Friday, 10 January 2020 07:41

“አረና” በትግራይ ክልል በአባሎቼ ላይ የሚፈፀመው እስርና እንግልት በርትቷል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

 “በትግራይ ክልል በአባሎቼና ደጋፊዎቼ ላይ የሚፈፀመው ማዋከብና እንግልት በርትቷል  ያለው “አረና” ፓርቲ፤ ሰሞኑን ሁለት አመራሮቹ መታሰራቸውን አስታወቀ፡፡  
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አምዶም ገ/ስላሴ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ በተለይ ህወሃት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር አለመዋሃዱ ግልጽ እየሆነ ከመጣ በኋላ ሊቀመንበሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ “በትግራይ ሰላም የሚነሱንን አንታገስም” ማለታቸውን ተከትሎ በተለያዩ ወረዳ ያሉ የፓርቲው አባላትና አመራሮች ለድብደባና እስራት መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በርካታ የፓርቲው ደጋፊዎችና አመራሮች እንዲሁም አባላት “ፀጥታ እያደፈረሳችሁ ነው” በሚል ሰበብ እስር እንግልትና ወከባ እየተፈፀመባቸው መሆኑን ያስረዱት አቶ አምዶም፤ ይህም ከምርጫ መቃረቡ ጋር ተያይዞ እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል፡፡
“የህወሃት ካድሬዎች የአረና አባላት ወዳሉበት ቦታ በመሄድ ሆን ብለው ፀብ በመፍጠር ራሳቸው ከሳሽ ራሳቸው ምስክር እየሆኑ አባሎቻችንን እያሰሩ ይገኛሉ” ያሉት አቶ አምዶም፤ “ህወሃት አባሎቻችን ለማሰር አዲስ ሴራ መፍጠሩን አረጋግጠልናል ብለዋል፡፡
“አረና” ለቀጣዩ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ አምዶም፤ ይህም በህወሃት በኩል  “በምርጫ እንሸነፋለን” የሚል ፍርሃት መፍጠሩን ተከትሎ ነው ማዋከብና እስራቱ በአባሎቻችን ላይ የበረታው ብለዋል፡፡
የትግራይን ሰላም መጠበቅ በሚል ሰበብ፣ የመንግሥት የፀጥታ ሃይሎች በሕዝቡ ላይ በከፍተኛ ጭቆና እያደረሱ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ቀደም ብሎ አራት የአረና አመራር አባላት በእስር ላይ የነበሩ ሲሆን ከሰሞኑ ከታሰሩት ጋር ቁጥራቸው ስድስት መድረሱን ያስረዱት አቶ አምዶም፤ በየቀኑ ሰበብ እየተፈለገ ታስረው የሚፈቱ አባሎቻችን ደግሞ በርካታ ናቸው ብለዋል፡፡

Read 3351 times