Sunday, 12 January 2020 00:00

የቀጣዩ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይፋ ይሆናል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ነባር የፖለቲካ ድርጅቶች የአዲሱን አዋጅ መስፈርቶች በ2 ወራት ውስጥ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል

             የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀጣዩን ምርጫ ጊዜ በ2 ሳምንት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡ ቦርዱ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሮ በማጽደቅ የምርጫ ጊዜውን ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ ቦርዱ ነባር የፖለቲካ ድርጅቶች በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት የሚጠበቅባቸውን መስፈርት በ2 ወራት ውስጥ አሟልተው እንዲቀርቡም አሳስቧል፡፡
አወዛጋቢ ሆኖ በፀደቀው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ምርጫ አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት ሁሉም ነባር የፖለቲካ ድርጅቶች አገር አቀፍ ከሆኑ 10 ሺህ ክልላዊ ከሆኑ 4 ሺህ ፊርማ አሰባሰበው በ2 ወራት ውስጥ እንዲቀርቡ ቦርዱ በሰጠው ማሳሰቢያ ላይ ገልጿል፡፡
ስለዚህ በተጨማሪም በፓርቲያቸው ደንብ መሰረት ጠቅላላ ጉባኤ ሳያካሄዱ ጊዜ ያለፈባቸው ፓርቲዎች በአዲሱ አዋጅ መሰረት በሁለት ወር ውስጥ ጉባኤ አድርገው መስፈርቱን አሟልተው እንዲቀርቡ ጠቅላላ ጉባኤ በወቅቱ ያካሄዱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ደግሞ በአዲሱ አዋጅ መሰረት መስፈርቶችን በሟሟላት ከምርጫው በኋላ እስከ ጥር 2013 ዓ.ም አጠናቀው እንዲቀርቡ እንዲሁም ክልላዊ ከሆኑ እስከ ታህሳስ 2013 እንዲያቀርቡ ቦርዱ አሳስቧል፡፡
አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሄረሰቦችን የሚወክሉ ፓርቲዎች ሕጉ ላይ ያለውን የመስራች አባላት (10ሺህ/ 4ሺህ) ቁጥር ከማሟላት መስፈርት ነፃ መሆናቸውንም ቦርዱ አስገንዝቧል፡፡
10 ሺህና 4 ሺህ ፊርማ የማሰባሰብ ግዴታን የሚጥለውን አዲሱን አዋጅ ከ70 በላይ ፓርቲዎች መቃወማቸው ይታወሳል፡፡

Read 9977 times