Saturday, 25 January 2020 11:40

በደንቢዶሎ የታገቱ ተማሪዎችን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተልኩ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

   - የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ
       - “መንግስት ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ጥረቱን ቀጥሏል” - ኮሚሽኑ

              በደንቢዶሎ ከወር በፊት የታገቱ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ለአዲስ አድማስ የገለፀው የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን፤ መንግስት የተማሪዎችን ህይወት አደጋ ላይ በማይጥል መንገድ ከእገታ የማስለቀቁን ተግባር እንዲያከናውን ጠይቋል፡፡
‹‹የተማሪዎቹ እገታ ጉዳይ በዋነኛነት የደህንነት አካሉ ኃላፊነት ነው›› ያሉት የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የመንግስት የፀጥታ ሃይል ልጆቹን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ከእገታው ማስለቀቅ መቻል አለበት ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ መንግስትም ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት ሚስጥራዊነትን የጠበቀ በመሆኑ ብዙ ጉዳይ ይፋ እንደማይደረግ ጠቁመዋል፡፡
በዚህ የማስለቀቅ ጥረት እስካሁን የተገኘ ውጤት አለመኖሩን የገለፁት ኮሚሽነሩ፤ የእገታው ድርጊት በባህሪው ብዙ መረጃ የሚገኝበት ባለመሆኑ ግርታን መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በዋናነት ትኩረት አድርጐ የሚሠራው ተማሪዎቹ የሚለቀቁበትን ሁኔታ መሻት ላይ መሆኑን ያስረዱት ዶ/ር ዳንኤል፤ ኮሚሽኑም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ በጣም ልብ የሚሰብር ነገር ነው፤ ነገር ግን መንግስት ችላ ብሎ የተወው ጉዳይ አይደለም፣ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን እናውቃለን›› ብለዋል - ኮሚሽነሩ፡፡
መንግስት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ድርድር እና ሽምግልና አንዱ መንገድ መሆኑን ኮሚሽኑ መረዳቱንም ዶ/ር ዳንኤል ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ “ሴታዊት” የተሰኘው የፆታ እኩልነት ላይ የሚሠራ አገራዊ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባወጣው መግለጫ፤ በደንቢዶሎ የታገቱ ተማሪዎች በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡
የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩም “ድርጅቱ” ጠይቋል፡፡
ቀደም ብሎ የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከታገቱት ተማሪዎች መካከል 22ቱ መለቀቃቸውን ገልፀው የነበረ ቢሆንም፤ ወላጆች ‹‹ተለቀዋል የተባሉ ልጆቻችንን ማግኘት አልቻልንም›› ማለታቸውን ተከትሎ ጉዳዩ ሲያወዛግብ መሰንበቱ ይታወሳል:: እስካሁን መንግሥት ውዝግብ ባስነሳው መረጃ ላይ ማብራርያም ሆነ ማስተባበያ አልሰጠም፡፡


Read 93721 times