Tuesday, 14 January 2020 00:00

የመን ዘንድሮም በአለማችን እጅግ የከፋው ሰብዓዊ ቀውስ ያጋጥማታል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ኢንተርናሽናል ሪስኪዩ ኮሚቴ የተባለው አለማቀፍ ተቋም በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2020 የእርስ በእርስ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ይፈጠርባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ የአለማችን አገራትን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የመን እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም ከአለማችን አገራት ሁሉ እጅግ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ያጋጥማታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት በእርስ በእርስ ግጭት የምትታመሰዋ የመን፣ 80 በመቶ ወይም ከ24 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝቧ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልገው እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፤ ባለፉት 5 አመታት ውስጥ ሩብ ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች በግጭቶች ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውንና የሰብዓዊ ቀውሱ በአዲሱ አመትም በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ተቋሙ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የእርስ በእርስ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በአገራት ውስጥ ሰብዓዊ ቀውሶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ ያላቸውን 76 ያህል የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም ባወጣው የዘንድሮው ዝርዝር፤ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶርያ፣ ናይጀሪያና ቬንዙዌላ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል::
የከፋ ቀውስ ያሰጋቸዋል ተብለው ተቋሙ ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ደረጃዎች የሰጣቸው አፍጋኒስታን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሶማሊያና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሲሆኑ፤ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች አገራት መካከልም ብሩንዲ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ማይንማር፣ ኒጀርና ሱዳን ይገኙበታል፡፡
ተቋሙ ባለፈው አመት ባወጣው የሰብዓዊ ቀውስ ስጋት ያለባቸው ዝርዝር ውስጥ ተካትተው የነበሩት ባንግላዴሽ፣ ሜክሲኮ፣ ኒካራጓና ፓኪስታን ዘንድሮ ከዝርዝሩ የወጡ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሶስቱ አዳዲስ አገራት ደግሞ ቡርኪናፋሶ፣ ብሩንዲና ቻድ ናቸው፡፡

Read 3114 times