Saturday, 18 January 2020 13:55

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ምኞትን አርግዤ
ጉጉት ላይ ተጭኜ ተስፋን ተመርኩዤ
በአገኝሽ ይሆናል ስባዝን… ስኳትን አንቺን ፍለጋ
ዘመንም ተሻረ ክረምት መሽቶ ነጋ
አወይ የኔ ነገር
አንቺኑ ፍለጋ
ፍቅርሽን ተርቤ
ተጓዝኩ እሩቅ አገር በእግር የለሽ ልቤ
ተራራውን ወጣሁ
ቁልቁለቱን ወረድሁ
ጅረቱን ተሻገርሁ ሜዳውን አቋረጥኩ
አንቺኑ ፍለጋ
ሲኦልም ወረድሁኝ
ከአጋንንቴ መሀል ፈለግሁ አሰፈልግሁኝ
ወጣሁ ፀረአርያም
ትኖሪ እንደሁ ብዬ መላዕክት መሀል
በዐይኔ አማተርኩኝ
ግና ምን ያደርጋል… አንቺን የመሰለ
አንድም ሴት አጣሁኝ፡፡
አበራ ኃ/ማርያም
መስከረም 13/1992
ማፍቀር ጽጌረዳ
ካይንና ከነገር
ልብ ውስጥ ቆፍረው
ያፀደቁት ማፍቀር
እያደር እያደር….
ለ ምልሞና ረዝም
እያደገ ደግሞ….
ምላስ ላይ ያብጥና
የስሜት እምቡጡ
ማፍቀር ጽጌረዳ
መቼ ታውቆ ድንገት
አፍ ላይ ሲፈነዳ!!
(የአገሬ ገጣሚ)
መስከረም 13/1992


Read 3250 times