Saturday, 18 January 2020 12:49

የአውሮፓ ህብረት የዘንድሮን ምርጫ ለመታዘብ አቅዷል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   በ1997 ዓ.ም የኢትዮጵያን 4ኛ አገራዊ ምርጫ የታዘበው የአውሮፓ ህብረት፤ መጪውን  ሀገር አቀፍ ምርጫ ለመታዘብ ማቀዱን አስታወቀ፡፡
ህብረቱ በሀገሪቱ በነሐሴ የሚካሄደውን ምርጫ እንዲታዘብ ባለፈው ታህሳስ ወር ከኢትዮጵያ መንግሥት ግብዣ እንደቀረበለት ትናንት ለጋዜጠኞች የገለፁት የአውሮፓ ህብረት የቅድመ ምርጫ ጥናት ቡድን፤ አባላት በቀጣይ 15 ቀናት ውስጥ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመዘዋወር ለምርጫው ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ እንደሚያጠኑ ጠቁመዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ምርጫውን ለመታዘብ የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩ፣ በየትኞቹ አካባቢዎች የሚካሄድ ምርጫዎችን ቢታዘብ የተሻለ እንደሚሆን፤ ሀገሪቱ በፀጥታና ደህንነት በኩል ለምርጫው ያላትን ዝግጁነት ያጠናል ይገመግማል ተብሏል፡፡  ለዚህ ጥናትና ግምገማ ይረዳው ዘንድ ድሬደዋና ሀረርን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ምልከታ እንደሚያደርግ ቡድኑ አባላት ገልፀዋል፡፡
ከዚህም ሌላ ከጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ከመንግሥት አካላት ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡
አጥኚ ቡድኑ ያገኘውን ግብረ መልስ ወደ አውሮፓ ይዞ በመመለስ የመረጃ ትንተና ከሰራ በኋላ ህብረቱ ምርጫውን ይታዘብ አይታዘብ በሚለው ላይ ውሣኔ ያሳልፋል፡፡ የውሣኔው ውጤት በቀጣዩ የካቲት ወር ይታወቃል ተብሏል፡፡

Read 10722 times