Saturday, 25 January 2020 13:09

የዘመኑ የአማርኛ ግጥም ዝንባሌና ስጋቴ!

Written by  ደ.በ
Rate this item
(1 Vote)

“በወጉ ቃላት መደርደር ያልቻሉ፣ድምጽና ቃላትን፤ ቃላትና ሃረግን ማዛመድ የማይችሉ ሰዎች ገጣሚ ተብለው አንገታቸው ላይ ለባለቅኔነት
ማሳያ እስከርቭ ይጠቀልላሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ አንዳች እንኳ ንባብ ያልቀመሱና ለምዘና የሚያበቃ አቅም የሌላቸው መደዴዎችን፣ ባለቅኔ በሚል ከፈን ጠቅልለው ወደ መቃብር እየሸኟቸው ነው፡፡”
         
               የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ወቅታዊ መልክና ቁመና ግራ የሚያጋባበት ሁኔታ ላይ እንዳለ ለመናገር ብዙ አዳጋች አይመስለኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ የዘፈንና የመዝሙር ሌሪኮች የመስራት አቅም ጠፍቶ ወይም የሃገሪቱ አጠቃላይ አውድ በፈጠረው ቀውስ ከመኮረጅና ተራ ነገሮች ላይ ከመሽከርከር አልወጣም፡፡ ረዥም ልቦለዱም ቢሆን በተወሰኑ ጸኃፍት፣ ለዚያውም በድህረ ዘመናዊ ሥነ ጽሑፍ ተቀንብቧል፡፡ ይሁንና የዛሬው ዐቢይ ጉዳዬ ይሄ አይደለም፡፡
ዛሬ የኮረኮረኝ በየቦታው እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል፣ ቦግ ብሎ እንደሚጠፋ ነበልባል፣ አደባባይ ላይ ተንጣጥቶ፣ ፍም እያጣ ያለው የግጥማችን ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ለመናገር፣ በሃገራችን ኢትዮጵያ እንደዚህ ዘመን ግጥም አንገቱን የመዘዘበትና ምላሱን ያረዘመበት፣ አደባባዩን የወረሰበት ጊዜ የለም:: በርካታ ገጣሚያን የህትመቱን ሰፈር ሸፍነው መታየታቸውም ለማንም እንግዳ ነገር አይደለም:: ከዚያ ሁሉ የወረቀት ክምር ፍሬው ስንት ነው? ሲባል ግን ለመናገር የሚያስፈራ የገለባ ክምር መሆኑ ይሰቅቃል፡፡ አንዳንዶቹ እንኳን ለገበያ ሊወጡ ነፍስ ላለው ጓደኛ ሊነበቡም የሚያሳፍሩ ናቸው፡፡ ይህን ለመዳኘት ደግሞ ወደ ጠለቀ ግምገማ፣ የግጥም ባህርያትና አላባውያን መግባት አያስፈልግም፤ ዜማና ቤት አመታት፣ የዘይቤ ልቀትና ድምቀት መመዘን አያሻም፡፡ ለዚያ የሚበቁት በአጠቃላይ ሃያ እንኳን አይሆኑም፡፡
የግጥም ምሁራኑ እንደሚሉት፤ ለተማረና ላልተማረ፣ ለወጣትና አዛውንት፣ ለሴትና ለወንድ በቂ ስሜት የሚሰጥ፤ ለሰው ልጆች ነፍስ ቅርብ የሆነ የጥበብ ቤተሰብ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑትና በግጥም ላይ ጥናት ያደረጉት  ሮበርት ሂሊየር፣ ይህን በሚመለከት በግርድፉ እንዲህ ይላሉ፡-
“ግጥም ሁለንተናዊ ቋንቋና ሰብአዊ መግባቢያና ተሰጥዖ ነው፡፡ ጥንታዊው ሰው ጀምሮት፣ ዘመናዊው ሰው ተቀብሎ፣ በራሱ ዘመን ዐውድ አበልጽጎ፣ በየራሱ ቅኝት የሚጠቀምበት ጥበብ ነው፡፡ በሁሉም ሀገር፣ በሁሉም ዘመን ግጥም ይጻፋል፤ይደመጣል፤በየትኛውም ሁኔታ፣ በየትኛውም ደረጃ ያሉ ሰዎች ለግጥም ጆሯቸው ክፍት፤ልባቸው ቅርብ ነው፡፡ ባላገር ውስጥ ካለው ፊደል ያልቆጠረ አንስቶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ እስካለው ፕሮፌሰር፤ ከተራዋ መንደርተኛ እስከ ሃገር መሪው --- በግጥም ተመሳጭና ለዜማ ስስ ናቸው፡፡ በዕድሜም የእናቱን ጡት ከጨበጠው ሕጻን፣ ምርኩዝ እስከ ጨበጡት አረጋዊ በግጥም ማላይ ናቸው፡፡”
ግጥም፤ አስተማሪም ሰባኪም አይደለም የሚሉት ደግሞ አሜሪካዊው የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ፔሪኒ ናቸው፡፡ ከሌሎች ዝርው ጽሁፎች የሚለዩት በዜማቸው መሆኑን ለማንም መንገር አያስፈልግም፡፡ ይሁንና ዜማ ሲፈጠር የየሃገሩ ስነ ልሳናዊ መዋቅሮች ልዩነት ማምጣታቸውን የተለያዩ አገራት  ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ የፈረንሳይና የኢጣልያ አወቃቀር፣ ከእንግሊዙ እንደሚለይና እንደሚቀልል ሮበርት ፍሮስት የተባሉት የዘመናቸው ታላቅ ገጣሚና ፕሮፌሰር በጻፉት ማስታወሻ አስፍረዋል፡፡ ሌሎችም ጸኃፍት ይህንን ሃሳብ ያጸድቃሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የእብራይስጡ ግጥም የተለየና የራሱ ዐመታት አለው፡፡ ከተለመደውና አሁን እኛና ሌሎች እንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከሚጠቀሙበት ይለያል፡፡ ምናልባት የኛ ጥንታዊ ቅኔዎች ከዚያ ጋር ተመሳሳይ አካሄድ ሳይኖራቸው የሚቀር አይመስለኝም፤ጊዜ ወስዶ ጥናት ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ኦሪትን ከመቀበሏ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ብዙ የቃላትና የሆሄያት ዝምድና እንዳለ የሚጠቁሙ ሰነዶች አሉ፡፡
ታዲያ በ14ኛው ክፍለ ዘመን በወረቀት ላይ ዳዴ የጀመረው የአማርኛ ግጥም፣ ለምን ብዙ መራመድ አቃተው? ብንል፣ ብዙ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡ ከነዚህ አንዱ ደግሞ ትኩረትና የዘመን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ዐውድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በተቋም ደረጃ፣ ለጥበቡ ቦታ ሰጥቶ የሚሰራ አለመኖሩ ስንዴውን ከእንክርዳዱ እኩል በመቀበሉ፣ አቅም ያለውና የሌለው እኩል በመዋሉ፤ ልዩነቱ እየጠፋ ጥበቡም እየረከሰና እየተናቀ ይሄዳል:: በኋላም አሁን እንደሆነው መጻህፍት ቤቶች የግጥም መጽሐፍ አንቀበልም እያሉ የገበያ በር ዘግተው፣ ማስታወቂያ መለጠፍ ይጀምራሉ:: ይህ ደግሞ ለትውልዱም ሆነ ለሥነ ጽሑፉ ትልቅ ውድቀት ነው፡፡
ዛሬ ግጥም እንደ እነ ደበበ ሰይፉ ዘመን፣ እንደ እነ ገብረክርስቶስ ጊዜ ክብር የለውም፡፡ ገጣሚውም ግጥሙም አይከበሩም፡፡ ምናልባት እንደ አዝማሪ፣ አንዳች ስሜት ማሄጃ እንጂ ፋይዳ ያላቸው ጥበቦች ሆነው አይታዩም፡፡ ወይም ግሪጎሪ ኮርሶ የተባለው ገጣሚ “in my country we honour poetry not poets” እንዳለው፣ ገጣሚውን እንኳ ባይሆን ግጥሙንም አያከብሩም፡፡
ምናልባት በእንግሊዝ የሥነ ጽሁፍ ታሪክ ማለዳ ላይ ሳንቲም ተቀብለው  እንደሚገጥሙት፣ “ministrel” እንደሚባሉት፣ ለዛዛ ፈዛዛ ሆነው ይታዩ ይሆናል፡፡ ግጥም ግን በቻይና ለሹመት የሚያበቃ፣ በስዊድን ከሰይፍ የሚያስመልጥ፣ በአሜሪካ  በፕሬዚደንት በዐለ ሲመት ያቆመ ክቡር ጥበብ ነው፡፡ በብዙ ሃገራትም እንደ ዶሮ ወጥ ቅመም ተቀምሞ፤ ሽንኩርት ተቁላልቶ፣ በዘይትና ቅቤ ተከሽኖ ሽታው ሃገር የሚያምስ፤ ትዝታው እስከ ማይጠፋ በልብ የሚቀርና ደግሞ እስኪቀመስ የሚናፍቅ እንጂ ለአዘቦት ገበያ የሚንተከተክ ሽሮ አይደለም:: ስልት ይጠይቃል፤በንባብ ያድጋል፤በክብር ጊዜ ተወስዶ ይሰራል፡፡ ምናልባትም አንድ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንዳሉት ተደጋግሞ፣ተደጋግሞ ይጻፋል፡፡
ወደ እኛ ሃገር ግጥሞች ስንመጣ፣ ባለፉት በርካታ ዐመታት፣ የሃገራችን ግጥም የሚጠቀምበት ዘውግ ሌሪክ ሲሆን ባብዛኛው ስሜት ጠገብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሃዘንና ደስታን፣ሙሾና ሽለላን ያጠቃልላል:: አጀማመሩም ከመዝሙር ጋር የተቆራኘ፣ ስያሜውም የሙዚቃ መሳሪያ የወለደው ነው:: ኤክስ ጄ ኬኔዲና አጋራቸው በጻፉት መጽሐፍ እንደሚያስረግጡት፤ ከ500 ዐመታት በፊት ለጽሁፍ ጠቀሜታ የዋለና በኋላ የህትመት ግጥሞች ቤተሰብ ሆኖ የተቆጠረ ነው፡፡ ስለዚህም የቃላት ሸክሙን ቀነስ አድርጎ፣ ጠለቅ ያለ ሃሳብና ፍልስፍና የያዘ ውስብስብ ስሜትን ለመግለጥ ጥቅም ላይ መዋል ጀመረ፡፡ የአማርኛ ሥነ ግጥም መጽሐፍ ደራሲ ብርሃኑ ገበየሁ፤ ይህን ዘውግ ‹‹ዐጭር፣ ሙዚቃዊ፣ ከመዝሙርና ከእንጉርጉሮ ጋር የተያያዘ፣ እጅጉን ስሜት ንክር ነው፡፡›› ይለዋል፡፡
ተፈጥሮ፣ ሕልም፣ ብሄራዊ ኩራት፣ ጓደኝነት፣ አርበኝነት ወዘተ ከዚህ ጋር ስለሚዛመድ ለኛ ሀገር ገጣሚ ጥሩ ምርጫ ይመስላል፡፡ ከተረት ወዳድነታችን ጋር የሚያያዘው ተራኪ ግጥም፣ በተለይም ኤፒክ እየከሰመ መምጣቱ ግን የዘመናችንን ሥነ ልቡና እንድንፈትሽ ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡ ሙሾ በመባል የሚታወቀው የሌሪክ ዘውግም ምናልባት በሙዚቃው ሌሪኮች ብቅ ብቅ ከማለቱ ውጭ ጭር ያለ ይመስላል:: ገጣሚዎቻችን ይህንንና መሰል መልካዎችን እየፈተሹ መሆኑን የሚያስጠይቅ ይመስላል፡፡
ይሁንና የዐለምን የግጥም የጥበብ ዘውድ የጫኑት በሌሪክ ዝርያ በተለይም ኢጣልያ ውስጥ በተወለደው ሶኔት ነው፡፡ ሼክስፒርን፣ጆን ኬትስንና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሂልየር፤ ጆን ሚልተንን በኤፒክ የሚደርሰው የለም ይበሉ እንጂ ሌሪኩንም የሚያደንቁለት ሞልተዋል:: እኛ ጋ ግን አንድ ቦታ ረግቶ በያዘው መንገድ ጸንቶ፣ ምሳሌ የሚሆነን ሰው በዚህ ዘመን አልታይ እያለ ነው፡፡ ፌስ ቡኩ ካላባተለው፣ ገጣሚ አሌክስ አብርሃም ተስፋ ያለው ይመስላል:: የዘመኑ ባተሌነት፣ የኢኮኖሚው ጉዳይ ትልቁ ተግዳሮት ነው፡፡ በዚያ ላይ ከላይ እንዳልኩት፣ የኛ ሃገር ግጥም የግብር ይውጣ ስራ የሆነ ይመስላል፡፡ ሁሉም ሰው ገጣሚ ነኝ ይላል፤ ሁሉም ሰው መጽሃፍ ያሳትማል፤ሁሉም ሰው ሾላ በድፍን ግጥምን ይገመግማል:: ተዋናዩ፣ ነጋዴው፣ ጋዜጠኛው ያለ ምንም ሀፍረት፣ በምን መመዘኛ እንደመዘነ ሃላፊነት ሳይሰማው፣ ወዳጁንና ዘመዱን ያነግሳል፡፡ በወጉ ቃላት መደርደር ያልቻሉ፣ ድምጽና ቃላትን፤ ቃላትና ሃረግን ማዛመድ የማይችሉ ሰዎች ገጣሚ ተብለው አንገታቸው ላይ ለባለቅኔነት ማሳያ እስከርቭ ይጠቀልላሉ፡፡ የባሰባቸው ደግሞ አንዳች እንኳ ንባብ ያልቀመሱና ለምዘና የሚያበቃ አቅም የሌላቸው መደዴዎች፣ ባለቅኔ በሚል ከፈን ጠቅልለው ወደ መቃብር እየሸኟቸው ነው:: በሽንገላ ብቻ ሳይሆን ግጥም ማለት ምን እንደሆነ፣ምንና ምን ማሟላት እንዳለበት ባለማወቃቸው፣ በግጥም አደባባይ ውለው፣ ለጥበቡ ባይተዋር የሆኑትን መቁጠር ያታክታል፤ ያሳዝናል፤ ያስለቅሳል!!
አዎ፤ ግጥም ለመጻፍ መማር ግድ አይደለም:: ይህንን ሊውኖራ ስፔየር የተባሉት እንስት ፕሮፌሰር ‹‹Teaching poetry›› በሚለው ጽሁፋቸው አጥብቀው ተናግረውታል፡፡ ንባብ ግን ለገጣሚና ደራሲ መተኪያ የለውም:: ቢያንስ ድምጽን ከፍና ዝቅ የሚያደርጉ አናባቢዎችን፣ የድምጽ መፈጠሪያ (መካነ ድምፆችን) ማወቅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ በቤት አመታት ላይ ያላቸው ሚና ቀላል አይደለምና!! ምጣኔና ምት ስለማያውቁ ብዙ ገጣሚ ነን ብለው የሚያስቡ ሰዎች፤ በጭብጨባ ስካር የሚያሰባብሩት ዜማ፣ አንጀት ከማራስ ይልቅ አንጀት ያቃጥላል፡፡ በአጠቃላይ አሰነኛኘት ላይ ያለው ችግር ደግሞ ቅጥ ያጣ ነው፡፡ አንድ ገጣሚ ግጥሙን ያለ ስርዐተ ነጥብ መጽሓፍ አድርጎ ሲያሳትም ለአሰነኛኘት ያለውን ዕውቀት የሚያሳይ ነው፡፡ ከአንጓ ወደ አንጓ በሚደረገው ሽግግር ያለውን ክፍተትና ትንፋሽ አለማወቅ ለግጥም ባይተዋር መሆንን የሚያሳይ ነው፡፡
በሌላ በኩል፤ በሃገራችን የተጀመረውና አዳራሾችን ያጣበበው ግጥምን በሙዚቃ መሳሪያ የማቅረብ ልማድ የፈጠረው በጎና በጎ ያልሆነ ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ይሁንና እንግድነቱ ለእኛ እንጂ ለሌሎች አይደለም፤ አሜሪካና እንግሊዝ ውስጥ ተቆልቶ፣ ተወቅጦ፣ ተፈልቶ የተጠጣና መቶ ዐመታትን በጥበብ ሜዳ የቆየ ነው፡፡ ስለዚህ ነገር መጽሐፍ ላይ ባነበብኩበት ጊዜ ጉዳዩ ግልጽ ባይሆንልኝም፣ እኛ ሃገር መጥቶ ሲያከራከር ይበልጥ ግልጽ ሆኖልኛል፡፡ ከዐመታት በኋላም አንድ ወዳጄ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ  ጽፎት አንብቤያለሁ:: ይሁንና በጊዜው በተቃውሞ በመጻፉ ከርሱ ጋር አልተስማማሁም ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደኛ አንባቢ ብርቅ በሆነበት ሀገር፣ አንባቢን እኛ ጋ እስኪመጣ ከመጠበቅ፣ አንባቢ ጋ ሄዶ ወደዚህ ማፍለስ ክርስቶስ ስለ ወንጌል እንዳስተማረው፣ ትምህርት ውጤት የሚያመጣ ነው ብዬ አምኜበት ነበር፡፡ እውነትም ብዙ አንባቢያንን ወደ መጻህፍት ሰፈር መንዳት ችሏል፡፡
አሜሪካዊው የስነግጥም ሊቅ ‹‹ግጥምን በሙዚቃ ማጀብ፣ አበባን ቀለም መቀባት ነው›› ያሉትን ግሳጼ ያልተቀበልኩት በሀገሬ ዐውድ መዝኜ ነበር፡፡ ይሁንና የግጥሙ ሰፈር በወረቀት ላይ የሚታተመውን ግጥም እምቅነት እያላላ፣ እየዘረጠጠና እያመነመነ መምጣቱን ውሎ ሲያድር እያየነው ነው፡፡ ከቃላት አጠቃቀምና የዘይቤ ድህነት እስከ ተሰባበረ ዜማ መውረድ፣ የዚህ ለአደባባይ የሚዘጋጅ ግጥም ዘልዛላነት ውጤት  ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ ለበርካታ ጊዜያት በነበሩኝ ቃለ ምልልሶች የአደባባይ/የጉባዔ ግጥሞች፣ አንባቢን ወደ ንባብ ማምጣታቸውን በመደገፍ ተናግሬያለሁ፡፡ በአጋጣሚ በዚህ ዓመት ከአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር የነበረኝን ቃለ ምልልስ በራሴ ፈቃድ ሰርዤ ነበር፡፡
ይሁንና አሁን አሁን የማያቸው የውድቀት ጥላዎች ነገሩን አስፈሪ እንዳደረጉት ታዝቤያለሁ:: አዳዲስ ገጣምያን በሸጋ ቀለም ብቅ ብለው፣ ብዙ የተስፋ ዛላ ይዘው ከመጡ በኋላ፣ ወደ ጉባዔው ሲወጡ፣ ዘልዛላና ልል ሲሆኑ ታዝቤያለሁ፡፡ ሌላው ቀርቶ ገጣሚ ነቢይ መኮንን በጻፋቸው ሁለት መጻሕፍት መካከል የታየው ሰፊ ልዩነት የዚሁ የአደባባይ ግጥም ዘልዛላ አካሄድ ነው:: ይህ አካሄድ ደግሞ ንዑስ ዘውጎችን እንኳ በመምረጥ ላይ ጥገኛ ማድረጉ የሚታይ ነው፡፡ እንደኔ እንደኔ፣ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራም፣ እዚያ አካባቢ ባያዘወትር እመርጣለሁ፡፡ ለጉባዔ ግጥም የሚስማማ ሁለንተና ያላቸው ሰዎች፣ ያንን መንገድ ቢጠቀሙ ግሩም ነው፡፡ በዚህ ረገድ ገጣሚ ደምሰው መርሻ የተጠቀመበትን መንገድ አድናቂ ነኝ፡፡ የራሱን አጻጻፍና ለየትኛው ተደራሲ ተስማሚ እንደሚሆን አውቆ፣ በድምጽ መጠቀሙ ትልቅ ብልሃት ነው፡፡
ስለዚህ ሌሎች ገጣምያንም እምቅ አቅማቸውን ባያባክኑና አዘውትረው በመጠቀም ጉልበታቸውን ባይመነዝሩ እመርጣለሁ:: ፓውንድና ብር፣ ዶላርና ብር በገበያ ላይ ያላቸውን አቅምና ክብር መለየት እሚከብድ አይመስለኝም፡፡ በተለይ ወጣት ገጣምያን አሌክስ አብረሃም፣ አበረ አያሌው፣ በለው ገበየሁ፣ መዘክር ግርማ፣ መስፍን ወንድወሰንና ሌሎች አቅምና ተስፋ ያላቸው ሁሉ ሚዛን እየጠበቁ ቢሄዱ፣ የዘመናችን ግጥም ባክኖ አይቀርም፡፡ እረኛ አጥቶ የተቅበዘበዘው ጥበብ፤ ወደ ክብር ማማው ይመጣል፡፡ ከጅምላ ጭብጨባና ጊዜያዊ ግርግር ይልቅ፣ ቀጣይነት ወዳለው ውበትና ግርማ መሸሽ ይሻላልና ልብ ያለው ልብ ይበል!!


Read 2260 times