Saturday, 11 January 2020 14:46

ለጋዜጠኛና ተርጓሚ ስለሺ ዳቢ ህክምና እርዳታ እየተሰባሰበ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ጋዜጠኛና ተርጓሚ ስለሺ ዳቢ (ትርጉም በስለሺ) ታህሳስ 23 ቀን 2012 ዓ.ም በስራ ላይ እያለ በድንገት በስትሮክ ህመም ተጠቅቶ ሆስፒታል መግባቱና ህክምና እየተከታተለ መሆኑ ታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC) የእንግሊዝኛ ክፍል ባልደረባና የህንድ ፊልሞችን ወደ አማርኛ በመተርጐም የሚታወቀው ጋዜጠኛ ስለሺ በስትሮክ ህመም ከተጠቃ ጀምሮ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በህክምና እየታገዘ ቢሆንም የሰውነቱ ግማሹ ክፍል መታዘዝ ባለመቻሉ በውጭ አገር የተሻለ ህክምና እንዲያገኝ እርዳታ መሰባሰብ መጀመሩም ተገልጿል፡፡
ጋዜጠኛ ስለሺ ለበርካታ አመታት በሺህ የሚቆጠሩ የህንድ ፊልሞችን ወደ አማርኛ በመተርጐም ብዙዎችን ከፊልም ጋር ያስተዋወቀ ሲሆን ይህም  “ትርጉም በስለሺ” የሚል ቅጽል ስም አሰጥቶታል፡፡ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና በኤፍ ኤም 104.7 በእንግሊዝኛው ክፍል በጋዜጠኝነትም ሆነ በኃላፊነት ደረጃ አገልግሏል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በፖለቲካል ሳይንስና የውጭ ግንኙነት የማስተርስ ዲግሪውን ያገኘው ጋዜጠኛ ስለሺ ባለትዳር ሲሆን የ5 እና የ2 ዓመት ወንዶች ልጆችን አፍርቷል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ስለሺ ዳቢ ከአገር ውስጥ ባለፈም በአሜሪካ፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳንና በተለያዩ አለማት በመንቀሳቀስ ዘገባዎችን የሰራ ሲሆን፣ በተለያዩ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በሰጣቸው ቃለ ምልልሶች የዳበረ ሙያዊ ልምድና ተሞክሮውን ለሌሎች የሚያካፍል አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው፡፡
“ታህሳስ 23 ቀን 2012 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አዳራሽ ውስጥ በስብሰባ ላይ እያለሁ በግራ የልቤ ክፍል በደረሰብኝ የስትሮክ ህመም ቀኙ የሰውነቴ ክፍል መታዘዝ አልቻለም” ሲል ለአዲስ አድማስ በስልክ የተናገረው ጋዜጠኛው፤ “ምንም እንኳን በጥቁር አንበሳ ላለፉት ዘጠኝ ቀናት አስፈላጊው ህክምና እየተደረገልኝ ቢሆንም፤ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ውስብስብ በመሆኑ ወደተሻለ ጤንነት ለመመለስ የግድ የውጭ ህክምና ያስፈልገኛል” ብሏል፡፡
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደየእምነቱ ፀሎት እንዲያደርግለትም ጠይቋል፡፡
ጋዜጠኛው በውጭ አገር የተሻለ ህክምና አግኝቶና ጤንነቱ ሙሉ ለሙሉ ተመልሶ ወደ ስራው እንዲመለስ ድጋፍ እየተሰባሰበ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በባንክ ሂሳብ ቁጥር 1000128435337 ስለሺ ዳቢ በዳኔ በሚል ሰዎች የቻሉትን ድጋፍ እንዲያደርጉ ወይም በ0963149459 ወይም በ0911963134 በቀጥታ በመደወል መደገፍ እንደሚቻል ድጋፍ አሰባሳቢዎቹ ገልፀዋል፡፡

Read 1298 times