Saturday, 25 January 2020 12:44

ሃይማኖትና ፖለቲካን የመደባለቅ ሴራ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

 በአሜሪካን ሀገር ሲኖር የገጠመውን አስገራሚ ታሪክ የጻፈው ደራሲ፤ሁሌ በሃሳብ ብቅ እያለ ይሞግተኛል፡፡ ደራሲው አሜሪካ ሀገር ተሰድዶ ሄዶ፣ ዕድሜ ዘመኑን ሲያጋምስ ሁሉ ያላወቀው ነገር ስለነበር መደነቁን ይገልፃል:: በቀደመችው ኢትዮጵያ ቅርሶች፣ መዛግብትና መጻሕፍት እንዳይወድሙ ይከላከሉ የነበሩት ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊሞች መሆናቸው ፈረንጁን ደንቆት ነበር፡፡ ነገሩን ቀድሞ ያላወቀው ደራሲም፤ ከእርሱ ይልቅ ባዕዳን፣ በጐ ነገራችንን አውቀው ማውራታቸው የቀንበር ያህል ከብዶት ነበር፡፡
ረዥም የመንግሥትነትና የሀገርነት ታሪክ ያለን ኢትዮጵያውያን፣ ብዙ የሚያስደንቁ በረከቶችና ጸጋዎችን የታደልን ነን፡፡ ይሁንና የሚያሳፍሩን ድክመቶችም ከጥንካሬያችን ጥላ ሥር ተደብቀዋል፡፡ የነዚያ አባቶቻችን ታሪክ የደነቀንን ያህል፣ ዛሬም የዚያ በጐነት እርሾ ከሥሩ ጠፍቷል ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋቢ የሚሆነን፣ አሁን በጥላቻ የሠከሩና የፖለቲካ ትርፍና የሥልጣን ወንበር የተጠሙ ጥቂቶች ሳይሆኑ፣ የሀገሪቱ አብዛኛውን ክፍል የያዘው የገጠሩ ማህበረሰብ ነው፡፡ ዛሬ ልዩነትን እያርገበገቡ እሳት የሚለኩሱ ሰነፍ ሰዎች ያሉትን ያህል፣ በቀደመ ኢትዮጵያዊ ክብርና አንድነት፣ በፍቅር የመኖር ባህል ሙስሊም ክርስቲያን ሳይሉ፣ የሁለቱንም ወገን ሃብትና ማንነት የሚያከብሩ መኖራቸውን ለማየት ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ከከተማ ወጣ ማለት በቂ ነው፡፡
ይህ መከባበር የመጣው እንደ ሰለጠነው ዓለም ግለኝነት ነግሶበት፣ እኔን አትንካኝ፣ አንተንም አልነካህም፣ በሚል ወይም ዴሞክራሲያዊ መብትን በማክበር ውስጥ የቱም ሃይማኖት የራሱን እምነት የማራመድ ነጻነት አለው በሚል የሰለጠነና በትምህርት የታገዘ ዕውቀት አይደለም፡፡ “የአንድ ሀገር ሰዎች ነን” ወይም “ፈጣሪ ለሁሉም መልካም እንድናስብ ይፈልጋል” በሚል የሃይማኖት ፈለግ ነው፡፡ በርግጥም በየትኛውም የሃይማኖት ታሪክ ቀዳሚ መሆናችን፣ ሕዝባችንን ተፈቃቅዶና ተከባብሮ በአንድነት እንዲኖር የረዳው ይመስለኛል፡፡
የዚህን ማንነት ትሩፋቶች ማግኘት ደግሞ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት፤ ከከተማ ወደ ገጠር ወጣ ብንል፣ የሙስሊሙ መስጊድ ሲሰራ ክርስቲያኑ ገንዘብ አዋጥቶ ሲሰጥ እናያለን፡፡ ግድግዳ ሲቆም ጣሪያ ሲመታ፣ ቡና አፍልቶ እንጀራ ወይም ዳቦ ጋግሮ “አሻም” ማለቱን እንሰማለን፡፡ እኔ የዛሬ ዓመት ገደማ የዚህ ዓይነት ገጠመኝ በዐይኔ አይቻለሁ:: ከአዲስ አበባ ወደ ሆሣዕና ሲኬድ አንዲት የሶዶ ወረዳ ከተማ አለች፡፡ ኬላ ትባላለች፡፡ ኬላ ከተማ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ አማኞች የሚኖሩባት ሲሆን የሙስሊሞች ቁጥር እጅግ በጣም ጥቂት ነው፡፡ እናም ሶላት የሚሰግዱበት ቦታ አልነበራቸውም፡፡
ዛሬ ግን ከአዲስ አበባ ወደ ሆሣዕና ሲኬድ፣ በቀኝ በኩል በቆርቆሮ የታጠረ የጨረቃ ምልክት ያለው ሰፊ ቦታ ታያታላችሁ፡፡ ያ ቦታ የመንግሥት አይደለም፡፡ ያንን ቦታ የሰጠው አንድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የከተማዋ ነዋሪ ነው፡፡ እንግዲህ ልብ በሉ፤ ዛሬ በጨሰ የመሬት ዋጋ፣ ሀብቱን ያለ ማንም አስገዳጅነት የሰጠው ኢትዮጵያዊ ሰው ነው፡፡ የሰጠው ደግሞ ለሙስሊም ኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ የነገረኝና ያሳየኝ ሙስሊም (በንግግሩ፣ በአስተሳሰቡ፣ በእጅጉ ሰልጠን ያለ) ወጣት ነው:: ስለዚህ ሰውዬ ሲያወራኝ፤ “ሰውየውን በዐይኔ ብቻ ላየው እናፍቃለሁ” ያለኝ፡፡
ዛሬ ዛሬ ግን ፖለቲከኞች፣ የብሔር ብሔሮችን በር አንኳኩተው አልሳካ ሲላቸው፣ ይህንን ቀዳዳ በማስፋት ብቅ ለማለት እየሞከሩ ነው፡፡ ይሁንና አሁንም ቢሆን ነገሮች ሰፍተው እንዳይሄዱ ያደረገው የትናንት አባቶቻችን ያስቀመጡልን እርሾ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ቅርስ የጠበቁ ሙስሊም አባቶች በጐነት ከቶውንም ሊረሳ አይችልምና፡፡
በቅርብ ዓመታት እንኳ በስልጣን ያበዱት የወያኔ ካድሬዎች፣ ሙስሊሙን እያሳደዱ፣ በየበዓላቱ ሲቀጠቅጡ ቤቱ እያስገባ የደበቀው ክርስቲያኑ  ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ከተለያዩ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በሚላኩ ጉርሻዎች ኪሳቸውን ያሳበጡና ሥልጣናቸውን አጥተው ቀልባቸውን የሳቱ አዛውንቶች በሚልኩት ሳንቲም፣ በህዝብ ደም የሚነግዱ ሰዎች እንዳያታልሉን መጠንቀቅና ማስጠንቀቅ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ በተለይ የወጣቶች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በስሜት ማዕበል መልህቋን እንዳትነቅል፣ ሁላችንም ከቤተሰቦቻችን ጀምረን መሥራት አለብን፡፡
አንድ ሰሞን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የብልጽግናን ፓርቲ መመስረት አሥመልክቶ የፓርቲው መሪዎች፣ በአብዛኛው ሙስሊሞች መሆናቸውን በመጥቀስ ነገር ለመለኮስ የሞከሩ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ማንም ሊሰማቸው ስላልቻለ ሌላ ቀዳዳ ፍለጋ መባተል ያዙ፡፡ እንግዲህ ሙስሊም ከሚባሉት መሪዎች አንዱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት  አቶ ሙስጠፌ ነው፡፡ ለመሆኑ ሙስጠፌን የመሰለ ድንቅ ሰው፤ በሃይማኖቱና በብሔሩ ብቻ የሚጠራ ነውን? ይገርማል! ሰውየው ለዋሾዎች ምላስ እንኳ የሚመች አይደለም፡፡ ሙስጠፌ ኢትዮጵያዊ፣ ከዚያም ያለፈ ሰው ነው፡፡ ለዚያውም የሰለጠነ አስተሳሰብ ያለው ምርጥ ሰው! ምናልባትም የዛሬ ሁለት ዓመቱ ለውጥ አመጣልን ብለን ከምንቆጥራቸው በረከቶች ውስጥ አቶ ሙስጠፌ፣ ዋነኛውና ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ከዚያም ለጥቆ የቤንሻንጉል ጉሙዙ ፕሬዚዳንትም ከቀድሞዎቹ የተሻለና የላቀ አስተሳሰብ ያለው ነው፡፡
ታዲያ የትኛውም የኔ ብሔርና የኔ እምነት ሰው ይምጣ፣ በምን ምክንያት ከሙስጠፌ በላይ ልወድደውና ልቀበለው እችላለሁ? ሰው በሚያመጣው ውጤትና ፍሬ እንጂ በብሔሩና ሃይማኖቱ ሊከበርና ሊመረጥ ይገባል ብዬ ካመንኩ፣ ከዱር አራዊቱ ጋር ለመቀላቀል አሁኑኑ ጉዞ መጀመር ሊኖርብኝ ነው፡፡ የትኛውንም ሃይማኖት ይከተል፤ ከየትኛውም ብሔር ይምጣ፣ የተመቸ አስተዳደር፣ የተሻለና ቀና አመራር የሚሰጥ ከሆነ ምርጫዬ ያ ሰው ነው፡፡ ከዚህ የወጣ ሃሳብ የሚያስቡት በመላ ሀገሪቱ ተወዳድረው የማሸነፍ አቅም የሌላቸው ሰነፎችና ደካሞች፤ “ዋርካ በሌለበት እምቧጮ አድባር ይሆናል” እንደሚባል፣ ብቻቸውን በየሠፈራቸው መንገሥ የሚፈልጉ ድንኮች ናቸው፡፡
በቡድን ማሰብና በቡድን መሾም ወንበር ያስገኝ ይሆናል እንጂ ዕውቀት አይሆንም:: ሲጀመርም ዕውቀት ያለው ሰው፣ ወይም ዕውቀቱን በተግባር ለማዋል ያዋሀደ (ጥበበኛ) ሰው ሌላውን ለማጥፋት እየሮጠ፣ እንቅልፍ በማጣት ጊዜውን አያባክንም፤ ይልቅስ በተሻለ መንገድ ሁሉንም የሚጠቅም መንገድ ፍለጋ ይታትራል፡፡
በብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ ሰሞን የተናፈሰው ወሬ ካበቃ በኋላ ደግሞ አሁን በቅርቡ፣ “አንድ የወንጌላውያን አማኝ ሰው፣ የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ሆነ” ተብሎ፣ ጫጫታና ፕሮፓጋንዳው ጦፎ  ነበር፡፡ ታዲያ ይህንን ስንፍና ምን ልንለው እንችላለን? ኢትዮጵያ ለየትኛውም ሃይማኖት ተከታይ ሀገሩ አይደለችም እንዴ? በብሔር ከፈሉና ከለሉን፤ እንደገና ሌላ የሃይማኖት ከለላ ደግሞ አሰቡልን ማለት ነው? አዲሱ ከንቲባ ዶ/ር መሀሪ ታደሰ፤ ለባህርዳር ህዝብ የሚጠቅም የትምህርት ዝግጅትና ዕውቀት ካለው፣ ሃይማኖቱ ምን ያደርግልናል? እንኳን ዛሬ፣ በንጉሡ ዘመን እኮ “ሃይማኖት የግል ነው፣ ሀገር የጋራ ነው” ተብሏል፡፡
ይህ ሁሉ ስበብ እንጂ ለህዝብ የመቆርቆር ሙሾ አይደለም፡፡ ደግሞስ በዘመነ ወያኔ ብዙ ያልተማሩ ሰዎች ሲያቦኩት የከረመውን ክልል፤ የተማረ ለዚያውም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በአሜሪካ ሀገር ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ሁለት ፒኤችዲ ያለው ብቁ ሰው፣ የባህርዳር ከተማን ቢያገለግል ክፋቱ ምኑ ላይ ነው? ዋናው ጉዳይ ሰውየው ለሀገሩ ምን ያህል ፍቅር አለው? ከተማዋንስ ይጠቅማታል ወይ? ብሎ መጠየቅ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ለመንግስት ሃላፊነት እገሌ ሙስሊም ነው፣ እገሌ ኦርቶዶክስ ነው፣ እገሌ ፕሮቴስታንት ነው ማለቱን ምን አመጣው? ለዕድገታችን በሚጠቅሙን ሃሳቦች ላይ ብንወያይ፣ የተሻለ ሀገር መፍጠር እንደምንችል እንዴት ይጠፋናል? ወይስ እየተበላላን፣ በኛ መበላላት ጥቂቶች ሆዳቸውን እያሳበጡ ቢኖሩ ነው የሚሻለው?
እውነት ለመናገር፣ በሃይማኖት ክብ ተቀምጠው፣ ነገር እያራገቡ ያሉትን ሰዎች ጀርባ ብንፈትሽ፣ በለውጡ ጓደኞቻቸው ከፍ ብለው ወደ ቤተ መንግስት የተጠጉባቸውና የተሻለ ዕድል ለማግኘት ሮጠው ያልተሳካላቸው ባከናዎች ናቸው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” በሚል የቱም ነገር ጠፍቶ እነርሱ ሹመት ያላገኙባት ሀገር፣ ዶጋ ዐመድ እንድትሆን ተራራ የሚቧጥጡ እኩዮች! በከፊልም መቄዶንያ በመግቢያቸው ዕድሜ፣ አሁንም ቤተ መንግሥት መመለስ የሚፈልጉ ቀውሶች ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡
ገጣሚ አሌክስ አብረሃም፣ የሀገር ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጐ የሚጽፍ የዘመናችን ወጣት ነው፡፡ የዛሬ ሃሳቤን እምብርት የሚነካልኝን ግጥም ወዲህ ላምጣውና እናስተያየው፡፡ “ሀገሬ ልርገምሽ” ከሚለው ግጥሙ እነሆ፡-
ፍቅር እየሰበከ፣ ከፈጣሪ ቀየ፣ ከመቅደሱ ጣራ፣
ያ የፍቅር ልሳን፣ ከቅዱስ ማጀቱ ልዩነት ከዘራ
ከሚናራው አናት ሰላም እያወጀ
ከመስጊዱ ማጀት ጥላቻ ካበጀ
ጥፋት የሰነቀ የሎጥ ዘመን ይምጣ
ጅምላ የሚጠብስ የሳት ንዳድ ይውጣ
ሕዋው ተሰንጥቆ ዲን ይዝነብ ከሰማይ፣
አዲስ ትውልድ ይትረፍ ክፋት ዞሮ ከሚያይ!
ከኋለኛው ጥፋት ምናምን ፍለጋ
ዞሮ አመድ ሚያፍስ፣
በቆመበት ያምጽ የደም እንባ ያልቅስ!
ግራና ቀኝ ማየት፣ የተናገረውን መተግበር ያቃተው ትውልድ፤ መድረሻውን ለማወቅ ሩቅ ማሰብ አያሻም፤ ሂሣብና ስሌትም አይጠይቅም::
ስለዚህ የማይረባውን ዲስኩርና ወሬ ትተን፣ ሰው ሰው ወደ ሚሸተው የሥልጣኔ ጉዞ ለመገስገስ አሁኑኑ ራሳችንን እናዘጋጅ!    


Read 1916 times