Monday, 13 January 2020 00:00

የአርሾ የ47 ዓመት ጉዞ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  በአገራችን በህክምናው ላብራቶሪ ሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ላለፉት 47 ዓመታት ሲንቀሳቀስ የቆየው አርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ያለፋቸውን የ47 ዓመታት ጉዞና ወደፊት ሊያከናውናቸው ያቀዳቸውን ተግባራት አስመልክቶ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ የአርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ማኔጂንግ ዳይሬክተር
ከሆኑት ከወ/ሮ ዘላለም ፍስሃ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡


             አርሾ ቀደም ብሎ የአርመናዊው የዶ/ር አርሻቬር ቴርዚያን ንብረት ነበር፡፡ አሁን የኢትዮጵያዊያን ንብረት ነው፡፡ እስኪ ሂደቱን ይንገሩን?
እውነት ነው፤ አሁን የኢትዮጵያዊያን ንብረት ነው፡፡ ሂደቱ እንግዲህ ያው ዶ/ር አርሻቬር በሕይወት የሉም፡፡ እርሳቸው ሲያልፉ በውጭ የሚኖሩ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ልጃቸው መጥተው ተቋሙን እንዲያስተዳድሩ ተወሰነ:: ነገር ግን ልጆቹ ረጅም ጊዜያቸውን በውጭ ያሳለፉ በመሆናቸው እዚህ አገር ሆነው አርሾን ለማስተዳደር አልቻሉም፡፡ ሁሉንም ነገር መላመድ አቃታቸው፡፡ ከዚያ ሸጠው ለመሄድ ወሰኑ፡፡ እኛ ደግሞ ከዶ/ር አርሻቬር ጋር በጋራ የምንሰራው ሌላ ስራ ስለነበረን፣ የቤተሰብ ያህል ቅርርብ ነበረን፡፡ እኔና ባለቤቴ ሌላ ሁለት ሰዎች ጨምረን ገዛነው፡፡ እንዳልሽው አሁን አርሾ በሶስት ኢትዮጵያዊያን ባለቤቶች የሚመራ ተቋም ነው፡፡
እስኪ እዚህ ለመድረስ ያሳለፋችኋቸውን ውጣ ውረዶች ይንገሩን?
አርሾ በመጀመሪያ በዶ/ር አርሻቬር ሸዋ ፋርማሲ በሚባል አንድ ክፍል ነበር የተመሰረተው፡፡ ሰራተኛ ሰፈር ያለው ደግሞ ሁለተኛው ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ የዶ/ር አርሻቬር የባለቤታቸው እናት ቤት ነበር፡፡ ነገር ግን ያኔ ገና ወጣት ተጋቢዎች ስለነበሩ የባለቤታቸው እናት ቤቱን በስጦታ ሲሰጧቸው ሸዋ ፋርማሲ ከሚባለው አንድ ክፍል ስራውን ሰፋ አድርገው በአዲሱ ቤታቸው ጀመሩት ማለት ነው። ዶክተሩ ይህንን ስራ ሲጀምሩ ገንዘብ ለማግኘትና ትርፍ ለመሰብሰብ አልነበረም፡፡ ይህንን በጤና ችግር የሚሰቃይ ሕዝብ እንዴት ልርዳ ብለው ነው የጀመሩት፡፡ ይህ አስተሳሰብ በአርሾ ሜዲካል ላብራቶሪ ውስጥ እስከ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ በሰራተኛውም ውስጥ በየትኛውም ቅርንጫፍ እንደ ባህል የሚንፀባረቅ ነው፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ የነበረው አስተሳሰብ የጤናና የትምህርት ጉዳይ የመንግሥት ሥራ ነው የሚል ስለነበር ወደነዚህ ዘርፎች የሚገቡት ጥቂቶች ነበሩ፡፡ አርሾም በኃይለ ሥላሴ ዘመን ተመስርቶ ስራውን ከቀጠለ በኋላ በደርግ ጊዜ ፈተና ገጥሞት ነበር፡፡
ምን አይነት ፈተና?
በዚያን ጊዜ በመንግሥት ደረጃ ፓስተር ኢንስቲትዩት ነበር የላብራቶሪ ስራ በጠቅላላ የሚሰራው፡፡ ከፓስተር ቀጥሎ አርሾ በግል ደረጃ ተመስርቶ እየሰራ እያለ ደርግ መጣ:: ደርግ የኮሚኒዝም ርዕዮተ ዓለም አራማጅ በመሆኑ የግለሰብ ንብረቶችን የመውረስ ስራ ላይ ተጠምዶ ነበር፡፡ አርሾ እንዴት ሳይወረስ አለፈ ለሚለው ጠለቅ ያለ መረጃ የለኝም። ነገር ግን እንደሚመስለኝ ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ ይመስለኛል። ሆኖም ዛሬ ይወረሳል፤ ነገ ይወረሳል የሚል ጭንቀትና ፈተና አልፏል:: ይሄ ደግሞ ስራን ተረጋግቶ ለመስራት ፈተና ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህ ተቋም ብዙ ሕዝብ ይጠቀም እንደነበርና ዶ/ር አርሻቬር አንዳንድ ለሕብረተሰቡ የሚጠቅሙ አስገራሚ ሥራዎችን ይሰሩ እንደነበር እሰማለሁ፡፡ ለምሳሌ ጡረተኞች ለአገልግሎት መጥተው የሚከፍሉት ሲያጡ ወይም አርጅተውና ተጎሳቁለው ሲመለከቱ በጣም ይረበሹና ስሜታቸው ይነካ ነበር፡፡ ከዚያ አንድ ቀን ‹‹በቃ ለተጧሪዎች በሙሉ ነፃ የሆነ ሕክምና እሰጣለሁ›› አሉ፡፡ ይሄ በስሜታዊነት የወሰኑት ውሳኔ ነው፡፡ በወቅቱ ሁሉንም ጡረተኞች በነፃ ማከም ይቻል አይቻል እንደሆነ ያጠኑት ነገር አልነበረም፡፡ እናም በቀጣዩ ቀን ፒያሳ በጡረተኞች መጥለቅለቁንና ማስተናገድ ከሚችሉት በላይ እንደሆነባቸው ሰምቻለሁ፡፡ ዶ/ር አርሻቬር እንደዚህ አይነት ርህራሄ ያላቸውና የሰው ልጅ ክቡር መሆኑን በመገንዘብ ይሰሩ ስለነበር ምናልባት አርሾ የሚሰጠው አገልግሎት መንግሥትንም የሚያግዝ መሆኑ ከግምት ውስጥ ገብቶ ይሆናል ሳይወረስ የቀረው፡፡ ያኔ ከዶ/ር አርሻቬር ጋር ይሰሩ የነበሩና አሁንም በስራው የቀጠሉ ባልደረቦች እነዚህንና መሰል ታሪኮችን ይነግሩናል፡፡
ሌላው ዶ/ር አርቫቬርን በሌላ ሥራ አውቃቸው ነበር ብዬሻለሁ፤ ታታሪና የማይደክማቸው ናቸው፡፡ ስራ የሚገቡት ሌሊት 11፡30 ነው፡፡ ገብተው መሳሪያዎቹን አፀዳድተው ተዘጋጅተው 12፡00 ላይ ደንበኞች መስተናገድ ይጀምራሉ፡፡ ያ ባህል አሁንም  በአርሾ ውስጥ አለ፡፡ እኛ እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም ድርጅቱን ከገዛነው ጀምሮ ላለፉት 16 ዓመታት የሥራ ባህሉን ጠብቀን ሕዝብን በታማኝነት፣ በቅንነትና በትህትና ማገልገላችንን ቀጥለናል፡፡
የአገራችን የጤና ፖሊሲ መከላከልን መሰረት ያደረገ ቢሆንም የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ ሕዝቡ በጤና እጦትና ሕክምና ፍለጋ በየሆስፒታሉ ደጅ ሲንከራተት ይታያል፡፡ ከየክልሉ እየመጣ በጎዳና ላይ የሚወድቀውና ለልመና የሚዳረገው የሰው ብዛት ብዙ ነው ይባላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአርሾ አበርክቶ ምን ያህል ነው? እንዴትስ ይገለጻል?
ያነሳሽው ሀሳብ ትክክል ነው፡፡ የአገራችን የሕክምና እድገት ደረጃ የተጠበቀውን ያህል ነው ወይ ስንል መልሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል፡፡ በጣም ገና ነን፡፡ እጅግ በጣም ገና ነን:: በዓለም የጤና ድርጅት ቻርት ላይ ስንመለከት እንኳን፤ የኢትዮጵያ የጤና እንቅስቃሴ ውጤት ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት አማካይ ውጤት በታች ነው፡፡ ይሄ የሚያሳየው የጤና ዘርፉ ምን ያህል ገና እንደሆነ ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ እነዛ ጥረቶች ግን ካለን የሕዝብ ብዛት አንፃር በጣም ገና የሚቀር ነው፡፡
ወደ አርሾ ስንመጣ ገና ‹‹አርሾ›› ሲባል ወደ አዕምሮ የሚመጣው ላብራቶሪ የሚለው ነገር መሆኑ እሙን ነው፡፡ ምንም እንኳን ብዙው እንቅስቃሴያችን በአዲስ አበባና በዙሪያው ቢሆንም በመላው ኢትዮጵያ በህብረት ስለምንሰራ በደንብ የሚታወቅ ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ጅግጅጋ ሄደን ስንጠይቃቸው በጅግጅጋም ይታወቃል፤ አብረን እንስራ ብለው ነው የጠየቁን:: እንዳልኩሽ በአራቱም አቅጣጫ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ከሚሰሩ የጤና ድርጅቶች ጋር በጋራ ስለምንሰራ በደንብ እንታወቃለን፡፡ በሁሉም አካባቢ ላሉት የመክፈል አቅማቸው እንዳይፈትናቸውና እንዳይጨነቁ የብድር አገልግሎት እናመቻችላቸዋለን፡፡ ሌላውና ዋናው የምንወደድበት፣ የምንታወቅበትና ለ47 ዓመታት የተጓዝንበት ነገር የምንሰጠው የአገልግሎት ጥራት ነው፡፡ ሌላው የተደራሽነት መጠናችን ነው የምንወደድበት ምክንያት፡፡ በተቻለ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እያጠናን የምርመራዎቹን አይነቶች እያሰፋንና እየጨመርን ነው የሄድነው፡፡ ከሦስት ዓመታት ወዲህ የጨመርነው ትልቁ ነገር ደግሞ ለምንድነው እዚህ አገር ብቻ የሚሰራውን የምንሰራው? ሰውስ የአውሮፕላን ትኬት ከፍሎ የሆቴልና የምግብ ወጪ አውጥቶ ለምን ለምርመራ ከአገር ውጭ ይጓዛል? በሚል ከተለያዩ የውጭ አገር ድርጅቶች ጋር ተነጋግረን፤ በተለይ በዱባይ ካለው ድርጅት ጋር ተነጋግረን የማህበረሰባችን የመክፈል አቅሙ ይሄ ነው ብለን አሳምነን በእኛ በኩል ናሙናዎች እየተሰበሰቡ እየሄዱ እንዲሰሩ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል፡፡ ይሄ ሰውን ከመንከራተትና ከብዙ ወጪ ታድጓል፡፡ ሰው እኛ ጋ መጥቶ ናሙና መስጠት ብቻ ነው የሚጠበቅበት፡፡
በሌላ በኩል ከፍርድ ቤቶች በኩል በጣም ጥያቄ እየሆነ የመጣው የደም ትስስር ምርመራ (DNA) አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ታዋቂና ምስጉን የሆነው አለም አቀፍ ላብራቶሪ ማን ነው? የሚለውን አጥንተን እንግሊዝ ውስጥ ያለ አንድ ላብራቶሪ ጋር ተነጋግረንና ስምምነት ፈጽመን እውቅና የሰጠውን አካል ሁሉ አረጋግጠን አብረን መስራት ጀምረናል፡፡ ጀርመን አገር  ‹‹ባዮሴንቲያ›› ከሚባል ታዋቂ ላብራቶሪ ጋርም ስምምነት ፈጽመን እየሰራን እንገኛለን፡፡ የእኛ አገር ማህበረሰብ ዋና ጥያቄ የወጪ ጉዳይ በመሆኑ በተቻለ መጠን ወጪውን እያወዳደርን ለሕዝቡ በጣም የማይጎዳውን እየፈለግን እየሰራን ነው፡፡
የደም ትስስር ምርመራዎች (DNA) እዚህ አገር የማይሰሩት ለምንድን ነው?
ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፡፡ በውጭ የሚሰሩት ምርመራዎች እዚህ አገር መሰራት ስለማይችሉ አይደለም፡፡ ለምሳሌ እኛ ያሉን መሳሪያዎች አብዛኛውን ምርመራ በደንብ መስራት ይችላሉ:: ነገር ግን እነዚህን ምርመራዎች ለመስራት ያንን ምርመራ የሚፈልጉ ናሙናዎች መምጣት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ከምርመራ መሳሪያው በተጨማሪ ለምርመራው የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብአቶች አሉ፡፡ እነዚህ ግብአቶች ተገዝተው ይመጡና የሚመረመረው ናሙና መጠን አነስተኛ ከሆነ እኛ ኪሳራ ውስጥ እንገባለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ግብአት ተገዝቶ ለ100 ናሙናዎች የሚያገለግል ከሆነ፣ የሚመረመረው ናሙና መጠን የግድ መቶ ይሙላ ባይባል እንኳን ከ50 በመቶ በላይ መሆን አለበት፡፡ ያ ግብአት ለሶስትና ለአራት ናሙና ተብሎ ከተከፈ በኋላ 96 ወይም 95 ያህሉ ሌላ ናሙና እስኪመጣ መቆየት አይችል ይሆናል፤ ቀኑ ሊያልፍበት ይችላል፣ ወይም እንደተከፈተ ስራ ላይ መዋል ሊኖርበት ይችላል፡፡ ለአራት ወይም ለአምስት ናሙና ተብሎ ለመቶ ናሙና የሚያገለግለው ግብአት ሲከፈት፣ 95ቱ ከጥቅም ውጭ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ኪሳራ ላይ ነው የሚጥለን እንጂ አብዛኛው ዱባይ የሚሰሩበት መሳሪያ እኛም ጋ አለ፡፡ የተመርማሪው ብዛት እየጨመረ ሲሄድ ግን ወደ ውጭ የሚሄዱትን ናሙናዎች እዚሁ አገር መስራት የሚያስችል አቅም አለን፡፡
የጀርምና ባክቴሪያ ማበልፀጊያ ዘመናዊ ላብራቶሪ እንዳላችሁ በጉብኝታችን ተመልክተናል፡፡ እስኪ ስለዚህ ላብ ይንገሩን?
አሁን አንቺ የጠቀስሽው ላብ በማይክሮ ባዮሎጂ ላይ የሚሰራውን ነው፡፡ የተለያዩ ባክቴሪያዎችንና ፈንገሶችን እዚህ በማሳደግ ምን አይነት ቫክቴሪያ ነው? ምንስ አይነት ፈንገስ ነው? የሚለውን በመለየት፣ ምን አይነት መድሃኒትስ ነው የሚያክመው? የሚለው የሚሰራበት ዘመናዊ ላብ አለን፡፡ በእርግጥ ብዙ ሰው አይጠቀምበትም፤ ነገር ግን ኢንቨስትመንት ወጥቶበታል፡፡ በአገራችን ‹‹ድራግ ሬዚስታንስ›› (መድሃኒትን የሚላመዱ) ባክቴሪያዎች ችግር ሆነዋል። እናም የትኛው ባክቴሪያ የትኛውን መድሃኒት ነው የሚላመደው የሚለውን ለማጥናትና ድራግ ሬዚስታንስን ለማስቀረት ነበር ብዙ ኢንቨስትመንት አውጥተን ላቡን ያቋቋምነው፡፡ እንግዲህ ላቡን ብዙ ማስተዋወቅ ሊያስፈልገን ይችላል፡፡ እኛ ክፍሉን ለማበልፀግ ፓክ ከሚባል ድርጅት ጋር ተነጋግረንና ኤክስፐርቶች መጥተው የክፍተት ትንተና (ጋፕ አናሊስስ) እየሰሩ ነው፡፡ ምንድነው የጎደለው? ያለው ችግርስ ምንድነው? ጥራቱስ በምን ደረጃ ይገኛል? የሚለውን እየሰሩ ነው፡፡ ይህ ካለቀ በኋላ ላቡን እውቅና ለማሰጠት ከፍተኛ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ከዚያ ውጭ በዚሁ ውስጥ የተለያዩ ምርመራዎች ይሰራሉ፡፡ ቫይረስ ምርመራዎች፣ የሰውነት ክፍል ምርመራዎች ለምሳሌ የልብ፣ የኩላሊት፣ የደም መርጋት፣ የኢንፌክሽን፣ የካንሰር፣ የታይሮይድና ሌሎችም ምርመራዎች በስፋት ይካሄዳሉ፡፡ ከጥራት ቀጥሎ በአርሾ ውስጥ ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንዱ የምርመራዎቹን አይነት ማብዛት ነው፡፡ አይነታቸውን ማለትም ሬዲየሳቸውን ማብዛት ሲሆን ሁለተኛው የምርመራ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጨመረ፣ የትኛውንም በውጭ የሚሰራ ምርመራ አገር ውስጥ የመስራት ከፍተኛ አቅም፣ ዘመናዊ መሳሪያና ብቁ ባለሙያዎች አሉን። እንደዚህም ሆኖ ካለን አቅም 34 በመቶውን ብቻ ነው የምንጠቀመው፡፡ ለምን የተመርማሪው ብዛትና የእኛ ዝግጅት አይገናኝም፡፡ ለምሳሌ ክሊኒካል ኬምስትሪን ብንወስድ፣ ኩላሊት፣ ልብና ሌሎች የአካል ክፍሎችን የሚመረምሩ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ አራት መሳሪያዎች አሉን፡፡ አንዱ መሳሪያ 800 አይነት ምርመራዎች በሰዓት መስራት የሚችል ነው፡፡ ይህንን አቅም እንዴት ነው መጠቀም ያለብን? ምን አይነት ናሙናዎችስ ቢመጡ ነው የምንጠቀምበት የሚለው ነው ጥያቄው፡፡ በዚያው ደረጃ ደሞ በኢትዮጵያ ብቃት ማረጋገጫ ድርጅት፤ የብቃት ማረጋገጫ ያገኙ ሀኪሞች አሉን፡፡ በነዚህ መሳሪያዎች ከሚሰሩ ናሙናዎች የተወሰኑት የብቃት ማረጋገጫ ያገኘንባቸው ናቸው።  ተጠቃሚ ከበዛ ሁሉንም የብቃት ማረጋገጫ ባለቤት ማድረግ እንችላለን።
አዲስ አበባ ውስጥና ከአዲስ አበባ ውጭ ምን ያህል ቅርንጫፎች አሏችሁ?
አዲስ አበባ ውስጥ የመጀመሪያው የሰራተኛ ሰፈሩ አለ፣ ካቴድራል፣ መገናኛ፣ (ዋናው መስሪያ ቤት ደግሞመስቀል ፍላወር) ጨው በረንዳ፣ ጉለሌ፣ ሳሪስ አሉን፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ በህብረት ደሴ፣ መቀሌ፣ በራሳችን ቡድን የምናስተዳድረው ጅግጅጋ ላይ አለን፡፡ ኦሮሚያ ውስጥም በትብብር ከሁለት ክሊኒኮች ጋር እንሰራለን፡፡ ከ80 በላይ እንደውም በዚህ ዓመት ወደ 100 ከፍ ብለዋል - ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ጋር አብረን እንሰራለን፡፡ እንዴት ካልሽኝ ወይ እነሱ ናሙናዎቻቸውን ይልካሉ ወይም እኛ ሄደን እንሰበስባለን፡፡ ክፍያዎችን በወር ውስጥ ነው የምንፈጽመው፡፡ ጥራቱን ጠብቀው እንዲሰሩ በጥሩ ሁኔታ ነው የምናበረታታው። የእናንተ አበርክቶ ምንድነው ላልሽው ጥያቄ፣ ይሄም ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ለምን? የሕክምና 60 በመቶው ምርመራ የሚካሄደው በላብራቶሪ ነው፡፡ የላብራቶሪ ምርመራ ወደቀ ማለት ሕክምናው ችግር ላይ ወድቋል ማለት ነው፡፡ ወይም የሚሰጠው ሕክምና ከደረጃ በታች ነው ማለት ነው፡፡ የላብራቶሪ ጥራት እንዲጠበቅ ክሊኒኮችንም ሆስፒታሎችንም ከእኛ ጋር እንዲሰሩ እናበረታታለን፡፡ ምክንያቱም በሕክምና ላይ ጥራትን ማምጣት የሚቻለው ጥራት ያለው ስራ ላብራቶሪ ላይ ሲሰራ ነው:: ለምሳሌ እኛ የምንሰራው ስራ ትክክል ነው ወይ? ጥራት ማስጠበቅ ችለናል ወይ ለሚለው ስራችንን ውጭ አገር ባሉ ላብራቶሪዎች እናስመረምራለን:: በሶስተኛ ወገን ማለት ነው፡፡ እኛም በራሳችን በየቀኑ መሳሪያዎችንን ካሊበር እናደርጋለን፤ የጥራት ቁጥጥር ይሰራል። ኳሊቲ ኮንትሮል ካሊብሬሽን የምንላቸው ውድ ነገሮች ናቸው፡። ለመቶ ምርመራ መስራትና ለ10 ምርመራ መስራት ይለያያል፡። ቁጥሩ እየጨመረ ሲመጣ ዋጋው እየጨመረ  ይመጣል፡፡ በዚህ ጥራትን እናስጠብቃለን፡፡ እኛም ከእኛ ጋር የሚሰሩትም ተገልጋዩም ተጠቃሚ እንሆናለን ማለት ነው፡፡
አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ አንገብጋቢ ምርመራ የሚያስፈልጋቸው ህመሞች ምንድን ናቸው?
እኔ አንገብጋቢ ናቸው የምላቸውና ቅድሚያ ቢያገኙ ደስ የሚለኝ ለምሳሌ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከማድረግ በፊትና በኋላ የሚደረጉ የጤና ክትትሎች አሉ እነሱን ቅድሚያ ብንሰጣቸው ደስ ይለኛል፡፡
ከንቅላ ተከላ በኋላ ብዙ ደንበኞች አሉ - ክትትል የሚያደርጉ፤ ነገር ግን ውስን ክትትል ነው የምናደርግላቸው ሁሉንም አይነት ክትትል ብናደርግላቸውና በዚህ ዘርፍ ብናግዝ ደስ ይለናል፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች ጤና ላይ በጣም መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን እኛ በስፋት እየሰራን ያለነው በሴቶች ጤና ላይ እና በካንሰር ላይ ነው፡፡ የአገራችንን ዴሞግራፊ ስንመለከት 67 በመቶው ከ40 ዓመት በታች ወይም አምራች ሀይል የምንለው ነው፡፡ ስለዚህ አምራች ዜጋውን ጤናማ ለማድረግ ቅድመ ምርመራዎች በስፋት መሰራት አለባቸው:: ይህ ቅድመ ምርመራ በስፋት መሰራት ያለበት በሴቶች ላይ ነው፡፡ ሴቶች፣ እናቶቻችን እህቶቻችን ናቸው፤ ከተለያየ ህመም ሊጠበቁ ይገባል፡፡ በተለይ በካንሰርና ከተላላፊ በሽታዎች ጋር በተያያዘ አሁን ላይ የምንሰማቸው በርካታ ድንገተኛ ህመሞች ቅድመ ምርመራ ካለማድረግ  የሚመጡ ናቸው፡፡ መንግሥትም ሆነ የግሉ የጤና ዘርፍ በትብብር፤ ይህ አምራች ዜጋ ወጣት ቅድመ ምርመራን ባህል እንዲያደርግ ማስተማር አለብን፡፡ ወጣት ሴቶች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የጡትና የማህጸን ቅድመ ካንሰር ምርመራ ማድረግ የግድ አለባቸው፡፡ ይህ የመጀመሪያ የአርሾ ዓላማ ነው፤ ቀጥሎ የዲኤንኤ ምርመራው ነው፡፡
አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት በሚባለው ቦታ በጣም ትልቅ ዘመናዊና ሪፈራል የሆነ ሜዲካል ላብራቶሪ ልትከፍቱ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ በዚህ ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡኝ?
ይህንን ላብራቶሪ መክፈት ከነበረብን በ6 ወራት ያህል ዘግይተናል፡፡
የመዘግየታችሁ ምክንያት ምንድን ነው?
ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በእኛው ውስጥ ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ከእኛ ውጭ ያሉ ችግሮች ናቸው:: አንዱ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ አለማግኘታችን ነው፡፡ አዲስ ኢንቨስትመንት እንደመሆኑ መጠን የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ተብለው የተፈቀዱልንን ነገሮች ለማግኘት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ምላሽ አላገኙም፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አሳንሰር ለመግጠም የጠየቅነው ከ40 ሺህ ዶላር በታች አልተፈቀደልንም፡፡
ሁለት ዓመት ተኩል ሆኖናል ምላሽ ሳናገኝ። ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ መሳሪያዎችም አሉ፡፡ እነዚህም መሳሪያዎች የግድ መምጣት አለባቸው፡፡ እኛ ይህንን ላብራቶሪ ባሰብነው ደረጃ አቅማችንን ሰብሰብ አድርገን በጥሩ ሁኔታ መጀመር ነው የምንፈልገው፡፡ በእርግጥ የገቡና ስቶራችን ውስጥ የተቀመጡ መሳሪያዎች አሉ፡፡ ሌሎቹን አሟልተን ሥራችንን እስክንጀምር ተጨማሪ ጊዜ ይወስድብናል፡፡ ውጭ ያለው ችግር የአገርም ችግር እንደመሆኑ አንዳንዱን እንረዳዋለን፡፡ የውጭ ምንዛሪው ጉዳይ የአገር ችግር ስለሆነ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡ እኛ የጤና ዘርፍ እንደመሆናችን፡፡ ቅድሚያ ይሰጠናል ብለን እናምናለን፡፡ በአጠቃላይ ግን ከ6 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ስራ እንጀምራለን ብለን አቅደናል፡፡
በአጠቃላይ ምን ያህል ሰራተኞችን እያስተዳደራችሁ ነው?
207 ሰራተኞች አብረውን ይሰራሉ፡፡ አዲሱ ሲከፈት ደግሞ ይህንኑ ያህል ሰራተኛ ልንጨምር እንችላለን፤ ምክንያቱም በአዲሱ ማዕከል ከላብራቶሪ በተጨማሪ ሌላም ሰፋ ያለ አገልግሎት የመስጠት አላማ አለን፡፡
ሰሞኑን በግል ጤና ተቋማት አሰሪዎች ማኅበር በተዘጋጀው የጤና ኤግዚቢሽን ላይ ተሳትፋችሁ፡፡ ሽልማትም ወስዳችኋል፡፡ እስኪ ስለ ሽልማቱም ይንገሩን?
እውነት ለመናገር አርሾ የሕዝብ ንብረት ነው፡፡ ሕዝብን ለማገልገል የተመሰረተ ነው፡፡ በመሆኑም ማህበራዊ ሀላፊነታችንን ለመወጣት በርካታ ሥራዎች እንሰራለን፡፡ ለረጅም አመታት በቋሚነት ለሕጻናትና አረጋዊያን ድጋፍ ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች ጥያቄ በቀረበ ጊዜ ሁሉ፣ የሕብረተሰብ አቀፍ ልማት ላይ  እንሳተፋለን፡፡ ለተለያዩ መንግሥታዊ ላልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች በቋሚነት ድጋፍ እናደርጋለን፡፡ በየዓመቱ ጤናን አስመልክቶ በሚከበሩ ቀናት ቁጥሩ እጅግ በርካታ ለሆነ ማህበረሰብ ነፃ ምርመራ በማድረግ እንታወቃለን:: ከዚህም በተጨማሪ ያልዘረዘርኳቸውን አገልግሎቶች እንሰጣለን፡፡
በቅርቡ በተካሄደው የጤና ኤግዚቢሽን ላይ 350 ሺህ የሚጠጋ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎት በነፃ ሰጥተናል፡፡ በጣም የተደሰትንበት አገልግሎት ነበር፡፡ በዚህም ማህበሩ በላብራቶሪ ዘርፍ ተሸላሚ አድርጎናል:: እውነት ለመናገር ከአንገት በላይም፣ በጠቅላላ ሆስፒታልነትም የተሳተፉት በሙሉ ሽልማትና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ 30 ሺህ ሰው ለማከም ታቅዶ 42 ሺህ ሰው ነው አገልግሎት ያገኘው:: ይሄ በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ ማህበሩም ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ እኛም የበኩላችንን አድርገናል፡፡ በቀጣይ በተሻለ አቅምና አገልግሎት እንሳተፋለን፡፡
የኢትዮጵያ የሕክምና ደረጃ የት ደርሶ ማየት ይፈልጋሉ?
እኔ ከምንም በላይ ሰዎች መታከም ፈልገው በአቅም ማጣት ሕክምና የማያጡበት ዘመን መጥቶ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ የኢኮኖሚ ጉዳይ ጭንቀት መሆኑ ቀርቶ ሁሉም የአገሬ ሕዝብ በጤና መድህን ታቅፎ ያለ ችግርና ያለ እንግልት ታክሞ የሚድንበት ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት እሻለሁ፡፡ ይህ እንዲሆን አርሾ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ይቀጥላል፡፡   

Read 8602 times