Print this page
Saturday, 18 January 2020 12:39

የጌዲኦ ዘመን መለወጫ ‹‹ደራሮ›› ጥር 16 ይከበራል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

   የጌዲኦ ዞን አስተዳደር ከጌድኦ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ጽ/ቤት እንዲሁም ከኤቪ ማስታወቂያና ኢቨንት ጋር በትብብር ‹‹ደራሮ ለሰላማችን አንድነታችንና ለብልጽግናችን›› በሚል መሪ ቃል የዛሬ ሳምንት ጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም በዲላ ከተማ እንደሚከበር የዞኑ አስተዳደር ገለፀ፡፡
የአስተዳደሩ ተወካዮች ማክሰኞ ጥር 5 ቀን 2012 ዓ.ም ረፋድ ላይ ልደታ አካባቢ በሚገኘው ሔቨን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ‹‹ደራሮ›› በጌዲዮ በትልቅ አክብሮትና ድምቀት የሚከበር ሲሆን በዓሉ የመተሳሰብ የመመሰጋገንና የስጦታ መለዋወጫ እንደሆነም የጌዲኦ ዞን አስተዳደሪ አቶ ገዙ አሰፋ ገልጸዋል፡፡
ስፖርታዊ ውድድር በባህልና ቋንቋ ላይ የሚደረግ ውይይት፣ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የበዓሉ አካል እንደሚሆኑ የገለፁት አስተዳዳሪው በበዓሉ ላይ ሁሉም እንዲታደሙ ከፍተኛ ዝግጅት መደረጉንም ጨምረው ገልፀዋል።
 የጌዲኦ ዞን ለምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ በርካታ ትክል ድንጋዮች ከግማሽ በላይ የሚገኝበት፣ ለአለም ገበያ የሚቀርበው የይርጋ ጨፌ ቡና መገኛ፣ የወናጎ ደን፣ ልዩ ልዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ መስህቦች ቦታ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በሆቴልና በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሰማሩ ትክክለኛ ቦታ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ደራሮን በማይዳሰሱ ቅርሶች ዘርፍ በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ የገለፁት አስተዳዳሪው በበዓሉ ላይ ሁሉም እንዲታደም ጥሪ አድርገዋል::

Read 1155 times