Saturday, 11 January 2020 14:23

“ከእኔ በላይ ለአሳር…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ የህግ ነገር ካነሳን አይቀር… ይህ የመንገድ ትራፊክ ህግ በሰርኩላር የተለወጠ ነገር አለ እንዴ!? ቀይ ከበራ በኋላ ጥሶ ለማለፍ ይህ ሁሉ እሽቅድምድም ምንድነው! ወይስ “ቀይ ቢበራም ለአምስትና ለሰባት ሰከንድ ያህል በፍጥነት ሽው ማለት ትችላላችሁ” የሚል እኛ የማናውቀው ህግ አለ?!”
          
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…‘ይህኛውም ዓመት’ መጋመሱ ነው እኮ! ለነገሩ ኑሮም እየገመሰን አይደል! የምር ግን የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ሽልማት ሊሰጠን አይገባም እንዴ?! አሀ…“የፉርኖ ዋጋ ጨመረ” ብለው አይደል እንዴ አደባባይ የሚወጡት! እኛ ‘ቀጫጭኖቹ’ ግን ይኸው ስንትና ስንት መከራዎችን ድምጽ አጥፍተን እያለፍን እኮ ነው! 
የምር ግን…አለ አይደል…አሁን፣ አሁን የሆነ በዓል በመጣ ቁጥር ስለ ዋጋ መወደድ ማውራቱ “እነዚህ ሰዎች በቃ እድሜ ልካቸውን መነጫነጭ አይሰለቻቸውም!” እንዳይሉን ብለን ብንሰጋ አይፈረድብንም፡፡ “በዘንድሮው በዓል ብዙ ነገሮች ዋጋ ቀነሱ!” የምንልበትን ዘመን ያፍጥልንማ፡፡
“ስማ እንትን ገበያ ብትሄድ በአንድ ሺህ ብር የምትገዛው በግ ለቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ለቤተዘመድ ጉባኤም ይተርፋል፡፡”
“አንድ ሺህ! ለአንድ በግ አንድ ሺህ ብር የማወጣው ይሄን ያህል ገንዘብ የተረፈኝ መሰለህ እንዴ?!”
እንዲህ የምንባባልበት ዘመን አይናፍቃችሁም!?
አሀ…ግጦሽ ካገኘች ወር ከሳምንት የሆናት የምትመስልና ደረት ሊጣልላት ምንም ያልቀራት በግ በአራትና በአምስት ሺህ ብር! በዚህ ያልተነጫነጭን በምን እንነጫነጭ! አንዴ ድስት ከገባች የማትወጣ የምትመስል ዶሮ በአምስት መቶ ብር! በዚህ ከቀጠለ እኮ ነገና ከነገ ወዲያ የመነጫነጭ ጉልበቱን ልናጣ ሁሉ እንችላለን፡፡
እኔ ምለው… አሁንም ከተማው ህንጻ በህንጻ ሲሆን የደላን አስመሰለብን እንዴ!? አሀ…ነገሮች ሲፋቁ ሌላ ነዋ! የምር ግን ጥሩ ህንጻዎች ቢኖሩ አሪፍ ነው፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ ወደ ውጪ የሚወጣው ሰዋችን የሚያሳየው ፎቶ ይበዛለታል፡፡ ከዓመታት በፊት እኮ አንድ ብቸኛው መሸለያችን መሀል አራዳ ያለው የማዘጋጃ ቤት ህንጻ ነበር፡፡ እሱንም ‘ፈረንጅ’ አያምንም ነበር አሉ፡፡
“ይኸውልህ፣ ይህ ህንጻ ዋና ከተማችን ውስጥ ያለ ነው፡፡”
“ሁዋት! ኢትዮጵያ ውስጥ ነው እንዲህ አይነት ህንጻ ያለው?”
“አዎ፣ አዲስ አባባ መሀል ላይ፡፡”
“እባክህ ቀልዱን ተው፡፡ ይሄ ወይ ካይሮ ወይ ጆሃንስበርግ ነው፡፡”
አሁን ባንኮችና ኢንሹራንሶች ምን የሚያካክል ህንጻዎች እየሠሩ አይደል! እኛ አሁን እያልን ያለነው እላያችን ላይ ‘ኤምፓየር ስቴት ቢልዲንግ የሚያካክል’ የችግር ህንጻ እየተገነባብን ስለሆነ ሐይ ይባልልን ነው፡፡ ለምን እንደሆነ እንጃ እንጂ… “በህግ አምላክ!” እያልን ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ የህግ ነገር ካነሳን አይቀር… ይህ የመንገድ ትራፊክ ህግ በሰርኩላር የተለወጠ ነገር አለ እንዴ! ቀይ ከበራ በኋላ ጥሶ ለማለፍ ይህ ሁሉ እሽቅድምድም ምንድነው! ወይስ “ቀይ ቢበራም ለአምስትና ለሰባት ሰከንድ ያህል በፍጥነት ሽው ማለት ትችላላችሁ” የሚል እኛ የማናውቀው ህግ አለ!
ሀሳብ አለን…ከሶስቱ መብራቶች አረንጓዴ፣ ቀይና ቢጫው ሌላ አራተኛ መብራት ይጨመርልን፡፡ የሆነ ከበድ ያለ ቀለም ይሆንና ትርጉሙ ምን መሰላችሁ… “ቀዩን መብራት ልትጥስ ትሞክርና ወዮልህ!” የሚል ይሆናል፡፡
እናላችሁ… በየመንገዱና በየስፍራው የምናየው “እኔ ብቻ…” አይነት ነገር ሲበዛ የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ “እኔን አስቀድሙና እናንተ ተገትራችሁ ቅሩ!” ባይ ቅድሚያ ፈላጊ መአት ነው፡፡ ህዝብ በስነ ስርአት ተሰልፎ ታክሲ በሚጠብቅበት ዘመን እኮ ገና እንደ ደረሰ “ፊት ካላስገባችሁኝ…” የሚል መአት አለላችሁ፡፡ ወይ ደግሞ ልክ የሆነ የልብስ ፋሽን የምታሳይ ይመስል ፊት አካባቢ ታንዣብብና ታክሲ ሲመጣ ዘላ ዘው የምትል ጄነፊር ሎፔዝ ነገር አለችላችሁ:: በጠዋት መጥቶ የተሰለፈው ህዝብ እኮ  የሥራ መግቢያ ሰዓት ደርሶበት እየተቁነጠነጠ ነው፡፡
“ስማ ተራህን ጠብቅ እንጂ፡፡ ይሄ ሁሉ ሰው ተሰልፎ ዘለህ ትገባለህ?”
“እቸኩላለሁ፣ ሥራ አለብኝ፡፡”
ልክ እኮ የስታዲየም ሰልፍ ይመስል የተኮለኮለው ህዝብ ስራ ፈት የሆነ ነው የሚያስመስሉት፡፡ (እኔ የምለው… ያ ሁሉ በጥናት ሳይሆን በፉክክር ሲሠራ የከረመው ስታዲየም ሁሉ… እንክብካቤ እያገኘ ነው?! ኮሚክ አኮ ነው… በብዙ መቶ ሺዎችና ምናልባት ከዛም በላይ ሥራ ፈላጊ ባለባት ሀገር በፉክክር  ፋብሪካዎች ከመገንባት ይልቅ በፉክክር ስታዲየም ስንገነባ መክረማችን ከእለታት አንድ ቀን ጣት ሳያቀሳስር ይቀራል ብላችሁ ነው!)
እናላችሁ… ሁሉም “ፊት ረድፍ ካልሆንኩ” ባይ ሲሆን አሪፍ አይደለም፡፡ አሀ… ፊት ያለ ሰው እንዲኖር እኮ በስተኋላ ሰዎች ሊኖሩ ይገባል! አንደኛ ለመውጣት እኮ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ ብሎም ውራ የሚወጡ ሰዎች መኖር አለባቸው፡፡
ስሙኝማ … እንግዲህ ዶሮዋ ተገነጣጥላ ከመቅረቧ በፊት የብልት ድልድሉ ተካሂዶ ያልቅ የለ፡፡ ለአባወራ ፈረሰኛ… አራት ነጥብ፡፡ (ስሙኝማ…ይቺ “አራት ነጥብ!” የሚሏት አባባል ‘ጌም ኦቨር’ ተብላ የቀረችው የአገልግሎት ዘመኗ አልቆ ነው፣ ወይስ አራት ነጥብ ማለት የቀድሞ ናፋቂ ያሰኛል ተብሎ ነው?! ቂ…ቂ…ቂ…!)
“ይህ ውሳኔ በተላለፈበት ሰዓት እኛ ስላልነበርንበት እንደገና ይታይ፡፡”
“እናንተ ባትኖሩም በተሰብሳቢው በአብላጫ ድምጽ እኮ ነው ያለፈው፡፡”
“አብላጫ የለም፣ በርጫ የለም፡፡ ወይ እንደገና ይታይ፣ አለበለዛ…”
አለበለዛ ምን? እሱ አይደል ችግሩ! እናላችሁ… የሀገራችን አንዱ ችግሯ “አለበለዛ…” ባዮች እየበዛን መሄዳችን ነው፡፡ “ይግባኝ የሌለው ፍርድ የምንሰጠው እኛ ብቻ ነን!” የምንል መብዛታችን ነው ችግሩ፡፡
“ምንድነው እሱ?”
“ምኑ?”
“የለበስሽው ምን የሚሉት ሹራብ ነው?”
“ደግሞ ምን ሆነ ልትል ነው!?”
“ቆይ እንጂ… እንዲህ ከቆዳ ጋር የሚጣበቅ ሹራብ የምትለብሽው አንቺ ባህር ጠላቂ ዋናተኛ ነሽ? ሞዴል ነሽ? የምን እዩኝ እዩኝ ነው! አሁን እሱን አውልቂና ሰፋ ያለ ሹራብ ልበሺ!”
“እኔ ተስማምቶኛል፡፡”
“ለውጪ ብያለሁ ለውጪ!”
“ለምን ብዬ…?”
“በቃ ተናገርኩ!”
እሷ አምሯት ለምትለብሰው እሱ ምን ቤት ነው?! ልክ እንዲሁ ህዝብ የፈለገውን በመረጠና የማይፈልገው ላይ ጀርባውን ባዞረ፣ እነ እንትና ምን አገባቸው?! እናላችሁ… “በቃ ተናገርኩ!” ባዮች እየበዛን… አለ አይደል… ሀገር “የእኔና የእኔ ነገር ብቻ ነው ትክክሉ!” ባይ ዜጎች ሲበዙባት መልካም አይሆንም፡፡
እናላችሁ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል … ናፖሊዮን ቦናፓርቴዎች በዝተናል፡፡ ታላቁ  እስክንድሮች በዝተናል፡፡ “የበረሀው ተኩላ…” ምናምን መባል የምንፈልግ በዝተናል:: እንዝርት የምታካክል ክንድ ያለን ጡንቸኞች በዝተናል፡፡ እኔ ምለው … የአንዳንድ ድርጅቶችን ጡንቸኝነት ነገሬ ብላችሁልኛል! ከወር እስከ ወር በአገልግሎት አቀራረብ ጉድለት ሲያማርሯችሁና ሲያበሳጯችሁ  ከርመው፣ ሂሳብ ለመክፈል ሁለት ቀን ብትዘገዩ፣ ከማሳሰቢያነት ይልቅ የዛቻ ቃና ያለው ነገር ትሰማላችሁ፡፡
“ያለባቸውን እዳ በአስር ቀን ውስጥ በማይከፍሉ ተገልጋዮች ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል…” አይነት የ“ወዮልህ” ቃና ሲበዛ  ልክ አይደለም፡፡ (ይሄም እኮ “እኛ ብቻ” አይነት ነገር ነው!) ራሳቸው ህግ ያላከበሩ ተቋማት ህጋዊ እርምጃ ስለ መውሰድ ሲያወሩ… አለ አይደል…ቀሺም “ሪያሊቲ ሾው” ነው የሚመስለው:: (አንድ ሰሞን “እዚህ ትሸናና ትሸነሸናለህ!” ምናምን የሚሉ ነገሮች በአደባባይ ‘ይለጠፉ’ ነበር፡፡)
በአንድ ወቅት “ከህብረተሰባችን ከሰላሳ እስከ አርባ በመቶ የሚሆነው በተለያዩ ሱሶች ተይዟል” የሚል ጥናት እንሰማ ነበር አይደል?! (እሱ ጥናት “ከእኔ በላይ ለአሳር!” ሱስን ይጨምራል እንዴ?)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1249 times