Print this page
Saturday, 11 January 2020 14:22

ኢትዮጵያ ድንቅና ረቂቅ ፍልስፍና አላት!!

Written by  ወልደ ጊዮርጊስ ይሁኔ
Rate this item
(1 Vote)

      (ካለፈው የቀጠለ)
‹‹ወዳጄ ልቤና ሌሎችም›› በሚል ርዕስ ብላቴን ሕሩይ ወልደ ስላሴ ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ፣ ገጽ 36 ላይ፣ እንዲህ የሚል ግጥም ሰፍሯል፡-
‹‹የተወለደ ካዳም፣
መሬት ያልገዛ የለም፤
ግብሩን መገበር አቅቷቸው፣
ገና ብዙ ዕዳ አለባቸው፡፡››
በዚህ ግጥም ላይ የሰው ልጆች ሁሉ ምድርን የመግዛት ስልጣን እንደተሰጣቸው ፤ ለዚህም ለሰው ልጆች በተፈጥሮ ከእንስሳት ሁሉ የተለየ እውቀትና ጥበብ እንደተቸሩ፤ ነገር ግን የተሰጣቸውን እውቀት በአግባቡ ካላዋሉት ወይም ካልተጠቀሙበት ችግር የሚገጥማቸው መሆኑን እንረዳለን፡፡ ‹‹መሬት ማናቸውንም ነገር ብትሰጥ በብድር ነው፡፡ ብድሯን ካልመለሱላት እንደ ባንኮች ሁሉ ታስቸግራለች፡፡… ምድር ያበደረችውን ነገር ሁሉ ካልመለሱላት ለወደፊት ስጭኝ ቢሏት ትለግማለች፡፡ ሄዶ ሳይመለስ የቀረባትም ሲበዛ ከናካቴው በጭራሽ እንቢ ትላለች፡፡ ተበድሯት ብድሩን ሳይመልስላት እንቢ ላለ ሕዝብ በረኃብና በበሽታ ትፈጃዋለች:: ይህ ቃል ሀሰት እንዳይደለ ማንም ባላገር ይመሰክራል፡፡››  (ነጋድራስ ገብረ ህይወት፣ 92) ከላም ወተት የሚፈልግ ሰው ላሟን ማብላት፣ ማጠጣትና መንከባከብ እንዳለበት ሁሉ፣ ከመሬት ጥቅም የሚፈልግ ሁሉ ምድርን መንከባከብ ይገባዋል፡፡ ይህን ካላደረገ ግን በደራሽ ጎርፍና በከባድ ማዕበል ይመታል፡፡ በሰደድ እሳት ይቃጠላል፡፡ በመሬት መደርመስና በአየር ንብረት መዛባት ህይወቱ ይከብድበታል::
‹‹ይህ ዓለም ውበት፣ ሕብር፣ ስነ ስርዓት አለው፡፡ የክረምትና የበጋ፤ የሌትና የቀን መፈራረቅ፤ የከዋክብትና የሩቅ ዓለማት መዘዋወር፤ የጽጌያትና የአትክልት ማበብ ማፍራት በዘፈቀደ የሚፈጸም አይደለም፡፡ እነዚህን ሁሉ ሕላዊያት የሚያስተዳድሯቸው የስነ ፍጥረት ሕግጋት በውስጣቸው ይገኛሉ:: የግሪኩ ፈላስፋ አናክሳጎረስ ሎጎስ አለው፡፡ ቃል በቃል ወደ አማርኛ ስንተረጉመው ሕሊና ማለት ነው፡፡ ከህሊና ዘይቤዎች አንዱ ሕግ ነው:: ሰው ቢቆም ቢቀመጥ፣ ቢሮጥ ቢተኛ፣ ቢናገር ዝም ቢል፣ ቢመርቅ ቢረግም በህሊናው ሕግጋት መሰረት ነው፡፡ በውስጣችን አስገዳጅ የሆኑ የሐሳብና የምግባር ያልተጻፉ ሕግጋት አሉ፡፡›› (እጓለ፣ 49) በማለት ያስቀምጣሉ፡፡ በመሆኑም የሰው ልጅ በተፈጥሮ በታደለው ተፈጥሮን የመመርመርና የመረዳት ጥበብ ተጠቅሞ ጥቅም ላይ ማዋል ችሏል፡፡ ሁልግዜም ይችላል፡፡ ይህን የተረዱት አያቶቻችንና  አባቶቻችን ወቅቱን ጠብቀው፣ የተለያዩ እህልና አዝዕርትን መሬት ቆፍረው ይተክላሉ፤ይዘራሉ፡፡ ወቅቱን ጠብቀው ደግሞ ምርታቸውን ይሰበስባሉ፡፡
በዚህ ንጹህ ህሊናቸው በመመራት የሰው ልጅ በህይወት ሲኖር፣ በጎ ተግባር ፈጽሞ ማለፍ እንዳለበት በኑረታቸው ከማሳየት አልፈው መልካም መንፈሳቸውን ለትውልድ ለማስተላለፍ በስነ- ግጥሞቻቸውና በተረትና ምሳሌያቸው ይገልጹታል፡፡ ለአብነት ያህል የሃሚና ማህበረሰቦችን ብናይ፡- ‹‹ወየው ዓለም የጀመረሽ እንጂ፤ የጨረሰሽ የለም፡፡›› የሚል አባባል አላቸው፡፡ ይህን የሚሉት በምትኖርበት ዘመን የበኩልህን መልካም ስራ ሰርተህ ማለፍ እንደሚገባ ለመግለጽ ነው፡፡ ከዚህ እሳቤ ጋር የሚመሳሰል ሀሳብ በስነ ግጥሙ ላይ ያነሳው ደግሞ ገጣሚ አበራ ለማ ነው፡፡
‹‹እንግዲህ አንተ ነህ፣ የወር ዘብ ተረኛ፤
ወይ ዘመኑን አንጋ፣ ወይ በቁምህ ተኛ፡፡››
ሌላ ምሳሌ ለመጨመር ያህል የክብር ዶክተር ደራሲ ከበደ ሚካኤል ስነ ግጥምን እንይ፡-
‹‹ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፤
ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም፡፡›› -- በማለት በመንፈስ እይታ ውስጥ ገብተው የሰው ልጅ ሟች መሆኑንና የማይቀርለት የተፈጥሮ ግዴታ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከሞት በኋላ ሌላ ዓለም ቢኖርም ባይኖርም፣ መልካም ስራ መስራት ተገቢ እንደሆነ ይመክራሉ፡፡
በሰዎች ኑረት ውስጥ የሚታየው የአብሮነትና የመተጋገዝ ስርዓት፣ የስነ- ምግባር ሕግጋት፣ በባህላቸውና በጠቅላላው ህይወታቸው መልክና ደርዝ ይዘው የሚገኙት ፍሬ ነገሮች የአንድ ህዝብ መንፈስ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ በእነዚህና ቀጥሎ በማነሳቸው ፍሬ ነገሮች ምክንያት ነው የኢትዮጵያ ፍልስፍና መንፈሳዊ ነው ያልኩት፡፡
***
ስለ ጥበብ እና እውቀት
በሀገራችን ከነበሩት ሊቀ ሊቃውንት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ፊት ላይ የሚገኘው ሊቁ ያሬድ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ፤ የሰው ነፍስ ውስጣዊ ሀብታት ብልጽግና መገለጫ ከሆኑት ጥበባት መካከል የዜማና የቅኔ (የስነ-ግጥም) ድርሰቶችን በትልቅ ደረጃ መድረስ ችሏል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በጊዜና በዘመናት መካከል ውስጥ ለነበሩት የሀገራችን ሊቃውንት የተጠሪነት (የመሪነት) ቦታውን ይወስዳል፡፡
‹‹እንደምናውቀው ቅዱስ ያሬድ የሃይማኖት ሰው ነው፡፡ ይህንን ሊቅ በኢትዮጵያ መንፈስ እንደራሴ ብለን ስንጠራ ለሀገሩ ስልጣኔ አንድ ጠባይ መስጠታችን ነው፡፡ ይህም ሃይማኖታዊነት ነው፡፡ በማናቸውም በኩል ብንመለከተው የኢትዮጵያ ህዝብ በዘመናት መካከል ያደረገው የታሪክ ጉዞ በሊቃውንቱ ጥረት በተከማቸው የመንፈስ ውጤት መሰረት ስናየው በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡›› (እጓለ፣63-64) ሲሉ ቅዱስ ያሬድ ትልቅ የስልጣኔ መንፈስ በሀገራችን የፈጠረ ታላቅ ሊቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የእሳቸውን ሀሳብ የሚያጠናክር ሀተታ ያቀረቡት ሌላው የሀገራችን ምሁር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ናቸው፡፡
‹‹ከኢትዮጵያ የተገኘው ቅዱስ ያሬድ፤ ልዩ ማህሌቶችን በመድረሱና ከአውሮፓውያን 700 ዓመታት አስቀድሞ ዜማ ምልክቶችን በመፈልሰፉ ልንኮራበት ይገባል፡፡” (ፍቅሬ፣ 231) በማለት ለኢትዮጵያውያን የጥበብ ምንጭ ሆኖ እንደሚታይ ያስረዳሉ፡፡
ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ የሀገራችን ቀደምት የኪነ ጥበብ ውጤቶች መካከል በጣና ገዳማት በሚገኙት አብያተ ቤተክርስቲያናት ውስጥ ተስለው የሚገኙትና በጎንደር ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙት ይጠቀሳሉ፡፡
በስነ ጽሁፍ ረገድ ከፍተኛ ስልጣኔ ላይ እንደነበርን ዋና ማሳያው ግን የቅኔ ትምህርት ነው፡፡ ‹‹ከማናቸውም ሀገር ስነ ጽሁፍ ጋር ሊወዳደር የሚችል የቅኔ ትምህርት ነው:: እንዲያውም አቻም የሌለው ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ቅኔ ወይም ግጥም በፈረንጆች ቀላል ነገር ነው፡፡ ሁሉም የሚረዳው ለተራው ህዝብ የሚሆን ነው፡፡…  የፍልስፍና ህዝባዊ አቀራረብ ግጥም ይባላል ማለት ነው፡፡ ቅኔ ስንል ግን ጨርሶ ሌላ ነገር ነው፡፡ ከባድ ነው፡፡ ምስጢር የተሞላ፣ የረቀቀ፣ ፍልስፍና የተከማቸበት ማለት ነው፡፡ ባለቅኔውም ሰሚውም በሕሊና ርቀት የተራመዱ ናቸው፡፡ አንድ ተመልካች ባለቅኔውን ከበረድና ከነጎድጓድ የበለጠ ኃይል ያለው ሆኖ አግኝቶታል፡፡›› (እጓለ፣73)  
 ዶክተር ዮሐንስ አድማሱ በ2004 ዓ.ም. ‹‹ቀኝ ጌታ ዮፍታዊ ንጉሤ አጭር የሕይወቱና የጽሑፍ ታሪክ›› በተሰኘ ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ ገጽ 15 ላይ ‹‹በጥይት የተመታ ከሞት በቀር ቁስሉ ይሽራል፡፡ ጠባሳው ይጠፋል፡፡ በቅኔ የተሰደበ ሰው ግን ዘላለም ሲሰደብና ሲዘለፍ ይኖራል፡፡ በቅኔ የተመሰገነም ዓለም ዘላለዓለም ሲመሰገንና በታሪክ ዓምድ ሲወሳ ይኖራል፡፡ ምስጋናው በግልጥም በስውርም ሲሆን ስድቡና አሽሙሩ ግን በምጸትና በሥውር በኅብር ነገር መሆን አለበት፡፡›› በማለት የቅኔን ረቂቅ ሃይልና አካሄድ በአጭሩ ገልጠውታል፡፡
የአንደበት (የቃል) ጉልበትና የሕሊና ርቀት ወይም መራቀቅ የሚገኘው በዚህ በዓለም ላይ የትም በማይገኝ የኢትዮጵያ ብቻ በሆነ ከጥበብ ዘርፍ አንዱ ክፍል በሆነው በቅኔ ነው:: ቅኔ በጽሁፍ መልክ ከመቅረቡ በፊት በቃል የሚነገር፣ የሚመሰጠርና የሚቀኝ ነው፡፡
ትምህርት እውነትን፣ ደግነትን፣ ሰናይ ምግባርን የመፈጸም ጠባይን ያጎናጽፋል፡፡ ‹‹የተማረ ሰው እውቀት ያለው ሰው ለሕይወት ዋጋዎች ሁሉ በትጋት ያስባል፡፡ በእውነት ይከራከራል፡፡ ለነጻነት ይታገላል፡፡ ለትክክል ፍርድ ይሟገታል፡፡ ለውበት ይደነግጣል፡፡ ያደንቃል፡፡ ይህ ከማናቸውም ጥቅሙ የበለጠ ደስታ ያስገኝለታል፡፡›› (እጓለ፣ 93) ስለ እውቀት ስንመለከት ከቀደሙት ሊቀ ሊቃውንት መካከል በጽሁፍ መልክ እውቀትንና ጥበብን ካስተላለፉልን መካከል አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፣ ወልደ አብ ወልደ ሚካኤል፣ መምህር አካለ ወልድ፣ አራት አይና ጎሹ እና እነ አለቃ ገብረ መድህን ይጠቀሳሉ፡፡
በአፍሪካ ለ20 ዓመታት ያህል ሲያሳልፉ፣ 14 ዓመታትን በኢትዮጵያ፣ 6 ዓመታትን ደግሞ በኬንያ ያሳለፉት የኖርዌይ ተወላጁ  ሪዶልፍ ሞልቬር፣ ዶክተር፤ (Reidulfe K. Molvaer) ባዘጋጁትና በሀገራችን ትልቅ ታሪክ ባለው “Black lion; the creative Lives of modern Ethiopian Literary Giants and Pioneers” የተሰኘ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሱት 32 ታላላቅ ደራስያንና ጸሐፍት መካከል፡- ህሩይ ወልደ ስላሴ፣ ከበደ ሚካኤል፣ ሀዲስ አለማየሁ፣ ደስታ ተክለ ወልድ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ መንግስቱ ለማ፣ በአሉ ግርማ፣ ተክለ ሃዋሪያት ተክለ ማሪያም፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ማሞ ውድነህና ጸጋዬ ገብረ መድህን ይገኙበታል፡፡ የፊተኞቹም ሆኑ የኋለኞች ሊቃውንት፣ ደራሲና ጸሐፍት፣ የአብዛኛዎቹ ታሪክ እንደሚያሳየው፤ ዕድገታቸውና የዕውቀታቸው መሰረት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ የክርስትና  ትምህርት ዘይቤ (የቄስ ትምህርት) ነው፡፡
መርስዔ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ ‹‹ትዝታዬ፤ ስለራሴ የማስታውሰው›› በሚል ርዕስ ለሁለተኛ ጊዜ በ2002 በታተመው መጽሐፋቸው፣ ከገጽ 241- 45፣ ስለ ቤተ ክህነት ትምህርት እንደሚከተለው ጽፈው እናገኛለን፡፡
‹‹የቤተ ክህነት ትምህርት በአራት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል፡፡
የንባብ ትምህርት-፡ ከፊደል አንስቶ ዳዊት እስከ መድገም ድረስ የሚሰጠው ትምህርት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ተማሪዎች ህጻናት ናቸው፡፡ በዚህ ሂደት እግዚአብሔርን መፍራት፣ አባት፣እናትንና አስተማሪን መውደድ፣ ሽማግሌዎችን ማፈርና ማክበር በአጠቃላይ ግብረ ገብነትን ይማራሉ፡፡
የዜማ ትምህርት ሲሆን በሶስት ክፍሎች ይከፈላል፡፡ ሀ፣ ጾመ ድጓና ድጓ፣ ለ፣መዋሥትና ዝማሬ ሐ፣ ቅዳሴ ማለት ነው፡፡ ከትምህርት በኋላ ፈሪሃ እግዚአብሔር፣ አንገትን ሰበር አድርጎ መሄድ፣ራስን ዝቅ ማድረግና በጎ አድራጊ መሆንን በግብር ያስተምራል፡፡
የቅኔ ትምህርት -፡ አእምሮን ለማነጽና በምስጢር ለመራቀቅ፣ የግዕዝን ቋንቋ ለማወቅና በቅኔ ስልት ለመራቀቅ የሚያገለግል ነው፡፡ በዚህ ትምህርት ታሪክን፣ ፈሪሃ እግዚአብሔርንና ሠናይን ይማራሉ፡፡
የትርጓሜ ትምህርት ሲሆን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል በሐተታ በመግለጽና በምስጢሩ መራቀቅ ነው፡፡ እነርሱም አራት ጉባኤያት ተብለው ይጠራሉ፡፡
ሀ. መጽሐፍት ብሉያት ሲሆኑ እነርሱም 46 መጽሐፍት ናቸው፡፡
ለ. መጻሕፍተ ሀዲሳት ሲሆኑ 35 መጽሐፍት ናቸው፡፡
ሐ. መጻሕፍተ ሊቃውንት፡፡ እነርሱም ሃይማኖተ አበው፤ ፍትሐ ነገስት፤ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ ቄርሎስ፤ ቅዳሴያት፤የቁጥር መጻሕፍት እና አቡሻክር ናቸው፡፡
መ. መጻሕፍተ መነኮሳት ሲሆኑ እነርሱም ማር ይሳሐቅ፤ ፌልክስዮስ፤ አረጋዊ መንፈሳዊ ናቸው፡፡
የመጽሐፍት መምህራን ለደቀ መዛሙርታቸው ነገረ እግዚአብሔርን  በማስረዳትና የመጻሕፍትን ምስጢር በመመርመር ጊዜአቸውን ሁሉ ያሳልፋሉ:: እግዚአብሔርን በመፍራት ምሳሌነታቸውን ለተማሪዎቻቸው ያተርፋሉ፡፡››
ከእነዚህ ታላላቅ ሰዎቻችን መካከል ካህናትና የቤተክርስቲያናት አገልጋይ ቢሆኑም በሱ ብቻ ግን አልተወሰኑም፡፡ መንፈሳዊነታቸው ህሊናቸውን አስገድዶት ለሀገራቸው በጎ የሚሉትን ዕውቀትና ጥበብ በከፍተኛ ጥረት፣ በልፋትና በድካም በርካታ መጽሐፍትና ድርሳናት ከትበው፣ እውቀትና ጥበብ ለመጭው ትውልድ እንዲተላለፍ፣ እንዲመረመርና ለሰው ልጅ ጠቀሜታ እንዲውል አድርገዋል:: ሃይማኖተኛ መሆናቸው ስለ ዓለማዊ አካላት እንዳይመረምሩ አላገዳቸውም፡፡ ለስራቸው ረዳት ሆኖ አገለገላቸው እንጂ፡፡
‹‹ሁሉንም መርምሩ፤ የተሻለውን ያዙ›› የሚለውን ሃይማኖታዊ አስተምህሮትና በፍልስፍና ደግሞ ለማወቅ ከፈለክ ጠይቅ፤ መርምር የሚለውን ገዢ ሀሳብ ተጠቅመውታል:: ኑረውታል፡፡ ከዚህ ላይ ሰው በእውቀትና በጥበብ ደረጃ በፈጣሪ ዘንድ ከዚህ አትለፍ ተብሎ ድንበር የተሰራለት ነገር እንደሌለ እረዳለሁ ፡፡ ስለሆነም ለሀገራችን የማደግና ያለማደግ ጉዳይ ከእምነት ጋር የማያያዙ ነገር ውሃ አይቋጥርም፡፡
ሰዎች በመንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ባሕረ ሀሳብን በግዕዝ (የዘመን አቆጣጠር ስልትን) ጽፈዋል፣ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሰሯቸው ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት እንደ ዘመናዊው ህንጻ አሰራር ዘመናዊ የልኬት (የሜትር) መሳሪያ ሳይፈጠርና አንድ ግዜ ውሃ ልኬቱ ቢበላሽ እንኳን ለማስተካከል እድል የማይሰጥን ፍልፍል ህንጻዎችን ከበርና ከመስኮት ጀምሮ አጠቃላይ ልኬታቸው ትክክልና በተሳካ ሁኔታ ማነጽ ችለዋል፡፡ የአክሱምን ሃውልት ያክል ትልቅ ቶን ያለው ድንጋይ እንዴት ሊያቆሙት እንደቻሉ የአሁኑ የሳይንስ ምርምር እንኳን አልደረሰበትም::
የአስራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን የስነ ህንጻ ውጤቶች ከሆኑት መካከል የይምርሃነ ክርስቶስ ቤተ መቅደስ አንዱ ነው፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያን ውቅር አይደለም፤ ግን ከውሃ ላይ በመሰራቱ የጥንት ኢትዮጵያውያን የስነ ሕንጻ ጥበብ የተንጸባረቀበት ነው፡፡ ስለዚህ እጹብ ድንቅ ስራ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ‹‹ጠጠሮቹ እና ሌሎች›› በሚል ርዕስ በ2004 ዓ.ም ባሳተመው መጽሐፍ ገጽ 108 ላይ ‹‹በምን አይነት የጂኦሜትሪ ጥበብ የዓምዶቹን መዓዝን እና የመስኮቶቹን ቅርጽ ለመስራት እንደተጠቀሙ? ጣራውን ሲያንጹ የተጠቀሙበት የመደገፊያ እና የኮንክሪት ጥበብስ ምን ይሆን? ለመሆኑ ይህንን ሕንጻ ከማነጻቸው በፊት ዲዛይኑን በምን ሰሩት?›› በማለት አስደናቂነቱን ይጠይቃል፡፡ ጥያቄው ግን ሳይንሳዊ መልስ አያገኝም፡፡ ምክንያቱም መለኮታዊ በሆነ ኃይል የተሰራውን ስራ ሳይንሳዊ በሆነው የቤተ ሙከራ መንገድ ማረጋገጥና ማወቅ አይቻልም፡፡
እዚህ ላይ አንድ ምሳሌ ላንሳ ፡- ታዋቂው ጀርመናዊ ደራሲ ጎተ “faust” በሚል በጻፈው የትራጄዲ ድራማ ላይ ፋውስት የተባለ ዋና ገጸ ባህሪ አለ፡፡ ይህ ሰው በመላ የነፍስ መንፈሱ ኃይል እየተመራ ሰውን ለማሻሻል፣ ትክክል ለመምራት የስነ ፍጥረትን፣ የዓለምን ባህሪይ በቀጥታ ለማወቅና ከዚያም በላይ የሰውነትን ድንበር አልፎ፣ ዘላለም ነዋሪን ተጠግቶ በመንካት፣ የመለኮት ህይወት ለመቅመስ የሚጥር ነው:: ‹‹ለዚህ ጥረቱ ሰብዓዊ መንገድ የማይበቃው ስለሆነ ከመናፍስት ጋር ግንኙነት እንደፈጠረ በድራማው ጥሁፍ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ የሚያሳየው አንዳንድ የተለዩ ሰዎች ረቂቅ የሆነ እውቀትና ጥበብ ለማግኘት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ነው፡፡
‹‹የሰው ተመልካችነት ወደ ውጭ ብቻ ሳይሆን ወደ ውስጥም እንዲሆን፣ የውጭውን ዓለም ብቻ ሳይሆን የውስጡንም ዓለም ባናት በደረቱ ያለውን የሀሳብና የስሜት ዓለም ደህና አድርጎ እንዲመረምር እጣቸውን እንዲያዛውር ነው፡፡ ሰው ትክክለኛውን ዕውቀት ካገኘ የሕይወት ጎዳና ብርሃን ሆኖ ስለሚታየው በሕሊናው መሪነት ከዓመጽ ከነውር ርቆ፣በንጹህ ሰብአዊ ተምኔት መሰረት በሰላም ለመኖር ይችላል፡፡›› (እጓለ፣ 89)


Read 1603 times