Print this page
Saturday, 18 January 2020 13:08

ለ2020 የኦስካር ሽልማት የታጩ ፊልሞች ይፋ ተደረጉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “ጆከር” በ11 ዘርፎች በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዟል

              በአለማችን ትልቁ የፊልም ሽልማት እንደሆነ ለሚነገርለትና ዘንድሮ ለ92ኛ ጊዜ ለሚከናወነው የ2020 የኦስካር ሽልማት የታጩ ፊልሞች ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ የተደረገ ዚሆን፣ “ጆከር” የተሰኘውና በ11 ዘርፎች የታጨው የወቅቱ አነጋጋሪ ፊልም በብዛት በመታጨት ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸር አርትስ ኤንድ ሳይንስስ ባለፈው ሰኞ ይፋ ባደረገው የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት እጩዎች ዝርዝር ውስጥ “ጆከር”፤ ምርጥ ፊልም፣ ምርጥ ወንድ የፊልም ተዋናይ፣ ምርጥ ዳይሬክተር እና ምርጥ ሲኒማቶግራፊን ጨምሮ በ11 ዘርፎች ለሽልማት በመታጨት ነው ቀዳሚነቱን የያዘው፡፡
አካዳሚው በ24 ዘርፎች የዘንድሮ የኦስካር ዕጩዎችን ይፋ ባደረገበት ዝርዝር፤ “ዘ አይሪሽማን”፣ “1917” እና “ዋንስ አፕ ኦን ኤ ታይም ኢን ሆሊውድ” የተሰኙት ፊልሞች እያንዳንዳቸው በተመሳሳይ በ10 ዘርፎች በመታጨት በሁለተኛነት እንደሚከተሉ ተነግሯል፡፡ በአመቱ ለእይታ ያበቋቸው ፊልሞች በብዛት ለኦስካር ከታጩላቸው ስቱዲዮዎች መካከል በቀዳሚነት የተቀመጠው ኔትፍሊክስ፤ ፊልሞቹ ለ24 ጊዜ የታጩለት ሲሆን ሶኒ ፒክቸርስ ለ20፣ ዲዝኒ ለ16 ጊዜ በመታጨት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ለዘንድሮው የኦስካር ሽልማት ከታጩት መካከል ከ33 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወይም 62ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ አመቱ በኦስካር ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ለሽልማት የታጩበት ቢሆንም፣ በምርጥ ዳይሬክተር ዘርፍ አንድም ሴት አለመታጨቱ አነጋጋሪ መሆኑ ተዘግቧል፡፡
የዘንድሮውን የኦስካር ዕጩዎች ዝርዝር አነጋጋሪ ካደረጉት ሌሎች ጉዳዮች መካከል የቀለም ልዩነት መንጸባረቁ ሲሆን፣ በምርጥ ተዋንያን ዘርፍ ከታጩት 20 ተዋንያን መካከል 19ኙ ነጮች መሆናቸውም ለአብነት ተጠቅሷል::
ለ5 ጊዜ ኦስካር የተሸለመውና ዘንድሮም ለ52ኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረበው ጆን ዊሊያምስ፣ በህይወት ከሚገኙ የፊልም ተዋንያን መካከል በብዛት ለኦስካር በመታጨት ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ የተነገረ ሲሆን ለ9ኛ ጊዜ ዘንድሮ በምርጥ ዳይሬክተርነት የታጨው ማርቲን ስኮርሲ፣ በምርጥ ዳይሬክተርነት በብዛት በመታጨት ታሪክ መስራቱ ተነግሯል፡፡
የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት አሸናፊዎች በመጪው የካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ሆሊውድ በሚገኘው ዶልቢ ቲያትር በሚካሄድ ስነስርዓት ይፋ የሚደረጉ ሲሆን ከ30 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ መድረክ መሪ ይከናወናል የተባለው የሽልማት ስነስርዓቱ፣ በኤቢሲ ቴሌቪዥን በቀጥታ እንደሚተላለፍ ይጠበቃል፡፡


Read 6116 times
Administrator

Latest from Administrator