Print this page
Saturday, 25 January 2020 12:09

‹‹ሥልጣን ወይም ሞት!›› ባዮች፤ እኛንም አገርንም ያጠፋሉ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(4 votes)


              የዛሬው ፖለቲካዊ ወጋችን ‹ሥልጣን በማንኛውም መንገድ› ለመመንተፍ በቋመጡ ፖለቲከኞች ወይም ፓርቲዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል፡፡  (ጠ/ሚኒስትሩ ‹‹ጭልፊቶች›› ወይም “መንታፊዎች” ያሏቸውን ማለቴ ነው!) ሆን ብላችሁ የፖለቲካውን ንፍቀ ክበብ ከተከታተላችሁ… በአሁኑ ወቅት “ሥልጣን
በማንኛውም መንገድ” (በምርጫም ያለ ምርጫም) በእጃቸው ለማስገባት ያነጣጠሩ የፖለቲካ ሀይሎች አይናቸውን በጨው አጥበው ብቅ ማለታቸውን ትገነዘባላችሁ፡፡
                                
            ወዳጆቼ፤ ባለፈው ሳምንት በተነጋገርነው መሰረት፣ በምርጫ ጉዳይ ላይ መወያየታችንን፤ መነጋገራችንን እንቀጥልበታለን፡፡ ወደን አይደለም:: መረጃና ዕውቀት በእጅጉ ያስፈልገናል:: በፖለቲከኞችና በምርጫ ሂደቱ ዙሪያ ናለቴ ነው፡፡ ግን መወያየት ብቻ አይደለም፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ አቋምና ማኒፌስቶ ሁሉ እናወጣለን (የመራጮች አቋምና ማኒፌስቶ ማለቴ ነው)
እንግዲህ ባለፈው ፖለቲካዊ ወጋችን … እኔና እናንተ (ውድ አንባቢያንን ማለቴ ነው!) ስምምነት ላይ የደረስንበት ጉዳይ አለ አይደል! ለነገሩ በዚህ ጉዳይ ላይ አንባቢም ባይሆንም እንኳን መስማማቱ አይቀርም ብዬ አምናለሁ፡፡  ለምን መሰላችሁ? ማንም ጤነኛ አዕምሮ ያለው ሰው (በተለይ ነገ የተሻለ ሕይወት ተስፋ የሚያደርግ ወጣት!) በምርጫ ጦስ ሕይወቱን ማጣት አይፈልግም (ሞት ሰልችቶናል!) በነገራችን ላይ--- ምርጫውን የምንፈልገው ለመሞት አይደለም፤ የተሻለ ሕይወት ለመኖር እንጂ! ለዚህ እኮ ነው ‹‹ለፖለቲከኞች ድምፃችንን እንጂ ነፍሳችንን አንሰጥም›› የሚል የመራጮች ማኒፌስቶ ያወጣነው:: ባለፈው ሳምንት ማለቴ ነው፡፡ መቼም “ለምርጫው ድምጼን ብቻ ሳይሆን ነፍሴንም እሰጣለሁ የሚል ሰው አይኖርም፡፡ (ራሳቸው ሥልጣን ፈላጊዎቹም ቢሆኑ!) ለእነሱ ሥልጣን ግን ህዝብ ህይወቱን ቢከፍል ደስታውን አይችሉትም፡፡ ገና ምርጫው ሳይደርስ እኮ ብዙ የህይወት መስዋዕትነት ያስከፈሉ እጩ  ፖለቲከኞች አሉ፡፡
እናላችሁ… በዘንድሮ ምርጫ በብልጣብልጥ ፖለቲከኞች እንዳንሸወድ በእጅጉ መጠንቀቅ አለብን፡፡ (ሕይወትን የሚያህል ውድ ዋጋ እንከፍላለን!) ልብ በሉ፤ አንዱ ፖለቲከኛ ወይም ፓርቲ ከሥልጣን ወርዶ ሌላው ሥልጣን እንዲይዝ (ያውም እኮ ጤነኛ ይሁን አይሁን አናውቅም!) አንድም ዜጋ ቢሆን ፈጽሞ መሞት የለበትም:: (ለምን ሲባል!?)
ይሄውላችሁ --- በምርጫው “ብልጽግና”ም ያሸንፍ “ኦፌኮ” አሊያም “ኢዜማ”ም ያሸንፍ “አብን” ምንም  ችግር የለውም፡፡ ዋናው ቁም ነገር… በምርጫው ማግስት ግጭትና ቀውስ መፈጠር የለበትም:: ሰው ሊሞት አይገባም፡፡ በዚህ መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አለብን፡፡ በዚህ እርግጠኞች ሳንሆን ወደ ምርጫው መግባት፣ ዓይናችን እያየ ወደ ጥፋት ቁልቁለት ማምራት ነው፡፡ (እያወቁ ጥፋት በሉት!)
ወዳጆቼ፤ እኛ እኮ የምርጫ ሱስ የለብንም፤ የኛ ሱስ የመኖር ሱስ ነው:: እናም ለመሞት በምርጫው መሳተፍ የለብንም፡፡ የምርጫው ዓላማ፤ የተሻለ ህይወት መፍጠር ሊሆን ይገባል፡፡
የዛሬው ፖለቲካዊ ወጋችን ‹ሥልጣን በማንኛውም መንገድ› ለመመንተፍ በቋመጡ ፖለቲከኞች ወይም ፓርቲዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን ይሆናል:: (ጠ/ሚኒስትሩ ‹‹ጭልፊቶች›› ወይም “መንታፊዎች” ያሏቸውን ማለቴ ነው!) ሆን ብላችሁ የፖለቲካውን ንፍቀ ክበብ ከተከታተላችሁ… በአሁኑ ወቅት “ሥልጣን በማንኛውም መንገድ” (በምርጫም ያለ ምርጫም) በእጃቸው ለማስገባት ያነጣጠሩ የፖለቲካ ሀይሎች አይናቸውን በጨው አጥበው ብቅ ማለታቸውን ትገነዘባላችሁ፡፡ (‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ባዮች ናቸው!) የትም ይፈጭ… እነሱ የሚፈልጉት ሥልጣን ብቻ ነው! በዚህ ሂደት ሕዝብ ተጋጨ?… የዜጎች ሕይወት ጠፋ?… አገር ተቃወሰች?… ደንታ የላቸውም፡፡ (እውነትም ጭልፊቶች!)
በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ አደገኛ ፖለቲከኞች መኖራቸው ጨርሶ ሊያስገርመን አይገባም፡፡ (እንኳ ዘንድሮ ድሮም ነበሩ!) ችግር ላይ የምንወድቀው መቼ መሰላችሁ? የዋህነታችን በዝቶ… ሊኖሩ አይችሉም ብለን ከተሸወድን ነው::  እናላችሁ… ‹ሥልጣን በማንኛውም› መንገድ” የሚሉ ሀይሎች፤ አሁኑኑ ‹No!› (በፍፁም!) ሊባሉ ይገባል:: (ቁርጣቸውን እንዲያውቁት!) አያችሁ… በማንኛውም መንገድ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመውጣት የሚቋምጡ ወይም የቋመጡ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፤ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ሥልጣን እንደ እህል ውሃ ተጠምተዋል፡፡ የሕዝብና የአገር ጉዳይ አያሳስባቸውም፡፡ ግጭትና ብጥብጥ ቢፈጠር አይጨንቃቸውም፡፡ እነሱን ወደ ሥልጣን እርካብ ያውጣቸው እንጂ ሁሉንም አማራጮች ይጠቀማሉ:: ጦቢያን መበታተንም ቢሆን ማለቴ ነው:: ደግነቱ ጠ/ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያን ለድርድር አናቀርብም!” ብለዋል፡፡ (ስንቱ ብልጣ ብልጥ፣ በነፃነትና በዲሞክራሲ ስም እየማለ ጉድ ሰርቶናል እኮ!) በዘንድሮ ምርጫ ግን ፈጽሞ መሸወድ የለብንም። ‹በማንኛውም መንገድ ሥልጣን› ባዮችን… ገና በእንጭጭነታቸው ‹No!› (በፍፁም!) ልንላቸው ይገባል፡፡ (ሥር ከሰደዱማ አንችላቸውም!) በዚህ በኩል መንግሥትም ሆነ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ምርጫ ቦርድ ያግዘናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን:: ‹‹ሥልጣን በማንኛውም መንገድ መያዝ›› ወይም ‹‹በየትኛውም አቋራጭ ቤተ መንግሥት መግባት›› እንደማይቻል በግልጽ የሚደነገግ ሕግ በማውጣት ማለቴ ነው፡፡ ሕጉ አለ ከተባለም --- ትንሽ ጠበቅ ጠበቅ ተደርጎ፣ በመላ አገሪቱ ዋና ዋና አደባባዮች መሰቀል አለበት:: ምርጫው ሲደርስ አይደለም፤ከአሁን ጀምሮ!
ወዳጆቼ፤ በተቻለ አቅም ሁሉ የጭልፊቶችን ቀዳዳ መድፈን የግድ ነው (ከጥፋት ለመዳን!) እኒህ የሥልጣን መንታፊዎች ዝም ከተባሉ እኮ… እንኳንስ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ልናደርግ ቀርቶ አገርም ጭምር አይኖረንም። (ሥልጣን ወይም ሞት ያሉ ጭልፊቶች… አገርና ሕዝብ ጉዳያቸው አይደለም!)
በመጨረሻ ሰሞኑን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፣ በቤተ መንግስት፣ ከደቡብ ክልል ከመጡ ተወካዮች ጋር ውይይት ባደረጉ ጊዜ፣ በምርጫ ጉዳይ የተናገሩት ምክር አዘል ሃሳብ አስደምሞኛል፡፡ “ማንም ይሁን ማን፤ ልማትን፣ አንድነትን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን ከተናገረ፤ እሱ ብልጽግና ነው፤ ምረጡት!” ብለዋል፡፡ እኔ በዚህ ንግግራቸው ብቻ እሳቸውን መረጥኩ፤ ጠ/ሚኒስትሩን!!
የነገ ሰው ይበለን!!

Read 4591 times