Saturday, 30 June 2012 10:33

ወጣቱ ፕሮፌሰርና ኪራይ ሰብሳቢው ጋዜጠኛ

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(1 Vote)

“አባይን የደፈረው ማነው?” የሚለው ጥያቄ ተደፈረ!

ወደ አንድ ወጣት ፕሮፌሰር መኖርያ ቤት ለመሄድ ታክሲ እየጠበቅሁ ነው፡፡ ወጣቱ የታሪክ ምሁር ነው፡፡ ሶስት ድግሪዎች “መጫኑን” ሰምቻለሁ፡፡ (የተቀሸበ ይሁን አይሁን ባላረጋግጥም) ሁሉንም ደግሞ በታሪክ ትምህርት ነው ያገኘው፡፡ ከሁሉም የገረመኝ ግን ይሄን ሁሉ ድግሪ ከአገር ውስጥ ብቻ ማግኘቱ ነው - ባህር ማዶ ሳይሻገር፡፡ እንኩዋንስ አውሮፓና አሜሪካ ይቅርና እዚች ጎረቤት አገር ኬንያም አልሄደም ይባላል፡፡ (ውጭ አገር የመሄድ ፍርሃት የሚባል ነገር አለ እንዴ?) ብዙ እድል መጥቶለት ንክች አላደርገውም እንዳለ ይነገርለታ (ሀገር መውደድ እንዲህ ይሆን?!)

ምሁሩ ኒዮሊበራሎችን ሲጠላቸው ለጉድ ነው - Arm Twister ይላቸዋል - እንደኢህአዴግ (እጅ ጠምዛች ለማለት ፈልጎ ነው) የኢህአዴግ ደግሞ ቀንደኛ  ደጋፊ ነው፡፡ “የኢህአዴግ ደጋፊ ምሁራን ፎረም” መስራችና ሊቀመንበር ነበር - ከመፍረሱ በፊት፡፡ ግን ደግሞ በሚደግፈው ፓርቲ ሁሌ አንጀቱ እንዳረረ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጨጉዋራ አሲያዘኝ እያለ ያማርራል -  መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፡፡ ለነገሩ ከአውራው ፓርቲ ጋር የከረረ ቅራኔ የለውም - ጠቡ ከበዛ ፍቅር የመነጨ ነው፡፡ (ማነው ደስ የሚል ስቃይ ያለው?) ኢህአዴግ ከዓለም ባንክና ከአይ ኤም ኤፍ ጋር መሞዳሞዱን አይወድለትም፡፡ ለሱ ሁለቱም የኒዮኮሎኒያሊዝም አራማጆች ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ለብድርና ለድጋፉ ቻይና መች አነሰች እያለ የሚከራከረው፡፡

በዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ዘንድ “ጭር ሲል አልወድም!” በሚል ቅፅል ስሙ ይታወቃል፡፡ ዝም ብሎ መቀመጥ ስለማይወድ ነው ስሙ የወጣለት፡፡ በሚዲያ የመናገር፤አቡዋራ የማስነሳት ክፉኛ ሱስ አለበት፡፡ በማንኛውም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ላይ ይናገራል - ሲሆን ሲሆን በመንግስት ሚዲያ ከጠፋ ግን በግሉ ፕሬስም ቢሆን (የግሉን ፕሬስ ባይወደውም) ሃሳቡን እና አቁዋሙን ይገልፃል (ገና ሳይጠየቅ!) ኢህአዴግ ስለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች፤ስለኪራይ ሰብሳቢ ባለስልጣናት፤ቢፒአርን ስለተካው አዲሱ የዜጎች ቻርተር፤ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ፤ስለአገር ገፅ ግንባታ፤ስለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰላምና ልማት አደፍራሽነት፤ስለ ፀረ ሽብርተኝነት፤ስለሙስናና ሙሰኞች --- ወዘተ ይናገራል ይደሰኩራል - ከታሪክ፤ ከፖለቲካና ከማህበራዊ ሳይንስ አንፃር፡፡ ፊት የሚሰጠው አጥቶ እንጂ ጠ/ሚኒስትሩ በቡድን 8 እና በቡድን 20 አገራት ስብሰባ ላይ ሲሳተፉ ያቀረቡት ንግግር ብቻ ሳይሆን የለበሱት ሙሉ ልብስ (suit) ለአገር ገፅ ግንባታ ስላለው ፋይዳ ቢያብራራና ቢተነትን ደስታውን አይችለውም፡፡ አንዳንዴ   ጋዜጣዊ መግለጫ ቢሰጥ ሁሉ አይጠላም ፤ግን ምን ቤት ነኝ ብሎ ይስጥ!፡፡

እዚህ ወጣት ምሁር ቤት ነው የምሄደው - ኢንተርቪው እንዳደርገው ከአለቃዬ ትዕዛዝ ደርሶኝ፡፡ የኢንተርቪው ሰበብ ደግሞ የዓመቱ ልዩ ሽልማት ተሸላሚ መሆኑ ነው፡፡ ግን ስለሽልማቱም ሆነ ለምን እንደተሸለመ የማውቀው ነገር የለኝም - አለቃዬን ጠይቄው ራሱ ይነግርሃል ብሎኝ ነው ከቢሮ የወጣሁት፡

በዕለቱ የወጣችውን ሳምንታዊ “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ባልገዛ ኖሮ፣ ከ22 ማዞርያ እስከምሁሩ መኖርያ ቤት (ጦር ሃይሎች ማለት ነው) ያለው ርቀት አላልቅ ብሎ ያስቸግረኝ ነበር፡፡ ባለቀለም መፅሄቱዋ “አዲስ ጉዳይ”፤ አቦይ ስብሃት ነጋን በሽፋን ገፅዋ ላይ ይዛ መውጣትዋ ትኩረቴን ስቦት ነው 10 ብሬን መርጬ የገዛሁዋት (አልቀመስ ባለ ኑሮ!) ወደ በረሃ ከወጡት የመጀመርያ የህወሃት ታጋዮች አንዱ የነበሩት አወዛጋቢው አቦይ ስብሃት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ማንም የኢህአዴግ ባለስልጣን “ያልደፈረውን” የግል ፕሬስ “በመድፈር” ፈር ቀዳጅ እንደሆኑ የኢትዮáያ ፕሬስ አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡ (አባይን የደፈረ…በሚለው ስሜትና ፍቺ ይወሰድልኝ)

አንዳንዶች በሚዲያ ከሚናገሩትና ከሚፅፉት ተነስተው “እንደልቡ!” የሚል ስያሜ ሲሰጧቸው፤ ሌሎች ደግሞ ሰውየው የመንግሥት ሥልጣን ባይኖራቸውም በኢህአዴግ ውስጥ አድራጊ ፈጣሪ መሆናቸውን በእርግጠኝነት ይናገራሉ (መረጃም ማስረጃም ሳይጠቅሱ!)

ለመፅሄቱዋ ሰፋ ያለ ቃለመጠይቅ የሰጡት አቦይ ስብሃት፤በኢህአዴግ ውስጥ የማይታይ ከፍተኛ የአመራር ድርሻ አላቸው ስለሚባለው ጉዳይ ተጠይቀው የመለሱትን በትኩረት አነበብኩት - ጠያቂውን ጋዜጠኛ እያመሰገንኩ፡፡

“በከፍተኛ አመራር ደረጃ የለሁም፡፡ ተራ አባል ነኝ፡፡ ብዙ ሃሳብ አቅርቤያለሁ ብዬ አልመካም፡፡ አንተም ሃሳብ ማቅረብ ትችላለህ (ማን ሊሰማው?) ሃሳቤን ገልጬ ሊሆን ይችላል፡፡ የተሰማኝን ሃሳብ በቀጥታ አስተላልፋለሁ፡፡ የሚታረም ሊኖር ይችላል፡፡ ተግባራዊ ሊደረግም ይችላል” በማለት አቦይ ስብሃት ጥያቄውን  በብልሃት መልሰዋል  -ግን በከፊል፡፡

በከፊል ያልኩት ለምን መሰላችሁ? በኢህአዴግ ውስጥ የማይታይ ከፍተኛ የአመራር ድርሻ አላቸው ስለሚባለው ጉዳይ ስላልነገሩን ነው፡፡ ምናልባት አንድ ቀን እንደ“አዲስ ጉዳይ”  ጋዜጠኛ አቦይን ኢንተርቪው የማድረግ እድሉን ካገኘሁ ይሄንኑ ጥያቄ አነሳባቸዋለሁ ብያለሁ፡፡ (ማመልከቻ መሰለ እንዴ?)

የመፅሄቱ ጋዜጠኛ ካነሳቸውና ትኩረቴን ከሳቡት ሌሎች ጥያቄዎች መካከል፤ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር በደርግ ዘመን ስለተፈፀመው በደልና እልቂት ማውራታችን የሚቆመው መቼ ነው የሚለው ነው፡፡ ትዝ ይላችሁ እንደሆነ… ዘንድሮ የግንቦት 20 ሃያ አንደኛ የድል በዓል ሲከበር ኢህአዴግ የደርግን ስም ሳያነሳ እለቱ ካለፈ ጉደኛ የልደት ኬክ ላሰራለት ቃል ገብቼ ነበር - ስፖንሰር አፈላልጌ፡፡ ደግነቱ ግን ኢቴቪ ቀኑን ሙሉ ደርግን ሲያወግዝ ዋለና እኔንም ገላገለኝ - በስፖንሰር ኬኩን ከማሰራት፡፡ አቦይ ስብሃት ኢህአዴግ ደርግን የሙጥኝ ማለቱን በተመለከተ  በሰጡት አስገራሚ መልስ፤ እንኳን አሁን ከመቶ አመት በኋላም ስለደርግ መነሳቱ አይቀርም ብለዋል (እንደ ታሪክ ነዋ!) “ገና መቀጠል አለበት፡፡ መቼም ማብቃት የለበትም፡፡ ነፍጠኝነት በአመለካከት ደረጃ በቀጣይነት መቀጥቀጥና ከዚህም በላይ መደምሰስ አለበት፡፡ መነገር አለበት፡፡ መሰረታዊ ችግሮቻችን፣ ያሳለፍነው መከራ ገና አልተፃፈም፡፡ ልጆቹ “እንዳይደገም” ብለው አልያዙትም፡፡ የደርግ ባለስልጣኖችን አስረናቸው ህዝብና ትውልድም ይማርበታል ብለን አስፈርደንባቸው በመፈታታቸው ችግር የለብኝም፡፡ እነሱ ተፈረደባቸው እንጂ ስርዓቱ ገና አልተፈረደበትም---” ሲሉ መልሰዋል (ወኔያቸውን በምናባችሁ አልሳላችሁትም?)

እኔ ግን ትንሽ ግራ ያጋባኝ ነገር አለ? “ልጆቹ እንዳይደገም ብለው አልያዙትም” ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ቆይ የትኞቹ ልጆች ናቸው? አዲሱን ትውልድ ከሆነ ---- ደርግን የት ያውቀዋልና ነው የሱን ታሪክ የሚደግመው? አዲሱ ትውልድ አሳምሮ የሚያውቀው እኮ ኢህአዴግን ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክ ከደገመም ኢህአዴግ ሲሰራ ያየውን ነው እንጂ የደርግን ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቅስ የእኔ ትልቁ ስጋቴ ምን መሰላችሁ? ኢህአዴግ የደርግን ስህተት እንዳይደግም ነው፡፡ እንዴት አትሉኝም--- አሁን ለምሳሌ የሸማቾች ማህበር ሲባል ሆዴን ሽብር ሽብር ይለዋል፡፡ የህብረት ስራ ማህበር የሚል ነገር ስሰማም ደርግ ነው ከች የሚልብኝ፡፡ በቅርቡ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በአሳታሚዎች ላይ ያወጣውን የውል ደንብ ስሰማም ያለፈው መንግስት ሴንሰርሺፕ ነው ገጭ ያለብኝ፡፡ ኢህአዴግ የሸቀጦች ዋጋ መናርን ለማስወገድ አስቦ ዘይትና ስኩዋር አከፋፍላለሁ ሲል የደርግ ራሽንና ህብረት ሱቆችን ነው ያስታወሰኝ፡፡ አንዳንድ  ደንቦችና አዋጆች ከአውሮፓ ተቀዱ ቢባልም የከፉ መሆናቸው ሲታይ “አረ ደርግ እንዳይደገም!” ያስብላል፡፡ እናላችሁ --- አቦይ የደርግ ዘመን እንዳይደገም ላሉት ስጋት ብቸኛው መፍትሄ ፓርቲያቸው ደርግ የሰራውን ከመድገም እንዲቆጠብ አጥብቆ መምከር ነው (ከተቻለም መቅጣት !)

አንድ ነገር እኮ ግልፅ ይመስለኛል - አዲሱ ትውልድ አገሪቱን የሚረከበው ከደርግ ላይ ሳይሆን ከኢህአዴግ ነው፡፡ ስለዚህ በርቀትም ቢሆን ደርግ ደርግ የሚሸቱ ነገሮችን መራቅና ማራቅ ያለበት ኢህአዴግ ነው፡፡ “የአዲስ ጉዳይ” ጋዜጠኛ በዚህ የደርግ ፋይል የመዘጋት ጉዳይ ላይ አቦይ ስብሃትን በቀላሉ አልተዋቸውም፡፡ ለነገሩ እሳቸውም አልተረቱለትም- “መዘጋት የለበትም እኮ ነው የምለው” ብለውታል፤ብለውናል (የደርግና የኢሰፓን ፋይል ማለታቸው ነው) “የአቀራረቡ ሲስተም መስተካከል አለበት እንጂ ዛሬም ነገም ከመቶ ዓመት በኋላም መነገር አለበት ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም መንጠሪያችን (Spring Board) ነው፡፡ እኛ የታሪክ ውጤቶች ነን፡፡ በአግባቡ ታሪካችንን ማወቅ አለብን፡፡ ታሪክ መቆም የለበትም፡፡ ይህ ታሪክ ኢትዮጵያ እስካለች፣ አፍሪካ እስካለች መቆም የለበትም” ባይ ናቸው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ? ታሪክ ሲተረክና ትውልዱ እንደተረት ሲያዳምጥ ሊኖር ነው ማለት ነው? (ምን በወጣው የጭራቅ ታሪክ የሚሰማው!)

እኔ የምለው ግን …ታሪክን ፅፎ ማኖር የታሪክ ባለሙያዎች አይደለም እንዴ? የታሪክ ቦታውስ የታሪክ መዛገብት አይደሉም? (ለአቦይ ሳይሆን ለራሴ ያጉተመተምኳቸው ጥያቄዎች ናቸው)

ጋዜጠኛው አቦይን ሌላም የጠየቃቸው አሪፍ ጥያቄ አግኝቻለሁ፡፡ በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አስተያየት ሲጠየቁ በፍርሃት ተሸብበው “ተውኝ ልጆቼን ላሳድግበት” የሚሉ ባለስልጣናትና ምሁራን ችግር ከምን ይመነጫል ሲል ላቀረበላቸው ጥያቄ በትችት የታጀበ  ምላሽ ሰጥተዋል “እነዚህ ሃሳብ የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ ብዙዎቻችን ስለ ሀገር አስበን አናውቅም፡፡ ወይ መንግሥቱ ወይም አፄ ኃይለሥላሴ ናቸው የሚያስቡት፡፡ ሃሳብ የሌላቸው ወይም እልም ያሉ አድርባዮች ይሆናሉ እነዚህ ምሁራን፡፡ በተረፈ ግን ስህተትም ቢሆን ዝም ከማለት ተናግሮ ሃሳብን ማስተካከል ይሻላል፡፡ የሚያውቁትን ዝም ማለት ስለ ሀገር አለማሰብ ማለት ነው፡፡ ግን ደግሞ ታፍነን ስለኖርን አትፍረድባቸው”

እንዴ… ምን እያሉ ነው አቦይ? ኢህአዴግ ከአፋኙ የደርግ ስርዓት ተላቃችሁዋል ካለን ሃያ አንድ ዓመት ሞላን አይደለም እንዴ? (ወይስ መስሎን ነው?) መቼም ከእሳቸውና ከፓርቲያቸው የበለጠ እናውቃለን ብንል አያምርብንም፡ (ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው እንዲሉ!) አቦይ ስለራሳቸውም ይናገራሉ “… ስለእኔ ከጠየከኝ ማንኛውም ኢትዮáያዊ ስለሃገሩ የመናገር፣ ሃሳብ የመስጠትና ለውጥ የማምጣት እድል እንደተሰጠው እኔም እሱን እያደረግሁ ነው፡ ሃሳቤን መግለፅ ደግሞ መብቴም ግዴታዬም ነው” ብለዋል፡ በዚህ ሙሉ በሙሉ ከአቦይ ጋር እስማማለሁ፡፡ ግን በፍርሃት ስለተለጎሙት የአገሬ ባለስልጣናትና ምሁራን ሲሉ አንዲት ውለታ እንዲውሉልኝ በአክብሮት እጠይቃቸዋለሁ፡፡ በፈሪነት የተፈረጁት እኒህ ወገኖች እንዴት ሃሳባቸውን በነፃነት መግለፅ እንደሚችሉ ከተመክሮአቸው ቢያጋሩልኝ ምስጋናዬ ወደር የለሽ ነው፡፡ ተከታታይ የማነቃቂያ ስልጠና ቢሆን ደግሞ ይመረጣል፡፡ አንዳንዴ እጃቸውን ይዘው ሁሉ በነፃነት መናገር ቢያለማምዱልንም አይከፋም፡፡ ያለዚያ እኮ ፓርቲያቸው የታገለለት ህገመንግስታዊ መብት ጥቅም ላይ ሳይውል መቅረቱ ነው (በርግጥ እርስዎ እየተጠቀሙበት መሆኑን አልዘነጋሁትም!)

የመፅሄቱን ሦስት ገፆች የፈጀውን የአቦይ ስብሃት ኢንተርቪው አንብቤ እንዳጠናቀቅሁኝ ነው ጦር ኃይሎች ደርሼ ከታክሲው የወረድኩት፡፡ የፕሮፌሰሩ ቤት በምልክት ስለተነገረኝ ትንሽ መደናገሬ አልቀረም፡፡ በሁዋላ ግን በአንድ ሊስትሮ ጠቁዋሚነት አገኘሁት፡፡

የበሩን ደወል ተጭኜ እስኪከፈትልኝ ድረስ ስለ ወጣቱ ፕሮፌሰር እያወጣሁ እያወረድኩ ነበር፡፡ የተራራ ክምር በሚያህሉ የታሪክ መፃህፍት መሃል ተደብቆ እያነበበ ወይም ደግሞ እየፃፈ እንደማገኘው ገምቼ ወይም ጠርጥሬ ነበር፡፡ ግምቴ የተሳሳተ እንደነበር የተገነዘብኩት ግን ገና የውጭው በር ሲከፈትልኝ ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ሰማያዊ ቱታ ለብሶ ከአንድ ረዳቱ ጋር ለግቢው ኮብል ስቶን እያነጠፈ ነበር - ምሁር ሳይሆን የቀን ሰራተኛ መስሎ፡፡ የኮብል ስቶን ሙያ የት አባቱ ተማረ ብዬ ተደነቅሁ፡፡  “ጋዜጠኛ፣ መጣህ?” ብሎ ጨበጠኝና ይዞኝ ገባ - ወደ ሳሎን፡፡

የገባንበት ቤት ሳሎን ሳይሆን የኢህአዴግ ፅ/ቤት ነው የሚመስለው፡፡ የኢህአዴግ አርማና ባንዲራ ብፌው ላይ ይታያል፤ከአፈጉባኤው ጀምሮ የሚኒስትሮችና የትላልቅ ባለስልጣናት ፎቶዎች ባማሩ ፍሬሞች ግድግዳ ላይ ተሰቅለዋል - እንደቅርብ ዘመዶች፡፡ ምናልባት ዘመዶቹ  ይሆኑ እንዴ? የሚል ጥርጣሬ አደረብኝ - ለሰከንዶች ያህል፡፡ ወዲያው ራሴን በወፋፍራም ጥያቄዎች አስጨነቅሁት፡፡ አንድ ሰው በምን ተዓምር ነው ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ሁሉ ሊዛመድ የሚችለው? “በሙስና” የሚል ምላሽ አገኘሁ - ከራሴ፡፡

የኢህአዴግ የታወቁ መፈክሮችና የአመራሮቹ ዝነኛ አባባሎች በኮምፒውተር ተፅፈውና በፍሬም ውስጥ ገብተው እንደፎቶዎቹ በየቦታው ተሰቅለዋል - በሳሎኑ ግድግዳ የተለያየ አቅጣጫዎች፡፡ ወጣቱ ተጣጥቦና ልብሱን ቀያይሮ ብቅ አለ - የፈገግታ ብርሃን እየረጨ፤ ለኔም ለቤቱም፡፡

መቅረፀ ድምፄን አውጥቼ የማሟሟቂያ ጥያቄዬን ላቀርብ ስል ፕሮፌሰሩ ቀደመኝ

“እኔ የምለው ጋዜጠኛ ---- ልማታዊ ነህ ኪራይ ሰብሳቢ?” በሚል ጥያቄ

ፈገግ ብዬ አየሁት - እየቀለደ መስሎኝ፡፡

“ከምሬ ነው … የሚጠይቀኝን ጋዜጠኛ ማንነትና ምንነት ማወቅ

አለብኝ --- ልማታዊ ነህ ኪራይ ሰብሳቢ?” ትክ ብሎ እያየኝ ደግሞ ጠየቀኝ፡፡

“ሁለቱንም አይደለሁም… ጋዜጠኛ ነኝ” አልኩት በተራዬ ትክ ብዬ እያየሁት፡፡

“አዬዬ…ከሁለቱ ውጭማ ልትሆን አትችልም… ተወው ጥፋቱ የእነሱ ነው…

እኔ መታወቂያ እንዲዘጋጅ ሃሳብ አቅርቤ ነበር… ግን የሚሰማ

የለም… ሁሉም ጆሮ የላቸውም፤ አፍ ብቻ!”

በማን እንደተንጨረጨረ ገብቶኛል - በፈረደበት አውራው ፓርቲ ነው፡፡ “በል መጀመር እንችላለን … በግማሽ ሰዓት ውስጥ ብንጨርስ ጥሩ

ነው --- ሌላ ቀጠሮ አለብኝ” አለ - ፕሮፌሰሩ፡፡የት ተወለዱ? የት ተማሩ? የሚሏቸውን የተለመዱ ጥያቄዎች አቆይቼ ከሽልማቱ ጀመርኩኝ   - ምን ሰርቶ እንደተሸለመና ማን እንደሸለመው በመጠየቅ፡፡ ጉሮሮውን ጠራረገና መመለስ ጀመረ - የታሪክ ፕሮፌሰሩ፡፡

“ይሄ ሽልማት ለእኔ እስከዛሬ ካገኘኋቸው ሽልማቶች ሁሉ የተለየ እና ትልቅ ቦታ የምሰጠው ነው… ማን ሸለመህ ላልከው ሰርቶ የሚያሰራው ኢህአዴግ ነዋ!”

እውነቱን ለመናገር ሸላሚው ኢህአዴግ ይሆናል የሚል ቅንጣት ታህል ግምትም ሆነ ጥርጣሬ አልነበረኝም፡፡ ያውም ለታሪክ ምሁር? (ኢህአዴግ ታሪክ ላይ እኮ እስከዚህም ነው!) እኔማ ምሁሩ አንድ ጥናት ሰርቶ ለሽልማት የበቃ ነበር የመሰለኝ! ለካ ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ የሆነስ ሆነና አውራው ፓርቲ ምን ስላደረገ ሸለመው ይሆን? መቼም ሃይለኛ ደጋፊ በመሆኑ ብቻ ለሽልማት አያጨውም (ቲፎዞ ይሸለማል እንዴ?)

ኢህአዴግ በሃይለኛ ደጋፊነት ልሸልም ካለማ የኢንዶውመንት ገቢው በሙሉ አይበቃውም፡፡ ለምን መሰላችሁ? ከßßሱ በላይ ካቶሊክ ነን የሚሉ በርካታ ደጋፊዎች ከያሉበት ብቅ ብቅ ማለታቸው ስለማይቀር ነው (እኔ ራሴ በግል የማውቃቸው የትየለሌ ናቸው)

“ምን መሰለህ… ዩኒቨርስቲው በኪራይ ሰብሳቢዎች ተጥለቀለቀ …ሆዳም በዛ …ግለኝነት ቅጥ አጣ… ለመታገል ሞክሬ ነበር አልቻልኩም… ጥዬላቸው ወጣሁና በማህበር ተደራጅቼ ወደ ኮብልስቶን ስራ ገባሁ…”

የምፅፈውን ማስታወሻ ገታሁና ቀና ብዬ ተመለከትኩት - በመገረምና ግራ በመጋባት ስሜት፡፡ እኔማ በመሃል ሌላ ሰው ጣልቃ ገብቶ የሚያወራኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን ራሱ ነበር- የታሪክ ፕሮፌሰሩ፡፡

“ወደፊት የኮብልስቶን ፋይዳ በኢትዮáያ ኢኮኖሚ  የሚል ታሪካዊ መፅሃፍ

የመፃፍ ህልም አለኝ” አለኝ - በዝምታዬ መሃል

“ሽልማቱ ገና ወደፊት ለሚፅፉት መፅሃፍ ነው ማለት ነው?” እኔም ጠየኩት-ምሁሩን ወጣት፡፡

“ኖኖኖ!… ሽልማቱማ ሦስት ዲግሪ እያለኝ ኮብልስቶን ወደ ማንጠፍ ስራ ስለገባሁ ነው…” አለና ከጠረጴዛው ስር አንድ መፅሄት አውጥቶ እውስጡ የተቀመጠውን የምስክር ወረቀት አቀበለኝ - እንዳነበው፡፡

“…በኮብል ስቶን ሙያ ባሳዩት የላቀ ብቃትና አፈፃፀም ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተሰጠ የምስክር ወረቀት…” ይላል፡፡ ዝቅ ብሎ ደግሞ መፈክር የሚመስል ነገር አነበብኩ “የኢትዮáያ ወጣቶች ህልም በኮብልስቶን ይሳካል!” የሚል፡፡ የምስክር ወረቀቱን መለስኩለት፡፡  ህልም መሰለኝ - ሁሉም ነገር፡፡ ወይም በልብ ወለድ ወስጥ የተቀረፀ ገፀ ባህርይ - ያውም ኢ-ተአማኒ!

“እና አሁን ኮብል ስቶን እየሰራህ ነው?” ግራ ቢገባኝ ነው የጠየቅሁት

“የስ…የኮብልስቶን ግንባታ ክህሎት ማዳበርያ ስልጠና ወስጄያለሁ እኮ… አላየህም ግቢዬን እንዴት እንዳሳመርኩት?” ፈገግ እያለ ጠየቀኝ፡፡

“አንድ ፕሮፌሰር እንዴት ኮብልስቶን ለመስራት ዩኒቨርሰቲ ለቆ ይወጣል ” አልኩት በሃይለ ቃል፡፡

ደግሞም እውነቴን ነው፡፡ እስከዛሬ ኢቴቪ እያዳነቀ ሲተርክ የሰማሁት ባለዲግሪና ባለዲፕሎማዎች ወደ ኮብል ስቶን ሥራ መግባታቸውን ነበር፡፡ አሁን ግን ሦስት ዲግሪ ያለው የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ኮብልስቶን እየሰራሁ ነው እያለኝ ነው፡፡ ይሄን አሁን ማን ያምናል?

“ምን መሰለህ የኔ ወንድም… ዩኒቨርስቲ ከማስተማር ኮብልስቶን ማንጠፍ በጣም አዋጭ ነው… ዩኒቨርስቲ እኮ ባስተማርከው ተማሪ ልክ አይከፈልህም - እዚህ ግን ባነጠፍከው ድንጋይ ልክ ይከፈልሃል… የማህበራችን ካፒታል ስንት እንደደረሰ ታውቃለህ? ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 2ሚ. ብር! ከእኔ በኋላ ሦስት የታሪክ ዲፓርትመንት መምህራን ከዩኒቨርስቲው ለቀው በማህበሩ ታቅፈዋል”

“አገሩ ሁሉ ኮብልስቶን  አንጣፊ ሊሆን? ” ለእሱ ሳይሆን ለራሴ ያጉተመተምኩት ነበር፡ ግን ሳይሰማኝ አልቀረም - የቀድሞው የታሪክ ፕሮፌሰር፡፡“አንተም ራስህ ወደ ኮብልስቶን ብትገባ ይሻልሃል… የዓለም ታላላቅ ህዝቦች የስልጣኔ መሰረት ድንጋይ ነው - ኮብልስቶን…እነ ላሊለበላን… እነአክሱምን…

እነግብፅን ተመልከት” በማለት ኮብልስቶን የህዳሴ ተምሳሌት እንደሆነና አገራዊ ራዕይን ለመፍጠር ብቸኛ አማራጭ መሆኑን እስኪበቃኝ ተገተገኝ፡፡

በአዲስ አበባ፣ በለገጣፎ፣ በጨፌ፣ በላፍቶና በመሳሰሉት አካባቢዎች የኮብል ስቶን ግንባታ 35ሺ ለሚጠጉ ወጣቶች ከፍተኛ የሥራ እድልና የገቢ ምንጭ እንደፈጠረም አከለልኝ - ፕሮፌሰሩ፡፡ ዓለም ባንክ ለዚሁ ዘርፍ 100ሚ. ዶላር ብድር እንደሰጠና ተጨማሪ 400 ሚ. ብር እርዳታ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመግለፅ አዋጭነቱን ሊያሳምነኝ ሞከረ፡፡ ጎትቶ ኮብልስቶን ውስጥ ሊከተኝ እንደቁዋመጠ ገብቶኛል፡፡

ይሄኔ ነው ማምለጥ - አልኩኝ፡፡ አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ላቀርብ ስል ቅድም ያላየሁት አንድ የትልቅ ሰው ፎቶግራፍ  ጥቅስ ግድግዳው ላይ ተሰቅሎ ተመለከትኩ - አባይን የደፈረ መሪ - ከምትል መግለጫ ቃል ፎቶግራፉ የማን እንደሆነ ገባችሁ አይደለ! ወንዳታ! ቅድም ሳነበው የነበረው መፅሄት ላይ ገን አቦይ ስብሃት አባይን የደፈረው መለስ አይደለም ብለዋል፡፡

አድናቂዎች (ጉድ ፈላባቸው)  ታዲያ ማነው? ኢህአዴግ? በፍፁም ይላሉ - አቦይ፡፡

አባይን የደፈረው የኢትዮያ ህዝብ ነው ብለዋል ቀለጠ ይሄ ፕሮፌሰር አልኩኝ - በሆዴ፡፡

 

 

Read 5459 times Last modified on Saturday, 30 June 2012 10:44