ከሰኔ 15 የባለስልጣናት ግድያ ጋር በተያያዘ ክስ የተመሰረተባቸው እነ 10 አለቃ መሣፍንት ጥጋቡና ክርስቲያን ታደለ፤ ከእንግዲህ ጉዳያቸውን የሚከታተሉት በችሎት ቀርበው ሳይሆን ባሉበት ማረሚያ ቤት ሆነው በፕላዝማ እንዲሆን ፍ/ቤቱ ወሰነ፡፡
ባለፈው ታህሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም በነበራቸው ቀጠሮ ወቅት በፍ/ቤቱ ግቢ ውስጥ ተቃውሞ መፈጠሩን ተከትሎ ፍ/ቤቱ ችሎት እየታወከ መሆኑን በመግለጽ ከእንግዲህ ጉዳያቸው የሚታየው ባሉበት ቦታ ሆነው በፕላዝማ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል፡፡
ቀደም ባለው ችሎት ተከሳሾች ከማረሚያ ቤት አያያዝ፣ፖሊስ ጋ ያለ ንብረት ከመመለስ ጋር ተያይዞ ባቀረቧቸው አቤቱታዎች የሚመለከታቸውን አካላት ምላሽ ለመስማት እንዲሁም በ1ኛ ተከሳሽ 10 አለቃ መሣፍንት ጥጋቡ ላይ ተሻሽሎ የቀረበውን ክስ ለማዳመጥ ለትናንት ጥር 8 ቀን ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ተከሳሾች ከነበሩበት ተሽከርካሪ ወርደው በችሎቱ ለመታደም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ውሣኔውን ሊያሳልፍ ችሏል፡፡
በማረሚያ ቤትና በፖሊስ ምላሽ ላይ ብይን ለመስጠት እንዲሁም 1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን የክስ ማሻሻያ ለማዳመጥና የቀሪ ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ፍ/ቤቱ ለየካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡