Tuesday, 07 January 2020 00:00

የገና ስጦታ ባለቤቱ ማነው?

Written by  ደ.በ
Rate this item
(1 Vote)

በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና የሕይወት መስመር ግጭቶች ምክንያት በሚፈጠሩ ስነ ልቡናዊ ቀውሶች የማይጠገኑ ስብራቶች፣ የማይድኑ ቁስሎች መስለው የሚቆዩ ሕመሞች አሉ፡፡ ከረዥም አመታትና ዘመናት በፊት ለዚያውም በዘመን አውድ ፍልስፍናና እምነት ተጠንስሶ ለተፈጸመ ነገር ዘላለም የሚያለቅሱ፣ ጥላቻቸው የማይነቀል ሰዎች ጥቂት አይደሉም:: ይሁን እንጂ ስር የሰደደ ጥላቻን ከህመም ለይቼ አላየውም፣ ጤናማ ያልሆነ ችግር አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡  
ከዚህ አይነት ህመሞች አንዱ የኛ የኢትዮጵያውያን ፈረንጅ ጠልነት ይመስለኛል፡፡ ለዚህ ደግሞ መነሻው የጣሊያን ወረራና በተለያዩ ጊዜያት ከእንግሊዝና መሰል ድንበርተኞችና ሌሎችም ወራሪዎች ጋር የነበረው ቁርሾ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኸርበርት ፎልክ የተባለው የደች ተወላጅ በጻፈውና ዮናስ ታረቀኝ በተረጎመው መጽሐፍ ላይ የቂሙን መነሻ እንዲህ ይገልጸዋል፡
“-ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በአውሮፓውያን የተከበበች በመሆኗ በፍጹም ወደ ባሕር መጠጋት አይቻላትም፡፡ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ ወደ ምስራቅ አፍሪካ በረሃ የሚወስደውን መንገድ የኢጣልያ ሶማሌ ዘግቶታል፡፡ የኤደን ባህረ ሰላጤ መተላለፊያን እንግሊዝ አግዶታል::…ቀይ ባህር በጣልያን ኤርትራ ምክንያት ሊደርስበት የሚቻል አይደለም፡፡ ምዕራቡን የእንግሊዝ ግብጽ ሱዳን ይጠብቀዋል:: --”  እያለ ይቀጥላል::
ይሁንና  የከበቡንንና የወረሩንን ያህል፣ ብዙ ነጮች ከእኛ ጋር ቆመው ጦርነቱን ተቃውመዋል፤ አብረውን ጦር ሜዳ ዘምተዋል፤ የድልና የጀግንነት ተጋድሏችንን ለአለም ያስነበቡም ሞልተዋል፡፡ ብዙዎቻችን ግን የጦርነቱንና የወረራውን ዘመን አውድ፣ አስተሳሰብ፣ ፍልስፍናና ሥነ ልቡና ሳናገናዝብ፣ ዛሬም ድረስ ፈረንጅ ሲባል ይዘገንነናል፡፡ እናም ዕውቀታቸውንና ጠቃሚ እሴቶቻቸውንም አብረን ለመግፋት እንታገላለን፡፡
እኔ ግን ፈረንጅ ጠልነቱ ላይ አልስማማም:: ፈረንጅን በድፍኑ መጥላት አዋጪ አይመስለኝም፡፡ ጥላቻም በሽታ እንጂ ጤንነት ነው ብዬ አላስብም፡፡ የሚጠቅመንን በመውሰድ፣ የማይረባንን በመተው አምናለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የውዴታ ግዴታም መሆኑን ማሰብም ማሳሰብም እፈልጋለሁ፡፡ የፍልስፍናና የጥበብ ምንጭ የሆነችው ግሪክ፣ የአርስጣጣሊስና የነአፍላጦን ሀገር፣ የፈረንጅ አገር መሆኗን ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይልቅስ የሮማው ዲስኩረኛ እንዳለው፤ ‹‹የጥንቱን እየወሰድን ከራሳችን ጋር በማዛመድ” አምናለሁ፡፡ የአለምን ጥበብና እውቀት ሁሉ ገፍተን፣ በራሳችን ጎጆ እንቆራመድ በሚለው የሞኝ ዘፈን  መጃጃልን አልቀበልም። ይልቅ የፈረንጅ ብልሹ ባህልና ልምምድ ማራገፊያ መሆን አይጠቅመንም፡፡ የራሳችንን ጠቃሚና ሥልጡን ባህልና ልማዶች እንከተል በሚለው በእጅጉ እስማማለሁ፡፡   
የገናን በዓል በሚመለከት ከዓመት ወደ ዓመት፣ አገራችንን እየወረረ የመጣው የሳንታ ክላውስ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ የገና በዓል ታሪካዊ ዳራ ሳንታ ክላውስ አይደለም፡፡ ሳንታ ክላውስ  ባልሠራው ታሪክ ቆሞ የታሪኩን አቢይ ጉዳይ መሸፈኑ፣ ከጣልያን ወረራ ያልተናነሰ ጥፋት እየፈጸመብን  ይመስለኛል፡፡
ለመሆኑ የገና በዓል መነሻው ምንና ማን ነው? ብሎ መጠየቅና ወደ ትክክለኛው መስመር መመለስ የሚያሻ ይመስለኛል፡፡ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ከተወለደው ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሰባት መቶ ዓመታት ቀድሞ ነቢዩ ኢሳያይስ ‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች›› ብሎ ትንቢት የተናገረለትና ዓመተ ዓለምን ወደ ዓመተ ምህረት የለወጠው ጌታ የተወለደበት ዕለት መታሰቢያ ነው፡፡ ዛሬ እሽሩሩ ተብሎ ቀይ ልብሱ አገራችንን ያጥለቀለቀው ሳንታ ክላውስ ደግሞ በዚህ በዓል ላይ ስጦታ ሰጠ ተብሎ ስሙ እየገነነ ነው፡፡  
እዚህ ጋ ቆም ብሎ መጠየቅ የሚያስፈልገው፣ የገና በዓል የፈጠረው ስጦታ ሰጪ ማን ነው የሚለው ነው? ሳንታ ክላውስ ለሕጻናት የሚሆን ስጦታ ሰጠን ብለን ሽር ጉድ ስንል፤ ለሰው ልጆች ሁሉ ሀጢአት ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ አንድ ልጁን በመስጠት ቸርነቱን ያሳየውን እግዚአብሔርን ምን እንለዋለን? ሐዋርያው ዮሐንስ በወንጌል ላይ ‹‹በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ አለሙን እንዲሁ ወዷልና›› ይላል። ታዲያ ሕይወትን የሰጠው እያለ፤ በሰጪው ቀን ላይ ጥቂት ስጦታ የሰጠን ማንገስ ምን ይባላል? በምንም ዓይነት ትክክል ሊሆን አይችልም! ይልቅ የፈረንጅ የባህል ወረራ ነው፡፡ ስጦታም ከሆነ በአገራችን የተሰሩ በቤተልሄም የበጎች ግርግም ውስጥ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዮሴፍና ሕጻኑ ኢየሱስ የሚታዩበትን የእጅ ስራ ገዝቶ በአሉን ማስታወስ የተሻለና ተመራጭ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ታሪኩ የሚመለከታቸው፣ ልደቱን ስናስብ ከልባችን ብቅ የሚሉት እነዚህ ሦስቱ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ስጦታ የሰጡትንና በኮከብ እየተመሩ የመጡ ሰብአ ሰገል እረኞችን ማስታወስ ይሻላል፡፡ ከዚህ አሁን በየአደባባዩ ከምናደምቀው ፈረንጅ የተሻለ የታሪክ ድርሻ እንዳላቸው የታሪክ መጻሕፍት ይዘክራሉና! ምናልባትም እግርግም ውስጥ የነበሩ በጎች እንኳ የበለጠ ጉዳዩን ይዛመዳሉ ማለት ይቻላል፡፡ ሳንታ ክላውስ ለታሪኩም ለሁነቱም በእጅጉ ሩቅ ነው፡፡ ስለዚህ ስር ሳይሰድ በጊዜ ልንወያይበትና ወደ መጣበት ልንመልሰው ይገባል፡፡ መድፍና ታንክ የሚያስፈልገው ባይሆንም፤ መራራ ጦርነት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ጉዳዩ ከባህል ብከላና ወረራ ያለፈ የሕይወት ትርጉም አለው፡፡
ገጣሚት ትዕግስት ማሞ ‹‹ፍቅር›› በሚል ርዕስ፣ “በጎደሉ ገፆች” መድበሏ ላይ ጥቂት ስንኞች ቋጥራለች፡፡
ዓለምን ባንድ ልብ፣ በይቅርታ ይዞ፣
በረዥም ፈተና፣ ለሚያደክም ስቃይ፣
            ለሚያደክም ጉዞ፣
ለሞት የታጨ ሕፃን፣ ሕልማም ምኞት ገዛ፣
            እንደ ሰው ታነጠ
በዘመመች በረት፣ በከብቶች እስትንፋስ፣
      ሕይወት አማማጠ፣
ሰው መሆን ስህተት ነው
    ሰው መሆን መረጠ፡፡
ምላሽ ሳይጠብቁ ብድራት ሳይሰፍሩ፣
ሰጥቶ መቀበልን ልዋጭን ሳይኖሩ፣
ዝም ብሎ መውደድ፣ ዝም ብሎ መሸነፍ
ዝም ብሎ ማፍቀር፣ ዝም ብሎ መክነፍ፣
ምን አይነት ኑረት ነው?
ለሰዶም ሁሉ ነፍስ፣ ለሎጥ ጽኑ እምነት
ለፈርኦን እብሪት፣ ለእስራኤል ክህደት፣
ለሚወዱት ፍቅር፣ ለጠሉትም ሕይወት፣
አምላክ ግን ሰው ሆነ…
    ሰው መሆን ግን ስህተት፡፡
የገና መታሰቢያ በዓል ዋና ጭብጡ፤ ትዕግስት ማሞ በግጥሙ ያሰፈረችው ሁነት ነው፡፡ አምላክ የሰው ልጆችን ሁሉ ለማዳን ስጋ ለብሶ፣ ሰው ሆኖ፣ ሰዎችን የተቀላቀለበት አስገራሚ ሁነት ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሰው ልጆች ሁሉ ስጦታ አድርጎ የሰጠበት ነው፡፡ ትዕግስት በግጥሟ እንዳለችው፤ ለሰዶም አመፀኞች ተመሳሳይ፣ ለከሀዲዎችም ሁሉ ዋጋቸውን ለመክፈል ዋስ ለመሆን፣ ነፍሱን ለመስጠት የመጣበት! ታዲያ እንዴት ሆኖ የአንዲት አፍታ ጥቃቅን ስጦታ ሰጪ፣ ለአለም ሁሉ በፍቅር ነፍሱን ከሰጠ ጌታ ጋር እኩል ሆኖ በየአደባባዩ ክብር ይቀበላል:: ይህ ስህተት ሕሊና ላለው ሰው ሁሉ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ነው፡፡
ከላይ እንደጠቀስኩት የፈረንጅ ልማድ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ከበአሉ ዋነኛ ጉዳይና ትኩረት አንፃር እንክርዳድ ነው፡፡ ስለዚህ የበአሉን ደራሲና ተራኪ ትተን፣ የበአሉ መከበሪያ አንዱ አንጓ ላይ እንደ ሰንደል ጢስ ያለፈውን ፈረንጅ እናስቀምጠውና የበአሉን የዘመን ፋይዳና ዘላለማዊ ትርጉም እየፈተሽን እናስበው:: አምላክ ሰው የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ እንደ ሰው የአለምን ሐጢአት የሚያስወግድ ሆኖ ነው:: ስለዚህ በአሉ የኢየሱስ ክርስቶስ መታሰቢያ በዓል እንጂ የቀይ ለባሹ ፈረንጅ የሳንታ ክላውስ ወይም በየደጁና በየቤቱ በመብራት ተንቆጥቁጦ የሚተከለው የላስቲክ ዛፍ አይደለም፡፡ ስለዚህ ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ!
መልካም የገና በዓል!!  


Read 6776 times