Saturday, 11 January 2020 12:28

“ተከፍቶ ያልተከፈተ”

Written by  ከቃል ኪዳን
Rate this item
(8 votes)

  አእምሮው ውስጥ እንደ እስረኛ ከአንዱ ጥግ ወደ ሌላው ጥግ እየተመላለሱ፤ እግራቸውን የሚያፍታቱት ሀሳቦቹ፤ ፔርሙስ ከመሰለው የሙዚቃ ማጫወቻ ውስጥ እንደ እንፋሎት የሚወጣውን ዜማ መልዕክት ተከትለው በስልት ያረግዱ ጀመር፡፡ ሙዚቃውን በትውውቅ የጫነለት የፊልም ማከራያ ባለቤት የሆነው አብሮ አደግ ጓደኛው ነው፡፡ እስከ ዛሬ ጓደኛው እሱን እንጂ አእምሮው ዉስጥ እየተርመሰመሱ የሚያጨናንቁትን ሀሳባት የሚያውቅ አይመስለውም ነበር፡፡
ከሙዚቃው ማጫወቻው አንድ የድሮ የአማርኛ ዘፈን ተንጠፍጥፎ ካበቃ በኋላ አንዲት ሴት ‹ጥሎብኝ፣ ጥሎብኝ…› እያለች ታዜም ጀመር፡፡ ቅንድቡን ወደ ላይ ወጥሮ፤ የሙዚቃ ማጫወቻውን እየገላመጠ፡-
‹‹እሺ አንቺን ደግሞ ምንድን ነው የጣለብሽ?›› አለ፡፡ አጠያየቁ ዘፋኞቹ ሁሉ ተራ በተራ እየመጡ ‹ጥሎብኝ› እያሉ ስሞታ ያቀረቡለት ይመስላል፡፡ ዘፋኟ እንዳልሰማችው ሆና መዝፈኗን ቀጠለች፡፡
የተቀመጠበት የተወላገደ ሶፋ ወገብ እስኪንጣጣ ድረስ ትከሻውን እያፍታታ አዛጋና ሲጋራ አንስቶ አቀጣጠለ፡፡ የሟች አጎቱን ክፍል ከወረሰና ብቻውን ማደር ከጀመረ በኋላ፤ ልክ እንደ በፊቱ ሲጋራ ለማጤስ፤ አገልግሎት መስጠት ወዳቆመው የአያቱ ኩሽና መሄድ አቁሟል፡፡
የአጎቱ ክፍል ውስጥ ከሙዚቃ ማጫወቻዋ በስተቀር ከእሱ በዕድሜ የሚያንስ የቤት ዕቃ የለም፡፡ አልጋው፣ የተቀመጠበት ሶፋ፣ የልብስ ቁምሳጥኑ፣ ማብሰያ ዕቃዎቹን ሁሉ ሰልቅጦ፤ ሆዱን አሳብጦ እንደ ዘንዶ ያንቀላፋው ገዳዳ ብፌ፤ ግድግዳው ላይ የተሰቀለው የያሲር አራፋት ፎቶ፤ ነብስ ካወቀ ጀምሮ የሚያውቃቸው ናቸው፡፡
አሁን የተቀመጠበት ሶፋ ላይ አጎቱ ተቀምጦ፤ በዝርግ ሰሀን ላይ ሠፍሮ የሚሰጠውን በእርድ የበጨጨ ሩዝ፤ ወለሉ ላይ ቁጭ ብሎ እየሠለቀጠ፤ ከያሲር አራፋት ፎቶ ጋሽ ያሲንን ፈልፍሎ ለማውጣት ይሞክር በነበረበት ጊዜ እንኳን እነዚህ የቤት ዕቃዎች በጉልምስና ዕድሜያቸው ላይ ነበሩ፡፡
ሲጋራውን ትንሽ ሳበና ጠራርጎ አጨሰ እንዳይባል እንደፈራ ሁሉ፤ የቀረውን፤ ስኒዋ ከተሰበረ በኋላ አሽትሬ የሆነችው የስኒ ማስቀመጫ ላይ በጣቶቹ እየረገጠ አጠፋው:: ዘፋኚቱም ‹ጥሎብኝ› የሚለውን ቃል፤ እያገላበጠች፤ ዜማውን አጠፋችና ሙዚቃዋን ጨረሰች፡፡
‹‹ጥሎብኝ!›› አለ ድንገት፡፡ ‹‹ጥሎብኝ! ጥሎብኝ!›› ቃሉን ደጋገመውና እንዳጠፋው ሲጋራ የጨለመ ፈገግታን ፈገግ አለ፡፡
ጥሎበት ቀይ ሴት ይወዳል፡፡ በተለይ ቀይ፣ ቀጭን ሴት ታስደነግጠዋለች፡፡ ከሠርገኛው የፍቅር ህይወቱ ቀይ፣ ቀይ የሆኑትን ሴቶች እየመረጠ ነው፤ ስላሳለፈው የፍቅር ህይወት የሚያወራው፡፡ ቀይ ሴትና ድንቡሽቡሽ ያለ ጠይም ወንድ ልጅ የትዳር ህይወቱ ግቦች ናቸዉ:: ስለ ነገ ሲያስብ የፈጣሪን ‹ጋዋን› ተውሶ፤ እራሱ ባበጃጀው ‹ላቦራቶሪ› ውስጥ ከጥቁር ቆዳውና ደንዳና ሰውነቱ ዘር ወስዶ በሚያገባት ቀይ፣ ቀጭን ሴት ላይ ዘርቶ፤ ድንቡሽቡሽ ያለ ጠይም ልጅ ያበቅላል፡፡ ወተት የመሰለችውን ሴት ወስዶ፤ ከቡናው ገላው ጋር አዋህዶ፤ ድንቡሽቡሽ ያለ ‹ማኪያቶ› ይጨምቃል፡፡ ከጉርምስናው በኋላ ይሄን ንድፈ ሀሳቡን ወደ ተግባር ሊለውጥ አይጥ ያላደረጋት ቀይ ሴት ሠፈሩ ውስጥ ተፈልጋ አትገኝም፡፡ ችግሩ ግን ሀሳቡ ሊሠምርለት አልቻለም፡፡
ቀዩ የፍቅር ታሪኩ፤ እንደ ውሃ ጋን በሁለት ቀይ ሴቶች ጀርባ ላይ ያረፈ ነው፡፡ የመጀመርያዋ ቀይ ሴት የልጅነት ፍቅሩና ፍቅር ምን እንደሆነ ያስተማረችው ናት፡፡ ሁለተኛዋ ደግሞ አሁን ላለው ምርጫው መለኪያ አድርጎ ያስቀመጣትና ማፍቀር ምን ማለት እንደሆነ አሳየችኝ የሚላት ሴት ናት፡፡
እነዚህ ሁለት ሴቶች ከሌሎቹ ቀያይ ሴቶችና ቆጠራ ውስጥ ከማይገቡት ሌሎች ቀይ ያልሆኑ ሴቶች በላይ በትዝታው ውስጥ ግዘፍ ነስተው ተቀምጠዋል፡፡ ስለ ፍቅር በሚያወጋበት ጊዜም፤ እንደ ርዕሰ ጉዳዩ ዓይነት እየተቀያየሩ፤ የወጉን ቅድምያ ያገኛሉ፡፡ እነሱን የሚቀድም ግን ማንም የለም፡፡ ከመንፈቅ በፊት የተለየችው የመጨረሻዋ ፍቅረኛው እንኳን በወጉ ውስጥ እራስ የመሆን ዕድል አግኝታ አታውቅም:: ስለ እሷ የሚጠይቀው ሰው ቢመጣ እንኳን በእነዛ ሁለት ሴቶች በኩል ካላቋረጠ እሷ ጋ አይደርስም፡፡
ሁለቱን ቀያይ ሴቶቹን ተራ በተራ አስታውሶ ሲመለስ በረጅሙ አዛጋና ሌላ ሲጋራ አውጥቶ ለኮሰ፡፡ ይሄኔ አያቱ ቢያዩት ኖሮ ምግብ ሲበላ እንደሚያደርጉት ‹‹ሁሉንም ሲጋራ ለኩፈህ፣ ለኩፈህ ከምትጥል አንዱን በደንብ አታጨስም? የሲጃራም እኮ ግፍ አለው!›› እያሉ ሊቆጡት ይችሉ ነበር፡፡
ሲጋራውን መጦ ጭሱን ሲተፋ፤ የተዘፈነ ሳይሆን የተተፋ የሚመስል ሙዚቃን፤ የሙዚቃ ማጫወቻው መትፋት ጀመረ፡፡  
‹‹ግቢበት በልቤ፤ ግቢበት በልቤ
ላንቺ አይደለም ወይ እንዲህ መንገብገቤ›› የሚል፤ ገና ያልወጣ የሚመስል ሙዚቃ ከፔርሙሱ፤ ጓል እንደበዛበት በሶ ቦጭ፣ ቦጭ እያለ መፍሰስ ጀመረ፡፡
‹‹ቆይ እንዴት ትግባ? ወይ መዝፈኑን ትተህ ደብዳቤ ጻፍላት›› አለ በቁጣ፡፡ ወጣቱ ዘፈኑንም ሆነ ዘፋኙን ያለዛሬም ሰምቶት አያውቅም:: በዘፈኑና በዘፋኙ ቢናደድም፤ ዘፋኙ በሻካራ ድምጹ እየደጋገመ ግቢበት በልቤ የሚላት ነገር ሀሳብ ውስጥ ከተተችው፡፡
ማፍቀርን አስተማረችኝ ከሚላት ፍቅረኛው ጋር የተለያየ ሰሞን፤ ልቡ ተሠብሮ ክፍሉን ዘግቶ ተኝቶ ሳለ፤ ብዙ የልብ መሠበር መከራን ያሳለፈችው አክስቱ ክፍሉ ድረስ መጥታ ‹‹ልብህን ክፍት አድርገህ ከጠበቅህ ትክክለኛው ሰውዉ ይመጣል›› ብላው በሩን ክፍት ጥላበት ወጣች፡፡ በሩን ክፍት አድርጋ የሄደችው ምስጢር ለመመስጠር ነው ብሎ አስቦ፣ ልቡን ሊከፍት ሦስት ቀን ከተጋደመበት አልጋ ተነሳ፡፡
‹‹ትንሳኤ ልብ ሥቡራን!›› አለ በራፉ ላይ ቆሞ ወደ ዋናዉ ቤት ለመግባት ከውፍረቷ ጋር ትግል የገጠመችውን አክስቱን እየቃኘ፡፡
አክስቱ ልጅ አገረድ ሆና ባለመገኘቷ የልጅነት ባሏ ጀርባዋ ሰምበር እስኪያወጣ ድረስ በጉማሬ አለንጋ ገርፎ፤ በሱ ላይ መሀሉ ተቧጦ የወጣለትን ደፎ ዳቦ አሳዝሎ (መሀሉን ቧጦ ያወጣው ድፎ ዳቦው እንዳይከብዳት አዝኖላት ይሆን?)፤ እግሯን በዱላ ሠብሮ ወደ ቤተሰቧ ከላካት በኋላ፤ ያገሬው ጎረምሳ እየተቀባበለ፤ ከሰባት ዓመት በፊት ላገባችው ባሏ አስረከባት:: አሁን በመጨረሻ ትዳር መሥርታ፤ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ያበቃት ልቧን ክፍት አድርጋ መጠበቋ እንደሆነ ለእህቷ ልጅ በምስጢር ነግራው ሄደች፡፡ ኧረ እንደውም ሦስት ቀን ሙሉ እንደ መቃብር የዘጋውን በሩን፤ መዝጊያውን አንከባላለት ሄደች፡፡
ከዛ በኋላ የልቡን መዝጊያዎች፣ የሲኦልን ደጃፎች ያህል ወለል አድርጎ ከፈታቸው፡፡ በወንድ አቅሙ የልቡን ወለሎችና ግድግዳዎች እበት ለቀለቃቸው፡፡ ፍቅረኛው ሠብራው የሄደችውን ልቡ ውስጥ ያለውን ዙፋን በዘነዘና ቀጥቅጦ ጠገነውና የለበሰውን ግምጃ አውልቆ አለበሰው፡፡ ከዛም ጭሳጭሱን አጫጫሰና እንደ ሴት አዳሪ የልቡ በር ላይ ቆሞ የልቡን ንግስት ይጠብቅ ጀመረ፡፡
ልቡን ክፍት አድርጎ ትክክለኛዋን ሴት መጠበቅ ከጀመረ ብዙ ጊዜያት ተቆጥረዋል:: በዚህ መሀል ‹ባዶ ልብ በክረምትን› እቤቱ ቁጭ ብሎ ላለማንጎራጎር ብዙ አዛጋሚዎችን ቢያፈራም፣ ከአዛጋሚዎቹ መሀል ግን ለአንዷም ቢሆን የልቡን መግቢያ ሊያሳያት አልፈቀደም፡፡ ችግሩ ግን ሁለተኛዋ ቀይዋ ፍቅረኛው አሳይታው የሄደችው ከፍታ ላይ የምታደርሰውን ቀይ ሴት ማግኘት አልቻለም፡፡
ከሀሳቡ በፍጥነት ሲመለስ ‹ጠይም ናት ጠይም መልከ ቀና በውበት ያጌጠች› እያለ ጥላሁን ሲያዜም ደረሰ፡፡ ‹‹የጥላሁን እውነተኛ ምርጫ ግን የትኛዋ ሴት ናት? ዛሬ ጠይም ናት ይላል፤ ነገ ስለ ቀይ ዳማዋ ይዘፍናል፤ ተነገወድያ ስለ ቀይዋ፤ ከዛ ስለ ጥቁሯ…›› ሲል አጉተመተመ::
ጠይምና መልከ ቀና የሆነቺውን አሁን አብሯት ያለውን ወይም አብራው ያለችውን ሴት እየፈራት ነው፡፡ እንዳይወዳት ጠይም ናት:: ጸባይዋ ግን ሸጋ እንደሆነ አምኗል፡፡ አክስቱም አያቱም ሁሉም ወደዋታል፡፡ አዛጋሚዬ ናት እንዳይል ካሰበው በላይ አብራው አዝግማለች:: ፈጽሞ አይደክማትም፡፡ እሱ ነገሯ ነው እያስፈራው ያለው፡፡
ሴት ፊት ሲነሷት ስትሸሸ ነው የሚያውቀው:: ይህቺ ሴት ግን ምን አስባ እንደሆነ ሊገባው አልቻለም፡፡ እስካሁን የገፋቸው ሴቶችን ክስ ይዛ ነገረ ፈጃቸው ሆና የመጣችም ይመስለዋል:: አንድ ቀን ልቡ መግቢያ እንደሌለው ነገራት፡፡ የዛኑ ቀን ወደ ልቡ መግቢያ ልታበጅ ቁፋሮዋን ጀመረች፡፡ እንድትሸሽ ማድረግ ስላልቻለ መሸሽ ጀመረ፡፡
የጥላሁን ሙዚቃ ከማብቃቱ ቤቱ ተንኳኳና ድብልብል አክስቱ እየተድበለበለች ገባች፡፡ ቀና ብሎ አያትና ሙዚቃ ማጫወቻውንና በእጁ የያዘውን ሲጋራ አጠፋፋ፡፡
‹‹የጥላሁንን ሙዚቃ ስሰማ እኮ ወንድሜ ያለ ሁላ ነው የመሰለኝ፡፡ ነብሱን ይማረው!›› አለችው፡፡
‹‹ኮሌክሽን ሙዚቃ አስጭኜ ነው፡፡›› አላት እንድትቀመጥ ወንበሩን እየለቀቀላት፡፡ ስትቆም ብዙ ነገር ስለምትከልል በጣም ትከብዳለች፡፡
‹‹እኔ እሄዳለሁ ቁጭ በል፡፡ ሰላም ልልህ ነው የመጣሁት፡፡››
‹‹ቁጭ በይ እንደውም ላዋራሽ ስፈልግሽ ነበር›› አላት ሄዶ መሬት የተጋደመው ፍራሽ ላይ እየተቀመጠ፡፡
‹‹ምነው በሰላም?›› አለችው ሄዳ ፍራሹ ላይ ከጎኑ ለመቀመጥ እየተንፈራገጠች፡፡ ደግፎ ሊያስቀምጣት አብሯት ትንሽ ተወራጨ፡፡ እንደ ምንም ተደላድላ ተቀመጠችና የሚላትን ለመስማት ሳይሆን የምትነግረውን ለማወቅ በጉጉት ተመለከተችው፡፡ እሱ ግን የሚነግራትን ለመስማት እንደጓጓች አስቦ፡-
‹‹ልብህን ክፈት አልሺኝ ልቤን ከፈትሁ፡፡ ግን ልቤ ውስጥ የምትገባ ሴት ላገኝ አልቻልሁም:: ቆይ ምን ያህል ነው መጠበቅ ያለብኝ?›› አላት ጥበቃ እንዳሰለቸው አናቱን እያወዘወዘ፡፡
‹‹ይህቺን ልጅ አሁንም አልወደድካትም ማለት ነው?›› አለችው በትዝብት፡፡
‹‹እሷን ተያት! ʻታይፔʼ አይደለችም አልኩሽ እኮ!? ደግሞ ትናንት ያልወደዱትን፤ ዛሬ መውደድ ይቻላል እንዴ?››
‹‹ለምን አይቻልም? ያላየኸውን ማየት ስትጀምር…አልገብቶህ የነበረው ሲገባህ…››
‹‹እኔ በመላመድ በሚመጣ ፍቅር አላምንም:: ፍቅር እንደወረደ ሲሆን ነው የእውነት የሚሆነው፡፡ ቀይ ቆንጆ ሴት አይቼ ድንግጥ ስል ነው ፍቅር እንደሆነ የማምነው፡፡ በመላመድ የሚመጣው ፍቅር ሳይሆን አብሮ፣ ተቻችሎ የመኖር ክህሎት ነው፡፡›› ንግግሯን ነጠቃት:: ንግግሩን ሰምታ ስታበቃ አክስቷ እራሷን በአሉታ ነቀነቀች፡፡
‹‹እውነቴን ነው፡፡ እሺ ቆይ መላመድ ፍቅር መሆን ቢችል ይሄን ያህል ቆይተን ለምን አልወደድኳትም? ሳልፈልግ አብሬአት መሆንን ግን ችዬበታለሁ!››
‹‹እንዳልወደድካት በምን እርግጠኛ ሆንክ? እስከዛሬ አብረሀት የቆየኸው ስለወደድካት ቢሆንስ? ከሌሎቹ ሴቶች ጋር ለምን ከሳምንት በላይ መቆየት አቃተህ?›› አክስት መስቀለኛ የመሰለ ጥያቄ ጠየቀች፡፡ ግራ ተጋብቶ ተመለከታት፡፡
‹‹እንዴ እራሷ እኮ ናት ጥብቅ ያለችብኝ!››
‹‹እየደወሉ እየጠሩ ጥብቅ አለችብኝ ብሎ ነገር አለ እንዴ? አልወደድኳትም ማለት እኮ አለመውደድ አይደለም፡፡››
‹‹እና ወደድኳት ማለት ነው?››
‹‹እሺ ቀይ አለመሆኗን ተወውና ከእሷ የምትጠላውን አንድ ነገር ንገረኝ?›› አክስት አፍጥጣ ጠየቀቺው፡፡ ግራ በመጋባት ትንሽ ሲያስብ ቆየና፡-
‹‹እንዴ! ቆይ የምጠላላት ምንም የለም ማለት እወዳታለሁ ማለት ነው እንዴ?››
‹‹እንደዛ ማለቴ አይደለም፡፡››
‹‹እናስ?›› አቋረጣት፡፡
ለመነሳት እየተንደፋደፈች ‹‹ያንተ ችግር…›› አለችና ንግግሯን በእንጥልጥል ትታ ተንደባላ ተነሳችና ቆመች፡፡
‹‹ቆይ ʻታይፔʼ ያልሆነችን ሴት አለመውደዴ ችግር ነው እንዴ?›› አላትና ቀጥ ብላ እስክትቆም ጠብቆ ሄዶ ፊቷ ተገተረ፡፡
‹‹ችግርህ ልብህ እንጂ ዓይኖችህ አልተከፈቱም፡፡ ልብ ካላየ ዓይን አያይም ይባላል:: ዓይን ካላየም ልብ አያይም! ልብህን ከፍተህ ጠብቅ ስልህ ዓይኖችህ የተከደኑ ይሆናሉ ብዬ አልጠበቅሁም ነበር፡፡››
በቆመበት ጥላው ወደ በሩ አመራች፡፡ ግራ በመጋባት በደመነፍስ ተከተላት፡፡ በሩ ጋ ደርሳ ቆመችና፡-
‹‹ቀይ ሴት ትፈልጋለህ፡፡ ቀይ ሴት አትፈልግ ልልህ አልችልም፡፡ ግን ከቀይ ሴት ቆዳ ጀርባ የጠቆረ ልብ ሊኖር እንደሚችል ማወቅ አለብህ:: በተቃራኒ ጥቁር ብለህ ከምትሸሻት ሴት ቆዳ ጀርባ፤ አንተ አይተህ የምትደነገጥላትን ቀይ ሴት ቆዳ የሚያስንቅ ንጹህ ልብ ሊኖር ይችላል:: ደግሞስ አንተን ብቻ ይህቺና ያቺን እያልክ የምትመርጥ፤ መራጭ ማን አደረገህ? ቢገባህ ይህቺ ሴት አንተን በመምረጧ እራሱ ዕድለኛ ነህ!››
ጥላው ከክፍሉ ወጥታ ሄደች፡፡ ከፍታ የገባችውን በር አልዘጋችውም፡፡ በቆመበት በሩን ክፍት ጥላው የሄደችው ዛሬም አንዳች ነገር ለመመስጠር አስባ ይሆናል ሲል አሰበ:: ወደ ሶፋው ተመልሶ ተቀመጠና ሙዚቃ ማጫወቻውን ከፈተ፡፡ ጥላሁን ‹ጠይም ናት ጠይም መልከቀና› የሚለውን ዘፈኑን ካቆመበት ቀጠለ፡፡ እሱ ግን ‹ልቤን ብቻ ከፍቼ ዓይኖቼን ከድኛለሁ እንዴ?› ሲል አዲስ ሀሳብ ማሰብ ጀመረ፡፡


Read 1753 times