Saturday, 25 January 2020 12:59

ከስሜት መፋታት!

Written by  ደራሲ - ጁሊ በርግማን ከስሜት መፋታት! ትርጉም- ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(7 votes)

  ሚስቴን በጣም ነበር የምወዳት:: ብቸኛ ወንድ ልጃችንን ካጣን በኋላ ከሃዘን ወጥታ ደስተኛ እንድትሆን ያልፈነቀልኩት ድንጋይ አልነበረም። ቤይሊ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ወይም እጦት ህይወቱ ስታልፍ ገና የ5 ዓመት ህፃን ነበር። ድህነታችን ምን ያህል የለውም - ያጣን የነጣን ድሆች ነበርን፡፡ የቱንም ያህል ብፈጋ ወይም ብተጋ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ያህል የማሟላት አቅም ኖሮኝ አያውቅም፡፡
በእጅጉ ጥፋተኛነት ይሰማኝ ነበር፡፡ የተጠያቂነት ስሜትም ክፉኛ ተጫውቶብኛል። ምስኪኗ ኤልዛቤት ግን በምንም ነገር ተወቃሽ አድርጋኝ አታውቅም፡፡ እኔም በውስጤ እሰቃይ እንደነበር ላሳያት ባለመቻሌ ይጸጽተኛል:: ሌሊት በቅዠት ስትጮህ---በላብ ስትጠመቅ----በሰቀቀን ስታለቅስ ከአጠገቧ ተለይቼ አላውቅም፡፡ ይሄ ሁሉ ስቃይና ሰቀቀን አልፎ አንድ ቀን ወደ ድሮ ማንነቷ ትመለሳለች የሚል ተስፋ ነበረኝ፡፡ ያ ቀን ግን ሳይመጣ  ቀረ፡፡
አንድ ቀን የመንደራችን ሰዎች፣ ልዩ ጥበቦችን በመጠቀም የሚፈውስ ሁነኛ ቴራፒስት እንዳለ ሲያወሩ ሰምቼ ተገረምኩ፡፡
ድንቄም ቴራፒስት! ብዬ  ማሾፌ ትዝ ይለኛል፡፡ የመንደሩ ነዋሪዎች ቀስ በቀስ መለወጥ ጀመሩ፡፡ ጠዋት ጠዋት ወደ ማዕድን ማውጫው ስሄድ፣ የዚያችን ደስተኛ ዳቦ ጋጋሪ የዘወትር ዜማ አለመስማቴ ክፉኛ ረብሾኝ ነበር። በመንገድ ላይ የማያቸው ሰዎች በሙሉ መሬት መሬቱን እያዩ ነበር የሚጓዙት፡፡ “ጤና ይስጥልኝም” ሆነ “ደህና አደራችሁ” መባባል ቀርቷል፡፡ ነዋሪው ራሱን ያገለለና የደነዘዘ ሆኗል። እያንዳንዱ ቀን አዲስ ድንዛዜን ይዞልን ነበር የሚመጣው፡፡ በየዕለቱ ከህብረተሰቡ ይበልጥ የተገለልኩ እየመሰለኝ መጣ። እኔ ብቻ ነኝ ስሜት ያለኝ ማለት ነው?
አንድ ቀን እቤቴ ስገባ ፈፅሞ ያልጠበቅሁት ዱብዕዳ ገጠመኝ፡፡ ሚስቴ ቤት ውስጥ አልነበረችም።
የምሆነው የማደርገው ጠፍቶኝ በጭንቀት ተዋጥኩኝ። በመንደሩ እየዞርኩ ሚስቴን ያየ ሰው እንዳለ ጠየቅሁኝ። ማንም አየሁ የሚል አላገኘሁም። በመንደሩ ኤልዛቤትን የማያውቃት አልነበረም። ሁሉም ይወዷት ነበር፡፡ አንዳንዴ ምግብ ሁሉ ያመጡልናል፡፡ የዚያን ዕለት ግን እሷን በመፈለግ የሚተባበረኝ እንኳን አጣሁ፡፡ ያስጨነቀኝ የሚስቴ ጉዳይ ብቻ አልነበረም፤በእያንዳንዱ ሰው ላይ የሰፈረው ግዴለሽነትም ጭምር እንጂ፡፡
በመጨረሻ ወደ ጫካው ሄጄ ልፈልጋት ወሰንኩና ነገሮቼን ልሸካክፍ ወደ ቤቴ ተመለስኩኝ። ወደ ውስጥ ስዘልቅ ትኩስ የዱባ ሾርባ ሽታ አየሩን አውዶታል። ኩሽና ሄድኩኝ፡፡ ሚስቴ የእሳት ምድጃው ጋ ቆማ ታበስላለች፡፡ ዓይኔን ማመን አልቻልኩም። ተንደርድሬ ተጠመጠምኩባትና፤ “የት ሄድሽብኝ ውዴ!?” አልኳት በለሆሳስ:: እሷም መልሳ በማቀፍ አፀፋዋን መለሰች፤ አንዲትም ቃል ግን አልተነፈሰችም፡፡  መቼም ልማረር ብል ጨርሶ አያምርብኝም፡፡ ሚስቴን መልሼ በማግኘቴ ተደስቼአለሁ::
ንግግራችን ጥቂትና ቁጥብ ነበር፡፡ ትዕግስተኛ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡ እናም ግፊት ላደርግባት  አልቻልኩም:: መጀመሪያ ላይ ያገባኋትን ሴት መልሼ እንደማገኛት ማሰቤ ድድብና ነበር:: ግን የፈጀውን ያህል ጊዜ ቢፈጅም ደስተኛ እስክትሆን ድረስ ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነበርኩ፡፡
ከዱባው ሾርባ አንድ ወር በኋላ ነበር፡፡ ለሚስቴ ስጦታ ልገዛላት ፈልጌ ለክፉ ጊዜ ያስቀመጥኩትን ገንዘብ ከመሳቢያው ውስጥ ስበረብር፣ ድንገት በቆዳ የተለበደ ማስታወሻ ደብተር አገኘሁ፡፡ የማን እንደሆነና እዚያ ውስጥ  እንዴት እንደገባ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ማስታወሻውን ስገልጠው የመጀመሪያ ገፁ ላይ የሚስቴ  ስም ተፅፎበታል፡፡ ከድኜ ላስቀምጠው ስል ከውስጡ ብጫቂ ወረቀት መሬት ላይ ወደቀ:: አንስቼ አየሁት፤ “ሊሊዝ ሲሞን” የሚል ስም ሰፍሮበታል፡፡ በመንደራችን ውስጥ ያለውን ሰው በሙሉ ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ስም የሚጠራ እንደሌለ አልተጠራጠርኩም። ወረቀቱን ስገለብጠው ከሰፈራችን የአንድ ሰዓት ጉዞ ርቀት ላይ ወደምትገኝ ትንሽዬ መንደር የሚወስደውን አቅጣጫ የሚያመላክት ካርታ ይዟል፡፡ ወደዚያ መንደር ጨርሶ ሄጄ አላውቅም። እዚያ የሚኖሩ ሰዎችን የተመለከቱ ታሪኮችን ግን ሰምቻለሁ፡፡ በእርግጥ አብዛኞቹ የተጋነኑ መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ራሴን ከፍርሃት ስሜት ማውጣት አልቻልኩም ነበር። የሆኖ ሆኖ ሊሊዝ ማን እንደሆነችና ሚስቴ ወደሷ ቤት የሚያደርሰውን ካርታ ለምን እንደያዘች ማወቅ ነበረብኝ፡፡
የዚያኑ ዕለት ለአደን እንደምወጣና አመሻሹ ላይ እንደምመለስ ለሚስቴ ነግሬያት ጉዞዬን ጀመርኩ። ለሚገጥመኝ ክፉ ነገር ሁሉ ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ እንደማልጠቀምበት ተስፋ ባደርግም በሱፍ ቦርሳዬ ውስጥ ሽጉጥ ይዤአለሁ፡፡
የእግር ጉዞው ያሰብኩትን ያህል ረዥም ባይሆንም ደክሞኝ ነበር፡፡ መንደሩ የእኛኑ መንደር ነበር የሚመስለው፡፡ ነዋሪዎቹ በውስጡ የሞቱበት መንደር! በተቻለኝ አቅም ከአካባቢው በፍጥነት መልቀቅ እንዳለብኝ አስቤአለሁ፡፡ በካርታው እየተመራሁ የሊሊዝን ቤት በቀላሉ አገኘሁት። ወደ በሩ ስቃረብ፤ “ሁሉንም ነገር መውሰድ  እችላለሁ” የሚል ማስታወቂያ አነበብኩኝ:: ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም:: ቀልቤ አካባቢውን በአስቸኳይ እንድለቅ እየነገረኝ ነበር፡፡ እናም ቶሎ የመጣሁበትን ማጠናቀቅ ነበረብኝ፡፡
በሩን አንኳኳሁ፡፡ ዕድሜዋ በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትመስል ሴት ከፈተችልኝ፡፡ ረዥም ሽበታም ፀጉር አላት፡፡ ቆዳዋ ግን አልተሸበሸበም። ረዥም የሃር ቀሚስ ለብሳ፣ አንገቷ ላይ ዶቃ አስራለች፡፡ ጣጣ ሳላበዛ  ስለሚስቴ ጠየቅኋት፡፡
“አዎ ወንድም አለም --- ኤልዛቤት ከወር በፊት መጥታ እረድቻታለሁ”
“ምንድነው የረዳሻት? ስራሽ ምንድነው?” ግራ በተጋባ ስሜት ጠየቅኋት፡፡
“ፈዋሽ ነኝ፡፡ ፈውስ እሰጣለሁ:: ያለማጋነን የሰዎችን ስቃይ እወስድላቸዋለሁ፡፡ ከዚያም እንደ ክፍያ ደስታና እርካታቸውን እቀማቸዋለሁ፡፡”
“ምን የሚሉት ፌዝ ነው?” አፈጠጥኩባት፡፡  
ሊሊዝ ዓይኔን ትክ ብላ እያየችኝ፤ “አየህ ሰዎች የስቃይ ኑሮ ይሰለቻቸዋል፡፡ በሃዘን መማቀቅ ይታክታቸዋል፡፡ እኔ ሃዘንና ስቃያቸውን እወስድላቸዋለሁ:: ግን ደግሞ ሁሉም ነገር ክፍያ አለው፡፡ የእኔ ክፍያ ደግሞ ደስታ ነው፡፡ እናም እወስድባቸዋለሁ”
“አሁን ቀልዱን ተይና የባለቤቴን ስሜት መልሽልኝ!”
“የተፈፀመ ክፍያ አይመለስም!”
የመደራደሪያ ሃሳብ ለመምጣት ከግማሽ ሰከንድ በላይ አልፈጀብኝም፡፡
“የሚስቴን ደስታ መልሽልኝና የእኔን መውሰድ ትችያለሽ” አልኳት፡፡
ሊሊዝ ፈገግ አለችና፤ “እንደዚያ ይቻላል…የሚያስከትለውን ውጤት ግን አስብበት” ስትል አስጠነቀቀችኝ፡፡
እንደ አበደ ሰው እየፈረጠጥኩ ወደ ቤቴ ተመለስኩ፡፡ ሚስቴን በፍጥነት ማግኘት ነበረብኝ፡፡ ሊሊዝ የእኔን ስሜት ከመወሰዷ በፊት ከኤልዛቤት ጋር የአንድ ቀን ጊዜ ብቻ ነው የሰጠችኝ፡፡ እናም እያንዳንዷን ሰከንድ በቅጡ ማጣጣም አለብኝ፡፡
ቤታችን  ስገባ ኤልዛቤት ጠብመንጃ ጭንቅላቷ ላይ ደግና ፊት ለፊቴ ቆማለች - ፊቷ በእንባ እየታጠበ፡፡
“የለም…የለም …እሱን ነገር ወደዛ አድርጊ!” ብዬ ጮህኩኝ፡፡
እጆቿና እግሮቿ እየተንቀጠቀጡ ነበር፤ ጠብመንጃው ግን ጭንቅላቷ ላይ እንደተደገነ ነው።
“ለምን እንዲህ አደረግህ ጆን? እኔ ላንተ ስል እኮ ነው ሁሉን ነገር የፈፀምኩት:: በሰቆቃ የተሞላሁ ነበርኩ ግን አንተም ያው እንደነበርክ አውቃለሁ፤ እኛን ለመታደግ ያደረግሁት እኮ ነው፡፡ ላንተ ስል ያደረግሁት ነው”
ጆሮ የሚበጥስ የተኩስ ድምፅ ተሰማ!!
ውድ አንባቢያን፡- ይህን አጭር ልብወለድ ከአዲስ አድማስ ድረገጽ ላይ በድጋሚ ያወጣነው ነው፡፡ እንደ 20ኛ ዓመት ትውስታ፡፡

Read 1193 times