Saturday, 11 January 2020 14:55

የሃድያ ዞን የደቡብ ክልል ም/ቤት ላይ ቅሬታ አቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

  ‹‹የደቡብ ክልል ም/ቤት ጥያቄዬን አፍኖብኛል›› ያለው የሃዲያ ዞን ም/ቤት የክልልነት ጥያቄው ተመርምሮ ምላሽ እንዲያገኝ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ቅሬታ አቀረበ፡፡
የሃዲያ ዞን የክልልነት ጥያቄ በዞኑ ም/ቤት ሙሉ ድምጽ አግኝቶ ከፀደቀ በኋላ ባለፈው ዓመት ታህሳስ 16 ቀን 2011 ለደቡብ ክልል ም/ቤት ጥያቄው መቅረቡን የገለፀው የቅሬታ ደብዳቤው  ም/ቤቱ ጥያቄውን ተቀብሎ ለማስተናገድ ፍቃደኛ አልሆነም ብሏል፡፡
የደቡብ ክልል ም/ቤት እስካሁን በጉዳዩ ላይም እንዳልተወያየና የሃዲያ ዞንን ጥያቄ በቸልታ መመልከቱን የዞኑ ም/ቤት ደብዳቤ ያመለክታል፡፡
የሃድያ ዞን የክልልነት ጥያቄ ተገቢውን መስፈርቶች በሙሉ ያሟላ መሆኑን ማስረጃዎች በመዘርዘር በደብዳቤው ያቀረበው የዞኑ ም/ቤት የፌዴሬሽን ም/ቤት ዳኝነት እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡
የደቡብ ክልል ም/ቤት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ እንዲደረግ እንዲሁም ጥያቄውን በሕገ መንግሥቱ መሠረት በ1 አመት ጊዜ ውስጥ ተመልክቶ ምላሽ መስጠት ሲገባው በማዘግየቱና ምላሽ ባለመሰጠቱ የደቡብ ክልል ም/ቤት በሕግ ጥሰት ሊጠየቅ እንደሚገባው ተገልጿል፡፡
የሃድያ ክልልነት ጥያቄ የፍትሃዊነት ጥያቄ ነው ያለው ደብዳቤው ላለፉት ዘመናት ብሄረሰቡ ጥያቄውን በተለያዩ አግባቦች ሲያቀርብ መቆየቱንም አስታውሷል፡፡

Read 1800 times