Saturday, 18 January 2020 13:28

የትናንት ወዲያው ዘግናኝ አጋጣሚ!!

Written by  ታገል ሰይፉ
Rate this item
(2 votes)

    “አቤት የሰዉ ድንጋጤ!… አቤት የሰዉ ሃዘን! … አቤት ትርምስ! … ለገሃር ሰማይን ድንኳንዋ አድርጋ ለቅሶ ተቀመጠች…. ያዙኝ ልቀቁኝ አለች…. ያልተሰማ ጩኸት…ያልተረጨ እምባ… ያልተደቃ ደረት… አልነበረም፡፡”
             
                  ከትናንት ወዲያ ለገሃር አካባቢ ያየሁት አይነት ዘግናኝ ትእይንት በህይወት ዘመኔ አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ ሐሙስ ጥር 7 ቀን 2012 ዓ.ም  ከቀኑ 9 ሰዓት ተኩል ግድም ነው:: አንድ የቆየ መጽሐፍ ለመግዛት ከቄራ ተነስቼ፣ በጨርቆስ በኩል አቋርጬ፣ ወደ ለገሃር አቅጣጫ በማምራት ላይ ነበርኩ፡፡
ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ ስታዲየም የሚያመሩትን መኪኖች ለማሳለፍ፣ እኛ ላይ የበራው ቀይ የትራፊክ መብራት ያስቆመን፣ የለገሃሩ ሃውልት አካባቢ ነው፡፡ ቁጭ ብሎ የመቆምን አሰልቺነት ለመቀነስ አንድ ወዳጄ ጋር ስልክ ደውዬ ወግ መጠረቅ ጀመርኩ፡፡ እያወራሁ አይኔን ከፊት ለፊቴ ከማየው ህንፃ ላይ ጣል አድርጌያለሁ፡፡  ህንፃው በግርማዊ ጃንሆይ ዘመን የተሰራ ይመስላል፡፡ በኋላ ላይ እንዳረጋገጥኩት፤ ከህንፃው አናት ላይ መለያ ስም የለውም፡፡ ከህንፃው ምድር ቤት ያነበብኩት ብቸኛ ስም “ኦክ ባርና ሬስቶራንት” የሚል ነው፡፡
ቀዩ መብራት ቶሎ አለቀቀንም፡፡ እኔ ከወዳጄ ጋር አወራለሁ፡፡ አይኖቼን ወደ ህንፃው ወገብ እንዳሻቀብኩ….. ድንገት ነው፡፡ ከፎቁ ወገብ ጀምሮ እየተውለበለበ ቁልቁል የሚምዘገዘግ ቡናማ ጨርቅ ያየሁ መሰለኝ፡፡ በህንፃው መስኮቶች ዙሪያ ምንም አይነት ልብስ ማስጫ ገመድ ስለሌለ፣ በከፊል አእምሮዬ “የምን ጨርቅ ነው እየተውለበለበ የሚወርደው?” እያልኩ ከወዳጄ ጋር የጀመርኩትን የስልክ ወግ ለመቀጠል ሞከርኩ፡፡ ግን አቃተኝ፡፡ ጨርቁ ወደ አንደኛ ፎቅ ሲቃረብ፣ በህንፃው አቅራቢያ የሚያልፍ የኤሌክትሪክ ገመድ በሃይል ሲነቃነቅ ተመለከትኩ፡፡
በዚያች ቅጽበት “አንድ ጨርቅ የኤሌክትሪኩን ገመድ እንዴት ይሄን ያክል ያነቃንቀዋል?” ለሚል ጥያቄዬ በቂ ምላሽ አላገኘሁም፡፡ በመምዘግዘግ ላይ ያለው ጨርቅም መሬት ሲነካ አላየሁም፡፡ ያ ጨርቅ መሬት ከመንካቱ በፊት በህንፃው ዙሪያ በተኮለኮሉት ዛፎችና ሌሎች ነገሮች ተጋርዶ የመምዘግዘግ ትእይንቱ ከአይኔ ተሰወረ፡፡
ብዙም ሳይቆይ “ዱዋ” የሚል የፍንዳታ ድምጽ ሰማሁ፡፡ ከዚያም የሆነ ነገር ሲፈነዳ በዙሪያው ያሉ ጠጠሮችና ስብርባሪ ነገሮች በየአቅጣጫው በሚፈናጠሩበት አይነት ሁናቴ፣ ብዙ እግረኞች በተለያየ አቅጣጫ ሲበታተኑ አየሁ፡፡ የፍንዳታውን ያክል  ሰዎች እያጉዋሩና እየተጯጯሁ ሲበታተኑ ተመለከትኩ፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር ከላይ እየተውለበለበ ሲምዘገዘግ ካየሁት ቡናማ ጨርቅ ውስጥ አንድ ሰው እንዳለ እርግጠኛ የሆንኩት፡፡ በጥቂት ሰኮንዶች ውስጥ በፍንዳታው ድምጽ በመደናበር፣  ደመ -ነብሱን ተበታትኖ  የነበረው ሰው ተሰበሰበ፡፡  የተሰበሰበው ሰው እጁን ወደ ሰማይ ወርውሮ፣ ደረቱን እየደቃ ይጯጯህ ጀመር፡፡
ቀድመው የከበቡት ከወደቀበት ህንፃ ጎን የሚገነባው ህንፃ ያሰባሰባቸው የቀን ሰራተኞችና ከአሸዋ ክምር መሃል ብቅ ያሉ ሰዎች ነበሩ:: በአካባቢው ላሉት ሰራተኞች፣ ሻይና ቁርስ ለማዘጋጀት ወዲያ ወዲህ የሚሉ ሴቶች፣ ጩኸትና እሪታ ይሰማል፡፡ የጠመጠሙ ሙስሊሞች…. መስቀል ግምባራቸው ላይ የተነቀሱ የቀን ሰራተኞች….. በአንድ ድምፅ ይጮሃሉ…. በአንድ ልብ ያነባሉ….. የጉራጊኛ ቃና ያለው ወዮታ…. የገጠር አማርኛ የተጫጫነው እግዚዮታ….. የትግርኛ ቃና ያለው ዋይ ዋይታ…… ኦሮምኛ የተቀላቀለ ለቅሶ….. (እነኚህ ባጋጣሚ ወደ ጆሮዬ የገቡ ድምፆች ናቸው፤ ምናልባት በሌላ ቋንቋ የተቃኙ ሃዘኖችና ርህራሄዎችም ልብ ሳልላቸው እንዳመለጡኝ እጠረጥራለሁ)
አቤት የሰዉ ድንጋጤ!… አቤት የሰዉ ሃዘን! … አቤት ትርምስ! … ለገሃር ሰማይን ድንኳንዋ አድርጋ ለቅሶ ተቀመጠች…. ያዙኝ ልቀቁኝ አለች….  ያልተሰማ ጩኸት…ያልተረጨ እምባ… ያልተደቃ ደረት… አልነበረም፡፡
እየተርበተበትኩ ከነበርኩበት መኪና ወርጄ፣ ወደ ግርግሩ መራመድ ጀመርኩ፡፡ በከተማችን ሰው ቁልቁል ሳይወርድበት፣ ሽቅብ የወጣ ህንፃ የለም ሲባል እሰማለሁ፡፡ የዚህ ሰው አወዳደቅ ግን ይለያል፡፡ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ አያሌ ዘመናትን ካስቆጠረ ህንፃ ላይ ነው የተምዘገዘገው፡፡ አሻቅቤ ሳየው ህንፃው ከአስር በላይ ፎቆች አሉት፡፡ ሟች ሲምዘገዘግ ማየት የጀመርኩት፣ ከአምስተኛው ፎቅ አካባቢ ላይ ነው፡፡
አሁን አስከሬኑ ከተነጠፈበት ስፍራ ደርሻለሁ፡፡ በደረቱ ነው የወደቀው፡፡ በቀኝ ጉንጩ መሬቱ ላይ የተጣበቀ ጠይም ወጣት ነው፡፡ ከድንጋጤዬ ብዛት ሸሚዝ ይሁን ሹራብ በቅጡ ያለየሁትን ቡናማ ጨርቅ እንደለበሰ ከህንፃው ስር ተጋድሟል፡፡ (ከላይ ሲወርድ በእግሩ ይሁን በጭንቅላቱ የጨረፈው ኤሌክትሪክም መወዛወዙን አላቆመም)
በዚህ አፍላ እድሜው ለምን ይህቺን አለም እንዲህ ባለ አሰቃቂ ሁናቴ መለየት ፈለገ? ወይስ ነብሰ ገዳዮች ገፍትረውት ይሆን? ራሳቸውን ይዘው ከሚያለቅሱት መሃል አንዳንዶቹን መጠያየቅ ጀመርኩ፡፡ “ልጁ ምናችሁ ነው?”፣ “ታውቁታላችሁ?” ለሚለው ጥያቄዬ፣ ያገኘሁት ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ምናቸውም አይደለም:: አያውቁትም፡፡ ይሄ ነበር ክፉኛ ልቤን የነካው:: እንደዚያ ደረት እየደቁና እንባ እየተራጩ፣ ለገሃርን ቀውጢ ካደረጓት በርካታ ሰዎች መሃል፣ ማንነቱን የሚያውቅ ማንም አልነበረም፡፡ ያ ሁሉ ጩኸት…. ያ ሁሉ ለቅሶ… ያ ሁሉ ደረት መድቃት… ከማያውቃቸው ሰዎች፤ ለሟች የተበረከተ የፍቅርና የርህራሄ መስዋእት ኖሯል:: ያለ ምንም ማጋነን፣ እናትና አባቱ እንኳ በዚያ ስፍራ ቢገኙ፣ ከዚህ የበለጠ ሊያዝኑለትና ሊንሰፈሰፉለት አይችሉም፡፡
ይህን ስገነዘብ በጣም አዘንኩ፡፡ አስፓልቱ ላይ ወድቆ ከቀረው ምስኪን ወጣት እኩል ዙሪያውን ከብቦ ለሚላቀሰው ህዝብ አዘንኩ፡፡ እያዘንኩም አንድ ጥያቄ ወደ አእምሮዬ መጣ፡፡ እራሴንም ደጋግሜ ጠየቅሁ፤
“በርግጥ የዚህን ህዝብ ማንነት፣ ከፋፋይ የብሔር ፖለቲካ ይመጥነዋልን?” ስል እራሴን ጠየቅኩ፡፡ ይህን በታላቅ ሀዘን እያውጠነጠንኩ፣ ከቴሌ ባር ጀርባ ወዳሉት የአሮጌ መጽሐፍት መሸጫ ሱቆች አመራሁ፡፡ በግምት ከአንድ ሰአት በኋላ የፈለግኩትን መፅሃፍ ሸምቼ ስመለስ በድጋሚ በዚያ ህንፃ በኩል ለማለፍ ተገደድኩ፡፡ ከማለፌ በፊትም ለጥቂት ደቂቃ ከመኪና ወርጄ አንዳንድ ነገሮችን ለማጤን ሞከርኩ፡፡
እኔ ስደርስ አስክሬኑ ተነስቷል፡፡ ከወደቀበት ስፍራ ጀምሮ ቁልቁል መቶ ሜትር ያክል የሚወርድ ውሃም ተመለከትኩ፡፡ ውሃውን ቀረብ ብዬ ሳጤነው፣ ከውፍረቱ ቀጠን፣ ከቅላቱም ደብዘዝ ያለ ደም ነበር፡፡ ያንን ደብዛዛ ደም ተሻግሬ በብዙ ሰዎች ወደተከበበች አንዲት ጎስቋላ ሴት አመራሁ…
ሟች በወደቀበት አቅራቢያ ኦቾሎኒና መሰል ቁሳቁሶችን የምትሸጥ ጠና ያለች ሙስሊም ሴት ነች፡፡ ከአይኖችዋ የሚወርደው እንባ ጉንጮችዋን አልፎ፣ ክንብንቧ ውስጥ ሲሰርግ ተመለከትኩ፡፡ ዙሪያዋን የከበቡዋት ሰዎች  “በዚህ ሁናቴሽ ምንም መስራት አትችይም፤ ወደ ቤትሽ ሂጂና አረፍ በይ” ይሏታል፡፡ ሟች ወደ መሬት ተምዘግዝጎ እንደ ባሉን ሲፈነዳ፣ በቅርብ ርቀት ከተመለከቱት አንዷ ነበረች፡፡
ብዙዎቻችን ያችን ኦቾሎኒ ሻጭ ምስኪን ለቅሶ ለመድረስና ለማጽናናት የተገደድነው አለምክንያት አልነበረም፡፡ መፅሃፍ ተራ ደርሼ እስክመለስ የሟቹም ሆነ የቤተሰቦቹ ማንነት አልታወቀም፡፡ ከወረደበት ህንጻ ላይ “ወንድሜን…. ወንድሜን….” ወይም “ልጄን…. ልጄን” እያለ ብቅ ያለ ሰው የለም፡፡ ልጁ ወደተወረወረበት ህንፃ ወጥቶ ስለ ሁናቴው ለማጣራት የደፈረም አልነበረም፡፡ እንደሰማሁት ፖሊሶቹም ቢሆኑ የሟች አስከሬን ወደተነሳበት ስፍራ ሰዎች እንዳይጠጉ በመከላከል ላይ ነበር ያተኮሩት፡፡
የቅድሙ ጩኸትና ሁካታ ቢያባራም፣ እንደ ሙስሊሟ ሴት ከድንጋጤና ከሃዘናቸው ያልተላቀቁ በርካታ ሰዎች ተመለከትኩ፤ በየጥጉ የጨው አምድ መስለው ቆመዋል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ክፉኛ አዘንኩ፡፡ ሟች ከዚህ አለም  ጭንቅ አንዴ ተገላግሏል፡፡ ጦሱ ግን የብዙዎችን አእምሮ በማናወጥ ላይ መሆኑን ተገነዘብኩ፡፡ ይሄ ነውጥ ምናልባትም እስከ እድሜ ልካቸው አይለቃቸው ይሆናል፡፡ እኔ ራሴ ቀስ እያለ የሚገነፍል መጥፎ ስሜት ወደ ሁለመናዬ ሲሰራጭ እየተሰማኝ ነው፡፡
ቶሎ ከዚህ ስፍራ መራቅ ነበረብኝ፡፡ የተሳፈርኩባት መኪና ለገሃርን በፍጥነት ለቃ ወደ ጨርቆስ መገስገስ ጀመረች፡፡ ከአደጋው ስፍራ በራቅሁ ቁጥር ከዚህ ወደ ከፋው አደገኛ ሁናቴ እየገሰገስን መሆኑ ተሰማኝ፡፡ ታላቋ ሃገራችን በትናንሽ ህሙማን እየተንገላታችና እየተገፋች፣ ወደ ምትንደረደርበት አደገኛ ሁናቴ….
ይሄን ከመሰለ የከፋ ሁናቴ አእምሮዬን ለማሸሽ ስል ተመልሼ ወደ ኋላ ደነበርኩ:: ተመልሼ የለገሃሩን አሰቃቂ ትእይንት ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ከፍንዳታው ድምጽ በኋላ በድንጋጤና በሃዘን ተቀስፈው ሲጯጯሁና ሲላቀሱ ያየኋቸው ሰዎች ፊቴ ድቅን አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አስክሬኑን ከበው ከማልቀሳቸውና ደረት ከመድቃታቸው በፊት “እሱ ማነው?… ዘሩ ምንድነው?…” አላሉም፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን እንዲህ ነን! በሆነ ምክንያት ሰው በሞተ ቁጥር፣ የሬሳ ዘር እየመረመሩና እየቆጠሩ፣ “ይሄን ያክል አማሮች አለቁ… ኦሮሞዎች ተገደሉ…. ትግሬዎች ቆሰሉ….” የሚሉ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች አይመጥኑንም፡፡
ይህን አሳዛኝ አጋጣሚ የሚሰሙና የሚያነቡ ፖለቲከኛ ነኝ ባዮች…… አክቲቪስት ነኝ ባዮች ሁሉ…….. “የሁሉም ሞት ያጎድለናል” ብሎ ለሁሉም ሰው መቆርቆርን፣ እንቆረቆርለታለን ከሚሉት ህዝብ ይማሩ!! ሳይለየን ያቆየን!!   

Read 2158 times