Sunday, 12 January 2020 00:00

‹‹በፓርቲነት መቋቋማችን ትግላችንን ያጠናክረዋል››

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

   - በዘንድሮው ምርጫ ለመወዳደር ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነን
                  - በሜዳ ላይ ነው የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ያካሄድነው
                  - በእኛ አካባቢ ለውጡ ገና ሽታውም አልደረሰም

              የቁጫ ሕዝብ የረዥም ጊዜያት የማንነት ጥያቄ ሲያቀርብና በዚህም ጥያቄ ብዙ መስዋዕትነት ሲከፍል መቆየቱን አዲስ የተመሰረተው የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁህዴፓ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሀብታሙ ሃይለ ጊዮርጊስ ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ጥያቄው በክልሉ ብሄረሰቦች ም/ቤትም ሆነ በፌደሬሽን ምክር ቤት ምላሽ አለማግኘቱን ይገልጻሉ፡፡ በለውጡ ማግስት ጥያቄያችን ምላሽ ያገኛል የሚል ተስፋ ሰንቀን ነበር፤ ነገር ግን ጭራሽ የተዳፈነ ይመስላል የሚሉት አቶ ሃብታሙ፤ በቁጫ ሕዝብ ስም ፓርቲ ማቋቋማቸው ትግላቸውን እንደሚያጠናክረው ያምናሉ፡፡ የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ቦርድ መስፈርትን አሟልቶ መመዝገቡንና ከምርጫ ቦርድ የምስክር ወረቀት አግኝቶ እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል፡፡ ስለ ፓርቲው አመሰራረት፣ የፓርቲው መመስረት ስላለው ፋይዳ እንዲሁም  ስለወደፊት ዕቅዱና ስለቀጣዩ ትግሉ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከቁህዴፓ ም/ፕሬዚዳንት ከአቶ ሀብታሙ ሀይለ ጊዮርጊስ ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጋለች፡፡ ባለፈው እሁድ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤውን ለማካሄድ የገጠመውን ችግር ነግረዋታል፡፡ እነሆ፡-


           እስኪ ስለ ፓርቲያችሁ አመሰራረት ይንገሩን?
የቁጫ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቁህዴፓ) በቅርቡ ነው የተመሰረተው፡፡ የምስክር ወረቀት ከምርጫ ቦርድ ያገኘውም ታህሳስ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ነው፡፡ ምንም እንኳ የምስክር ወረቀቱ የተሰጠን በቅርቡ ቢሆንም፣ ከዚያ በፊት ምርጫ ቦርድ በሰጠን ፈቃድ መሰረት ለወራት ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ እንግዲህ ፓርቲውን ስንመሰርት እንዲሁ ፓርቲ ተመሰረተ ለማለት ብቻ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እናንተም እንደምታውቁት፣ በቁጫ ሕዝብ ላይ ብዙ ችግርና መከራ ሲደርስ ቆይቷል፡፡
በተለይ ቀደም ሲል ቁጫ ወረዳ ብቻ ተብሎ ሲተዳደር የነበረውና በቅርቡ ለሶስት የተከፈለው ማህበረሰብም ማለትም ቁጫ ወረዳ፣ ቁጫ አልፋ ወረዳና ሰላም በር ከተማ አስተዳደር ተብሎ በተከፈለው አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ፤ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር የማንነት እውቅና ጥያቄ አቅርቦ፣ ከዚህ ጥያቄ ጋር በተያያዘ የብዙ ሰው ነፍስ ጠፍቷል፣ ብዙዎች በግፍ ታስረዋል፣ በርካቶችም ከመኖሪያ ቀያቸውና ስራቸው ተባረዋል፡፡
ብዙ መከራዎችም ደርሰዋል፡፡ ይህ ሁሉ መስዋዕትነትም ተከፍሎ የሕዝቡ የማንነት ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ይህ በአዲስ አድማስ ጋዜጣም በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡ በፌደራልም በክልል ደረጃም ያሉት ምክር ቤቶች ለጥያቄያችን አንድም ምላሽ አልሰጡንም፡፡
ፓርቲ ማቋቋማችሁ ለዚህ ትግላችሁ ምን ያህል ያግዛችኋል? እስከ ዛሬስ ፓርቲ ያላቋቋማችሁት ለምንድን ነው?
እስከ ዛሬ ፓርቲ ያላቋቋምነው የሕዝቡ ጥያቄ ፓርቲ የማቋቋም ሳይሆን የማንነት ጥያቄ እውቅና ማግኘት ስለነበር ነው፡፡ የማንነት ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት የግድ ፓርቲ ማቋቋም ያስፈልጋል ብለንም አላመንም ነበር፡፡ በመደበኛው የሕግ አካሄድ ማለትም በአቤቱታ፣ ደብዳቤ በመለዋወጥና በሕዝቡ ውክልና ባገኙ የኮሚቴ አባላት ምላሽ እናገኛለን የሚል እምነት ነበረን፡፡ ግን አልሆነም፡፡ አሁን ፓርቲ ሲቋቋም ሕዝቡ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተወካይ ይኖረዋል፤ በፌደራል፣ በክልልም ሆነ በወረዳ ደረጃም ቢሆን ድምፁ የሚሰማበት የፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ በመሆኑ በዚያ መልኩ ተፅዕኖ ለመፍጠርና የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ነው ያቋቋምነው::
ከዚህ አንፃር የፓርቲው መቋቋም ትግሉን በእጅጉ ያግዘዋል፡፡ የሕዝቡ ጥያቄ ቢመለስ እንኳን ከዚያ ባለፈም ፓርቲው ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ አካባቢ ለሚሰራ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አስተዋጽኦ ይኖረዋል:: ለሚፈጠሩ ችግሮችም የመፍትሄ አካል ለመሆን ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ መንቀሳቀሱ ፋይዳ አለው ብለን አምነንበታል፡፡
በነገራችን ላይ እንደ ቁጫ ሕዝብ፣ ፓርቲ አናቋቁም እንጂ ከዚህ ቀደም ከኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጋር ብዙዎቻችን የቁጫ ተወላጆች ስንታገል ቆይተናል፡፡ በ97 ምርጫም ኢዴፓ ላስመዘገበው ውጤት የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገናል ማለት ነው።
በፊት ቁጫ ወረዳ ይባል የነበረው አሁን ወደ ሦስት መከፈሉ ጠቃሜታው ምንድን ነው?
ጥቅሙ ከፍተኛ ነው፡፡ ለምን ካልሽኝ፤ ቁጫ ወረዳ ብቻ ተብሎ በሚተዳደርበት ወቅት ጥሩ አስተዳደር አልነበረም፡፡ እጅግ ብዙ ቀበሌዎችንና ከተማን ይዞ በአንድ ወረዳ ብቻ መተዳደሩ አግባብ አልነበረም፡፡ ብዙ አስተዳደራዊ በደሎች ሲደርሱ የቆዩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የቁጫ ሕዝብ ብዛት ከሩብ ሚሊዮን በላይ ነው፡፡ በግምት ወደ 300 ሺህ ይጠጋል፡፡
ይህንን ሁሉ ሕዝብ በአንድ ወረዳ አጭቆ ማስተዳደር ከባድ ነው፡፡ የሕዝቡ ብዛት ብቻም ሳይሆን መልክአ ምድራዊ አቀማመጡም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ተራራማ፣ ሸለቋማና የተራራቁ በተለይም ከቀድሞ የወረዳው ማዕከል ሰላም በር ከተማ እጅግ የራቀና እስከ መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ቀበሌዎች ሁሉ አሉ፡፡
በዚህ ምክንያት ፍትህ የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው፡፡ በዚያ ላይ አካባቢው አለማም፣ መንገዶች አልተሰሩም፡፡ ስለዚህ ከሩቅ ቦታ እየመጡ ፍትህ፣ ዳኝነት፣ የጤና አገልግሎትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከተማም ራሱን ማስተዳደር ስላለበት በሶስት መከፈሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡
የቁጫ ሕዝብ የማንነት ጥያቄ ማንሳት የጀመረው መቼ ነው?
ጥያቄው በሕዝብ ዘንድ መነሳት ከጀመረ ረጅም አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ነገር ግን በጽሑፍና የሕገ መንግስት አንቀጾች ተጠቅሰው፣ በተደራጀ መልኩ መቅረብ የጀመረው ከ2005 ጥር ወር ወዲህ ነው፡፡ አሁን ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሰባት አመታት ተቆጥረዋል ማለት ነው፡፡  
በሰባት ዓመት ጊዜ ውስጥ ብዙ ችግሮች፣ ብዙ መከራዎች ማለፋቸውን ቀደም ሲል አንስቼልሻለሁ፡፡ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ምላሽ አልሰጡም፡፡ ከዚህ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ብዙ ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ ጥያቄው አለመመለሱ ብቻ ሳይሆን ከዚሁ ጋር የተያያዙ አዋጆችና ደንቦችም ተጥሰዋል፡፡
ለምሳሌ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር የወጣው አዋጅ 251/1993 ምን ይላል? የማንነት ጥያቄ ለብሔረሰቦች ምክር ቤት ቀርቦ በሁለት ዓመት ውስጥ ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡  ይህ ካልሆነ ወደ ፌደራሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይቀርብና ፌደሬሽን ምክር ቤትም በሁለት ዓመት ውስጥ መልስ መስጠት አለበት ይላል:: ሁለቱም በአዋጁ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ምላሽ ካልሰጡ፣ እንደ አማራጭ የተቀመጠ ሌላ የሕግ አንቀፅ የለም፡፡ የቁጫ ሕዝብ ጥያቄ ግን ይሄው ሰባት ዓመታት ሳይመለስ እንደተንጠለጠለ ይገኛል፡፡ ይሄ ማለት በአዋጅ የተቀመጠው ሕግ ተጥሷል፡፡ ይህን ለማስፈጸም የተቀመጡ አካላትም፣ ይህንን በማስፈጸም ረገድ ያደረጉት ነገር ስለሌለ ሕግ ጥሰዋል፤ ሊጠየቁ ይገባል እንላለን፡፡
አሁን እንዲያውም ጭራሽ ተቀዛቅዟል፡፡ ይሄ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽን ሲቋቋም፣ ምክር ቤቶቹ በኮሚሽኑ በኩል ይፈፀማል የሚል ሀሳብ የያዙ ይመስለኛል፡፡ በመደበኛ ጉባኤዎች ሁሉ ማንሳት ትተዋል፤ ወይ አይሆንም አይባልም ወይ ሌላ አማራጭ አይታይም፤ በደፈናው የደበዘዘ ነገር ነው ያለው፡፡ ኮሚሽኑም ወደ እኛ አካባቢ አባላቱን ልኮ አንዳንድ ሙከራ ሲያደርግም እያየን አይደለም፡፡
ለውጡ ከመጣ በኋላ ጥያቄያችሁ ምላሽ የማግኘት ተስፋው የለመለመ እንደሆነ አጫውተውኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከምን ተነስተው ነበር እንደዚያ ያሉኝ?
ትክክል ነሽ፡፡ ለውጡ እንደመጣ አካባቢ በጣም ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ ለምን ቢባል፣ ያለው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የተሻለ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ምንም እንኳን በተለያዩ አካባቢዎች የፀጥታ ችግሮች ተከስተው የነበረ ቢሆንም፣ ዕድሎች ተገኝተው ተስፋ ፈንጥቆ ነበር፡፡ ኮሚሽኑም የተቋቋመው ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መምጣት ወዲህ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ጉዳዩ ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው አምነን ነበር፡፡ ነገር ግን መሬት ላይ ያለውን ነገር ስንመለከት፣ ስትራክቸር ተቋቋመ እንጂ ስለ ጉዳዩ ሲነሳም አልሰማንም:: ይሄ ነው የሚባል ነገር የለም፡፡ በእርግጥ በይፋ መግለጫ ሲሰጡ ሰምተናል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምም ሆኑ የክልሉ ብሄረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ለማ ገዝሙም አራት ማህበረሰቦችን ጠቅሰው፡- ወለኔ፣ ዶርዜ ቁጫና ጌዞ በትክክልና በተሟላ ሁኔታ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፤ እንዲያውም እስካሁን ምላሽ ባለመስጠታችን ጥፋተኞች ነን፤ ጉዳዩ ታይቶ በአፋጣኝ ምላሽ መሰጠት አለበት ብለዋል፡፡
በተለይ የደቡብ ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት አፈ ጉባኤው፡፡ ይህንን ተስፋ በማድረግ የብሄረሰቦቹ ተወካይ ኮሚቴ አባላት ቀርበው ሲጠይቁ፤ “አሁን ክልሉን እያስተዳደረ ያለው የክልሉ መንግስት ሳይሆን ወታደራዊ ሀይል ነው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በኮማንድ ፖስት ስር ነው ያለው፤ በዚህም በጣም ችግር ላይ ነው ያለነው” የሚል መከራከሪያ አንስተዋል፡፡ ሆኖም ይሄ ምላሽ እስከ መጨረሻው ለጥያቄው መልስ ሳይሰጡ ዝም እንዲሉ አያደርጋቸውም፡፡
አዲስ የተቋቋመውን የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ኮሚሽኑን ለማነጋገር ሞክራችኋል?
ሙከራ እያደረግን ነው፡፡ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለሰላም ሚኒስቴር ነው፡፡ ስለዚህ ከአድራሻቸው ጀምሮ ለማግኘት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ሁለት ሶስት ጊዜ ተገናኝተን ገና ስራ አልጀመሩም የሚል ምላሽ ነበር ያገኘነው፡፡ አሁን ስራ መጀመራቸውንም አድራሻቸውንም አውቀናል:: በቅርቡ ፓርቲያችን በጉዳዩ ዙሪያ ከኮሚሽኑ ጋር የመነጋገር ሀሳብ አለው።
ባለፈው እሁድ በቁጫ ሰላም በር ከተማ ጠቅላላ ጉባኤ ስታደርጉ ችግር ገጥሟችሁ እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ምን እንደተፈጠረ ይንገሩን?
ፓርቲያችን በቅርቡ ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸውን አዳዲስ መስፈርቶች ለማሟላትና በሌሎች ጉዳዮችም ላይ ለመወያየት የመጀመሪያውን የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ለማድረግ ሰላም በር ከተማ ላይ ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡
አስቀድመንም የሰላም በር ከተማ የሕዝብ አዳራሽ እንዲፈቀድልን የወረዳውን አስተዳዳሪ ጠይቀናል፡፡ ምንም እንኳን በደብዳቤ ባይጽፉልንም ችግር እንደሌለውና አዳራሹ እንደሚፈቀድ አስተዳዳሪው ስለነገሩን፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና የዚያው አካባቢ አባላት በሰዓቱ እዚያው ተገኘን፡፡ ቀርበን የአዳራሹ ቁልፍ እንዲሰጠን ስንጠይቅ አዳራሹን የመፍቀድና ቁልፍ የመስጠት ሃላፊነት የተሰጣቸው የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ‹‹አይ እኔ ከወረዳው ዋና አስተዳዳሪና ከከተማው ከንቲባ ሳልመካከር ቁልፍ አልሰጥም›› አሉ፡፡
ከንቲባው ለወረዳ አስተዳዳሪው ‹‹ያንተ ሀላፊነት ነው››፤ ያኛውም ለዚህኛው ‹‹ያንተ ሀላፊነት ነው›› እየተባባሉ ሀላፊነት ሊወስዱ ስላልቻሉ፣ ጉዳዩን ወደ ጋሞ ዞን ወሰድነው አሉ:: የብልጽግና ፓርቲ የጎፋ ዞን ቅርንጫፍ ሀላፊ ተጠየቁ፡፡ ብዙ ሰበቦችን ደረደሩ፡፡ ‹‹የምርጫ ቦርድ መዋቅር በዚህ አካባቢ የለም፤ የጸጥታ ችግር ቢከሰት ሃላፊነት አንወስድም፤ ክልሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚተዳደር ነው›› እያሉ ጉዳዩን ወዳልተገባ ነገር ወሰዱት፡፡
ከዚያስ?
ከዚያ ወደ ዞኑ ም/አስተዳዳሪ ስልክ ደውለው ‹‹ይሄ ነገር ያስቸግረናል፤ መፈቀድ የለበትም›› አሉ፡፡ ስንሟገት እስከ 8፡00 ጠብቁ ተባልን፡፡ ሕዝቡ ከተማውን ሞልቶ የስብሰባውን መጀመር በጉጉት ሲጠብቅ ቆየ፤ እስከ 10፡00 ምላሽ የለም፡፡ ምላሽ ስናጣ ግን እዛው ወረዳው ም/ቤት ግቢ ውስጥ ሜዳ ላይ በሚያሳዝን መልኩ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄድን፡፡ ለስብሰባው የመጡ ወጣቶችና ሌሎችም ተቆጥተው ነበር በክልከላው፡፡ ነገር ግን አረጋግተን ‹‹ተው›› ብለን ባዶ ሜዳ ላይ ነው ስብሰባ ያካሄድነው፡፡
ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ በጣም የሚገርመው፤ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ‹‹አዳራሹ የብልጽግና ፓርቲ ንብረት ነው፤ ለእናንተ ማን ሰጣችሁ?›› ብለው በግልጽ ሳያፍሩ ነው የተናገሩት፡፡ እኛ ግን ሜዳም ላይ ቢሆን ጉባኤያችንን አከናውነን አጀንዳችንን አንስተን፣ በወደፊት ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፈን ተለያይተናል፡፡ እዚያ አካባቢ ለውጡ ገና ሽታውም አልደረሰም፤ አሁንም ችግሮቹ ቀጥለዋል፡፡
በዘንድሮው ምርጫ የመወዳደር ዕቅድ አላችሁ? ምን ያህልስ ዝግጁ ናችሁ?
ምርጫ የመወዳደር ዕቅድ በደንብ አለን፡፡ ለዚያ ነው ነገሮችን በፍጥነት እያካሄድን ያለነው:: የሚያስፈልገውን ዝግጅት ዋጋም ከፍለን ቢሆን እናደርጋለን - አይቀርም፡፡
የበጀት ጉዳይ ተግዳሮት አይሆንባችሁም?
ዋናው ጉዳይ እሱ ነው፡፡ ነገር ግን በጀት ከሌላ ከማንም ሳይሆን ከአባላት መዋጮ ነው የምንጠብቀው፡፡ በጠቅላላ ጉባኤው በአፅንኦት ካነሳናቸው ጉዳዮችም ቀዳሚው በጀት ነው፡፡ የአባላት መዋጮው በአስቸኳይ እንዲካሄድ የገቢ ደረሰኞችና የፋይናንስ ዶክሜንቶች ታትመው ተዘጋጅተዋል፡፡ በሁለትና በሶስት ቀናት ውስጥ ያንን ወደ መተግበር እንገባለን፡፡ ያለንን አቅም ሁሉ አሟጠን ለመጠቀም ቆርጠን ተነስተናል፡፡
ሕዝቡም በእሁዱ ስብሰባ በእጅጉ ደስተኛ እንደሆነና ከጎናችን እንደሚቆም ነው የገለፀልን:: ከመደበኛ መዋጮ በተጨማሪ ልዩ መዋጮም ለማዋጣት ቃል ተገብቷል፡፡ ነገሮች ሁሉ ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡
ቁጫ በጣም የምትታወቀው ጥራት ባለው ቅቤዋ ነው አይደል?
የቁጫ ቅቤ ብራንድድ ነው፡፡ በመንግሥት የልማት ተቋማትም ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ለአለም ካስመዘገበቻቸው ብራንዶች ውስጥ የቁጫ ቅቤ አንዱ ነው፡፡ በሌሎች የግብርና ምርቶችም ትታወቃለች፡፡ ለውዝ በስፋትና በጥራት የሚመረትበት አካባቢ ነው፡፡
እንደ ኮረሪማ ያሉ ቅመማ ቅመሞችም ይመረቱበታል፡፡ የእንሰት ምርቶችም ቡናም አለ:: ሌላው በኢትዮጵያ ከሚገኙ የተፈጥሮ ብሄራዊ ፓርኮች ውስጥ የሚገኘው ‹‹ማዜ›› ብሄራዊ ፓርክ 75 በመቶው የሚገኘው በቁጫ መሬት ላይ ነው፡፡ ለመጎብኘትም ለኢንቨስትመንትም አመቺና ሊጎበኝ የሚገባው ድንቅ ቦታ ነው፡፡
እርስዎ በሙያዎ ሶሲዮሎጂስት ነዎት፡፡ ከዚህ ቀደም በቁጫ ሕዝብ ታሪክ ላይም መጽሐፍ ጽፈዋል፡፡ መጽሐፉ በቁጫ አካባቢ ተሰብስቦ የመቃጠል ሙከራ ተደርጎበት እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ተረፈ?
እውነት ነው፡፡ የቁጫን ሕዝብ ታሪክና ባህል የሚዘክር በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ በ256  ገፆች የተሰናዳ መጽሐፍ ነው፡፡ በዞኑ ሊቃጠል ጫፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጣልቃ ገብቶ፣ በሕዝብም ትብብር ከቃጠሎ ተርፏል:: በአካባቢው ከኔ መጽሐፍ በፊት ‹‹ማዶላ›› የተሰኘ በቁጫና በጋሞ ታሪክና ባህል ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ተጽፎ ነበር፡፡ ይሄ መጽሐፍ በጋሞ ዞን አስተዳደር ሕገ ወጥ ውሳኔ ተቃጥሏል፡፡
መጽሐፌ ለወደፊቱ እንቅስቃሴም፣ ቁጫን ለማስተዋወቅም ትልቅ ፋይዳ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡             


Read 3186 times