው፡፡ ድንኳናቸውንም ብታይ፣ ወይ ክብ ነው ወይም ደግሞ ሬክታንግል ነው፡፡ የጋሞ ቤት ክብ ነው፡፡
ከዛሬ 10 ዓመት በፊት አንድ አውሮፓዊ ፕሮፌሰር መጥቶ ሲያጠና፣ በስራችን ምክንያት አውሮፓን አሜሪካንና አፍሪካን ለልምድ ልውውጥ አዘዋውሮናል፡፡ በዛን ጊዜ ምን እንዳለኝ ልንገርሽ… “ይሄ የእናንተ ሀብት ነው፤ ሌላው ቀርቶ ከድንኳን ሰሪዎች የፈጠራ መብት ባለቤትነት (ፓተንት ራይት) ቢኖራችሁ ኖሮ፣ ዛሬ ህዝባችሁን ሙሉ የሚመግብ ሀብት ታገኙ ነበር፡፡ ስልጣኔ በሙሉ የተወሰደው ከዚህ ነው” ብሎ በአንደበቱ ነግሮኛል፡፡ እኛ ራሳችንን ባህላችንን ንቀናል፤ ‹‹ይሄ ኋላ ቀር ነው፤ ይሄ አልሰለጠነም›› እንላለን፡፡ ግን ትክክል አይደለም፡፡ እኔ ዘመናዊውን ትምህርትም ተምሬያለሁ፡፡ ከአንድም ሁለት ዲግሪ አለኝ፤ በማኔጅመንትና በኢኮኖሚክስ ማለት ነው፡፡ በህግም ዲፕሎማ አግኝቼ፣ ዳኛም አቃቤ ህግም ነበርኩኝ፡፡ ባህልን ከዘመናዊ እያሰናሰልኩ ነው የምሰራው፡፡ ዘመናዊውን ከባህሉ እያቻቻልኩ ነው ስሰራ የቆየሁት፤ ዝም ብዬ ባህላዊውን ንግስና ይዤ ብቆይ ኖሮ እዚህ አልደርስም ነበር:: ዓለም ምን ይፈልጋል? ትውልዱ ምን ይላል? የሚለውን ጠንቅቆ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡ አሁን እዚህ መጥተን የምናስተላልፈው መልዕክትም፤ ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ሥልጣኔ ያስፈልጋል፡፡ ስልጣኔ ግን መሰረታችንን ሊያሳጣንና ሊያስጥለን አይገባም፡፡ አገር በቀል እውቀት፣ አገር በቀል ዕፅዋት፣ አገር በቀል አመጋገብ… ትልቅ ዋጋ ያላቸው ናቸው፡፡ የሰሜኑ የአገራችን ክፍል በህንፃ ግንባታ ሲካን፣ ደቡቡ ክፍል ደግሞ በአልባሳት ጥበብ የተካነ ነው፡፡ አመጋገብንም ብትወስጂ፤ በእኛ አካባቢ አንድ የመጨረሻ ደሃ የሚባል ገበሬ፣ በቀን ውስጥ ስድስትና ሰባት አይነት ምግብ ይመገባል፡፡ ይህን የሚመገበው ከጓሮው ነው፡፡
የአገሪቱን ወቅታዊ ችግር እንዴት ያዩታል?
ወቅቱ የፈተና ወቅት ነው፤ ወደ ድል የምንሻገርበት ፈተና ስለሆነ ተስፋ አትቁረጡ እላለሁ፡፡ ያለንበት ወቅት አስቸጋሪ ነው፤ እኛም ስንትና ስንት ኪሎ ሜትር አቋርጠን ጐንደር የተገኘነው፣ የወቅቱን የአገሪቱን አስቸጋሪ ሁኔታና ሥጋት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ በጋሞ አባቶች ባህል፣ የአንድነትና የሰላም ጉዞ ለማድረግና የመፍትሔ አካል ለመሆን ነው፡፡ ዛሬ የደረስንበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው፡፡ በፖለቲካው ምክንያት ይህን የመሳሰሉ የቤተ መንግስት ህንፃ የሰሩ አባቶች እንዴት ይረገማሉ? እንዴት ይሰደባሉ? እነሱን ለመራገምና ለመስደብ እኮ ከእነሱ የተሻለ ስራና ሁኔታ ላይ መገኘት አለብን::
አሁን በበዓሉ እለት ማታ የቤተ - መንግስቱን የእራት ግብዣ ተመልክተሻል፡፡ እውነትም ጐንደር የአገሪቱ ዋና ከተማ ነበረች፡፡ አዲስ አበባ እንኳን እዚህ ስልጣኔ ላይ አልደረሰችም እኮ፡፡ ታዲያ እነዚህን ስልጣኔዎች ያመጡትን ሰዎች… እንዴት የተሻለ ሳንሰራ እንረግማቸዋለን፡፡
ስልሳና ሰባ ታላላቅ ሰዎችን በአንድ ጉድጓድ የከተተ ሥርዓት፣ እንዴት አድርጐ ነው ይህን ስልጣኔና ያመጡትንና አገር የገነቡትን የምናንኳስሰው?! እስቲ ንገሪኝ! እውነተኛ እርቅ ይምጣ ከተባለ፣ ወደ ኋላ ሄደን አሁን እየተረገሙ ያሉት የሰሩትንም ሆነ የተሰራባቸውን ሃጢያት፣ እንደገና ደርግ የሰራውና በእሱ ላይ የተሰራው፣ ደርግ በኢህአዴግ ላይ የሰራውና ኢህአዴግ ደግሞ በዜጐች ላይ የፈፀመውን ሀጢያት ሁሉ ይቅር ለእግዚአብሔር መባባል ነው ያለብን፡፡
እስኪ ስለ ጉዞው መነሻ ይንገሩኝ?
እንግዲህ የጉዞው መነሻ፤ ይህቺን አገር በደም በአጥንታቸው ገንብተው ያቆዩን አባቶች የአጽምና ነፍስ ለቅሶ ነው፡፡ ‹‹ትላንት የሞትንላት አገር ስትበታተን፣ ልጆቼ እንዴት ዝም አላችሁ?›› ብሎ አጥንታቸው በምድር፣ ነፍሳቸው በሰማይ ያለቅሳል፡፡ እኛንም ያስለቀሰን ይሄው ነው፡፡ ሊፀለይላቸው ሲገባ እንዴት እንርገማቸው!
ከአርባ ምንጭ ተነስታችሁ እስካሁን (ረቡዕ ረፋድ ላይ ነው ቃለ ምልልሱ የተደረገው) ያደረጋችሁት ጉዞና አጠቃላይ ክንውኑ ምን ይመስላል?
እኔ ከግምት በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ ከተነሳንበት ጀምሮ እስከ መዳረሻችን ጐንደር ድረስ ያየሁት ነገር ለማመን ይከብደኛል፡፡ ህዝቡ በየደረስንበት ያደርግልን የነበረው አቀባበል፣ ያሳየን ፍቅር ቀላል አልነበረም፡፡ አዲስ አበባም ቤተ መንግስት ገብተን ተንበርክከን፣ ስለ ሰላምና እርቅ መልዕክት አስተላልፈናል፡፡ የአዲስ አበባን ህዝብ ስሜትና ፍቅር አይተናል፡፡ ባህርዳር ስንገባም የተደረገልን አቀባበል፣ የተቸረን ክብር ልዩ ነው፡፡ የአንድ የሀብታም አገር መሪ ሲመጣ የሚደረግለት አቀባበልና አጀብ ነው ያገኘነው፤ እናም ተገርመናል ተደንቀናል፡፡
በባህርዳር በተደረገልን የእራት ግብዣ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ በርካታ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ በአረንጓዴ ሳራችን መልዕክት አስተላልፈን፤ ለእነሱም አደራ ሰጥተናል፡፡ ለወጣቶቹም ቢሆን የተሻለ ነገር እስኪመጣ፣ ለአገራቸው መልካም መልካሙን እንዲሰሩ ተማጽነናል፡፡ በእኛ አገር ባህል ምን አለ መሰለሽ? እየመራ ባለ መንግስት ላይ መጥፎ ፀሎት አይፀለይም፡፡ ለምሳሌ አባቴ በደርግ ነው የሞተው፡፡ እኔ ግን ‹‹ደርግን ዛሬ አጥፋልኝ›› ብዬ ወደ ፈጣሪ አልፀለይኩም፡፡ አንዲትም ቀን ቢሆን አገሬ ያለ መሪ እንድታድርና ጥፋት እንዲጠፋ አልፀልይም፤ ነገር ግን ጥሩ መሪ እንዲመጣ፣ አሊያም ያለውን መንግስት ልብ እንዲሰጠው፣ በወጉ እንዲያገለግል ነው የምንፀልየው፡፡
ስለዚህ ለክልሉ ባለስልጣናት፤ ወጣቶቹን እንደ አመላቸው፣ ሽማግሌዎቹን እንደ ታሪካቸው እንዲይዙ አደራ ሰጥተን መርቀን፣ ሳራችንን በትነን፣ ተግባብተን በደስታ ነው የተለያየነው፡፡
እዚህ ጐንደርም እንደምታይው… ፍቅር ብቻ ነው፤ ስንገባ በማርሽ ባንድ ነው የታጀብነው፡፡ እዚህም አደራ ሰጥተናል፡፡ ጐንደር ዩኒቨርስቲ የተሰራው ተዓምር ነው፡፡ ተማሪው መምህራኑ፣ እኛም፣ የዩኒቨርስቲው መሪዎችም… ሁላችንም ነን የተላቀስነው፡፡ እኛ ተንበርክከን ‹‹እባካችሁ›› ስንል ሁሉም ተላቀሰ፤ ሁሉም ብሶተኛ ነው፡፡ ተማሪው በሙሉ ‹‹ሁለተኛ እጃችንን ለጥፋት አናነሳም›› ብለው ቃለ መሃላ ተገብቶ ነው የተለያየነው፤ ይሄ ትልቅ ተልዕኮ ነው፡፡
አሁን እኔና እርስዎ ያለንበት ካሳሁን ሎጅ አካባቢ በሚገኝ ፓርክ ላይ ከ60 በላይ ችግኝ ተክላችሁ ስትጨርሱ፣ ከኦባንግ ሜቶ ጋር ስትነጋገሩ የሰማሁት ነገር አለ፡፡ በቀጣይ ምን እያሰባችሁ ነው?
እውነት ነው፡፡ ዛሬ እዚህ ቦታ ላይ 60 ችግኝ ተክለናል፤ አብረን የተከልነው ግን ፍቅርንም ነው፡፡ ይሄ የጋሞ አባቶች መታሰቢያ የፍቅር ችግኝ እንዲሆን ነው የተከልነው፡፡ ችግኝ የፍቅር መትከል ተምሳሌት ነው፡፡ እዚህ ከእኔ ጋር የመጡ የጋሞ አባቶች እድሜያቸው ትንሽም ትልቅም ቢሆን የተለያየ ድርሻ ያላቸው፣ በማህበረሰባችን የተከበሩ አባቶች ናቸው:: ስለዚህ የእኛን የፍቅር ችግኝ ለመንከባከብ 20 ወጣቶች እንደተመደቡ ሰምቻለሁ፡፡ እኛም ከችግኝ ተከላው በኋላ ችግኞቹም ፍቅራችንም እንዲለመልም ፀልየን ተመራርቀናል፡፡ ከሰዓት ከጐንደር ከተማ የአገር ሽማግሌዎች ጋር የምንገናኝበትና ሥምምነት የምናደርግበት መርሃ ግብር አለ፡፡ ችግኞቹንም ለወጣቶች አደራ ሰጥተን አስረክበናል፡፡ ለአቶ ኦባንግ ሜቶ ስነግረው የነበረውም፣ ለወደፊት ያቀድነውም፣ በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች አመራሮች የተማሪ ተወካዮች፣ የመንግስት መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ የአገሪቱ መንግስት ካቢኔዎች ባሉበት ተገኝተን፤ ለሁሉም ስለ አገራችን ሰላምና አንድነት መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን፡፡ አልቅሰን ተንበርክከንና ተዋርደን፣ በእነሱ ፊት የሰላም ጥያቄያችንን ለፈጣሪያችን እናቀርባለን:: ተማሪዎች ሊማሩ ከቤተሰባቸው ተነጥለው ሄደው ጫካ ውስጥ የሚታገቱበት ወይም ከት/ቤት ወደ ወላጅ አስክሬን የሚላክበት ዘመን ማብቃት አለበት፡፡ የዚህ ትውልድ ዘመን አሻራ ይሄ መሆን የለበትም፡፡ የአባቶቻችን አጽም እየወቀሰን ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ይህን የእልቂት ሥራ አቁሙ፤ መንግስትም በሰላማዊ መንገድ ይሸጋገር፤ የህዝብ ውሳኔ ይከበር፤ የህዝብን ውሳኔ በትዕግስት ተቀበሉ፤ ያለፈውን ይቅር ተባብላችሁ ለሰላም እጃችሁን ዘርጉ፣ ሰራዊቱም ትውልዱን በሰላም ይጠብቅ፤ አፈሙዙን ይመልስ፡፡ እያንዳንዱ ከጀርባው ያለውን ለሰላምና ለፍቅር ያሰማራ›› ብለን እንጠይቃለን፡፡ ለአገር ሰላምና አንድነት ዝቅ ማለት፤ መንበርከክ፤ መዋረድ ክብር እንጂ ማነስ አይደለም፡፡
ጐንደር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመጡት?
አዎ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የመጣሁት፡፡
እንዴት አገኙት?    
እኔ ጐንደርን በቴሌቪዥን ነው የማያት የነበረው፤ ነገር ግን ይሄ የጥንቱ ቤተ መንግስት ብቻ ነው በአብዛኛው የሚታየው፡፡ ጐንደር አሁን ያለበት ሁኔታ ለሌላው አካባቢም ለአለምም በደንብ አልታየም ብዬ አምናለሁ፡፡ ምን ችግር እንዳለ አላውቅም፡፡ የቤተ መንግስቱ አካባቢ ከከተማው፤ አንድ አስረኛ አይሆንም እኮ፡፡ እኔ መጥቼ ሳያት፤ አራት አምስት ጐንደር ነው ያለው፡፡ ለምንድነው አጠቃላይ ገጽታው የማይታይና የማይተዋወቀው? ከእድሜና ከታሪክ አንፃር አድጋለች ባይባልም፤ ያደገችውን ያህል ግን እየታየችና እየተዋወቀች አይደለም:: ይህም እንዲስተካከል አስተያየት ሰጥተናል:: በተረፈ ህዝቡ ፍቅር የሆነ ህዝብ ነው፡፡ ለዚህ ፍቅር ህዝብ የሚገባ ሥልጣኔ ነው ያኔ የነበረው፡፡ እዚህ የከተመውም በህዝቡ ባህርይ ይመስለኛል፡፡ ህዝቡ የእውነት ኢትዮጵያዊ ነው:: የአባቶቻችንንም ስራና ስልጣኔ እዚህ ከተማ ላይ አይተናል፡፡ ይሄ ትውልድ የዚያን ጊዜውን ከፍታ የሚያመጣ ያድርገው፤ ከፍታችንን ፈጣሪ ያምጣልን! እላለሁ፡፡
እኛም አገር ሰላም እስክትሆን ቀውስ እስኪበርድ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት እስኪረጋገጥ፣ በአራቱም የአገራችን አቅጣጫዎች በመዘዋወር የአንድነት የሰላምና የእርቅ ሥራችንን ያለመታከት እንቀጥላለን፡፡

Read 3120 times