Tuesday, 21 January 2020 00:00

እንደምንም ብሎ መሞት ቢቀርብንስ?!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 ‹‹ተጣጥሮ ከመኖር ተጣጥሮ መሞት ምን ይባላል?››
   የአድማስ ትውስታ
               በጅምላም በነፍስ ወከፍም የሞታችን መጠን መጨመሩን ለማወቅ ስንት ዓመት አንድ ተራ የሚመስል ማስረጃ ሰምቼ ነበር፡፡ ይኸውም ዱሮ ዕድርተኛ፣ አስከሬን በመንገድ ሲያልፍ ካየ ‹‹ማነው የሞተው?›› ሲል ይጠይቅ ነበር:: የሟቹ መጠንና የአሟሟት ዓይነት ከመብዛቱ የተነሳ ዕድርተኞች ቀባሪ ባዩ ቁጥር ‹‹ሟቹ ማነው›› ማለቱ ሰልችቷቸው ‹‹የማን ዕድር ነው?›› ብለው መጠየቅ ጀመሩ:: ይህም ቢሆን ሟቹ ዕድርተኛቸው ከሆነ ባለመቅበራቸው እንዳይቀጡ ሲሉ ብቻ ነው፡፡ ቅርብ ጊዜ ደግሞ (አምናና ካቻምና) ሳምባ፣ ወባ፣ ኤድስና ባልደረቦቻቸው እየተጋገዙ፣ በድህነት አስተናጋጅነት አንገቱን ደፍቶ፣ የቁም ስቃዩን እየተመገበ ያለውን ሕዝብ እንደ ቅጠል ያረግፉት ገቡ፡፡ ሞት እጅጉን ተመቻቸና እንደ ዱሮው ከመካከላችን መምረጡን ትቶ፣ ከመሐልም ከዳርም፣ ከፍጆታ በላይ መደዳውን መጥረግ ያዘ፡፡ ዛሬም በጣም ቅርብ ካልሆነ በቀር ማን በማን ሞት ይደነቃል? ከመኖር የበለጠ መሞትን እየለመድን መጥተናል፡፡ በበሽታና በርሃብ ፈርዶብንም ሆነ ሰንፈን የማለቃችንን ነገር ማሳሰቢያና መፀለያ ላናጣለት እንችላለን:: ድህነት፣ የግንዛቤ ጉድለት፣ የምዕራባውያን ቸልተኝነት፣ የግዜር ቁጣ… እያልን የሞታችንን መንስኤ በመደርደር ማለት ነው፡፡ እውነትም ይሁን ሐሰት በሁለቱም (በበሽታና በረሀብ) የእልቂታችን ምክንያቶች፣ የሞታችን መጠን፣ በዓለም ወደ አንደኝነቱ እያመራ መሆኑን የማያውቅ ኢትዮጵያዊ አይኖርም:: ይህንን ገመናችንን እንዳለ በጉያችን እናቆይና ለዛሬው በምድር ላይ አንደኝነታችን በጥናት ስለተረጋገጠበት፣ እንደ ምንም ብለን እያለቅን ስላለንበት ጉዳይ እንነጋገር እስቲ፡፡
በዚህ የለየለት ኃጢአታችንም እንኳ ከዛሬ ጀምሮ እንደ ምንም ብሎ መሞት ይቅርብን ብለን ልብ እንደ መግዛት ለራሳችን ሰበብ መስጠትና እግዜርንም በፀሎት ከመማፀን ይልቅ በፀሎት ማታለል ለምዶብናል፡፡
አሁንማ ከዕለት ወደ ዕለት እንዲህ ዓይነቱንም አሟሟት ለመድንና፣ ከናካቴው ከኤድስና ከወባ ተራ የችግር ሰልፍ መያዙ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም የተዘነጋው ይመስለኛል፡፡ ይህን የምለው ወሬ ለማሞቅ አይደለም፡፡ ለመሆኑ አንድ መቶ ሃምሳ የክስ ወረቀት ይዞ መናገሻ ከተማ ውስጥ ለመቶ ሀምሳ አንደኛው ክስ እንደ ልብ መኪና መንዳት የሚፈቀድበት አገር፣ ከኢትዮጵያ ሌላ መኖሩን የሚያረጋግጥልን ሰው አለ? እዚህ ላይ አንባቢ ልብ እንዲልልኝ የምሻው ነገር፣ እያወራሁ ያለሁት አልፎ አልፎ እንደ የትኛውም አገር እኛም ዘንድ ስለሚከሰተው የመኪና አደጋ ሳይሆን የትም አገር ስለሌለው የኢትዮጵያ ተጨማሪ መለያ ስለሆነው፤ እንደ ምንም ብሎ በመኪና ስለ መግደልና መሞት ጉዳይ ነው፡፡
ለዚህ እንደ ምንም ብሎ የማለቅና የመጨረስ አባዜ፣ ብዙ ጊዜ የመንገድ መበላሸት፣ የምልክቶች አለመኖር፣ የመኪኖች መብዛትና የመሳሰሉ ችግሮች እንደ ዋነኛ ሰበብ ሆነው ሲጠቀሱ ይሰማል፡፡ በርግጥ እነዚህ ምክንያቶች በመንገድ ላይ ከሚመዘገቡት ሞቶችና ውድመቶች፣ በመኪና አደጋ ለሚፈጠሩት ለጥቂቶቹ ሊጠቀስ ቢችልም፣ እንደ ምንም ብሎ በመኪና በመሞትና በመግደል ለሚከሰት ችግር ግን ፈጽሞ ማሳሰቢያ ሊሆን አይችልም:: በኛ መንገዶች ላይ ከሚከሰተው አብዛኛው ሞትና ውድመት፣ የሰውን ልጅ ሕይወት እንደ ዋዛ ከመመልከት የሚመነጨው ይሆን ብሎ ገዳዩ አነዳድ ነው፡፡ በዓለም ላይ የመኪና ሞት ቁንጮ ያደረገንም ይኸው እንደ ምንም ብለን የምንሞትበትና የምንገደልበት ሥርዓት ነው። ለመሆኑ ‹‹እንደምንም ብለን ነው የምንሞተውና የምንገለው?››
ለዚህ አንዳንድ ግልጽና የቀን ተቀን ምሳሌዎችን ከጎዳና መዋስ እንችላለን፡፡
አሽከርካሪዎች
- ለሌላ ተሽከርካሪ ቅድሚያ መስጠት
በብዙ አሽከርካሪዎች ዘንድ እንደ መበለጥ፤ እንደ ሞኝነት እንዳለመሰልጠንና እንደ ፈሪነትም ይወሰዳል፡፡
- መስመርና ምልክት ጠብቆ መንዳት
ይሄም የጀማሪ ነጂዎች ነው ተብሏል፡፡ ምልክትም መስመርም በሌሉበት ትዕግስት አድርጎ ከመንዳት ይልቅ በተቻለ መጠን ሁሉም ብልጥ ሆኖ ጥሩምባ እየነፋ፣ ለብዙ ሰዓት ተጠላልፎና ተሳስሮ መንገድ ዘግቶ መቆም ይመረጣል፡፡
- ትዕግሥትና ግብረ ገብነት
በራስ ሆነ በሌሎች ተሳፋሪዎች እንዲሁም በእግረኞች አካል ውስጥ ዳግመኛ የማይተካ ነፍስ እንዳለ በኢትዮጵያ አብዛኛው አሽከርካሪ፣ በተለይ በብዙሀን የታክሲ ሾፌሮች ዘንድ ከተረሳ ቆይቷል፡፡ ፈጥኖና አስፈራርቶ መታጠፍ፣ ማቋረጥ፣ መጠምዘዝ፣ መሮጥ፣ መጋፋት የጉብዝና ምልክት ነው፡፡ በተለይ በብዙሀን የታክሲ (የሚኒባስ) አሽከርካሪዎች አካባቢ፣ ካንደበቱ የታረመ አለመሆን የነጂነት መስፈርት ይመስላል፡፡ ትዕግስት ማጣት፤ የቅልጥፍና ምስክር ሲሆን ዝግታና ማስተዋል የእርጅናና የፈዛዛነት ምልክቶች ናቸው፡፡
ድፍረት
በቂ ርቀትን ጠብቆ መጓዝ ገልጃጃ ያሰኛል፡፡ መቀደምን፣ መገልመጥንና የጥሩምባ ጩኸትን ሲያስከትል፣ በትንፋሽ ታህል ርቀት እግረኛን ጨርፎ መሄድ፣ መኪናን ታኮ መንዳትና ማቆም ደግሞ የፍፁምነት መሊያዎቸ ናቸው፡፡
መብራት መጣስ
ቀይ የትራፊክ መብራት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀንና ፖሊስ ሲኖር ቁም ማለት ሲሆን ሌሊትና ፖሊስ በሌለበት ደግሞ ሂድ ማለት ነው:: ይህ ትርጉም እንዲህ ሆኖ የሚጣመመው እዚህ አገር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጠማማ ትርጉም የሚገለገሉት ሲቪል አሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የተሻለ የሥነ ሥርዓት አስተምህሮት አላቸው የሚባሉ ወታደሮችና ‹‹ሥነ ሥርዓት አስከባሪ›› ፖሊሶች ጭምር መሆናቸውን ባይኔ በብረቱ ተመልክቻለሁ፡፡ መብራት ብቻ ሳይሆን ማናቸውም የትራፊክ ሕግ፣ ለሰው ልጅ ሕይወት ደህንነት ሳይሆን ለፖሊስ ቁጣና ክሰ ሲባል ብቻ የሚከበር ነው፡፡ አሁንማ ፖሊስ ቆሞ እያለ፣ አረንጓዴ ሳይበራ፣ ቢጫም ሳያስጠነቅቅ፣ ‹‹ተራዬን መች አጣሁት›› አይነት፣ ቀይ መብራት ላይ ቀድሞ መንገድ ማጋመስ በሕግ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል፡፡ ከዚህ የሕግ መጣስ ተግባር፣ ሕግ አከብራለሁ ብሎ የዘገየ ነጂ እንኳ ቢኖር፣ በትራፊክ ፖሊስ ‹‹ቶሎ ተመሳሰል›› የሚል ዓይነት ግሳፄ ሊከተለው ይችላል፡፡
ተሽከርካሪዎች
ጠቅላላ ይዞታ
ቢያንስ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከሚነዱ መኪኖች፣ ያለማጋነን ግማሾቹ እንደ ጋሪ ከመናገሻዋ የመባረር ጊዜያቸው የደረሰ ነው፡፡ ዝገው ነቅዘው ከማብቃታቸው በላይ እንደ ልብ ከጎዳናዎች ላይ ለሕይወት በማያሰጋ ሁኔታ፣ በመተማመን የሚነዱ አይደሉም፡፡
የጎን መስታወትና
መብራትና/ ዋና ዋና አካላት
አዲስ አበባ ውስጥ ሲጠመዘዙና ሲያቆሙ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መብራት ማሳየት በተለይ በታክሲዎች ዘንድ ቀርቷል፡፡ የጎን መስታወት የሌላቸውና ግፋ ቢል ባንድ በኩል ብቻ የቀራቸውን ቆጥሮ መዝለቅ ያስቸግራል:: ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዓመታዊ ምርመራ ወቕት ከአንድ መኪና ላይ መስታወት እየነቀሉ፣ ተራ በተራ ለሰላሳ መኪናዎች በማሰር ቦሎ እንደሚያወጡ አይቻለሁ፡፡ በየአምስት ሜትሩ ሲርመሰመሱ ከሚታዩት የታክሲ መኪኖች መቀመጫቸው የማይወዛወዝ ወይም መስታወታቸው ቀዳዳ የሌለው፣ ወለላቸው አቧራ የማያስገባ ወይም በሮቻቸው በቤት መቀርቀሪያ የማይሸጎር ወይም በገመድ የማይጠፈር፣ ገመድ ሲያልቅ በወያሎች እጅ የማይያዝ ተሽከርካሪ፣ ከጠቅላላው ቁጥር ግማሹን አያህልም፡፡
እነዚህ በጣም በጣም ጥቂትና የተለመዱት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ፍፁም ኃላፊነት የጎደላቸውና ደፋር፣ ሕገወጥ አሽከርካሪዎች በግማሽ አካላቸው ከቀሩ መኪኖች ጋር ተደምረው፣ ራሳቸውንና ሌሎች ሰዎችን ይገድላሉ፣ ይሞታሉ፣ ይጠፋሉ፣ ያጠፋሉ፡፡
የነርሱ ሕገወጥ የአነዳድ ሥርዓት ያዲሳባን መንገድ ሞልቶታል፡፡ ቀሪዎቹ ጥቂቶች ደግሞ ከዚያ ሕገወጥና አደገኛ መስመር ጋር ራሳቸውን ካላስተካከሉ አደጋ ስለሚያገኛቸው ጊዜያቸውም ስለሚቃጠል፣ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ዜጎች (ዲፕሎማቶችም) ጭምር ቀስ በቀስ ሳይወዱ በግድ ሕገወጥ አሽከርካሪ መሆን ብቸኛ አማራጫቸው ሆኗል:: አንድ የትልቅ አገር ዲፕሎማት ሥራውን ጨርሶ ከዚህ አገር ሲሰናበት በጠራው ግብዣ ላይ ብዙ ሰው ወደፊት ስለዚህች አገር ትዝታው መጽሐፍ ይጽፍ እንደሆን ጠይቀውት፤ ‹እንዴት አወቃችሁብኝ?› ዓይነት በመደነቅ ‹‹አዎን በጣም ጠንካራ ዕቅድ አለኝ›› አለ፡፡ አንዱ የኔ ብጤ አደብ የነሳው ‹‹ስለ ላሊበላ ነው ስለ አክሱም? ወይስ ስለ ተራራና ሸንተረሩ? ወይስ ደግሞ ስለእንግዳ ተቀባይነታችን?›› ይለዋል:: ዲፕሎማቱ ‹‹በፍፁም! በፍፁም! እሱንማ ብዙዎች ጽፈውታል፡፡ ነገር ግን የትም አገር የሌለ እዚህ ብቻ የማውቀው፣ ብሥራተ ገብርኤል ጋ እግዜር በተአምሩ ደርሶልኝ የዳንኩበት፣ የዚህ አገር የመኪና አነዳድ ሥርዓት ነው›› ማለቱ ትዝ ይለኛል፡፡ ያንን መጽሐፍ ፈጠነም ዘገየ እናገኘው ይሆናል፡፡
ጊዜ ጥምቡን በጣለበት አገር ባልጠፋ ቦታ ጎዳና ላይ ትዕግሥት የሚያሳጣቸውን ደንታ ቢስ አሽከርካሪዎች ምን እንደሚያደርጉ ግራ የገባቸው ሕግ አስከባሪዎች፤ አካለ ጎደሎ ተሽከርካሪ የሰው ሕይወት ተሸክሞ እንዲነዳ ፈቃድ ከሰጠ የመንግሥት አካል ጋር ሆነው እንደ ምንም ብለን እንድናልቅ ተጨማሪ ሰበቦች ሆነዋል፡፡ መቶ ጊዜ የተከሰሰን ሰው፤ መቶ አንድ እስኪ ሞላ እንዲነዳ መፍቀድና በሩ በገመድ የሚታሰር መኪና እንዲሽከረከር ማሳለፍ በሞት ከመስማማት ሌላ ምን ሊባል ይችላል? የሆነ ሆኖ በግብረ ገብነት እጦትና የጥቂት ሰኮንዶችን ትዕግሥት የሚጠይቁ ጥቂት ሕጎችን ባለማክበር እንደ ምንም በመሞትና በመግደል ላይ ያለን እኛ ኢትዮጵያውያን፤ ይህን መድሀኒትና ገንዘብ የማይጠይቅ ሞት ለማቆም፣ ጠባያችንን ካልቀየርን፣ ገንዘብና መድሀኒት ለምነን ኤድስና ወባን መቀነስ የምንችል ይመስላችኋል?
የመሞቻቸው መቅሰፍት በተበራከተበት አገርስ፣ ተጣጥሮ ከመኖር ተጣጥሮ መሞት ምን ይባላል?



Read 7895 times