Saturday, 25 January 2020 11:47

‹‹በሕዝብ የተሰጠኝ ኃላፊነት ሊከበር ይገባል›› ህወኃት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(7 votes)

   ‹‹ምደባው ከብሔርና ከማግለል ጋር አይገናኝም›› -ጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት


            የህወኃት አመራር አባላት ከፌደራልና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የኃላፊነት ቦታዎች መነሳታቸውን ህወኃት የተቃወመ ሲሆን ድርጊቱ በሕዝብ የተሰጠኝን ሕጋዊ ኃላፊነት የሚጻረር ነው ብሏል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የህወኃት አመራሮችና አባላት በመሆናቸው ብቻ ከፌደራል መንግሥትና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የኃላፊነት ቦታዎች እንዲነሱ እየተደረገ ነው ያለው ህወኃት፤ ይህ ተግባር ፍፁም ተቀባይነት የለውም፤ ሊታረም ይገባል ካልሆነ ግን ይህን ተከትሎ ለሚፈጠር ሁኔታ ኃላፊነት የሚወስደው ይህን ሕገ ወጥ ተግባር እየፈፀመ ያለው አካል ነው ብሏል - በመግለጫው፡፡
ህወኃት ከተፈጠረው አዲስ ፓርቲ ጋር እንደማይዋሃድ ቢወስንም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠው የፌደራልና የክልል መንግሥት ግዴታና መብትን አክብሮ ለመጓዝ አሳውቆ እንደነበር የጠቀሰው መግለጫው፤የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሕአዴግን መርጦ የሰጠው ኃላፊነት እስከ ቀጣይ ምርጫ በጥብቅ ሊከበር ይገባል ብሏል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢሕአዴግን ነው የመረጠው፤ መንግሥት እንዲመሰርቱም እንዲመሩም ስልጣን የሰጣቸው ለእነዚህ ድርጅቶች ነው›› ያለው ህወኃት፤ከዚህ ውጪ ሕዝብ ያልመረጠው ሌላ አዲስ ድርጅት ስልጣን እንዲይዝም ሆነ አገር እንዲመራ ማድረግ፣ የሕዝቡን ሥልጣን መቀማትና ሕገ መንግሥቱን መርገጥ ነው›› ብሏል፡፡ በዚህም በፌዴራልም ሆነ በአዲስ አበባ ደረጃ ህወኃት ያለው ስልጣን ሊነሳ እንደማይገባ መግለጫው አሳስቧል፡፡
በሌላ በኩል፤ ህወኃት የኢህአዴግን የሀብት ክፍፍል አስመልክቶ በፍ/ቤት ተከራክሮ መብቱን ለማስከበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ቀደም ብሎ አስታውቋል፡፡ ቀደም ሲል የአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባና የከተማዋ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ሰለሞን በላይ እንዲሁም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የነበሩት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ከሰሞኑ በሌላ መተካታቸው ይታወቃል፡፡
ለዚህ የህወኃት ወቀሳ ምላሽ የሰጠው የጠ/ሚር ጽ/ቤት በበኩሉ፤ የከፍተኛ መንግሥት ሥራ ሃላፊዎች ምደባ በብሄርና ከማግለል ጋር አይገናኝም›› ብሏል፡፡ የሽግሽግና አዳዲስ ሹመቶች ጉዳይ የተለመደና ለስራ ቅልጥፍና የተሻለ አፈፃፀም ለማረጋገጥ ሲባል በየጊዜው የሚከናወን ስራ ነው ብሏል - መግለጫው፡፡
አሁን የተደረገው ሽግሽግም የሥራ ድክመት የታየባቸው ተገምግሞ እንዲሁም የሥራ ጉድለቶች ታይተው የተደረገ አዲስ ምደባ መሆኑን መንግሥት አስታውቋል፡፡


Read 16300 times