Monday, 27 January 2020 00:00

የጋዜጠኛው አስገራሚ የዘገባ ገጠመኞች

Written by  መታሰቢያ ከሳዬ
Rate this item
(3 votes)

        - “ተገዳ ተደፈረች ለተባለችው ሴት አህያ” ምን ተፈረደላት?
               - ጋዜጠኛው ቤተክርስቲያን እንዳይገባ ተከልክሎ ነበር…
               - ለ12 ዓመት በስደት በኖረባት ለንደን ምን እየሰራ ነው?


         ለበርካታ አመታት ባገለገለበት የጋዜጠኝነት ሙያ እጅግ ብዙ የሚባሉ ፈተናዎችንና መሰናክሎችን አልፏል፡፡ መንግስታዊ የሆኑትን “እፎይታን” እና ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስትና የግል ሚዲያዎች ላይ ሰርቷል፡፡ በተለይም የምርመራ ጋዜጠኝነት፣ ለእሱ በእጅጉ የሚመቸውና በርካታ ዘገባዎችን የሰራበት የጋዜጠኝነት ዘርፍ ነው፡፡ ከምርመራ ዘገባዎቹ የተለያዩ ችግሮች ደርሰውበታል፡፡ የ1997 ምርጫን ተከትሎ በአገሪቱ በተፈጠረው ችግር ፈተናዎቹን ተቋቁሞ በአገር ውስጥ የመቆየቱን ጉዳይ የማይታሰብ አደረጉት፡፡ ጓደኞቿ ሲታሰሩ ሲንገላቱና ሲሰደዱ እያየ መቀመጡ አልሆነለትም፡፡ በወቅቱ የነበረው ብቸኛው ምርጫ ስደት ነበር - ወደ ለንደን በስደት ሄደ፡፡ ከ12 ዓመታት በላይ በስደት በኖረባት ለንደን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በሙያው ሲሰራ የቆየ ሲሆን ሉሲ ሬዲዮ የተባለ የራሱን ሬዲዮ ጣቢያ ከፍቶ ላለፉት 10 ዓመታት እየሰራ ይገኛል፡፡ ስደተኛው ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ፡፡ ዘውዱ ሰሞኑን ከፋና ቴሌቪዥን ጋር አንድ ውል ለመፈፀም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በነበረበት ወቅት ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ ጋር ቆይታ አድርጐ ነበር፡፡  



               ምርጫ 97 ላይ ታዛቢ ነበርክ፡፡ በምን አግባብ ነው ለታዛቢነት የተመረጥከው?  በምርጫውስ ምን ታዝበህ ነበር?
ሲአርዲኤ በሚባለው ድርጅት ነው የተመረጥኩት፤ ከእነ አና ጎሜዝ ግሩፕ ጋር፡፡ መጀመሪያ የሄድነው ወደ ደሴ ነበር፡፡ ባህር ዳርና ጎንደርም ከሄድንባቸው ቦታዎች ውስጥ ነበሩ። ሕዝቡ ሌሊቱን ሙሉ ድምፃችንን ሳናስቆጥር አንሄድም ብሎ ይጠብቅ ነበር። ተዘዋውረን ባየንባቸው ቦታዎች ላይ ሁሉ የሕዝቡ ስሜት በጣም አስገራሚ ነበር። ከእኛ ጋር የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ነበሩ - የምርጫውን ውጤት የሚዘግቡ፡፡ ጋዜጠኞቹ ጠዋት ጀምረው በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ውጤቶችን ሪፖርት ሲያደርጉ ቆዩ፡፡ በሁሉም ስፍራዎች ኢሕአዴግ ተሸንፏል። እነሱም ይህንኑ ሪፖርት እያደረጉ ነበር፡፡ በኋላ ግን ጋዜጠኞቹ ሪፖርት ማድረጉን እንዲያቆሙ ታዘዙ፡፡ ጠዋት ተነስተን ጎንደር ሄደን፤ ጎንደርም ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር:: ባህር ዳር ስንገባም ኢሕአዴግ በሰፊ ልዩነት በቅንጅት ተሸንፎ ነበር፡፡ ወረቀቶቹ ሁሉ ተለጥፈው አልቋል ኢሕአዴግ መሸነፉ ማለት ነው፡፡ ማታ ላይ ዜና ለማዳመጥ ስንሰበሰብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወጥተው “በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል ኢሕአዴግ አሸነፈ” ሲሉ ተናገሩ፡፡ ሕዝቡ ቀድሞ በሰማው ውጤት ተደስቶ የቅንጅትን ማሸነፍ ለማክበር እየጠጣና እየተዝናና በነበረበት ሁኔታ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደዛ ማለት የሕዝቡን ስሜት በእጅጉ አስቆጣው፤ እናም አንድ ሰው ትዝ ይለኛል… ይጠጣ የነበረውን ቢራ ጠርሙስ ወርውሮ ቴሌቪዥኑን ሰበረው፡፡ ሁኔታው ሲባባስና ግርግሩ ሲጨምር እኛ ወጥተን ወደ ማደሪያ ክፍላችን ሄድን፡፡
ከምርጫ 97 በኋላ ነው ከአገር የወጣኸው:: ከአገር ለመውጣትህ ዋንኛ ምክንያትህ ምን ነበር?
ከምርጫ 97 በኋላ ነገሮች ይበልጥ እየተበላሹ ሄዱ፡፡ በርካታ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳረጉ፡፡ ብዙ ጋዜጦችም ታገዱ፡፡ ሥጋቱ እየተባባሰ ሄደ፡፡ ስለዚህም በጓደኞቼ ላይ የደረሰው እስርና ችግር እኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ከአገር መውጣት እንዳለብኝ ወሰንኩና በጀርመን በኩል እንግሊዝ ገባሁ፡፡ እንግሊዝ አገር እጄን ሰጥቼ የመኖሪያ ፈቃድ ፕሮሰስ ጀመርኩ፡፡ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ፈቃዱ ተሰጠኝ፡፡ በእንግሊዝ አገር ለነበረው የመኖሪያ ፈቃድ ጥያቄ ፕሮሰስ እዚህ አገር እያለሁ የሰራኋቸው ዘገባዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያለ የተዛባ ፍትህ ያለበት አገር ላይ እንዴት መስራት ይቻላል? በሚል ሀሳብ የፈቃድ ጥያቄዬን ተቀብለው፣ አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ የመኖሪያ ፈቃዴን ሰጡኝ:: ይኸው እንግዲህ ላለፉት 12 ዓመታት ለንደን ውስጥ እየኖርኩ ነው፡፡
ለንደን ውስጥ በሙያህ እየሰራህ ነው፡፡ የራስህ የሬዲዮ ጣቢያም አቋቁመሃል፡፡ ይህንን እድል እንዴት ልታገኝ ቻልክ?
እዚህ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማርኩት ጋዜጠኝነት ነበር፡፡ እዛ ከሄድኩ በኋላም ይህንኑ ሙያ ተማርኩ፡፡ ከዛም ቢቢሲ የተማርኩትን ሙያና የሰራኋቸውን ነገሮች አቀረብኩና እንዲቀጥሩኝ ጠየኩ፡፡ አንዳንዴ የዕድል ጉዳይ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ብቃት ቢኖርሽ፣ ምንም ያህል ነገር ብትሰሪ፣ በሙያሽ ስራ ላታገኚ ትችያለሽ፡፡ ፒኤችዲ ይዘው መኪና የሚያጥቡ፣ ኪችን ውስጥ የሚሰሩ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡ እናም አንዳንዴ ዕድልም ነው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ደፍሮ የመጠየቅ ነገር ነው እንጂ በሙያ ሥራ ማግኘት የማይታሰብ ነው። ምናልባት ሕክምና ካጠናሽ ነው ስራ የማግኘት ዕድል የሚኖርሽ፡፡ እናም ቢቢስ ለ6 ወር ያህል የኮንትራት ስራ ቀጠሩኝ፡፡ እሱን ከሰራሁ በኋላ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ ሳስብ ቆየሁና የራሴን የሬዲዮ ጣቢያ መክፈት እንዳለብኝ አሰብኩ:: እዛ አገር የአማርኛ የሬዲዮ ጣቢያ የለም፤ ስለዚህ እሱን መጀመር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ከዛ ፈቃድ አወጣሁ፡፡ ቢቢሲ ስሰራ የሚያውቁኝ ሰዎችም ረዱኝ፡፡ ብዙ ገንዘብ ስለሚጠይቅ ፈንድ ማግኘት ነበረብኝ፡፡ በተለይ ጃማይካዎች በጣም አገዙኝ፡፡ “ሉሲ ሬዲዮ” በሚል ፈቃድ አወጣሁ፡፡ ቢቢሲም መሰረቴ፣ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ውስጥ ማገልገሌ፣ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ መስራቴ፣ በጣም አገዘኝ፡፡ እዛ አገር በምንም መልኩ… በነፃም ይሁን በገንዘብ ዋናው ነገር መስራትሽ ነው የሚፈለገው፡፡ ይህ በጣም ያግዝሻል፡፡ እንደኛ አገር ደብዳቤ፣ ሄዲንግ ፔፐር፣ ማህተም የሚባል ነገር የለም፤ አንድ ሰው ሪኮመንድ ካደረገሽ በቂ ነው፡፡ ከዛ የሬዲዮ ጣቢያው ተከፈተ አሁን አስረኛ ዓመቱን ይዟል። እስካሁንም እሱን እየሰራሁ ነው፡፡
እዚህ እያለህ በጋዜጠኝነት ስትሰራ፣ ከዘገባዎችህ ጋር በተገናኘ ብዙ አስገራሚ ገጠመኞች እንዳሉህ ሰምቻለሁ…
በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ በርካታ ገጠመኞች ይኖራሉ፡፡ ስራችንም ለየት ላሉ ገጠመኞች የተጋለጠ ነው፡፡ እንዳው ትዝ የሚሉኝን ላጫውትሽ፡፡ ሁልጊዜም የማይረሳኝ አንድ አስገራሚ የፍርድ ውሣኔ ነበር፡፡ ክልሉን መጥቀስ አሁን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል:: ጉዳዩ እንኳንስ በሕግ ባለሙያ በማንም ስለ ህግ ዕውቀት የለኝም በሚል ሰው እንኳ ሊሰጥ የማይችል እጅግ አስገራሚ ውሳኔ ነበር:: በእንስሳ ላይ የተሰጠ ውሣኔ ነው፡፡ “አንድ ወንድ አህያ ሴት አህያን አስገድዶ ደፈረ” የሚል ክስ ነበር የቀረበው፡፡ ከሳሽ የሴቷ አህያ ባለቤት ነበር:: “ወንዱ አህያ አህያዬን አስገድዶ በመድፈር ጉዳት ያደረሰባት ስለሆነ ለደረሰባት ጉዳት የወንዱ አህያ ባለቤት ካሳ ሊከፍለኝ ይገባል” የሚል ነበር ክሱ፡፡ የወንዱ አህያ ባለቤት በክሱ በጣም ግራ ተጋባ፤ “ምንድነው የምታወሩት? ይህ እንዴት ካሳ ሊቀርብበት የሚገባ ጉዳይ ሆነ? ብሎ በጣም ተከራከረ፡፡ ሆኖም ፖሊሶች ተከሳሹንም ደፈረ የተባለውን አህያም ወስደው አሰሩዋቸውና፣ ፍርድ ቤት አቀረቧቸው:: ክርክሩ ቀጠለ፡፡ የወንዱ አህያ ባለቤት በሁኔታው በጣም በመበሳጨቱ፤ የደረሰውን ጉዳት መጠን የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ ይምጣልኝና ካሳውን እከፍላለሁ” አለ፡፡ ክስ አቅራቢው የሴቷ አህያ ባለቤትም “እዚህ አገር ያሉ የእንሰሳት ሃኪሞች ይህንን ዓይነት የሕክምና ማስረጃ ለመስጠት አቅሙ ስለሌላቸው አህያዋ ተጭና ወደ ደብረ ዘይት የእንስሳት ሕክምና ተቋም ሄዳ እንድትመረመርና ማስረጃው እንዲሰጠኝ?” የሚል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ሁኔታው የወንዱን አህያ ባለቤት በእጅጉ አበሳጨው:: ሆኖም ምንም ማድረግ አይችልም ነበርና፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ እቀበላለሁ ይላል፡። ዳኛውም የወንዱ አህያ ባለቤት፣ ተገዳ ተደፈረች ለተባለችው ሴት አህያ ባለቤት 425 ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም የጉዳት ካሳ እንዲከፍል ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ አህያዋ በዛን ወቅት ብትሸጥ አንድ መቶ ብር እንኳን አታወጣም ነበር፡፡ የወንዱ አህያ ባለቤት በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ይጠይቃል:: ይህ ጉዳይ ነው እንግዲህ ለእኔ የደረሰኝ፡፡ ጉዳዩን ተከታትዬ ከአህያው ባለቤት፣ ከፖሊስ ጣቢያው፣ ከአካባቢው ሰዎችና ስለ ጉዳዩ ከሚያውቁ መረጃዎችን አሰባስቤ፣ ውሳኔውን የሰጠው ዳኛ ጋር ገባሁ፡፡ “እንዴት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ልትሰጥ ቻልክ” ብዬ ጠየኩት፡፡ “በአገራችን የፍታ ብሔርም ሆነ የወንጀል ሕግ ላይ በእንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ክስ ሊቀርብም ሆነ ተከሳሹን ሊያስቀጣ የሚችል ጉዳይ የለም፤ እናም በምን መነሻ ይህንን ውሳኔ ልትሰጥ ቻልክ?” ስል ጠየኩት፡፡ “አንተ ለመሆኑ ማነህ? አለኝ፡፡ ጋዜጠኛ መሆኔን ነግሬ መታወቂያዬን አሳየሁት፡፡ “ውሰዱና  እሰሩት” ሲል አዘዘና ወስደው አሰሩኝ፡፡ ያለሁበት ቦታ ከአዲስ አበባ ክልል ውጪ ስለሆነ መታሰሬ ለምሰራበት “እፎይታ” መጽሔት እንዲደርስልኝ አደረኩ:: በወቅቱ አለቃዬ ተስፋዬ ገብረአብ ነበር:: እሱ ደውሎ ተናግሮ እንድፈታ ተደረኩኝ፤ እንደተፈታሁ ጉዳዩ በይግባኝ ወደ መጣበት ወደ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሄድኩና ጠየኩ፤ ገና እንዳልደረሳቸው ነገሩኝ፡፡ ከዛም እኔ ጉዳዩን በምሰራበት “እፎይታ” መጽሔት ላይ ዘገብኩት:: ኢትዮጵያ ሬዲዮ ደግሞ ጉዳዩን ከጋዜጣው ላይ ወስዶ ዘገባው፡፡ ከዛ በኋላ በክልሉ መንግሥት ፕሬዚዳንት ትዕዛዝ ተያዝኩና ታሰርኩ፡፡ የክልሉን ስም አጥፍተሃል ተብዬ ማለት ነው፡፡ ከዛም የክልሉ ፕሬዚዳንት ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ሲደወልባቸው፣ ፈርተው ከእስር እንድፈታ አደረጉኝ፡፡ ይህም ፍትህ ምን ያህል የተዛባ እንደነበር የሚያመላክት ጉዳይ ነው፡፡
ከለንደን ካፌ ጋር የተያያዘ ዘገባም እንዲሁ ለችግር ዳርጎህ ነበር ይባላል?
አዎ፡፡ የለንደን ካፌው ጉዳይ ደግሞ የገጠመኝ “ኔሽን” ጋዜጣ ላይ ስሰራ ነው:: ለንደን ካፌ የነበረበት ቦታ የኪራይ ቤቶች ሕንጻ ላይ ነው:: ስፍራው የሕንጻዎቹ ግሪን ኤሪያና የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ነበር፡፡ የለንደን ካፌ ባለቤት ቦታውን ይገዙና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አርማን የለጠፈውን አውሮፕላን አቁመው፤ ሥፍራውን የመጠጥና ሌሎች ነገሮች መሸጫ ሥፍራ አደረጉት፡፡ እንግዶች መኪና ውስጥ ሆነው እየተስተናገዱ፣ ከኢትዮጵያዊያን ባህልና ሥርዓት ውጪ የሆኑ ነገሮችን እየፈፀሙ ይዝናኑበታል፡፡ ይህ ሁኔታ በአካባቢው ሕንጻዎች ላይ በሚኖሩ ነዋሪዎች ውስጥ ቅሬታን ፈጠረ፡፡ ልጆች የሚጫወቱበት ስፍራ በለንደን ካፌው ስለተወሰደባቸው፣ በሕንጻው ላይ ሆነው ቁልቁል የሬስቶራንቱ እንግዶች በመኪናቸው ውስጥ ሆነው የሚሰሩትን ከባህላችን ያፈነገጠ ድርጊት ማየት የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ሆነ፡፡ በሁኔታው የሕንጻው ነዋሪዎች በእጅጉ ቅር በመሰኘታቸው ጉዳዩን ለሚመለከታቸው አካላት አመለከቱ፤ ምላሽ ማግኘት ግን አልቻሉም፡፡ ስለ ጉዳዩ ጥቆማ እንደደረሰኝ መረጃዎችን መሰብሰብ ጀመርኩ:: ከነዋሪዎቹ ጀምሬ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሁሉ አነጋገርኩና በመጨረሻ ወደ ለንደን ካፌ ሄድኩኝ፡፡ የካፌው ሥራ አስኪያጅ ስለዚህ ጉዳይ ምላሽ መስጠት የሚችሉት ባለቤቱ ናቸው:: ለእሳቸው እንነገርልሃለን” አለኝ፡፡ ከቀናት በኋላ የካፌው ባለቤት ደውለው እንደሚፈልጉኝ መልዕክት ተውሉኝ፡፡ እኔ ቀደም ብዬ ንግድ ሚኒስቴር፣ ኪራይ ቤቶች፣  አየር መንገድ ሁሉ ኢንተርቪው አድርጌ መረጃዬን ሰብስቤአለሁ:: የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የሕዝብ ሀብት የሆነውን የአየር መንገድ ሎጎ በአንድ ግለሰብ ንግድ ቤት ላይ ተለጥፎ እንዲሰራበት የፈቀደው በምን አግባብ ነው? ኪራይ ቤቶችስ የሕዝብ መገልገያ ግሪን ኤሪያን በምን አግባብ ለካፌው ሊሰጥ ቻለ? ለሁሉም ጥያቄዎቼ የተሰጠኝን ምላሽ አሰበስቤ ይዤ፣ የካፌውን ባለቤት ያገኘኋቸው  በመጨረሻው ሰዓት ላይ ነው፡፡  በስልክ በተሰጠኝ ቀጠሮ ወደ ካፌው ሄድኩ፡፡ ወደ አንድ ክፍል አስገቡኝ፡፡ ከዚያም “በል በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረፅከውን ድምጽና ያነሳኸውን ፎቶ ሁሉ አምጣ” ተባልኩ፡፡ “አንተ ማነህና ነው እንዲህ አይነት ሥራ የምትሰራው” ተባልኩ፡፡ ከዛ ሌላ እርምጃ ሁሉ ሊቀጥል ሆነ፡፡ ሁኔታው እየከረረ መምጣቱን ስመለከት ከጉዳዩ ማምለጥ የምችልበትን መንገድ መፈለግ ጀመርኩ፡፡ እሳቸው ከእኔ በፊት ሌሎች ጋዜጠኞች ደውለው አስፈራርተዋቸዋል፡፡  በዚያ ተበሳጭተውም ነበር፡፡ “እኔ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ሁሉ ሄጄ ለእርስዎ ድጋፍ የሚሆን መረጃ ነው የሰጡኝ ብዬ አለሳለስኳቸው፡፡ ከዛ ይቅርታ ጠይቀው ለቀቁኝና ወደ ቤቴ ሄድኩ፡፡ ቤቴ ከደረስኩ በኋላ “ኢትዮጵስ” የምትባል ጋዜጣ ላይ ለሚሰራ ጓደኛዬ ስለ ጉዳዩ አጫወትኩት:: “ዛሬ ለንደን ካፌ በዚህ ጉዳይ ሄጄ… እንዲህ ብለው አስፈራርተው ለቀቁኝ” ብዬ ነገርኩት፡፡ የእነሱ ጋዜጣ ማታውኑ ለሕትመት ትገባ ነበር፡፡  ጠዋት ላይ ጋዜጣዊ “ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ በለንደን ካፌ ባለቤት ሊደርስበት ከነበረው የመግደል ሙከራ አመለጠ” የሚል ዜና ይዛ ወጣች፡፡ ሁኔታው በወቅቱ በጣም አስደንግጦኝ ያለፈ ገጠመኜ ነው፡፡ በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ እንደምታውቂው የተለያዩ ነገሮች ያጋጥሙሻል፡፡ ያው ገጠመኞቹ አንዳንዴም ለከፋ አደጋና ጉዳት ሊዳርጉሽ ይችላሉ፡፡ ጋዜጠኛው ግን ሁልጊዜም ለሚሰራቸው ሥራዎች በቂ መረጃዎች ሊኖሩትና ሊጠነቀቅ ይገባል፡፡ በቂ መረጃ ሳይያዝ በተለይም የምርመራ ጋዜጠኝነትን መስራት ራስን ለአደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ አስታውሳለሁ አንድ ጊዜ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የተያያዘ አንድ ጥቆማ ደረሰኝ፡፡ አንድ ቄስ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ሕግና ሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ፣ ከተሰጣቸው የቅስና ማዕረግ ጋር በተያያዘ ለደረሰኝ ጥቆማ መረጃዎችን ሰብስቤ ዜናውን አጠናቅሬ ሰራሁት፡፡ በ “እፎይታ” ላይ ወጣ፡፡ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ከጋዜጣው ላይ ዜናውን ወስዶ ይዘግበዋል፡፡ በማግስቱ እኔ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ፣ ከቤተ ክርስቲያኑ እንድወጣ ታዘዝኩ፡፡ ቄሶቹ ሊደበድቡኝ ከበቡኝ፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱን ስም አጥፍተሃል ተባልኩ፡፡ “እኔ አላጠፋሁም፤ ጥፋት የፈፀመውን አንድ ቄስ ወንጀል ነው ያጋለጥኩት” አልኩ፡፡ የሚሰማኝ አላገኘሁም፡፡ በማግስቱ ጳጳሱ ጋር ገብቼ ስለ ጉዳዩ ነገርኳቸው፡፡ ይቅርታ ጠይቀው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንድገባ ተፈቀደልኝ፡፡
ከስራህ ጋር በተያያዘ ለከፋ እስርና እንግልት የተዳረግህ አጋጣሚዎች አሉ?
ያው ቅድም እንደነገርኩሽ፤ ከአህያው ጋር በተያያዘው ዘገባና በምርጫ 97 የደረሱብኝ ነገሮች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው የጋዜጠኝነት ሙያ ፈተና አንጻር ስታይው፣ የእኔ በጣም አነስተኛ ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣህበት ጉዳይ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ ዝርዝሩን ብትነግረኝ?
አዎ፤ አሁን ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በፋና ቴሌቭዥን “ሕይወት በአውሮፓ” የሚል በመላው አውሮፓ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመስራት ነው። ፕሮግራሙ እዚያው አውሮፓ ተሰርቶ አልቆ የሚመጣ ሲሆን ከፋና ቲቨ ጋር ፕሮግራሙን ለተመልካች ላስታላለፍ ውል ፈጽሜአለሁ፡፡

Read 13648 times