Saturday, 18 January 2020 13:09

ለባሕረ ጥምቀቱ

Written by  ታደለ ገድሌ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

  “በያመቱ ጥር 10 ቀን የጥምቀት ዋዜማ ወይም የከተራ ዕለት ከሰዓት በኋላ ታቦታት ሁሉ ከየመንበረ ክብራቸው በካህናትና ምዕመናን ታጅበው፣ ወደ ባሕረ ጥምቀት ሲወርዱ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ዝማሬና ምስጋና ይደረጋል፡፡ “
               
            በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ዘንድ በያመቱ ጥር 10 እና 11 ቀን በከፍተኛ ድምቀት ከሚከበሩ በዓላት ውስጥ አንዱና ዋነኛው የጥምቀት በዓል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ጥር 12 ቀን በዕለተ ሚካኤል ቃና ዘገሊላ ይከበራል፡፡ በተለይም የቅዱስ ሚካኤል ታቦተ ሕግ (ጽላት) ያለበት ደብር ሁሉ ታቦተ ሕጉ ወደ መንበረ ክብሩ የሚመለሰው፣ እዚያው ባሕረ ጥምቀት ላይ ሁለት ቀን ከአደረ በኋላ ነው፡፡ የበዓሉ ዋነኛ ምክንያትም ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ፣ በእደ ዮሐንስ መጠመቁን ለማስታወስ ነው፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 1፤ ቁጥር 76 ላይ እንደተጻፈው፤ ካህኑ ዘካርያስ ልጁ ዮሐንስ ሲወለድ ‘ወአንተኒ  ሕፃን ነቢየ ልዑል ትሰመይ፤ ወተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ ትፂሕ ፍኖቶ (አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱንም ትጠርግ ዘንድ በጌታ ፊት ትሔዳለህ’) ብሎ አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮ ነበር፡፡
በመሆኑም የግመል ጸጉር እየለበሰና ማርና አንበጣ እየበላ በበረሃ ያደገው ዮሐንስ፤ በዘመነ ሄሮድስ ዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለ አገር  በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መጥቶና በምድረ በዳ እየጮኸ፣ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ አስተምሮ ነበር፡፡ በወቅቱም ’እኔ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፡፡ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት እማይገባኝ ከእኔ የሚበረታ ይመጣል፤እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፡፡ መንሹም በእጁ ነው፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፡፡ ስንዴውንም በጎራው ይከታል፡፡ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል’ እያለ ሕዝቡን ሲያጠምቅ፣ ኢየሱስም በቦታው ተገኝቶ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ሲጠመቅና ሲጸልይ ሰማይ ተከፈተ፤መንፈስ ቅዱስም  በአካል መልክ እንደ እርግብ በእርሱ ላይ ወረደ፡፡ “የምወድድህ ልጅ አንተ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል የሚል” ድምጽ ከሰማይ መጣ፡፡
እናም በዚህ አምሳል  ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ለኃጢአት ሥርየት ተጠማቂውን ክርስቶስንና አጥማቂውን ዮሐንስን እያስታወሰ መጠመቅ አለበት፡፡ ለምን ቢሉ በማርቆስ ወንጌል ምዕራፍ 16፤16 እንደተነገረው፤ “ያመነ፤ የተጠመቀም ይድናል፡፡ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” ይላልና ነው፡፡ ስለዚህ በያመቱ ጥር 10 ቀን የጥምቀት ዋዜማ ወይም የከተራ ዕለት፣ ከሰዓት በኋላ፣  ታቦታት ሁሉ ከየመንበረ ክብራቸው በካህናትና ምዕመናን ታጅበው፣ ወደ ባሕረ ጥምቀት ሲወርዱ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ዝማሬና ምስጋና ይደረጋል፡፡  
በዚህ ረገድ  ዲያቆናቱ፤ ቀሳውቱ፤ ደባትሩ፤ ሊቃውንቱ፤ ጳጳሳቱ እያሸበሸቡ፤
’እምሰማያት ወረደ፤ ወእማርያም ተወልደ፤ ተወልደ፤
ከመ ይኩን ቤዛ ለኵሉ ዓለም፤
ለብሰ ሥጋ ማርያም፡፡
(ከሰማያት ወረደ፤ ከድንግል ማርያም ተወለደ፤ የዓለም ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ የድንግል ማርያምን ሥጋ ለበሰ)
ተጠምቀ ሰማያዊ፤
በእደ መሬታዊ፤
ሖረ ኢየሱስ፤ ሖረ ኢየሱስ፤
እምገሊላ፤ እምገሊላ ኀበ ዮሐንስ፡፡
-ሰማያዊው አምላክ በምድራዊው ሰው በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ኢየሱስ ከገሊላ ወደ ዮሐንስ ዘንድ ሔደ፡፡
ኦሪት በውስቴታ፤ ታቦት በውስቴታ፤ ይከድንዋ፡ በወርቅ ይከድንዋ፡ (በውስጥዋ ኦሪት፤ እንዲሁም ታቦት አለች፤ በወርቅም ይሸፍኗታል፡)
ጽላት ዘሙሴ፡ ዕፀ ጳጦስ ዘሲና፤ ጸናጽል፡ዘውስተ ልብሱ ለአሮን ካህን (የሙሴ ጽላት ነሽ፤ የሲና በረሃ፤ የጳጦስ እንጨት ነሽ፡ የአሮንም የካባው ውስጥ ጸናጽሉ ነሽ)---’ እያሉ፤ ከበሮ እየደለቁ፤ ጸናጽል እያንሹዋሹ፤ በተረጋጋ ጉዞ ይተምማሉ፡፡ ታቦታቱ ከባሕረ ጥምቀቱ ደርሰው እስኪያርፉ ድረስ መዝሙሩ እየተቀያየረ ይቀጥላል፡፡
ሐዲጎ ተሥዓ ወተሥዓተ ነገደ ነገድ፤ማእከለ ባሕር፤ ማእከለ ባሕር፤ ቆመ፤ ማእከለ ባሕር፡፡ (ዘጠና ዘጠኙን ነገደ መላእክት ትቶ በባሕር ላይ ቆመ፡፡)
በቃና ዘገሊላ ፤አእጋሪሁ እለ ሖራ በቤተ ከብካብ (በቃና ዘገሊላ እግሮቹ ወደ ሰርግ ቤት ሔዱ፡፡)
ሥልጣነ ክህነት የሌለው ሕዝበ ክርስቲያኑም፤ የክት ልብሱን ለብሶ፤ በግራና በቀኝ፤ በፊትና በኋላ ታቦታቱን አጅቦ፤ ወንዱ በሆታ፡ ሴቱ በእልልታ፤ በጭብጨባ፡ በባህላዊ ዘፈን ጉዞውን ያደምቀዋል፡፡ ጎረምሳው ዱላውን ከዱላ ጋር እያማታ፡-
‘አሃይ ጉማ ለታቦቱ ነወይ ለላይኛው ጌታ፤
ይዘፈን የለም ወይ ለሰው ጋለሞታ፡፡  
ለባሕረ ጥምቀቱ ያልዘፈነች ቆንጆ፤
ቆማ ትቀራለች እንደ ድሀ ጎጆ----፡፡
ባልቴቶችም፡-
በሕይወት ግባ በሕይወት፤
የተክልየ ታቦት፤
የእመቤቴ ጽላት፡፡
እዩት ቅኔውን ሲመራ፤
ያገራችን ደብተራ ----፡፡ እያሉ ሲያመሰግኑ ቆነጃጅቶችም፡-
ቅዱስ ጊዮርጊስ የሔደበቱ፤
ቅዱስ ሚካኤል የገባበቱ፤
እግዚአብሔር አብ ያደረበቱ፤
ቅዱስ ገብርኤል የወረደበቱ፤
ዕጣን ዕጣን ይሸታል ቤቱ፡፡
ወይን አበቀለ ጽድህ፤
ቅዱስ ሩፋኤል የማረብረቢያህ፤
ቅዱስ ዑራኤል፡የማስረገጃህ፡፡
ሸንኮራ አገዳ ይዟል በእጁ፤
ቅዱስ ዮሐንስ ለወዳጁ፡፡
እመቤቴ ማርያም ልጇን አዝላ፤
ብትንከራተት በገሊላ፤
ዕንባዋንም ብታነባ፤
አብቅሎ አደረ ቀይ አበባ-----እያሉ በመዘመር ታቦታቱን ከባሕረ ጥምቀቱ ያደርሷቸዋል፡፡
ታቦታቱ ከባሕረ ጥምቀትም ደርሰው፣ ምስጋናው፣ ሌሊቱን ሙሉ ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ በባሕረ ጥምቀቱ ላይ በሚቆመው ማኅሌት ካህናቱ፣ ከመዝሙረ ዳዊት ቁጥር 113፣ ጌታ ሲጠመቅ የተፈጸመውን ምሥጢር (ልበ አምላክ ዳዊት) የተነበየውን ትንቢት በማውሳት፡-
‘ባሕርኒ ረእየት ወጎየት፤ ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤ አድባር አንፈርዐፁ ከመ ኀራጊት፤ ወአውግርኒ ከመ መሐስአ አባግዕ (ባሕር አየች፤ ሸሸችም፡፡ ዮርዳኖስ ወደኋላው ተመለሰ:: ተራሮች እንደ ጊደሮች፤ እንደ ኮርማዎች፤ ኮረብታዎችም እንደ በግ ጠቦቶች  ዘለሉ) እያሉ ያዜማሉ፡፡ ከመልክአ ኢየሱስ ደግሞ፤
‘ሰላም ለክሳድከ ግብረ መንፈስ ቅዱስ ኬንያ፤
ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይ ወሐዋርያ፤
አመ ወጽአ ስሙአቲከ በአድያመ ኵሉ ሶርያ፤
ብፁዓት አዕይንት ኪያከ ዘርእያ፡ እያሉ ካህናቱ ያመረግዳሉ፡፡ (የመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ሥራ ለሆነው አንገትህ ሰላም ይሁን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ነቢይና ሐዋርያ ነህ፡፡ በሶርያ አውራጃዎች ሁሉ ስምህ በተነገረ ጊዜ አንተን ያዩ ዓይኖች የተባረኩ ናቸው)፡፡
በዚህ መንገድ ታቦታቱ ባሕረ ጥምቀት ላይ በተዘጋጀው ድንኳን ውስጥ አድረውና የቅዳሴውና የማኅሌቱ፤ የጥምቀቱ ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ፣ በክብርና በምስጋናም ተነሥተው  ወደየ መንበረ ክብራቸው ይገባሉ:: የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ደግሞ ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህንን የሚታየውን እንጂ በእጅ የማይዳሰሰውን በዓለ ጥምቀት ቅርስ፤ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት፣ የዓለም ድንቅ የባህል ሀብት እንዲሆን ባስመዘገበችበትና ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የላቀ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ባደረገችበት ወቅት ላይ መከበሩ ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ካስመዘገበቻቸው አራት የማይዳሰሱ ቅርሶቿ ውስጥ (በዓለ መስቀል፤ የገዳ ሥርዓት፤ ፍቼ ጫምበላላ፤ የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመት) አንደኛው ጥምቀት ሆኗል ማለት ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሐዋርያትን ትምህርት አስፋፍታና የጥምቀትን በዓል በብሔራዊ ደረጃ ተቀብላ ማክበር የጀመረቺው በ530 ዓ.ም ከዓፄ ገብረ መስቀል ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እንደሆነ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ በ1140 ዓ.ም ላይ ደግሞ ካህን የነበረው ዓፄ ላሊበላ ለጥምቀት በዓል ልዩ ትኩረት አድርጎ በያመቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲከበርና ታቦታት ሁሉ ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርደው፣ ውኃውን እንዲባርኩ በአዋጅ ጭምር አጽንቶታል፡፡ እንደዚሁም ዓፄ ዘርዐ ያዕቆብ በ1426 ዓ.ም ታቦታት በጥምቀት ዋዜማ በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ወንዝ ወርደው በማደር፣ ትውልዱን እንዲባርኩ አዋጅ አስነግሮ ነበር፡፡ በተመሳሳይ በ1486 ዓ.ም ዓፄ ናዖድ፣ ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀት  ወርደው እስኪመለሱ ድረስ  በብሔራዊ ደረጃ፣ በደመቀ መንፈስ እንዲከበሩ አዋጅ አስነግሯል፡፡
መልካም የጥምቀት በዓል ይሁንላችሁ!!


Read 839 times