Saturday, 18 January 2020 12:53

‹‹ባልደራስ›› መስራች ጉባኤውን በቅርቡ ያደርጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 “ወግ አጥባቂ ፓርቲን እንመሰርታለን


                ‹‹ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ›› በሚል በእነ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የተመሠረተው የፖለቲካ ፓርቲ፤ ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የእውቅና ሰርተፊኬት ያገኘ ሲሆን መስራች ጉባኤውን ጥር 17 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡
ጋዜጠኛ እስክንድር፤ ፓርቲው በዋናነት አዲስ አበባን የማዳን አላማ ይዞ መነሳቱን አስረድቷል፡፡
‹‹አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት፤ መመራትም ያለባት በነዋሪዎቿ ነው›› ያለው የፓርቲው ጊዜያዊ ሊቀመንበር ፓርቲያቸው በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ዝርዝር ፖሊሲዎችንና የፖለቲካ ፕሮግራም እንዲሁም የምርጫ ማኒፌስቶ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአመዛኙ በአገሪቷ እየተንቀሳቀሱ ያሉት የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉም ግራ ዘመም ፖለቲካን እንደሚያራምዱ የገለፀው እስክንድር፤ ‹‹እኛ የምንመሰርተው ፓርቲ ለየት ባለ መልኩ ቀኝ ዘመም (ወግ አጥባቂ) የሆነ ነው ብሏል፡፡
የአገራችን ፖለቲካ ከግራ ዘመም ወደ ቀኝ ዘመም እንዲያጋድል በማድረግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለመፍጠር ተዘጋጅተናል ያለው ጋዜጠኛው፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ፖሊሲያችንም የሚዘጋጅበት በዚሁ መንገድ ነው ብሏል።
ቀኝ ዘመም (ወግ አጥባቂ) ፓርቲዎች በባህሪያቸው ለማህበረሰብ ባህል፣ ወግና የአባታዊ ሥርዓት ቀናኢ የሆነ እንደሆነም ይታወቃል። የፖለቲካ ቅኝቱም ከዚሁ አተያይ የሚመነጭ ነው፡፡
ፓርቲው መስራች ጉባኤውን ካደረገ በኋላ ቀጥታ በአዲስ አበባ የማደራጀትና መራጮችን የማዘጋጀት ተግባር እንደሚያከናውን ተገልጿል::
ፓርቲው በዋናነት አዲስ አበባ ላይ ያተኩር እንጂ ፖሊሲዎችንና ፕሮግራሞችን የሚቀርፀው አገር አቀፍ ሁኔታዎችን ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ያስረዳው ጋዜጠኛ እስክንድር፤ ከሌሎች አላማውን ከሚደግፉ ፓርቲዎች ጋርም ቅንጅት ፈጥሮ ለምርጫው የመወዳደር እቅድ እንዳለውም ጠቁሟል፡፡    


Read 11983 times