Saturday, 18 January 2020 13:34

የዘንድሮው ምርጫ ገና ጉድ ያሳየናል!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(6 votes)


             የሰሞኑ አቢይ አጀንዳ የሆነው የምርጫ ጉዳይ፣ ብዙዎቻችንን ያነጋገረ ሲሆን በቀጣይም ማነጋገሩ አይቀሬ ነው፡፡ ጉዳዩ በሁሉም ሰው ልብ ውስጥ ሲጉላላና አሁንም ምቾት የሚነሱ ተጨባጭ ምክንያቶችን በጀርባው ያዘለ ነው፡፡ የዘንድሮን ምርጫ ከወትሮው ለየት የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮችና ምክንያቶች  አሉ፡፡ በይበልጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከያሉበት፤ አንዳንዶቹም ከተሰደዱበት ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ዕድል ማግኘታቸውና የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱ እንደ አንድ ምክንያት የሚታይ  ነው፡፡
በተጨማሪም ቀደም ሲል የነበረው ወያኔ መራሹ መንግስት በሃይል ይጠቀምበት የነበረው አገዛዝ አላዋጣ በማለቱ በተደረገው ትግል ለውጥ መደረጉና ለውጡም በገቢር ይገለጥ ዘንድ ግድ የሚሉ አደረጃጀቶችና ቡድኖች (እንደ ፋኖና ቄሮ ያሉ) መፈጠራቸውና አሁንም መኖራቸው እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ከዚያም ባሻገር ዕድሜ ዘመናቸውን በአፈ-ሙዝ መታገል ያዋጣናል ብለው ያልተሳካላቸውና ዛሬም ቁጭቱ ያልለቀቃቸው የፖለቲካ ሃይሎች፤ ጋናቸውን በባሩድ አጥነው፣ ጠላቸውን የመጥመቅ አባዜ የተጠናወታቸው መሆኑ ስጋትን ያንራል፡፡  
በሌላ ወገን ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ የለውጡ መንግስት፣ ወታደራዊ ሀይልን ለመጠቀም ያሳየው ለዘብተኝነት ምርጫውን ቆፍጠን ባለ ሁኔታ ለማካሄድ ጥንካሬ ይጎድለዋል የሚል ፍርሃት መፍጠሩ ነው፡፡ ፍቅርና አንድነትን በመስበክ ብቻ ጠማማው ይቀናል ብሎ የሚደክመው የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፤ በምርጫው ወቅት በዚሁ ከቀጠለ ሀገር ትቀወጣለች የሚለው ስጋት፣ በየሰው ልብ ተራራ ሆኖ እንደተቆለለ መቀጠሉ አይቀርም፡፡
በዚህና በመሳሰሉት ምክንያቶች የምርጫው ጉዳይ ሲያጨቃጭቅ ከርሟል፡፡ ምርጫው መራዘም የለበትም የሚሉት ወገኖች በአብዛኛው ወያኔና ሌሎች ግርግሩን ተጠቅመው፣ መንግስትን ባተሌ ካደረገው የደህንነት ጉዳይ እንዳይወጣ በየቦታው ግጭት የሚጭሩ የስልጣን ጥመኞች ይመስላሉ፡፡ አንዳንዴም ግራ እስኪገባን ድረስ በሬ ወደ አራጁ ጉያ እንደሚገባ፣ ወደ ትናንት አሳሪና ገራፊዎቻቸው የሚሸሸጉትን ስንመለከት የስልጣን እብደት ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ሊሆን እንደማይችል እንገምታለን:: ስለዚህም ነጋ ጠባ ጩኸታቸውና ሙሷቸው ‹‹ምርጫው በጊዜው ይካሔድ›› የሚል ነው፡፡
ለ27 ዓመታት ኪሱን በብር ያሳበጠውና በምርጫ ሰበብ በአደባባይ ወጣቶችን በጥይት የደበደበው ወያኔም፤ የዲሞክራሲና የፍትህ ተሟጋች መስሎ ብቅ ማለቱ የምርጫው ድራማ አስቂኝ ክፍል ነው፡፡ የምርጫ ከረጢት እስከ መስረቅ ድረስ የሄደው ያ ቡድን፤የምርጫ ወቅት መከበር አለበት ብሎ ስለ ዲሞክራሲና ህገ መንግስት ሲከራከር ሰምተን፣ “ያልሞተ ሰው ስንት ያያል!” ብለናል፡፡ በተለይ በቅርቡ ያንጠለጠላት የታጠበች አሮጌ ሻንጣ ታስቃለች:: ሰሞኑን ፌዴራል ስርዓቱ ሊናድ ነው የሚለው ማለቃቀሻው ጉድ የሚያሰኝ ነው፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ ፌዴራሊዝምን አስፍኖ ነበር ወይስ ሞኖፖላይዝ አድርጎ?! አማራን በማን እንደገዛ፣ ኦሮሞን እንዴት በሞግዚት እንዳስተዳደረ የማናውቅ አድርጎ ለመገመት አምስት አመት እንኳ ሳይቆይ ብቅ ማለቱ የድርቅናውን ልክ ማሳያ ነው፡፡ ለመሆኑ ደቡብን በአንድ ላይ ጨፍልቆ መግዛቱንስ እንዴት ረሳው!! ለውጡ አሃዳዊ ስርዐት ለመመስረት መምጣቱን ለመለፈፍ የሚያበቃ ፍንጭስ ከየትኛው ጉዳጓድ ቀዳ!! ጅብ በማያውቁበት ሃገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ማለቱን ማረጋገጫው ይህ ውሸትና ቅዠት ነው፡፡
በአብዛኛው እንደምንታዘበው፤ ወያኔ ብቻ ሳይሆን ጥቂት የማይባሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ የሃገሪቱ ደህንነት ጉዳይ ያሳሰባቸው አይመስሉም፤ ይልቅስ ልባቸው ደረታቸውን የሚደበድበው ሥልጣን ላይ ለመንጠልጠል ይመስላል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ምርጫው እስኪደርስ መንግስትን ለማጣደፍ ዛሬ በየዩኒቨርሲቲው ሳይቀር ነገር እየቆሰቆሱ መንግስትን በማዋከብ፣ የፖለቲካ ቁማራቸውን አጧጡፈዋል፡፡ የሃገር ጉዳይ እንደማያገባቸው ጥግ ይዘው ቆመው የሚስቁም ፖለቲከኞች አልጠፉም፡፡ ስልጣን ያለ ሀገር የሚገኝ የመሰላቸው ሰነፎችም በዚሁ በፖለቲካው ሰፈር አሉ፡፡ ምናልባት ተስፋ የሚሰጠው “ትግላችን ሁሉ ለፍትህና ለዴሞክራሲ፣ ለሰላምና ለአንድነት ነው›› ብለው  የሀገሪቱን ድባብ እያዩ፣ ራሳቸውንና ፓርቲያቸውን ከሃገር ቀጥሎ የሚያስቀምጡ እንዳሉ ስናይ ነው፡፡
ይህ ምርጫ ለአንዳንዶች የሰርግ ዋዜማ፣ ለሌሎች ደግሞ የምጥ ጣዕር መጀመሪያ ይመስላል፡፡ ስለ ስልጣንና የግል ክብር አብዝተው የሚቃዡቱ፣ ምርጫው በጥድፊያ መደረጉ የሰርግ ድግስ እንደሚሆንላቸው ያስባሉ፤ መንግስት ከተረጋጋ እድሉን እንነጠቃለን ብለው ይሰጋሉ፡፡ በሌላኛው ወገን ያሉት ጥቂቶቹ ደግሞ ስልጣንም ክብርም የሚገኘው ሃገር ስትኖር ነውና፣ ምርጫው ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነ በኋላ ቢደረግ እንደሚመርጡ አቋም እስከ መያዝ ደርሰዋል፡፡
የተለመደው ዐይን አውጣነት ያለቀቀው ወያኔም ባንድ በኩል፣ በክልሉ ብቅ ብቅ ያሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እያሰረና እየደበደበ፣ በሌላ በኩል ምርጫው በጊዜው መካሄድ አለበት እያለ ይለፍፋል፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍ ዘመኑ ሲያበቃ፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ ቀንበሩን ጭኖ ዘመን መግፋት መመኘቱም የሚያስቅ ድርቅና ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ በአፈ ሙዝ ተገድዶ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱ ተረግጦ የሚኖርበት ጊዜ እንዳያበቃ ደፋ ቀና ማለቱም፣ ዛሬም ከእንቅልፉ እንዳልነቃ የሚያረጋግጥ፣ የጅል ዘፈን ይመስለኛል፡፡ በድሮ በሬ የሚያርስ የደርግ ዘመን ታጋይ፣ ዘመኑን የማይመጥን ነው፡፡
እንግዲህ የዘንድሮ ምርጫ የዚህ አይነት ውጥንቅጥ የበዛበት ነው፡፡ ኦነግ በብዙ ተበትኖ፣ ከፊሉ ለነጻ ምርጫ ወደ ሰላማዊ አደባባይ መጣሁ ሲል፣ ሌላው ሃገር እያመሰ፣ ወገን እያስለቀሰ ነው፡፡ ማን ጤነኛ፣ ማን በሽተኛ እንደሆነ እንኳ በቅጡ ለማወቅ ግራ ያጋባል:: አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል፣ ኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና ሌሎቹም የየራሳቸውን ዜማ እያዜሙ፣ ብሶታቸውን እየዘከዘኩ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ አንድነትና በሰላማዊ ትግል ውስጥ እንደ አርአያ የሚጠቀሱት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ በፓርቲያቸው ውስጥ የቀድሞውን አክቲቪስት ጃዋር መሃመድ ማካተታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፤ ምናልባትም በኦሮምያ ክልል ውስጥ የሚኖረውን የድምጽ ክፍፍል ይቀይረዋል የሚል ግምትም ፈጥሯል፡፡
ሌላው በዚህ ዓመት ምርጫ ያስተዋልነው፣ ያልተጠበቁ ግለሰቦች አቅም አግኝተው መምጣታቸውን ነው፡፡ እሳቸውም በቃኝ ብለው፣ እኛም አበቃላቸው ብለን የተውናቸው አቶ ልደቱ አያሌው ቀዳሚው ናቸው፡፡ ሰውየው በተለይ ስለ ምርጫውና ስለ ሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በየሚዲያው ላይ የሚናገሩት ነገር ቀልብ ሳቢ እየሆነ ነው፡፡ በውይይቶችም ላይ ታሪክ በመጥቀስና ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማመሳከር የሚሰጡት ማሳመኛ እየተደነቀ ነው:: ለዚህም ሰሞኑን በኤልቲቪ ስለ ፌዴራሊዝም ያደረጉት ውይይት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ስለዚህ አቶ ልደቱ አያሌውና ፓርቲያቸው፣ ወደ ሌላ ግምት እንድንገባ ያስገድዱናል፡፡
አቶ ልደቱ ምርጫው በቅርብ መደረግ እንደሌለበት ሲሞግቱ የቆዩ ሲሆን አሁንም ምርጫ ቦርድ የቆረጠውን ጊዜ ትክክል አይደለም ሲሉ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ በተለይ ምርጫው በክረምት መደረጉ ክዋኔውን ያሰናክለዋል የሚል ፍርሃት አላቸው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ ውሳኔውን ይፋ እስኪያደርግ ድረስ ብዙዎች፣ ምርጫው ይራዘም  ወደሚለው አዘንብለው ነበር፡፡ ይሁንና ብዙም የስልጣን ጥማት የማይታይበት የዶ/ር ዐቢይ መንግስት፤ ምርጫው በዚሁ ዓመት እንዲደረግ ያለውን ቁርጠኝነት  አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ  የኛ ልብ አሁንም አልተረጋጋም፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ሃገራችን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡ ገና ክልሎቻችን ከእርስ በርስ ጦርነት ተላቅቀው፣ ባልተረጋጉበትና ህግ በቅጡ ሞገስ ባላገኘበት ድባብ ውስጥ ሆነን፣ ብዙ ቅዠትና ምኞት ያለበትን ምርጫ በስኬት እናካሂዳለን ማለት የሚከብድ ይመስላል፡፡
ይህ ክብደት ደግሞ ነገ ወደ ዕብደት ተቀይሮ መያዣና መጨበጫው ወደሚጠፋበት አቅጣጫ እንዳይሄድ መንግስት ነገሮችን ቢፈትሽ ብለን መመኘታችን አይቀርም፡፡ በየዩኒቨርሲቲው የሚታየው እብደትና ቅብጠት፣ በየጎጡ ያለው የስልጣን ሽሚያ ልክ ሳይገባና ሳይሰክን፣ በጥድፊያ ምርጫ ውስጥ መግባት ውጤቱን ለመገመት የሚያሰጋ ነው፡፡ ምንም እንኳን በመንግስት በኩል ያለው ዝግጅት ምን ዐይነትና ምን ያህል እንደሆነ ባናውቅም፤ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ስጋት የሚፈጥር ነው፡፡ ከእንግዲህ ባለፉት አመታት የከፈልናቸውን አሰቃቂ መስዋዕትነቶች መክፈል ያለብን አይመስለንም:: በየቦታው መፈናቀል፣ በብሄር ተቧድኖ እርስ በርስ መጋደል ዳግመኛ ዝር ማለት የለበትም፡፡
በተለይ የሃገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉና የሰላማዊ ትግል ጽንሰ ሃሳብና ልምድ ያዳበሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፤ ሃገሪቱን የጦርነትና የሽብር ሱስ ከተጠናወታቸው ወገኖች ለመታደግ መትጋት አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን የመሳሰሉ አንጋፋ ፖለቲከኞች ሚና ይኖራቸዋል ብዬ እገምታለሁ:: መንግስትም  የብዙዎችን ሕይወት ከቀጠፈው የቀድሞው ምርጫ ልምድ በመውሰድ፣ ከወዲሁ የቅድሚያ ጥንቃቄ  ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይ የህዝቡን ደህንነት ማስከበር የሚችል ወታደራዊና ስነ ልቡናዊ ቁመና ያለው ሰራዊት ማዘጋጀት ግድ ይላል፡፡
እንደ አንድ ሃገር ወዳድ ዜጋም፣ ውጤቱ ለሃገሪቱ አንድነት ወሳኝ በመሆኑ፣ ለቀጣዩ ዘመን የተሻለ ራዕይ ያላቸው ፓርቲዎች ድል ይቀዳጁ ዘንድ ህዝቡም በጥንቃቄ አመዛዝኖ፣ ድምጽ እንዲሰጥ ማሳሰብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡ ሰሞኑን በኤርትራ የኦነግ የስልጠና ሃላፊ የነበሩት ኮሎኔል የተናገሩትን ልብ ማለትም ያስፈልጋል:: በመለሳለስ ብዛት ሃገር እንዳትፈርስ ጠንካራ አቋም መያዝ ይገባል፡፡ በተለይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡ፣ በዚህ ረገድ፣ ከአሁኑ ቁርጠኛ አመራር መስጠት እንዳለባቸው ማሳሰብ የግድ ነው፡፡ መጪው ምርጫ የዲሞክራሲና የአዲስ ተስፋ እንጂ የጥፋት እንዳይሆን፣ ወደ እብደቱ ሳንገባ፣  በሰከነ መንፈስ በትጋት መስራት አማራጭ የለውም፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉትንና ለምርጫ ቦርድ የቀረቡ ከምርጫ ጊዜና አፈጻጸም ጋር የተያያዙ አስተያየቶችና ስጋቶችን የተቋሙ ሃላፊ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳና ባልደረቦቻቸው ምላሽ  ሊሰጡበት ይገባል፡፡ በተረፈ ግን ቀጣዩ ምርጫ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ የመሆን ተስፋ እንዳለው አንዱ ማሳያ፣ አብዛኞቹ ፖለቲከኞች እምነት የጣሉባቸው ቆፍጣናዋ ዳኛ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ቦርዱን ሪፎርም አድርገው፣  እየመሩት መሆኑ ነው፡፡

Read 12884 times