Sunday, 19 January 2020 00:00

ድህረ ዋለልኝ፤ ዞረን የምናየው ሃምሳ ዓመት

Written by  በሔኖክ ገለታው
Rate this item
(1 Vote)

  “በድህረ ዋለልኝ ያለፉት ኀምሳ ዓመታትም፣ የ”ብሔሮች ጥያቄ” እና “የመነጠል ፉከራ” ያልተዘጉ አጀንዳዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያችን ህላዌም ሁሉን በፈጠረ አምላክ ላይ፤ ከእርሱ በመለስም በመከላከያ ሰራዊት ነፍጥ ላይ እንደቆመ፣ ሁለተኛውን ሀምሳ ዓመት ጀምረናል፡፡
            በሔኖክ ገለታው


            መንደርደሪያ
ግራም ነፈሰ ቀኝ የኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት (state) ኅላዌ እስካለንበት ዘመን ጸንቷል፡፡ ታዲያ የዘመናት ተላውጦዎችን ተሻግሮ ዛሬን መዋጀቱ በጥንካሬ ስሌት ውዳሴ የሚቸረውን ያህል፤ እዚህና እዚያ ለሚታዩት መደባዊ ቅራኔዎች መፈጠር ቀጥተኛ ተጠያቂ አድርገው የትችት መርግ የሚያዘንቡበት ወገኖችም አልጠፉም፡፡
ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው ግን ፖለቲካዊ ተዋስዖዋችን (Discourse) በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ተቀይዶ ግማሽ ክፍለ ዘመን መዝለቁ ነው:: ለዚህ ደግሞ ዓቢይ ምክንያቱ የሚመነጨው ታሪክ (History) የዛሬው ፖለቲካ አንጽሮተ ኅልዮ እንዲሆን በመገደዱ ነው፡፡ ዛሬ በሀገራችን በግልጽ እንደሚታየው፤ ሥልጣንን ኦሜጋቸው አድርገው ለሚነሱ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት “ጭፍለቃ” እና የብሔረ መንግሥት (Nation building) “ስልቀጣ”፣ ተበልተው ያላለቁ ዕቁቦች ናቸው፡፡ ይህ ከታሪክ ይልቅ “ተረክ” የፖለቲካችን ድጋፍ የመሆኑ እውነታ፣ “መብቴን ከዜግነት ሳይሆን ክፍለ ዘመናትን ከተሻገረው ታሪክ ልቅዳ” የሚለውን ወገን አበርክቶታል፡፡
ለዚህ አደገኛ አዙሪት ዋቢው ደግሞ “ዘመናዊ” የሚባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ይዞ የተነሳቸው ያልተመረመሩ ጥያቄዎች ናቸው:: እንደ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ዕምነት፤ በድኅረ ዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ፣ “ጨቋኝ” የተባለውን የአጼውን ሥርዓት ለመቀየር፣ ከሥር ነቀልተኝነት ለውጥ በመለስ ያሉ በብስለትም በጥራትም ክቡድ ዋጋ የሚሰጣቸው ትግሎች፣ ከ1920ዎቹ እስከ 1953ቱ ሥዒረ መንግሥት ድረስ በእምር ግለሰቦች ቢደረጉም (ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝ፣ታከለ ወልደ ሀዋርያት፣ብርሃኑ ድንቄ፣ሀዲስ ዓለማየሁ፣…)፣ “ዘመናዊ” ተብለው ለመጠራት ግን በ”ሳይንሳዊ ሶሻሊዝም” አማኙ፣ የ1960ው ትውልድ አልታደሉም፡፡ ይኽ አለመታደል ነው እንግዲህ “ዘመናዊ” የተባለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ታሪክ፣ ከተማሪዎች ንቅናቄ “አሃዱ”እንዲባል ምክንያት የሆነው፡፡
“ዘመናዊ”ው የተማሪዎች እንቅስቃሴ
ከ1960 በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ዘንድ ገፍተው ወደፊት ከወጡ የትግል አጀንዳዎች መካከል፣ በአነታራኪነቱ ግማሽ ምዕተ ዓመትን የተሻገረው የብሔር ጥያቄ ዋነኛው ነው፡፡ ለዚህ ጦሰኛ ጥያቄ ወደ ፊት መምጣት ቀጥተኛ ባለ ሚና ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ በቀድሞ ወሎ ጠቅላይ ግዛት፣ በቦረና አውራጃ፣ መካነ ሰላም ከተማ፣ ከወይዘሮ ዘነቡ ግዛውና ከአቶ መኮንን ካሣ የሚወለደው ዋለልኝ መኮንን ነው:: ዋለልኝ የብሔር ጥያቄን ካነሳበት ምህዋር አንስቶ ጉዳዩን እስከ ተነተነበት (articulate) መንገድ ድረስ ተቃራኒ ዋልታዎች ላይ የቆሙ ሙገሳዎችና ወቀሳዎች ሲንጸባረቁበት፣ ይኸው ኀምሳ ዓመት ሊደፍን ነው፡፡ ዋለልኝ ገና በሃያ አራት ዓመቱ ዛሬም መቋጫ ያጣውን የማንነት ፖለቲካ ስሱ (sensitive) አድርጎ ለማቅረብ የሞከረበት አግባብ፣ ሀገሩን ፋታ ለማይሰጥ ስቃይ ዳርጓታል። በተማሪው እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ ብልጭ ብሎ በአጭር የተቀጨው ይኽ ወጣት ግን፣በግራው ፖለቲካ ትግል ውስጥ የገነነ ሥም ከነበራቸው የኢህአፓ እና መኢሶን አብዮተኞች በላቀ ሥሙ ሳይዘነጋ ዛሬ ደርሷል:: ዋለልኝ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ላይ ይሰነዝራቸው ከነበሩ ትችቶች በዘለለ ፖለቲካዊ ብልጫ (advantage) ለመውሰድ ሲል፣ ከአጋሮቹ ጋር በግብታዊነት ባደረገው የታህሳሥ 1 ቀን 1964 ዓ.ም አውሮፕላን ጠለፋ ሕይወቱ አልፏል፡፡ በአካለ ሥጋ ቢነጠቅም፣ ኅዳር 17 ቀን 1962 ዓ.ም በታገል መጽሔት፣ ቅጽ 5 ቁጥር 2 ያሳተመው “A question of nationalities in Ethiopia” መጣጥፍ (article) ግን ዛሬ ለምንራኮትበት የዘውግ ፖለቲካ ጽንሰ ሃሳባዊ ቅንፍ (Conceptual frame work) በመስጠቱ ወድደን የማናነሳው ፤ጠልተንም የማንረሳው ሰው ሆኗል፡፡
ይኽ የዋለልኝ “የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ” መጣጥፍ፤ ጥቅል በሆነው ማዕከላዊ ጭብጡ “ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ነች” የሚል አንድምታ ይንጸባረቅበታል፡፡ ከዚህ ድምዳሜው በላይ ግን ይኽንን አቋሙን ለማጽናት ሲል የኢትዮጵያን ኅልው መሆን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ስሌት መጠቀሙ፣ ለኢትዮጵያዊ ብሔርተኞች፣ ሁሌም በቀና ልቦና እንዳንቀበለው ምክንያት ይሆነናል፡፡ ጥያቄው እንኳንስ ኀምሳ ዓመትን ወደፊት ተሻግሮ ዛሬ ላለነው ትውልድ ዳፋው ተከምሮብን ይቅርና፣ ለዘመን አቻዎቹም የተዋጠ አልነበረም (ለዚህ አስረጂ አቅርቡ የሚለን ካለ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የሰሜን አሜሪካ ሕብረት፣ 17ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔን ጠቁመን ማለፍ እንችላለን)፡፡ ወደ ዋለልኝ ጽሑፍ ስንመለስ፣ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ካስማዎችን ለማፈራረስ የሄደባቸውን ስሁት መንገዶች ነቅሰን ከመመልከታችን በፊት ግን ይህንን ጽሑፍ ሲጽፍ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን አስመልክቶ ያለው መረዳት በራሱ ምሉዕ መሆኑ ላይ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርገንን አንድ ፍንጭ ይዘን፣ ጥቂት ነገር ማለት ይኖርብናል፡፡ ይህ ፍንጭ ከተጠቀሰው የዋለልኝ ጽሑፍ መግቢያ የሚመዘዝ ነው:: በጽሑፉ መንደርደሪያ እንዲህ የሚል ሃሳብ እናገኛለን፤ “የጽሑፉ ዓቢይ ዓላማ በሀገራችን እጅጉን አንገብጋቢ በሆነው “አይነኬ” የብሔሮች ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማጫር ይሆናል፡፡ ይኽ ጽሑፍ ለአንድ የተለየ ምክንያት ተዘጋጅቶ የነበረ (ዝርዝር ዘገባው በግሌና በሌሎች አመቺ ባልሆኑ ምክንያቶች ሳይቻል የቀረ) በመሆኑ፣ባልተሟሉ ትንታኔዎች እንዲሁም የጅምላ ድምዳሜዎች የተነሳ በተወሰነ መልኩ ያልተሟላ ያደርገዋል::” (የተራማጆቹ መጨረሻ፤ ገጽ 335)
ይኽ መንደርደሪያ በጽሑፉ ከሰፈሩት ሃሳቦች ጀርባም ሆነ የራሱን የዋለልኝን የተነሳስዖት መግፍዔ በትንታኔ ሥነልቦና ሂስ (Psycho analytic criticism) ገፍቶ ለመመርመር ዕድል ሰጪ ነው፡፡ የጉዳዩን “ታቡ”ነትም ሆነ መዘዙን ከግምት አስገብተን፣ ዋለልኝ በጎዶሎ መረጃ ጉዳዩን ለማስጮህ የደፈረበት አመክንዮ “ምን ይሆን?” ካልን፣ ለብዙ መላምት መጋለጣችን አይቀሬ ነው፡፡ በተደጋጋሚ በተማሪው እንቅስቃሴ ላይ እንደሚሰማው ትችትም፣ “ኮሚዩኒዝሙ ሀገሩን የማያውቅ እንጭጭ ነው”ብለን የሀሳቡን ጠንቀኝነት ከዋለልኝ ፍላጎት አሻግረንና ሻዕቢያን አሳብረን፣ ወደ ዘመናት ቄሳራዊ ተንኮል ጠንሳሽ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር መድረስ እንችላለን።
ከዚህም በላይ ደግሞ አንዳንድ የዕድሜ ዘመን እኩዮቹ፣ በዚህ ዋለልኝ “ጻፈው” በሚባለውና አደገኛ ድምዳሜዎች በሰፈሩበት ጽሑፍ ላይ ጥርጣሬያቸውን ከመግለጽ ወደ ኋላ ያላሉበት ሁናቴ፣ ነገሩን በደንብ መመርመር ያሻዋል በሚለው አቋም ላይ ያጸናናል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁሩ ሹመት ሲሻኝ (ፕሐር) ከዓመታት በፊት በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ሃሳባቸውን ሲያካፍሉ፤ ዋለልኝ ይህንን ጽሑፍ ለመድረክ ከማብቃቱ አንድ ወር በፊት በጭብጡ ከተንጸባረቀው የተለየ አቋም እንደነበረው ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ በአንጻሩ እንደ ሀሰን አዳል መሐመድ (ዶሐር) ያሉ ምሁራን ደግሞ ዋለልኝ “ነበረ” የሚለውን የማንነት ጭቆና ሃቲት ቅቡል ባያደርጉም፣ ያቀረበውን መራዥ ጽሑፍ ግን አዎንታዊ ማረጋገጫ (positive justification) በመስጠት ሲያምታቱ በግልጽ ይታያል (“ቋንቋ እና ብሔርተኝነት” የሚለው መጽሐፋቸውን ያነቧል):: ለማንኛውም ግን ሃምሳ ዓመታትን ወደፊት ተሻግሮም፣ ለንትርክና ፖለቲካዊ ምስቅልቅላችን ቀጥተኛ መነሻ በሆነውና ዋለልኝ “የተሟላ ትንታኔ አልቀረበበትም” ባለው በዚህ “የብሔሮች ጥያቄ” መጣጥፍ፣ በድፍረት ያነሳቸውን ሁለት አደገኛ ነጥቦች ነቅሰን፣ ከሀቀኛ ኢትዮጵያዊ ሥነልቦና አንጻር በአጭሩ እንመርምር፡፡
፩) የብሔር ጭቆና ሃቲት
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ የሀገረ መንግሥት ምስረታ፣ ጥንስሱን ከሰሜኑ ክፍል (ጎንደር) አድርጎ ዕርገቱ በመካከለኛ ክፍል ሸዋ ሆኗል:: በዚህ ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ በ”ገብር አልገብርም” ውጊያም፣ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች መፈጠራቸው እሙን ነው:: በንጉሥ ምኒልክና በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት “እምቦቦ” ላይ ከተደረገው ውጊያ አንስተን፣ ልጅ እያሱን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሰገሌ ድረስ እስከ ተካሄዱት አስራ አራት ያህል ጦርነቶች ብንቆጥር፣ ውጤቱን፣ በዛሬው ቋንቋ “አማራ ከአማራ ጋር ተዋግቷል” ብለን በአደባባይ ለመናገር የሚያበቃ ማስረጃዎች አሉን፡፡ ማዕከላዊው የሸዋ መንግሥት በጦር ኃይል አመራር፣ ፖለቲካዊ ሹመትና ኢኮኖሚያዊ ሞኖፖሊ ብሎም ስብጥር ውስጥ የሸዋ (ኦሮሞዎች፣ አማሮች፣ ጉራጌዎች) እና ትግርኛ ተናጋሪዎች ተሳታፊ የነበሩበት ሥርዓተ መንግሥት መኖሩን አሁንም በማስረጃ ለመሞገት አናንስም፡፡
ይኽ ማለት በተጠቀሱት ወሳኝ ሁነቶች ውስጥ የወሎ፣ የጎጃምና የጎንደር አማሮች የተገፉ ነበሩ ብለን አፋችንን ሞልተን ለመናገር የሚያበቃ ድፍረቱን ይሰጠናል ማለት ነው፡፡ ለሀገር ምስረታው ስምረት ቁልፍ ሚና የነበራቸው “አማርኛ ቋንቋ” እና “የኦርቶዶክስ ሃይማኖት”ም የአንድ ብሔረሰብ ርስቶች ተደርገው ሊቆጠሩ የሚያስችላቸው ተፈጥሯዊም ሳይንሳዊም መሠረት እንደሌለ፣ ነባራዊ እውነታውን (The existing objective fact) ከትናንት ይልቅ ዛሬን እንደ ዋቢ በመውሰድ፣ ዘውጌዎች ጋር መፋጠጥ እንችላለን (“አማርኛ ቋንቋችሁ የሆነ?” ቢባል አማራ ብቻ እጁን ሲዘረጋ ይታያችሁ፤ ኦርቶዶክስም እንደዛው...)፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሣዊ አገዛዝ፣ ታሪካዊ የሥልጣን መነሾውን፣ ከሰለሞን ሥርወ መንግሥት ማድረጉም፣ ለይቶ በኢትዮጵያ ብቻ ክሱት የሆነ እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ ቅባትን መነሻ አድርጎ ሲመት ማግኘትም፣ ድኅረ ዘመናዊነት (Post Modernism) ላይ በደረሰችው የዛሬዋ ዓለማችን፣ ከአውሮፓዊቷ እንግሊዝ እስከ ሳዑዲ አረቢያ ዓይንን ገልጦ ማየት ነው፡፡ ዋለልኝ በተጠቀሰው ጽሑፉ ግን እንዲህ ይለናል፤ “…ይኽ የኢትዮጵያ እውነተኛ ምስል ነው፡፡ በእርግጥ በገዢው መደብ የተስፋፋና በግዴታ የዋሃን የተቀበሉት፤ ሌላው ቀርቶ የሚያዛምቱት ሃሳዊው የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አለ፡፡ ታዲያ ይኽ ሃሳዊ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ምንድ ነው? እንደው በቀላሉ አማራና በተወሰነ ደረጃ የአማራ - ትግሬ የበላይነት አይደለምን? ማንኛውም ሰው የኢትዮጵያ ባሕል ምንድነው ብለው ይጠይቁት? ማንኛውም ሰው የኢትዮጵያ ቋንቋ ምን እንደሆነ ይጠይቁት? ማንኛውም ሰው “የብሔረሰቦች አለባበስ” ምን እንደሆነ ይጠይቁት? የአማራ ወይም የትግሬ-አማራ ነው” (ዝኒከማሁ፤ ገጽ 336 - 337)
ይኽ ያልተገራና ሽንቁሩ የበዛ ድምዳሜ፤ ከኢትዮጵያዊ ዕሳቤ አንስቶ ኢንዱስትሪ ብርቅ ሆኖበት ጎበዝ ሸማኔ በጥበቡ ሰርቶ ቆዳውን እስከ ሸፈነበት ልብስ ድረስ የእርሱ ነው የተባለው “አማራ”ን በደንብ ማጥናትን የሚጠይቅ ነው:: አማራ በየትኛው አካባቢ እንደሚኖር፣ ምን ዓይነት “ወጥ” የሆነና የተባለው ዓይነት አለባበስ እንደሚለብስ? ማንስ ሸምኖ እርሱን [አማራውን] እንደሚያለብሰውና ማንስ የተሸመነውን “የአማራ ነው” ብሎ ሌላውን ከልብሱ ባለቤትነት እንደቀነሰው? ከማኅበረሰብ ጥናት (ሶሲዮሎጂ) እስከ ሥነ ሰብዕ (አንትሮፖሎጂ) መርምረን ዶርዜን፣ አገውን፣ ጉራጌን፣ ጅማን፣... ጥግ ማስያዝ ይጠበቅብናል፡፡ በዋለልኝ ጽሑፍ አንድምታ ኢትዮጵያዊ ብሔረተኝነት “ሃሳዊ” ነው፡፡ ይኽ ደፋር ድምዳሜ በዘመናችን “የጋራ የሚባል ታሪክ የለንም” ብለው ለተነሱ የኋለኞቹ ነቢያት ማስረጃ ሆኖ እያገለገለ ነው፡፡ “ሃሳዊ” የተባለው ኢትዮጵያዊ ማንነት የተገነባባቸው የድል ታሪኮቻችን፣ ጥንታዊ ጥበባችን፣ ፊደላችን፣ የዘመን ቀመራችን፣… ኹሉ በዋለልኝና በእርሱ ወለድ ስሁት ዕሳቤ ለተመቱ የመንፈስ ልጆቹ፣ “የአንዳችን እንጂ የሌላችን አይደሉም”:: ኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ዜጎች በዘመናት አብሮነት ውስጥ የወለዱት የጋራ መለዮ ሳይሆን በዋለልኝ አገላለጽ፤ “በግዴታ የዋሃን የተቀበሉት” ባዕድ ማንነት ነው፡፡ ከነዚህ ጭብጦች የሚነሳው የዋለልኝ “የተሟላ ትንታኔ አልቀረበበትም” ያለው “የብሔር ጭቆና” ሃቲት ቢሰላ፣ ላለፉት ዓመታት ካበጀው ይልቅ የፈጀው ኅልቆ ነው፡፡
፪) የመገንጠል መብት ሃቲት
ኢትዮጵያ ላይ የተዘረጋው የዋለልኝ ጨንገር፤ “ብሔረሰቦች ጭፈራቸውን፣ ውዝዋዜያቸውንና ቋንቋቸውን የሚያሳድጉበት መንግሥት የላቸውም” ብሎ መጋረፉን በተጠቀሰው ጽሑፍ ቀጥሏል:: ዋለልኝ ይኽን ሲል ግን ዘመናዊ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረበትን የጊዜ ልኬት አስልቶ አይመስልም፡፡ ከተጀመረም በኋላ ሥርዓተ ትምህርቱን (curriculum) የሚቀርጹትና የማስተማሪያ ቋንቋውን የሚመርጡትም ቄሳራዊ ተልዕኮን ያነገቡ እንግሊዛዊያንና ፈረንሳዊያን (አልፎ አልፎም ግብጻዊያን) ስለመሆናቸው ታሪካዊ ዳራውን ለመመርመር የፈለገም አይመስልም:: በዳግማዊ ምኒልክ ዘመናዊት ሐቤት ተምረው የውጪ ሃገር የትምህርት ዕድል ካገኙት የመጀመርያዎቹ አስራ አንድ ተማሪዎች መካከል ምን ያህሎቹ አማራ፣ ስንቶቹ ኦሮሞ፣ ስንቶቹስ ሀዲያ፣ ጉራጌ፣ ትግሬ፣ …እንደሆኑ ለመጠየቅ፤ “ሙስሊሞችስ ነበሩበት ወይ?” የሚለውንም በቅጡ ለመፈተሽ ጊዜ የነበረው አይመስልም፡፡ አማርኛ ቋንቋ የመንግሥት የሥራ ቋንቋ ከመሆን ዘልሎ ዘመናዊ ትምህርት ቤት ከተከፈተበት 1906 ዓ.ም በኋላ፣ እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ለመሰጠት ምን ያህል አሥርታትን እንዳረፈደስ አጥንቶ ይሆን? ዳሩ የትምህርት ቋንቋው ፈረንሳይኛና እንግሊዘኛ ስለ መሆኑ፤ አማርኛን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ለመስጠት እንደነ መርስዔ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ ዓይነቶቹ ዘመናዊ የቋንቋ ሊቃውንት እስኪመጡ 1942 ዓ.ም መድረሱን ማን ይነግረዋል?! አስገራሚው አያዎ (Paradox) ግን የዋለልኝ ጥያቄ ኀምሳ ዓመትን ተሻግሮ፣ “የብሔር ብሔረሰብ መብት ተከብሯል” ተብሎ ነጋሪት በሚጎሰምበት ዛሬ፣ ከሰማንያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ብሔረሰብ አለባት በምትባለው ኢትዮጵያ፤ የትምህርት ቋንቋዎች ከሃያ አምስት ያልበለጡበት አመክንዮን ደፍሮ ጠይቆ፣ “ጭቆናው ስለቀጠለ ነው” የሚል ምናምንቴ ምላሽ የሚሰጠን የ“ፌዴራሊስት” ኃይል መጥፋቱ ያሳዝናል፡፡ ዋለልኝ መጠነ ሰፊ ነው ብሎ የገለጸው ይኽ የብሔር “ጭቆና” አርነት ከሚያገኝባቸው መንገዶች መካከል አንዱ፣ “መገንጠል” መሆኑን ከላይ “..የሚያሳድጉበት መንግሥት የላቸውም” ብሎ በገደምዳሜ ቢያስቀምጠውም፣ ዝቅ ብሎ ግን በግላጭ ይጠቁመዋል፡፡ ቀንጭበን እንመልከት፤ “አሁንም በድጋሚ አንድ ነገር እርግጥ ነው:: እነዚህ እንቅስቃሴዎች የመገንጠል ስለሆኑ ብቻ አልቃወማቸውም፡፡… የመገንጠሉ ጥያቄ በላብአደሩና በጎስቋላ አርሶአደር እየተመራ ዓለማቀፋዊ ግዴታዎችን እስካሟላ ድረስ የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን የወታደራዊ እርዳታ የሚደረግለት ይሆናል፡፡ እኔ በጨቋኙ ጫማ ተተክቼ እስክትነቃ ልበዝብዝህ ማለት ኋላ ቀርነትና እራስ ወዳድነት ይሆናል፡፡” (ዝኒከማሁ፤ ገጽ 340)
እንግዲህ በዚህ ሃሳብ ውስጥ በኢትዮጵያ በ1960ው ብረት አንስተው እንቅስቃሴ ለማድረግ ሙከራ እያደረጉ የሚገኙት የኤርትራና የሌሎች አማጽያን ትግል መቋጫ አንድ መንገድ፣ እስከ መገንጠል የሚደርስ መሆኑን እንደ “ርትዕ” መቁጠሩን መታዘብ ይቻላል። ይህ የዋለልኝ የመገንጠል ሃሳብም ሆነ ለእርሱ መነሻ ሆኗል ብሎ ያስቀመጠው የብሔር ጭቆና፣በኹለት መንገድ ኢትዮጵያ የቆመችበትን አምድ ለማፍረስ ምክንያት ሆኗል ብሎ በድፍረት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የመጀመርያው የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት የሄደችበትን ዳና በመከተል ሙሉ በሙሉ ለኢትዮጵያ “ችግር” መውጫ አድርጎ የሌኒንን ሃሳብ ይዞ መከሰቱ ነው፡፡ ይኽም የዋለልኝን ብቻ ሳይሆን በጥቅል የ”ያ ትውልድ” አባላትን ኢትዮጵያን በተመለከተ ስለነበራቸው የጎደለ መረዳት ትዝብት ላይ ይጥላቸዋል:: በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘመናትን በፍልሰት፣ በስደት፣ በጦርነትና በሌሎችም መደበላለቆች የገነቡትን ማኅበራዊ ትስስር በመገንዘብና አብሮ ለመኖር እርግማን እንደሌለባቸው በማመን፣ የተሻለ ሥርዓትን ለማንበር አዲስ መንገድ አለመከተላቸው፣ “ጥራዝ ነጠቅ” ከመሆናቸው በባሰ፣ ለሀገሪቱ መቀጠል ደንታ እንዳልነበራቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያልና መነጠልና መገነጣጠል የዶሮ ብልትን ያህል በዋለልኝ “ምክረ ሃሳብ” ውስጥ ግዘፍ ነስቶ ሊቀመጥ ችሏል:: ኹለተኛው ስሁት አካሄድ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት (state) ዕውቅና ካለ መስጠት ባህሪያዊ ችግር ይመነጫል፡፡ ይህ አካሄድ መሰረታዊ ሊባል በሚችል ደረጃ የ“ያ ትውልድ” መግባቢያ ስለ መሆኑ አያከራክርም:: ያሳትሟቸው በነበሩ የትግል መጽሔቶች ላይ ኢትዮጵያን እንደ “ግዛተ አጼ” (Empire State) አያሳፍርም። የተሰራችበችን ቅርጽ (Political land scape) በሥር ነቀልተኝነት አውድሞ በፍርስራሹዋ ላይ “ትንንሽ ሃገሮች እንገነባለን” የሚል ተምኔታዊ መሳከር በጉልህ ስለ ማንጸባረቃቸውም ለታሪክ ከተቀመጡት ልሳኖቻቸው መታዘብ ይቻላል:: የዋለልኝ መኮንን ከ “ሸማና ዶሮ ወጥ የአማራ በመሆናቸው...” ተረክ የተሻገረ ወሳኝ መደባዊ ቅራኔዎች ባልተተነተኑበት ጽሑፍ፣ “መገንጠል”ን እንደ ቀላል የባልና ሚስት ጉዳይ አድርጎ የማሰብ “ምክንያታዊነት”ም የሚመነጨው፣ ከዚሁ ለኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት ዕውቅና ካለመስጠት ችግር ነው፡፡
መደምደሚያ
ዋለልኝ መኮንንና የዘመን ተጋሪዎቹ፣ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ካስማዎች ላይ በደነቀሯቸው ጋሬጣዎች፣ ኢትዮጵያ ህልውናዋን በማይናወጥ መሰረት ላይ ተክላ እንዳትቆም፣ ዛሬም አደጋ የሆኑባት የአስተሳሰብ ሰንኮፎች አልተነቀሉም፡፡ በድህረ ዋለልኝ ያለፉት ኀምሳ ዓመታትም፣ የ”ብሔሮች ጥያቄ” እና “የመነጠል ፉከራ” ያልተዘጉ አጀንዳዎች ሆነው ቀጥለዋል፡፡ የኢትዮጵያችን ህላዌም ሁሉን በፈጠረ አምላክ ላይ፤ ከእርሱ በመለስም በመከላከያ ሰራዊት ነፍጥ ላይ እንደቆመ፣ ሁለተኛውን ሀምሳ ዓመት ጀምረናል፡፡ በቃችሁ ይበለን፡፡


Read 1496 times