Saturday, 11 January 2020 14:56

ግጭት በፈጠሩ ተማሪዎችና መምህራን ላይ ዩኒቨርሲቲዎች እርምጃ እየወሰዱ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)


           የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር በ22 ዩኒቨርሲቲዎች በሚገኙ 170 ተማሪዎች ላይ ከትምህርት የማገድ እርምጃ መወሰዱን የገለፀ ሲሆን ዩኒቨርሰቲዎች በበኩላቸው  ተጨማሪ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን እንደወሰዱ ታውቋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስተዳደራዊ እርምጃ የወሰደባቸው 170 ተማሪዎች በዋናነት በዩኒቨርሲቲዎቹ በተከሰቱ ግጭቶች ቀጥተኛና ዋነኛ ተሳታፊ ሆነው በመገኘታቸው እንደሆነ አስታውቋል፡፡
280 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን ይህን ጉዳይ የፌደራል ፖሊስ እንደሚከታተለው ተገልጿል፡። 50 ተማሪዎችም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው ተብሏል፡፡ ከተማሪዎች በተጨማሪም ከፍተኛ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን ላይም እርምጃ መወሰዱ ታውቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 11 ተማሪዎችን ሲያባርር፣ ሶስት መምህራንና 8 የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም አንድ የጤና መኮንን ሰራተኛ ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ፤ በ355 ተማሪዎች፣ በሁለት የአስተዳደር ሰራተኞችና በአንድ መምህር ላይ እርምጃ መውሰዱን ያስታወቀ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በቀጣይ በሕግ የሚጠየቁም እንዳሉ ተጠቁሟል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተፈጠሩ ግጭቶች ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ለሶስት ጊዜያት ትምህርት የተቋረጠ ሲሆን በግጭቶቹም የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉ ይታወቃል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በ51 ተማሪዎች ላይ እርምጃ የወሰደ ሲሆን 29 የጥበቃ ሰራተኞችን ከሥራ አባርሯል፣ 28 ሰራተኞችንም  በጡረታ አሰናብቷል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ የአስተዳደር ሽግሽግ ማድረጉንም አስታውቋል።
ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የማጣራትና የመመርመር ሥራ እያከናወኑ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ትምህርት ያልጀመሩ ዩኒቨርሲቲዎች በአስቸኳይ እንዲጀምሩም መመሪያ ተላልፏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው እንደሚገኙም የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ከተባረሩ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች መካከል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን ላለፉት ሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት የመሩት ዶ/ር ያሬድ ማሞ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በአሁኑ ወቅት በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ የሚገኝ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውም ይታወቃል፡፡



Read 10241 times