Saturday, 18 January 2020 12:48

ኢትዮጵያ ያለፈውን ዓመት በግጭቶችና መፈናቀሎች አሳልፋለች ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

  አለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች፤ አለም በ2019 እንዴት ከረመች በሚለው አጠቃላይ ሪፖርቱ፤ በኢትዮጵያ ግጭቶችና መፈናቀሎች ተበራክተው መክረማቸውን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ፤ በአፍሪካ ሀገራት በአመዛኙ ተቃውሞ፣ ግጭት፣ መፈናቀል እንዲሁም ህዝብ ከመሪዎች ጋር ያለመግባባት ሁኔታ ሠፍኖ ነው የከረመው ብሏል፡፡
በኮንጐ ዲሞክራቲክ ሪፖብሊክና በኢትዮጵያ በዋናነት በተለያየ መልኩ ግጭቶች እና  የዜጐች ከመኖሪያ ቀዬአቸው መፈናቀል መከሰታቸውን በጊኒና ሱዳንም የመንግስት ለውጥ በሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ሲናጡ እንደነበር ተቋሙ አትቷል::
አንድ መቶ የአለም ሀገራትን ሁኔታ በ652 ገፆች አደራጅቶ ያቀረበው ተቋሙ የሰኔ 15 የባለስልጣናት ግድያና እሱን ተከትሎ የተፈጠሩ ቀውሶች፣ ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ቀውስና በዚህ ቀውስ 53 ሰዎች መሞታቸውን፣ ጃዋር መሐመድ “የጥበቃዎቼ ሊነሱ ነው” የሚል መልዕክት ማስተላለፉት ተከትሎ ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ 86 ሰዎች የመሞታቸውን ጉዳይ ጠቅሷል፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በአንፃራዊነት እየተከበረ ቢሆንም፣ አሁንም በሀገሪቱ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አፋኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራቸውን ይገልፃል - ሪፖርቱ፡፡
የጋዜጠኞች ለዘገባ ወጥተው መደብደብ የሲዳማ ሚዲያ ኔትዎርክ አመራሮችና የባለአደራ ም/ቤት አባላት መታሠርም ሃሳብን በነፃነት በመግለጽ በኩል ላለው አፈና ማሳያ ሆነው  ቀርበዋል፡፡
በ2019 በሀገሪቱ 1.6 ሚሊዮን ሰዎች ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እንደነበሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ 66.4 በመቶ የሚሆኑት የግጭት ተፈናቃዮች ናቸው ብሏል፡፡
ብሔር ተኮር በሆነ ግጭትም በኦሮሚያ አማራ፣ ሶማሌና ደቡብ ክልል በዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ 522ሺ ያህል አዳዲስ ተፈናቃዮች የመጠለያ ካምፖችን እንደተቀላቀሉ ይጠቁማል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና ሰብአዊ መብት እንዲከበር ጥረት እያደረጉ መሆኑን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ይህን ጥረታቸውን አጠክረው እንዲቀጥሉ መክሯል፡፡  


Read 756 times