Saturday, 25 January 2020 13:14

ዩኒቨርሲቲዎች ካልተለወጡ፤ ተማሪዎቻቸው አይለወጡም

Written by  ተመስገን.ታ
Rate this item
(1 Vote)

  “በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባለስልጣን ማለት ለጥበብ፣ ለእውቀት፣ ለእውነት፣ ለፍትሕ ማስረጃ የጨበጠ፣ በአእምሮው ኃይልና በኅሊናው ንጽሕና ጓደኞቹ ክብርን ያጎናጸፉት ነው። ለዚህም ዋልታና ማገሩ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ነው።”
    
              በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የተጀመረው የተማሪዎች ንቅናቄ መሰረቱ የሥር ነቀል ለውጥ ፈላጊነት ሲሆን የ1953ን መፈንቅለ መንግስት በመደገፍ፣ በ1957 በፓርላማው ፊት የተደረገው የመሬት ላራሹን ጥያቄ በማስተባበርና በመምራት አብዮቱን ለማዋለድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ሶሻሊስት ርዕዮት ዐለምን መሰረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ገበሬን ችግር እንፈታለን ብለው የተነሱት ቀደምት ተማሪዎች በእነ ብርሀነመስቀል ረዳና ባሮ ቱምሳ በተመሩ ሰልፎች፣ የገበሬውን ብሶት አደባባይ ላይ ቢያሰጡትም፣ ከአምስት አምታት በኋላ ወደ አደባባይ የወጣው አጀንዳ፣ የሀገሪቷ ቀዳሚ ችግር መሆኑ ታምኖበት፣ ሀገሪቷን ከባድ መስዋዕትነት ባስከፈለ የእርስበርስ ጦርነት ቢያሳልፋትም፣ ዛሬም ወላፈኑ እየገረፈን ለመኖር ተገደናል። በ1962 በልደት አዳራሽ በዋለልኝ መኮንን የቀረበው የብሔር ጥያቄ ፅሁፍ፤ ሃምሳ አመታትን ተሻግሮ፣ ዛሬም የሀገሪቷ ዋነኛ የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑ አስገራሚ ነው።
ዋለልኝ በልደት አዳራሽ የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ የሚለውን ፅሁፍ በንባብ ካቀረበ በኋላ በዕለቱ ተገኝቶ ያዳመጠ ተማሪ በአብዛኛው በተደበላለቀ መንፈስ አዳራሹን እንደለቀቀ የሚነግሩን ዓለማየው አረዳ (ዶ/ር)፤ ”ምሁሩ” በሚለው ስራቸው ነው። ከዚያን ቀን በኋላ የተፈጠረውን ሁኔታ እንዲህ በማለት ይገልፁታል፡-
“በዩኒቨርሲቲም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ በት/ቤቶች ሕይወታችን አብዛኛዎቻችን ማለት ይቻላል፣ ለየግል ነገዳዊ ማንነታችን ብዙም ትኩረት ሳንሰጥ ወይም እንዳንሰጥ ተደርገን ያደግን በመሆናችን፣ ነገዳዊነትን በሆነ መልኩ የሚያንፀባርቁ ተማሪዎችን እንደ ጎጠኛ ቆጥረን ዝቅ አድርገን ስናይ፣ በይበልጥም በትግላችን ሒደት የጋራ ሀገራዊ መፈክር ይዘን ባንድነት እንጮህ፣ እንፈክር፣ እንዘምር ወዘተ--᎐የነበርን ወጣቶች፣ ከዚያች እለት በኋላ አንዳችን የሌላችንን ነገዳዊ ማንነት ለማወቅ ወደ ጎን መተያየት የጀመርን ያህል ይሰማኛል።”
እንግዲህ ዶ/ር  እንደሚሉን ከሆነ፤ የዋለልኝን ፅሁፍ በማዳመጥ ብቻ ወደ ማመን አዘንብለዋል። የዋለልኝን ፅሁፍ እንደ አንብሮ (thesis) ብናየው እንኳ ምንም አይነት ውይይትና ክርክር ሳይደረግ ተቃራኒ ሀሳብ ወይም አንፅሮው (anti thesis) ሳይቀርብ፣ አብዛኛው ተማሪ ወደ ጎን መተያየትና የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክቶችን ወደ መቀበሉ አዘንብሏል።
“በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባለስልጣን ማለት ለጥበብ፣ ለእውቀት፣ ለእውነት፣ ለፍትሕ ማስረጃ የጨበጠ፣ በአእምሮው ኃይልና በኅሊናው ንጽሕና ጓደኞቹ ክብርን ያጎናጸፉት ነው። ለዚህም ዋልታና ማገሩ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ነው።” ይላሉ ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም፤ ሀምሳ አመታትን በተሻገረው “ዩኒቨርሲቲ ምንድን ነው?” በሚል ጽሁፋቸው። አሁን ላይ በሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች እየታዩ ላሉ ዘውጌንና ሃይማኖትን መሰረት ላደረጉ ግጭቶች፣ ከላይ በፕሮፌሰር መስፍን የተጠቀሱት እሴቶችና መርሆች ባለመኖራቸው መሆኑ ክርክር የሚያሻው ጉዳይ አይደለም። ለእነዚህ እሴቶችና መርሆች መሰረት ደግሞ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ሲሆን ይህ ልዩ የአእምሮ ነፃነት ሦስት ዋና ዋና ዘርፎች እንዳሉት ፕሮፌሰሩ በፅሁፋቸው ገልፀውልናል። አንደኛው የንግግር ነፃነት ነው፤ ሁለተኛው የመጻፍና የማሳተም ነፃነት ነው፤ ሦስተኛው የድርጅትና የማህበር ማቋቋም ነፃነት ነው። እነዚህን ሦስት የነፃነት መሰረቶች፣በእኛ ሀገር ዩኒቨርሲቲዎች በቀን ፋኖስ ይዘን ብንዞርም አናገኛቸውም። ከራሴ ተሞክሮ ስነሳ የመጀመሪያ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኜ፣ የዶርመንተሪ ህንፃ መግቢያ ላይ የተለጠፈ ሦስት ማስጠንቀቂያ ሁሌም ያስገርመኝ ነበር።
በዶርም ውስጥ ምንም አይነት የፖለቲካ ውይይት ማድረግ አይቻልም ሲሆን፤ እንግዲህ አስቡት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ስለ ሀገሩ ፖለቲካ ካልተወያየ ማን ሊወያይ ነው?
በዶርም ውስጥ ምንም አይነት የሀይማኖት ክርክር ማድረግ አይቻልም ሲሆን፤የዚህ ማስጠንቀቂያ ሀሳብ ምን አልባት ብዙ ጊዜ እኛ ሀገር የሀይማኖት ክርክር ሲባል ከስብከት ጋር በማገናኘት፣ አንድ ሀይማኖት ከሌላው ሀይማኖት በልጦ በመገኘት ምዕመናን ከማሰባሰብ አንፃር እንጂ በሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መነፅር የማየት ልማድ ስለሌለን ይመስለኛል። አሁን ላይ የሚታዩ የሃይማኖት ግጭቶችም የዚሁ ውጤቶች ይመስሉኛል።
በዶርም ውስጥ ምንም አይነት ብሔርን መሰረት ያደረገ ክርክር ማድረግ አይቻልም ሲሆን፤ የዚህም ማስጠንቀቂያ ሀሳብ ከላይ ስለ ሀይማኖት ባነሳሁት መንገድ ከሆነ ውጤቱን እያየነው ነው። ነገር ግን በአንድ ሀገር ልጅነት እሳቤና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ውይይት ማድረግ ባህልን ለመወራረስና ወንድማማቻዊ ትስስርን ለማጥበቅ ወሳኝ ሚና አለው ብዬ አምናለሁ።
የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለእውነትና ፍትህ የቆመ፤በእውቀት ላይ ተመስርቶ ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ምልከታዎችን ማቅረብ የሚጠበቅበት እንደመሆኑ፣ እነዚህን የመናገርን ነፃነት የሚገድቡ አፋኝ ህጎችን ሳንሻገር የመጻፍና የማሳተም ነፃነት እንዲሁም የድርጅትና የማህበር ማቋቋም ነፃነት ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ከላይ የገለፅኳቸው አይነት ህጎችን በመለወጥ እንዲሁም እውነትንና ማስረጃን መሰረት ያደረገ ውይይትና ክርክር እንዲጎለብቱ፤ ልማድ እንዲሆኑ፤ የንባብ ባህል እንዲያድግ ባጠቃላይ ምክንያታዊ ማህበረሰብ እንዲገነባ ዩኒቨርሲቲዎች ሊሰሩ ይገባል።
ሌላው ሀገሪቱን እየናጣት ያለው ዘውጌን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም፤ በዩኒቨርሲቲዎችም መዋቅሩን መዘርጋቱ ለግጭቶች መፈልፈል አብይ ምክንያት ሲሆን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቆሙለት የአለም አቀፋዊነት መርሆች እንዳይበለፅጉ ትልቅ ማነቆ ሆናል። ዩኒቨርሲቲዎች አለም አቀፋዊ ተቋማት እንደመሆናቸው የሚዋቀሩበት መዋቅራዊ ቅርፅም በእነዚሁ መርሆች መሰረት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ዩኒቨርሲቲዎቻችን፤ አሁን የተዋቀሩበትን ዘውጌን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት በማፍረስ እውቀትን፣ ብቃትንና አለም አቀፋዊነት መሰረት አድርገው እንደ አዲስ መደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡

Read 2046 times