Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 30 June 2012 10:33

ኤርትራውያን ስደተኞች ተስፋ ስለቆረጡባት አገራቸው ይናገራሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በኤርትራ ያለው መንግሥት አስከፊነቱና ጨቋኝነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ለመምጣቱ ምስክሮቹ ዜጐቹ ናቸው፡፡ በአገሪቱ የሰፈነውን የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ድህነትና ጉስቁልና ለማምለጥ ድንበር ተሻግረው ኢትዮጵያ የሚገቡ የኤርትራ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በወር አንድ ሺ የሚደርሱ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ሲታወቅ በትግራይ ክልል በሚገኙ ሦስት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከተጠለሉ 350ሺ ስደተኞች መካከል 60ሺዎቹ ኤርትራውያን ናቸው፡፡ ባለፈው ሳምንት “የዓለም ስደተኞች ቀን” በማይ አኒ ስደተኞቹ ጣቢያ “አንድም ስደተኛ ቢሆን ተስፋው ሊጨልምበት አይገባም” በሚል መሪ ቃል የተከበረ ሲሆን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው በስፍራው ተገኝታ ኤርትራውያን ስደተኞችን አነጋግራለች፡፡ ስደተኞቹ ስለአገራቸ

“በአገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየት ጀመርን”

ብርሃኔ ገ/እግዚብሔር እባላለሁ፡ ከኤርትራ ዞባዶብ ከሚባል ስፍራ ነው የመጣሁት፡፡

ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ገባህ፤ የጉዞህን ሁኔታ ንረገን?

ቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ አልመጣሁም፡፡ ሱዳን ገብቼ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስ አንድ ሙሉ ሌሊት ተጉዤ ነው የደረስኩት፡ ጉዞውን ያደረግነው ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር በመሆን ነው፡፡ በመንገዳችን ላይ ሌቦች ሽፍቶች አሉ፤ ገንዘብ ይነጥቃሉ፤ ሴቶችን ይደፍራሉ፡፡ እነሱን በገንዘብ ለመሸንገል ተዘጋጅተን ነው የወጣነው፡፡ በተደጋጋሚ በየመንገዱ ሲያስቆሙን በኪሴ ውስጥ ያለውን እያወጣሁ እሰጣቸው ነበር፡፡ አጠቃላይ ዘጠኝ መቶ የሱዳን ገንዘብ ሰጥቻለሁ፡፡ ሚስቴንና የደረሰች ልጅ ስለያዝኩ እንዳይተናኮሉብኝ፣ እንዳይደፍሩብኝ ሰግቼ ነበር፡፡ እኛ ኢትዮጵያን መርጠን ነው የመጣነው፡፡

ነገር ግን ከእኛ ጋር ተነስተው ወደ ሊቢያ የሄዱ ከ40 በላይ ኤርትራዊያን ጓደኞቻችን፣ ጎረቤቶቻችን በረሃ ላይ በሽፍታ መገደላቸውን በስሚ ስሚ አውቀናል፡፡ ኤርትራዊ ዜጋ ማለት በአሁኑ ጊዜ ብኩን፤ የሚያሳዝን ፍጡር መሆኑ ነው የሚሰማኝ፡፡ ከኤርትራ ወደ ሱዳን የገባነው ሸገረጊ ከተባለ ስፍራ ተነስተን ነበር፡፡ እንዴት አሰቃቂ እንደሆነ አልነግርሽም፡፡

ለስደት ያበቃህን ችግሮች ብትነግረኝ…

በአገሪቱ ያለው መንግስት፤ ለህዝቡ ክብር አልሰጥ ስላለ አገሬን ጥዬ መጣሁ፡፡

የራሴ ታክሲ ነበረኝ፡፡ ከዛም በቡና ቤት  ውስጥ መስራት ጀመርኩ፤ ግን ሁኔታው አልመች አለ፡፡ ብዙ የስራ ዓይነት እየቀያየርኩ ኑሮን ለማሸነፍ እታገል ነበር፡፡ አሠራሩ ስርዓቱ በደሉ በዛ፡፡ በሀገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየት ጀመርን፤ ስለሆነም ድንበር ተሻግሬ ስደትን መርጬ አገር ጥዬ መጣሁ፡፡

የ17 ዓመት ልጅ ነበረኝ፡፡ በውትድርና በግዳጅ ወሰዱብኝ፡፡ በዚያው ቀረ … ይሙት ይኑር አላውቅም፡፡ ብዙ ወጣቶች ይወጣሉ ተመልሰው አይመጡም፡፡ የእድሜ ገደብ እንኳን የላቸውም፤ ታዳጊዎችን ከቤተሰባቸው ነጥለው ይወስዳሉ፡፡ እዚህ ካምፕ ውስጥ የምታዪው ታዳጊና ወጣት ወንዶች እንደዚህ በዝተው የምታያቸው አገራቸውን ጠልተው እንዳይመስልሽ … ምሬት ነው ለስደት የዳረጋቸው፡፡ ለእንደ እኔ ላለውም አይመለሱም፡፡ ነገር ግን እኔ እግሬ በሽተኛ ስለሆነ አልወሰዱኝም … ደግሞም እኮ ታጋይ ነበርኩ፡፡

መቼ?

በደርግ ጊዜ ስርዓቱን በመቃወም ከ1980-1994 ዓ.ም የህዝባዊ ግንባር ሻቢያ ታጋይ ነበርኩ፡፡ በበረሀ ነው ህይወቴን ያሳለፍኩት፡፡ ከትግሉ በኋላ በስራ ላይ ቆይቼአለሁ፡፡

ከዛ ስወጣ የጡረታ ደመወዝ እንኳን አልሰጡኝም፡፡ ያ ሁሉ ታልፎ ዲሞክራሲያዊ መብትና ስርዓት ያልተከበረበት እጅግ መራር የሆነበት አገር ነው፡፡

ከእኔ ጋር ሳህል የሚባል ቦታ በትግል የነበሩ በሚኒስቴር ደረጃና በትልልቅ የመንግስት መ/ቤቶች ውስጥ እየሰሩ ነው፡፡ በእርግጥ በብዛት በትግሉ የነበሩት ሞተዋል፡፡

የታገልኩለትና እድሜዬን የገፋሁበት ድርጅቴ ለእኔ ካልሆነ ለማን ይሆናል ብዬ ተመረርኩ፡፡

አንድ ልጄን ጥዬ ሶስት ልጆቼንና ባለቤቴን ይዤ መጣሁ፡፡ ደግሞ መንገዱ እኮ አስፈሪ ነው… በድንበር ላይ ጥግ ጥጉን የሚጠብቁ የኤርትራ መንግስት ወታደሮችና ደህንነቶች ቢያገኙኝ እስከ ቤተሰቤ አሟሟቴ እጅግ የከፋ ነበር የሚሆነው፡፡

ከኤርትራ ድንበር አልፎ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ሲሻገር የተገኘውን ግደለው ነው የተባሉት፡፡

በየትኛው የድንበር አቅጣጫ ነው ወደ ኢትዮጵያ የገባኸው?

በሁመራ በኩል ነው የገባነው፡፡ ከዛም ማይ-አኒ የስደተኞች ካምፕ መጣን፡፡ በርግጥ እዚህ ያለው ህይወት ይሻላል፡፡ ስንዴ፣ ዘይት … የመሳሰሉትን እናገኛለን፡፡ ህይወታችን እንዴት ይቀጥላል የሚለው ነው ስጋታችን፡፡

“አይ ኢሳያስ! እግዜር ይይለት”

ስምሽ?

አለም አርአያ

ወደ ኢትዮጵያ እንዴት መጣሽ?

ከአሰብ ነው የመጣሁት፡፡ በኤርትራ ያለው መንግስት አሠራሩ ከህዝብ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ጭቆና በዛ፡፡ አፍሽን ሞልተሽ መናገር አትችይም፡፡ ለችግራችን መፍትሄ የሚሰጠን አጣን፡፡ የአሰብ ነዋሪዎችን ለየት ባለ አገዛዝና ረገጣ ነው ይዞን ያለው፡፡ እኛ አማርኛ ተናጋሪዎች ነን፡፡ አማርኛ በመናገራችን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የምንታየው፡፡ “አምቼ” የሚል ስም ተሰጥቶናል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ በላያችን ላይ ስለላ ይደረግብናል… ማን ምን ያስባል የሚለውን፡፡ ሌላው ቢቀር ከአገር ወደ አገር ተንቀሳቅስን ሰርተን መኖር አንችልም፡፡ ለውጥ የሌለው አገር ሆነ፡፡ #እነዚህ እምነት የሌላቸው፤ የወያኔ ደጋፊዎች ናቸው$ እንባላለን፡፡ የሚገርምሽ ግንቦት 24 የነፃነት ቀን ነው … እኛ በዓሉን ስናከብር ግን “እነዚህ ዜግነታቸው አይታወቅ፤ እምነት የላቸው” ብለው ያገሉናል፡፡

በምን ስራ ትተዳደሪ ነበር?

የቤት እመቤት ነበርኩ፡፡ አራት ልጆች አሉኝ፡፡ ነገር ግን የአንድ ዓመት ልጄን ብቻ ነው ይዤ የመጣሁት፡፡ ሶስቱ ልጆቼን ከዘመድ አስጠግቻቸው በእናት አንጀቴ ጨክኜ መጣሁ፡፡ ያው ከባሌ ጋር ስለተለያየሁ…

ስለ ልጆችሽ ደህንነት ትሰሚያለሽ?

ምንም አልሰማም፡፡ ይሄው እንደ ሳር ደርቄ የምታይኝ በምን ሆነና? … አይኔ ሌት ተቀን በለቅሶ ሟሟ … እንዴት ድምፃቸው እንደናፈቀኝ … አይ ኢሳያስ …እግዜር ይይለት!! (እያለቀሰች) የአንድ ዓመት ህፃን ይዞ የስደት ጉዞ አስቸጋሪ ነው…

የቆረጠ ሰው ቆረጠ ነው … ስመጣ ከአሰብ በአድቋላ አድርጌ ነው፡፡ ለሳምንት በመኪና ከተጓዝኩ በኋላ ነው በእግር ያቋረጥነው፡፡

ከአዲቋላ ራማ ግንባር ለመድረስ የአንድ ቀን የእግር መንገድ ነው፡፡

በእርግጥ በአምላክ ኃይል በመንገድ ላይ አስጨናቂ ነገር አልገጠመንም፡፡ 16 የሚባሉ የኤርትራ ወታደሮች አሉ፤ እነሱ ቢያገኙን ኖሮ ዛሬ በህይወት የለንም ነበር፡፡

በህይወታችን ፈርደን ነው የገባንበት፡፡ ግን ተረፍን፡፡ ብዙ ሰዎች ነን፡፡ የመንገዱ መሪዎችም እኮ አሉ፡፡

የእነሱ ብር እየከፈልን መንገድ ያሳዩናል፡፡ እጄ ላይ የነበረውን ስድስት መቶ ናቅፋ የሰጠሁት… መንገዱን ለመራኝ ሰው ነው፡፡

እስቲ ስለ አሰብ ንገሪን?

ችግር ነው፡፡ አሰብ የንግድ ልውውጧ ከኢትዮጵያ ጋር ነበር፡፡ በቃ አይዘራ፣ አይታጨድ… የወደብ ከተማ ናት፡፡

24 ሰዓት ስራ የለም፡፡ የወፎች መጫወቻ ነው የሆነው፡፡ ከልባችን የሚያሳዝነን ይኼው ነው፡፡ በቃ ምንም የለም፡፡ እንቅስቃሴ የለ ፀጥ ረጭ … ያለ ነው፡፡

እዚህ ኑሮው ምን ይመስላል?

መቼም ይሻላል፡፡ ለአንድ ሰው በወር 15ኪሎ ስንዴ ይሰጣል፡፡ ስራ የለም… የእኔንና የልጄን 30 ኪሎ ስንዴ እቀበልና 15 ኪሎዋን ሸጬ፤ 15 ኪሎዋን ደግሞ ለወር ቀለብ አደርጋታለሁ፡፡  ይህቺ 15 ኪሎ ስንዴ ግን ታንሰናለች፡፡

ስለወደፊት ህይወት ምን ታስቢያለሽ?

ወደ ፊት ሰርቼ የምበላበት፣ የምንቀሳቀስበት አገር … እመኛለሁ፡፡ በገዛ አገር እንደ ሁለተኛ ዜጋ ከመታየት በሚል አገር ጥዬ የተሰደድኩት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ነው፡፡

ልጆቻችን ወንዶች መሆናቸውን ሲመለከቱ ለእነሱ ደስታቸው ነው፡፡

ቄራ ሊታረድ እንደሚቀርብ ከብት ያጓጉዋቸዋል፡፡

እኔ አሁን ተስፋዬ ፍላጐቴ ሰርቼ … የተሻለ ህይወት ኖሮኝ… አሰብ ጥያቸው የመጣኋቸውን ልጆቼን አግኝቻቸው … ከጎኔ ሆነው የሚኖሩበት ዘመን ነው የናፈቀኝ፡፡

“ጋዜጠኞች ይታፈናሉ፤ በዙሪያችን ብዙ ሰላይና ጠባቂ አለብን”

ኡስማን ሰዒድ እባላለሁ፡፡ በኤርትራ ቴሌቪዥን የአረብኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ ነበርኩ፡፡

በጋዜጠኝነት ምን ያህል ዓመት አገለገልክ?

12 ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ በፈረንጆች አቆጣጠር በ2007 ዓ.ም ተቃዋሚ ነህ ተብዬ አንድ ዓመት ታሰርኩ፡፡ በ2008 ዓ.ም ከፈቱኝ በኋላ በድጋሚ አሰሩኝ - 6 ወር፡፡ ቤተሰቦቼ በጣም ተቆጡ፡፡ “ልታስፈጀን ነው፡ ቤተሰቦቻችንን ልታስጨርስ ነው፤ ከዚህ ጥፋ” አሉኝ፡፡ ምርጫ አልነበረኝም፡፡ ከሚስቴ ጋር ተማከርኩ፡፡ ኢትዮጵያን የመጀመሪያ ምርጫችን አድርገን ዘጠኝ ሆነን መጓዝ ጀመርን፡፡ በመንገድ ላይ የኤርትራ ወታደሮች አንድ ላይ እንዳያገኙን በሚል ከሚስቴ ጋር ልጆች ተከፋፍለን ነው የተጓዝነው፡፡ እኔ አራቱን ልጆቼን ይዤ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ በጣም አስፈሪውንና አስጨናቂውን መንገድ አልፈን ወደ ሁመራ ለመሻገር የነበረው መከራ የሚነገር አይደለም፡፡ ውሃ ውስጥ ገብተን ነበር፤ ዋና አንችልም፤ ከእነ ልጆቼ ልንሰጥም ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ በእጄ ይዤው የነበረውን ባትሪ ሳበራ የኢትዮጵያ ወታደሮች በፍጥነት ደርሰው ከእነ ቤተሰቦቼ አወጡኝ፡፡ … ባለቤቴና ልጆቼ የት እንደደረሱ አላውቅም ነበር፡፡ ባለቤቴ ሱዳን ገብታ ወደ ኤርትራ ደወለች “እኔ በሰላም ሱዳን ገብቻለሁ … እሱ መሞት መዳኑን ንገሩኝ” ብላ ስትጠይቅ “እሱማ በሰላም ኢትዮጵያ ገብቷል፤ ወሬውን ሰምተናል” አሏት፡፡ እሷም ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ አራት ልጆቻችንን ይዛ መጥታ እዚሁ ካምፕ ውስጥ ተገናኝተን አሁን በሰላም እንኖራለን፡፡

አሁን ህይወት ምን ይመስላል?

የምንበላው የምንጠጣው የተቸገርነው ነገር የለም፡፡ ግን የኤርትራ መንግስት “በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የመጠለያ ጣቢያዎች የእኛ ሰላዮች አሉ” እያለ ያስወራል፡፡ ይሄ ደግሞ ልክ ነው፤ እርስ በርሳችን አንተማመንም … እንፈራራለን፡፡ “ኡስማንን እኮ የተጠለለበት ቦታ ድረስ ሄደን ገለነዋል፡፡ በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንወስዳለን” እያሉ ያስወራሉ፡፡ የደህንነታችን ጉዳይ በካምፓችን ውስጥም ያሰጋናል፡፡

በኤርትራ የጋዜጠኞች አያያዝም ሆነ የፕሬስ ነፃነት አስከፊ ነው ይባላል…

እንግዲህ እኔ ነኝ ለዚህ ጥሩ ምስክር፡ ከአንድም ሁለት ጊዜ ታሰርኩ፤ ከስራ ተባረርኩ፣ በደል ደረሰብኝ፡፡ እነሱ ተቃዋሚ ብለው ይፈርጁኝ እንጂ እኔ የራሳቸው አባል ነበርኩ፡፡ በሰራሁበት የቲቪ ጣቢያ ያለው አሰራር ከጋዜጠኝነት ስነ ምግባር ያፈነገጠ ነው፡፡ ዜና የሚተላለፈው የማስታወቂያ ሚ/ሩ፣ የውጪ ጉዳይ ሚ/ሩ፣ ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ አይተውት ወይም ኤዲት አድርገውት ነው፡፡

ለምሳሌ እኔ ለመዘገብ ስወጣ በመንገድ ላይ የገጠመኝን ሰው መጠየቅ አልችልም፡፡

የምትጠይቂው ሰውም ተመርጦልሽና ጥያቄ ተዋጥቶልሽ ነው፡፡ ከዛ ውጪ የምትሰሪው ነገር አይኖርም፡፡

እስር በኤርትራ እጅን ኪስ ውስጥ አስገብቶ እንደማውጣት ቀላል ነው፡፡ ጋዜጠኞች ይታፈናሉ ይታሰራሉ፤ በዙሪያችን ብዙ ሰላይና ጠባቂ አለብን፡፡ የኤርትራ መንግስት ሰባኪና አቀንቃኝ እንድትሆኝ ነው የሚፈለገው፡፡ ሲጀመር የፖለቲካው አካል ያልሆነ ጋዜጠኛ አይመደብም፡፡

በኤርትራ የግል ሚዲያ የለም…

አንድ እንኳን የለም፡፡ የመንግስት ቴሌቪዥን አለ፤ በስሩ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚታተሙ ጋዜጣዎች አሉ… በቃ፡፡ የግል የሚባል ለምልክት እንኳን የለም፡፡ እንኳን የግል ሊኖር … ዘፈን እንኳን አንዲት መንግስትን የሚነካ ወይም ቅኔ አለው ተብሎ የሚታሰብ ከተላለፈ … ጋዜጠኛው እስር ቤት ነው እጣው፡፡

ለምሳሌ የኤርትራ ዘፋኞች በውጭ ሆነው የተለያዩ ዘፈኖች ይዘፍናሉ፤ ነጻነትን የሚናፍቁ ዘፈኖች ዓይነት፡፡ ሁለት ሶስት ትርጉም ያለው ዘፈን ተሳስተሽ ብታስተላልፊ የሚጠብቅሽን ታውቂያለሽ፡፡ ስለዚህ የምታስተላልፊውን ዘፈን እንኳን በደንብ መስማትና መምረጥ አለብሽ፡፡

አሁን ምን ታስባለህ?

ብዙ አስባለሁ፡፡ መፅሀፍ መፃፌ አይቀርም፤ እየተዘጋጀሁበት ነው፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የተሻለ ኑሮ ለመምራት መንቀሳቀስ… እንዳለብኝ አውቃለሁ፡፡

“ከኤርትራ የማይሻል ነገር የለም”

በመጠለያ ጣቢያ የሦስት ወር ጊዜ ያስቆጠረችው ዮርዳኖስ ተሻለ፤ የ21 ዓመት ወጣት ስትሆን የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ነው ወደ ኢትዮጵያ የገባችው፡፡ አማርኛ ከትግርኛ ጋር እየቀላቀለች ስለ ስደት ጉዞዋ አጫወተችን፡፡

ለምን ወደ ኢትዮጵያ መጣሽ?

ኤርትራ አልተመቸኝም፡፡ ከአድቋላ የኤርትራ ድንበርን አቋርጠን ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ከቤተሰብ ጠፍተን መጣን፡፡ የወንድ ጓደኛዬ በመንገድ የምናልፋቸው ስፍራዎችን ሁሉ … ለእኔ ሲል እየተጨነቀና በብር እያባበለ ነበር የሚያልፈው፡፡ …ሽፍታዎች አሉ፡፡ … መንገድ ላይ አንዳንድ ሰዎች አስቁመው ሊተናኮሉን ሲፈልጉ ገንዘብ ይሰጣቸው ነበር ለዚሁ ያዘጋጀነው 45ሺ የኤርትራ ገንዘብ (ናቅፋ) ይዘን ነበር፡፡ መንገዱ በረሃማና ድንጋያማ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከውፍረቴ ጋር አልቻልኩትም፡፡ ሁለት ቀን ሙሉ ተጉዘናል፡፡ ከአድቋላ፣ እንደ ገርግስ … ከዛ ረማ … የኤርትራ ወታደሮች ጉዳት እንዳያደርሱብን በጥንቃቄ ነበር እንቅስቃሴያችን፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያስወሰነሽ ምንድን ነው?

ድህነት አስጠላኝ፡፡ ቤተሰቦቼም አልተመቻቸውም፡፡ ከወንድ ጓደኛዬ ጋር ተማክሬ ከብዙ ሰዎች ጋር ሆነን ወደ ኢትዮጵያ መጣን … በኤርትራ ያለው ሁኔታ … የእንጀራ እናት ያህል ክፉ ነው፡፡

ሁሉ ነገር ውድ ነው፤ ብር የለም፤ ብዙ ሰው ይታመማል፡፡ ሲሰለቸኝ እና ምንም ተስፋ አልታይ ሲለኝ ነው ከቤተሰቦቼ ጠፍቼ ትምህርቴን አቋርጬ፣ ለህይወቴ ሳልሳሳ የመጣሁት፡፡

እዚህ ኑሮ እንዴት ነው?

ዋይ! በርግጥ አሁን የእኔ እጮኛ በማይ አኒ የለም፡፡ አዲስ አበባ ሄዷል፡፡ ጉዳዬ ተመርምሮ እኔም ከስድስት ወር በኋላ እሄዳለሁ፡፡ እዚህ ሆኜ በስልክ አገኘዋለሁ፡፡

ግን እኔን የተመቸኝ ምኑ መሰለሽ… በቃ ከኤርትራ የማይሻል ነገር የለም፡፡ ሙቀቱ ብቻ ያስቸግራል፡፡ እዚህ አገር ዲሞክራሲ አለ፤ ነፃ ሰው ነሽ፤ በቃ እንደልባችን እንኖራለን፡፡ በጣም ተመችቶኛል፡፡

 

 

Read 13704 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 13:16

Latest from