Saturday, 18 January 2020 12:55

የዘንድሮ ጥምቀት በጐንደርና አዲስ አበባ በድምቀት ይከበራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(17 votes)

 - በጐንደር ኤርትራውያንን ጨምሮ 2 ሚሊዮን እንግዶች ይገኛሉ
          - የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች በዓሉን በጐንደር ያከብራሉ

 
            የዘንድሮ ጥምቀት በዓል በአዲስ አበባና በጐንደር የዩኔስኮ ተወካዮች፣ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ብፁዕ አቡነ መርቆርዮስ ፓትሪያሪክ እንዲሁም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ እንግዶች በሚታደሙበት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል ተብሏል፡፡
ጥምቀት በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች ከተመዘገበ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚከበረው በዚህ የዘንድሮ ጥምቀት በዓል ከአዲስ አበባና ጐንደር በተጨማሪ በአሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ በአስረጅነት የተወሰዱ የምስል ዶክመንተሪዎች በተዘጋጁባቸው ላሊበላና አክሱምም ደምቆ ይከበራል ሲሉ መጋቢ ሠላም ቀሲስ ሰለሞን ቶልቻ፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌልና ሀዋሪያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የበዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የዘንድሮ ጥምቀት በዋናነት በዩኔስኮ በመመዝገቡ የቱሪስቶች ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት ኃላፊው ቱሪስቶችም በአዲስ አበባ ጃንሜዳ፣ በጐንደር፣ በላሊበላ እና በአክሱም የንግስተ ሳባ መዋኛ ገንዳ በሚከበሩ በዓላት ላይ ይታደማሉ ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከሚገኙ 250 አብያተ ክርስቲያናትና ደብሮች መካከል 177 ያህሉ ታቦታቶች በከተማዋ በሚገኙ 74 የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ላይ ወጥተው በዓሉ እንደሚከበርም ኃላፊው ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
እነዚህ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ከእንግዲህ አለማቀፍ እውቅና ያላቸው በመንግስት ሊከበሩ የሚገባቸው ናቸው ያሉት መጋቢ ሠላም ቀሲስ ሰለሞን፤ በክልሎች ያሉ የማክበሪያ ቦታዎችም ያሉባቸው ችግሮች ተፈትተው እውቅና እንዲሰጣቸውና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ቤተክርስቲያኗ አጥብቃ ትጠይቃለች ብለዋል፡፡
“ማክበሪያ ቦታው ከሌለ በዓሉ አይከበርም፤ ዩኔስኮም ሲመዘግብ ይሄን ታሳቢ በማድረግ ነው፤  ከእንግዲህ ሀገሪቷ የዩኔስኮን ስምምነት የመጠበቅ ግዴታ ያርፍባታል፤ ከዚህ አኳያ በተለይ በክልል ያሉ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል - ኃላፊው፡፡
አያይዘውም በአዲስ አበባ የሚገኙ 74 የጥምቀት ማክበሪያ ቦታዎች ህጋዊ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተሰጥቷቸው ቦታዎቹ ተገቢውን ጥበቃ እንዲደረግላቸው ቤተክርስቲያኗ በበዓሉ አከባበር ላይ በጽኑ ትጠይቃለች ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በሚደረገው በዓል ላይም የዩኔስኮ ተወካዮች እንደሚገኙም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው ጐንደርም፤ በዓሉ ከዚህ ቀደም ከነበረው በላቀና  በተለየ ድምቀት እንደሚከበር የተናገሩት ኃላፊው፤ የጐንደሩ አከባበር በፓትሪያሪክ ብፁዕ አቡነ መርቆሪዎስ የሚመራ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ በዓል ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያንን ጨምሮ ከመላ ሀገሪቱ የተውጣጡ 2 ሚሊዮን ያህል ምዕመናንና የበዓሉ አክባሪዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በዚህ በዓል ላይ በአስታራቂነታቸው ሀገራዊ ክብርን ያገኙት የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎችም በልዩ እንግድነት ተሣታፊ እንደሚሆኑ ታውቋል::


Read 11825 times