Print this page
Saturday, 25 January 2020 12:18

የውሸት አራቢ፣ የጥፋት አራጋቢ፣ የክፋት ጋላቢ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 ሁለት ልጆች ናቸው - ገና  ዘጠኝና ስምንት ዓመት ታዳጊዎች፡፡ ሆስፒታል ውስጥ፣  ጎን ለጎን አልጋ ላይ ተኝተው በየግላቸው ይቁነጠነጣሉ፡፡ ፈርተዋል። ግን፣ ‹‹ፈሪ›› እንዳይባሉ፣ ሰው እንዳያውቅባቸው፣ ስሜታቸውን አምቀው ለመደበቅ፣ ከራሳቸው ጋር እየታገሉ ነው፡፡ ተለቅ ያለው ልጅ፣ ራሱን ለማረጋጋት፣ ታናሽዬውንም ለማደፋፈር ወሬ ጀመረ፡፡
‹‹ምንህን ነው የምትታከመው?›› ብሎ ጠየቀ፡፡
‹‹ቶንሲል ታውቃለህ? መድሃኒት ይሰጡኝ ነበር፡፡ አሁን ግን፣ ቀዶ ህክምና አሉኝ›› ብሎ መለሰ አነስ ያለው ልጅ፡፡
‹‹ይሄማ ቀላል ነው፡፡ አትፍራ››
‹‹ቀዶ ሕክምና’ኮ ነው››
‹‹እኔም ቶንሲል አሞኝ ፈርቼ ነበር፡፡ ቀዶ ሕክምና ብለው አስተኙኝ፡፡ ማደንዘዣ… ምናምን ብለው፣ ምንም ሳይታወቀኝ፣ አለቀ፡፡ ሚጣፍጥ ከረሜላ ነገር ሰጥተው፣ በ10 ደቂቃ ወደ ቤቴ… በቃ፡፡ ምንም አያምም›› አለ ተለቅ ያለው ልጅ፡፡
አነስ ያለው ልጅ፣ ዘና አለ፡፡
ዘና ብሎም ‹‹አንተስ ምንህን ልትታከም ነው?›› ብሎ ጠየቀ፡፡
‹‹ለመታከም ሳይሆን፣ ለመገረዝ ነው››
‹‹ተውንጂ! እኔኮ ተገርዣለሁ፡፡ ግን ስለመገረዝ ስሰማ፣ በፍርሃት እንቀጠቀጣለሁ››
‹‹መገረዝ ያማል እንዴ? እውነቱን ንገረኝ፡፡››
‹‹እኔማ እንዴት እነግርሃለሁ፡፡ እናቴ ትንገርህ፡፡ ለአንድ ዓመት ያህል፣ በእግሬ መቆምም መራመድም መሮጥም አልችልም ነበር›› አለ፣ ምን ያህል አስፈሪ እንደሆነ ለመናገር እየዘገነነው።
ለመገረዝም የመጣው ልጅ፣ በድንጋጤ ተነስቶ ተፈተለከ፡፡  
በእርግጥ፣ አስፈሪ ታሪክ ሲተርክ የነበረው ልጅ፣ በተወለደ ገና ወር ሳይሞላው ነው የተገረዘው፡፡ እንደማንኛውም ሕጻንም አመት እስኪሞላው ድረስ፣ መራመድና መሮጥ አይችልም ነበር፡፡
‹‹አልዋሸም፤ ግን ተሳስቷል›› ልንል እንችላለን፡፡ በመገረዙ ሳይሆን ጨቅላ ሕጻን ስለነበረ ነው፣ መራመድ ያልቻለው፡፡ ታዲያ፣ ነገርን የሚያጋንን ስህተት ብቻ ሳይሆን፤ ነገር አቅልሎ የማየት ስህተትም ያጋጥማል፡፡
ሰውዬው፣ የተላከበትን ጉዳይ ለመጨረስ፣ የያዘውን ዕቃና ደብዳቤ ቶሎ አድርሶ ለመመለስ ቸኩሏል፡፡ ቢሆንም ግን፣ ከመንገድ ዳር፣ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ፣ ዙሪያውን ለከበቡት ሰዎች በምሬት የሚናገርና የሚያለቅስ ገበሬ ሲያይ፣ ቆም ብሎ ጠየቀ፡፡
‹‹ምን ተጎድቶ፣ ምን ተበድሎ ነው የሚማረረው? የሚያለቅሰው?›› ብሎ - አንዱን ሰው ጠየቀ፡፡
‹‹ተዘረፈ፡፡ በጠራራ ፀሐይ በቀማኛ ተዘረፈ፡፡ ሕግ ጠፋ፡፡ ይሉኝታ ተረሳ። ምን ቀረን!›› እያለ፣ በሁኔታው እያዘነና እየተቆጨ ሄደ፡፡
መንገደኛው ፍርሃት ገባው፡፡ ግን ቸኩሏል። በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ? አለ - በስጋት፡፡
‹‹አዎ›› ብሎ መለሰ የተዘረፈው ሰውዬ፡፡
‹‹ገመዱን እንዲህ በመዳፌ ይዤ፣ ከገበያተኛ ጋር ተከራክሬ መለስ ስል፣ ገመዱ ከእጄ የለም፡፡ ዞሬ ስመለከት አንጡራ ንብረቴ የለም፡፡››… እያለ ይተርካል፡፡ ዙሪያውን ተሰብስበው የሚሰሙ ሰዎችም፣ ሃዘናቸውንና ንዴታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ችኩሉ መንገደኛ፣ ነገሩ ግር ቢለውም ጉዞውን ቀጠለ፡፡ በቅንጣት ገመድ እንዲህ መንገብገብ ምን ይባላል? ብሎ ተገረመ፡፡ ብዙም ሳይርቅ፣ የሰዎች ሁካታ ገጠመው። ‹‹ዘራፊው ተያዘ፡፡ ተያዘ›› ይላሉ ብዙ ሰዎች፡፡
‹‹ብዙ ዓመት መታሰሩ አይቀርም›› አሉ አንድ ነዋሪ፡፡
‹‹እጅ ከፍንጅ ተይዞ? በያዘው ገመድ አስሮ መግረፍ ነበር›› አለ ሌላኛው ነዋሪ፡፡
መንገደኛው ይህን ሲሰማ፣ ግራ ከመጋባትም አልፎ፣ ተደናገጠ፡፡ ገመድ የሰረቀ… ብዙ ዓመት ይታሰራል? ገመዱ ጫፍ ላይ፣ የገበሬውን የአመት ገቢ የሚሸፍን የደለበ በሬ ታስሮ እንደነበር ለመስማት ጊዜ አልነበረውም የችኮላ ነገር፡፡
አንዳንዴ ካለማወቅ የተነሳ ስህተት እንናገራለን፡፡ ሌላ ጊዜ ከችኮላ የተነሳ፣ ተሳስተን እናጠፋለን፤ ችግር ላይ እንወድቃለን፡፡ አዎ፣ ሰው አዋቂ ሆኖ አይወለድም፡፡ ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለም፡፡ ያላወቅነውን ማወቅ፣ የሳትነውን ማስተካከል እንችላለን፡፡
በስንፍና ከአላዋቂነት ጋር ከተዛመድን፣ ነገርን ሳያጣሩ፣ ጊዜ ሰጥተው ሳያገናዝቡ፣ ጥሩና መጥፎን ሳይዳኙና ሳይመዝኑ በችኮላ መፍረድ፣ ልማድ ከሆነብን ነው ክፋቱ፡፡
የባሰም አለ፡፡ ሳያውቁ ሳይሆን እያወቁ የሚዋሹ፣ በስህተት ሳይሆን በድፍረት የሚያጠፉ ጥቂት ሰዎች፤ ነገርን ያደፈርሳሉ፡፡ በተለይ፣ በአላዋቂነት የምንተባበራቸው፣ በችኮላ እየተሳሳትን የምንዘምትላቸው ከሆነ፣ ሰፊውን ባህር ያደፈርሳሉ፡፡
ከትንሽ ገመድ ተነስተው፣ ለሚወዱት ሰው በሬ የሚያክል ሙገሳ ይጨምሩለታል:: ለጠመዱት ሰው ደግሞ፣ በሬ የሚያክል ጥፋት ጎትተው ጫንቃው ላይ እየጫኑ ይወነጅሉታል፡፡ ሲያሰኛቸው፣ የተራራ ያህል ብቃትንና ስኬትን ችላ ብለው፣ ከተራራው ስር የወደቀች አንዲት ጠጠር ላይ፣ አገር በንትርክ እንዲናወጥ ይራወጣሉ፡፡ ሲያሻቸው ደግሞ፤ እንደ ግዙፍ ተራራ ጥላውን ዘርግቶ አገሬውን ያጠቆረ ጥፋት፣ በቃላት ብዛት ተሸፋፍኖ እንዲደበቅ ይመኛሉ፡፡ ከዚህም አልፈው፣ ክፋትን አቆንጅተው ለማሳየት ይሞክራሉ።
ከእንዲህ አይነት ክፋት የምንድነው፣ የውሸት አራቢ፣ የጥፋት አራጋቢ፣ የክፋት ጋላቢ ከመሆን የምንናመልጠው፣ በአስተዋይነትና በእውቀት ብቻ ነው፡። ነገርን የማጣራት፣ ጊዜ ሰጥቶ የማገናዘብ፣ ጥሩና መጥፎን፣ ክፉና በጎን ለይቶ የመዳኘት የአዕምሮ ብቃት፣ ዋና ነገራችን ይሁን፡፡    

Read 17847 times
Administrator

Latest from Administrator