Print this page
Saturday, 18 January 2020 13:10

የሴት ብልት በተፈጥሮ የራሱ ወታደር….አለው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(13 votes)


                አንድ ጥያቁ አለኝ? እኔ ከብልቴ የሚወጣ መጥፎ ሽታ ያለው ፈሳሽ አለኝ፡፡ በምን ምክንያት ይሆን? እንዴትስ ነጻ መሆን ወይንም ሽታውን ማስወገድ እችላለሁ? የሚለው ጥያቄ የቀረበው Center for Young Women›s Health የተባለው ድረገጽ ላይ ለባለሙያዎች ነው፡፡ ጥያቄው ይህ ብቻም አይደለም ሌሎች መልስ የተሰጠባቸው ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ወደአማርኛው መልሰ ነዋል:: ታነቡ ዘንድ እንጋብዛለን፡፡Center for Young Women›s Health ለንባብ የበቃው እ.ኤ.አ. June/2019 ነው፡፡
ሴቶች ብዙ ጊዜ የሴትነት አካላቸውን ወይም ብልት በምን መንገድ ማጽዳት እንዳለባቸውና የማጽጃ እቃዎቹ ወይንም ኬሚካሎቹ ምን እንደሆኑ ለይቶ ለማወቅ ይቸገራሉ ወይንም ግራ መጋባት ይታይባቸዋል፡፡ በተለይም አየሩ ሞቃት በሚሆንበት ጊዜ ወይንም ሞቃታማ አካባቢ የሚኖሩ ለሰውነታቸው ተገቢውን ጥንቃቄ ካላደረጉ ችግሩ Infection ወይም መጥፎ ጠረን መከሰቱ አይቀርም:: ነገር ግን የሴት ብልትን ማጽዳት በጣም ቀላል ሲሆን የተለየ ጠረን ወይንም የማጽዳት አቅም ያለው ሳሙና በጠጣሩም ሆነ በፈሳሽ መልክ ለመግዛት መጨነቅ አይገባቸውም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ኬሚካሎች የሴት ብልትን እንዲቆጣ ወይንም የማሳከክ የመሳሰለውን ስሜት ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ነው፡፡
የሴቶች ብልት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ድረገጹ እንደሚከተለው አስቀምጦታል፡፡ እኛም መጠሪያው ወይንም ስያሜው ሳይንሳዊ ስለሆነ በቀጥታ ወደአማርኛ መተርጎሙ ስለማይቻል ምን ማለት እንደሆነ ብቻ አገልግሎቱን ወደአማርኛ መልሰናል፡፡ መጠሪያዎቹን ከምስል ጋር ለማስተያየት ያግዛል፡፡
Mons pubis or “mons” በጸጉር የሚሸፈነው ከላይ ያለው አካል ነው፡፡
Clitoris - በመቀጠል የምትገኘው ስትነካ ስሜት ሰጪ የሆነች ተፈጥሮ ነች፡፡
Urethra - ይህ አካል ሽንት መሽኛ ነው፡፡
Labia majora - ወፈር ያለ ወይንም ከብልት ከውጭ በኩል ያለ በግራና በቀኝ የሚገኝ ብልትን ከጉዳት የሚከላከል አካል ነው፡፡  
Labia minora ከውስጥ በኩል የሚገኝ ሳሳ ያለ አንዳንድ ጊዜ ከንፈር ተብሎ የሚጠራ አካል ነው፡፡
Anus- ፊንጢጣ፡- የሴት ብልት ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች ከላይ የተመለከቱት ሲሆኑ ጽዳትን በሚመለከት በምን መንገድ መሆን እንዳለበት ማወቅ ጤንነትን ለመጠበቅ ይረዳል፡፡
አካልን በሚታጠቡበት ወቅት የሴት ብልትን ለሰስ ባለ ሙቅ ውሀ እና ሽታ በሌለው ወይም ሽታው ጠንካራ ባልሆነ ሳሙና መታጠብ ይመከራል፡፡ ውሀው ከባድ ሙቀት የሌለው መሆኑን ማረጋገጥ እና ከባድ ጠረን እና ኬሚካል ያላቸውን መታጠቢያዎች ማስወገድ መረሳት የለበ ትም፡፡
ሴቶች ብልታቸውን እንዴት ማጽዳት እንዳለባቸው ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የገለጹት እንደሚከ ተለው ነው፡፡ ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የማህጸንና ጽንስ እስፔሻሊስት ሐኪም ናቸው፡፡
‹‹…በአሁኑ ሰአት ያሉ ሴቶች ያው ወደ ስልጣኔ አየመጡ ስለሆነ ንጽህና ማድረግ እንዳለባቸው ያምናሉ፡፡ ድሮም ቢሆን ስልጣኔም ባይኖር እንኩዋን ያው እናቶች ግብር ይወጣሉ፡፡ ይህም ማለት ጠዋትና ማታ በመታጠብ ንጽህናቸውን ይጠብቃሉ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ የንጽህና ማጣት ሳይሆን ብዙውን ጊዜ የንጽህና ስልት አጠባበቁ  ነው፡፡ የንጽህና ስልት አጠባበቅ ጉድለት ማለት አንዳንዶቹ ብልታቸውን በጣም ደጋግሞ በመታጠብ ንጽህናቸውን የጠበቁ ይመስላቸዋል፡፡ነገር ግን ንጽህናን የሚጠብቀው ደጋግሞ በመታጠብ አይደለም፡፡  ጠዋትና ማታ ከታጠቡ ይበቃቸዋል:: በእርግጥ በሃይማኖት ምክንያት ደጋግመው የሚታጠቡ አሉ፡፡ ሃይማኖት የሚያዘውን ነገር ማድረጉ ትክክል ቢሆንም ነገር ግን ከሚፈቀደው በላይ በተጋነነ መልኩ መታጠብ ችግር ያስከትላል:: በሳሙና፣ በዲቶል፣ የተለያዩ ኬሚካሎችን ብልትን ለማጽዳት መጠቀም አግባብ አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮች አላስፈላጊ የመጠቀሚያ ኬሚካሎች ናቸው:: ምክንያቱም አካባቢውን እንዲቆጣና እንዲቆስል ያደርጋሉ፡፡
እንደሚታወቀው የብልት አካባቢ ስስና ለአደጋ ተጋላጭ ነው፡፡ ይህ አካባቢ የተፈጥሮ ፈሳሽ የሚያስፈልገው ነው፡፡ የብልት አካባቢ ተፈጥሮአዊ እርጥበት ከሌለው ድርቀትን ያመጣል፡፡ በድርቀት ምክንያት ቆዳው ስለሚሰነጣጠቅ በቀላሉ አጥቂ ህዋሳቶች ገብተው ኢንፌክሽን ይፈጥራሉ:: ብልት በተፈጥሮ የራሱ ወታደር ወይም የራሱ የመከላከያ ኃይል አለው፡፡ ያ የመከላከያ ኃይል አሲድ ያመነጫል:: ያ አሲድ ደግሞ አጥቂ ህዋሳቶች በሚመጡበት ጊዜ ይከላከላቸዋል፣ ይገድላቸዋል፣ ነገር ግን ብዙ ሴቶች ብልታቸው ውስጥ የሚኖረውን ተፈጥ ሮአዊ ፈሳሽ ወይም እርጥበት እንደ ቆሻሻ በመቁጠር እውስጥ ድረስ እየገቡ ይታጠባሉ፡፡ በዚህ ድርጊታቸው የተፈጥሮን ፈሳሽ ስለሚያስወጡና ብልት ስለሚደርቅ በቀላሉ ለኢንፌክሽን ይጋለ ጣሉ:: እንደዚህ የሚያደርጉ ሴቶች በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜም ህመም ይኖራቸዋል፡፡ እናም በማህጸንና በአካባቢው የሚከሰቱ የኢንፌክሽን ሕመሞች አንዱ ምክንያት  ከንጽህና አጠባበቅ ስልት ጉድለት ነው፡፡
ስለዚህም ሴቶች ብልታቸውን በሚያጸዱበት ጊዜ የሚከተለውን መንገድ ቢከተሉ ይጠቅማል እንደ ዶ/ር መብራቱ ገለጻ፤-
ንጽህናን ለመጠበቅ ጠዋትና ማታ መታጠብ በቂ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ     
በንጹህ ውሀ መታጠብ፣
በአንድ ሊትር ውሀ ላይ ሶስት የሻይ ማንኪያ ጨው ጨምረው ሲሙዋማ በሱ ጠዋትና ማታ መታጠብ፣
በዚህ መልክ ቢታጠቡ የተፈጥሮአቸውን የፈሳሽ አሲድነት ያበረታታውና ኢንፌክሽን በቀላሉ እንዳይዛቸው ያደርጋል፡፡ ስለሆነም ለመታጠብ ተፈጥሮአዊ የሆኑ ነገሮችን መጠቀም እንጂ ኬሚካሎችን ብዙ ጊዜ አዘወትሮ መጠቀም ጥሩ አይደለም፡፡
ሴቶች በሚታጠቡበት ጊዜ እጃቸወን ከታች ወደላይ በመውሰድ ፊንጢጣቸውንና ብልታቸውን አብረው እያሹ መሆን የለበትም፡፡ ምክንያቱም በፊንጢጣ አካባቢ ከሰገራ ጋር ብዙ አጥቂ ሕዋሳቶች ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ በሶፍት ወይንም በወረቀት በሚጸዳዱበት ጊዜ እጃቸውን ከጀርባ ወስደው ከሁዋላ ወደሁዋላ ቢያደርጉት ወደፊት ወደ ብልታቸው የሚመጣውን የኢንፌክሽን ምክንያት ያስወግዳሉ፡፡ በውሀ በሚታጠቡበት ጊዜም ውሀውን ከፊት ለፊት በማፍሰስ እጃቸውን ከሁዋላ በኩል አድርገው ወደሁዋላ መጸዳዳት አለባቸው፡፡ እንዲሁም የግብረስጋ ግንኙነት ከአባላዘር በሽታዎች በተጨማሪ ኢንፌክሽን በማምጣት እንደምክንያት ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ብዙውን ጊዜ ግብረስጋ ግንኙነት ከመደረጉ በፊት የፊንጢጣን አካባቢ በደንብ መታጠብ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በቀጥታ ብልት ለብልት ግንኙነት ከመደረጉ በፊት አካባቢው ስለሚነካካ በአካባቢው ያሉ ቆሻሻዎችን የወንዱ ብልት ወደ ውስጥ ይዞ ሊገባ እና ለኢንፌክሽን ምክንያት ስለሚሆን ነው፡፡
Center for Young Women›s Health እንደሚገልጸው ከብልት መጥፎ ጠረን ሊወጣ የሚችለው በእጥበት ምክንያት ከሚመጣው የጤና መታወክ ብቻ ሳይሆን ከሚለበሱ ልብሶችም አንዳንድ ጥንቃቄ የጎደለው አጠቃቀም ሲኖር ጭምር ነው:: ስለዚህም ምን ማድረግ እንደሚገባ የሚከተለውን መክሮአል፡፡
ከውስጥ የሚለበሱ የውስጥ ሱሪዎች (Pants) ከመለበሳቸው በፊት በደንብ አጽድቶ ማጠብ ያስፈልጋል፡፡ የውስጥ ሱሪዎች በሚታጠቡበት ጊዜ የታጠቡበት ሳሙና እስከሚለቅ ድረስ በደንብ አድርጎ ማጽዳት የሚገባ ሲሆን ከባድ የሆኑ የማጽጃ ኬሚካሎችን መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡
የውስጥ ሱሪዎች እንዲሁም ልብሶች ከጥጥ የተሰሩ እንዲሆኑ ይመከራል፡፡ የሴት ብልትን ሊያስቆጡ የሚችሉ አይነት ልብሶች መልበስ አይገባም፡፡
በብልት ላይ ሽታ ያላቸውን ነገሮች (ዶደራንት፤ ሽቶ፤ ሽቶነት ያላቸውን ዘይቶች ወይንም ቅባቶች፤ በብልት ላይ መጠቀም አይገባም፡፡ እንደዚህ አይነት ኬሚካሎች ተፈጥሮአዊውን መከላከያ ፈሳሽ ሊያጠፉና ብልትን ጉዳት ላይ ሊጥሉ ይችላሉ፡፡  
ሰውነትን የሚያጠብቁ ልብሶችን ማስወገድ ይመከራል፡፡  

Read 25609 times