Print this page
Monday, 06 January 2020 00:00

ኢትዮጵያ ድንቅና ረቂቅ ፍልስፍና አላት!!

Written by  ወልደ ጊዮርጊስ ይሁኔ
Rate this item
(0 votes)

አንድ ሀገር የምትሄድበት ወይም እንድትሄድበት የሚፈለግበት መንገድ ፍልስፍና ይባላል፡፡ በመሆኑም የማናቸውም ሀገር ህዝብ የሚመራበት የራሱ የሆነ አሊያም ከሌሎች ሀገራት የተቀዳ ፍልስፍና አለው፡፡ ይህን ስንል ምን ማለታችን ነው? የፍልስፍናስ ትርጉም  ምንድነው? የሚሉትን መሰረታዊ ጥያቄዎች መመለስ ተገቢ ነው፡፡
ለፍልስፍና አንድ ወጥ ብያኔ ለመስጠት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ይህን ሀሳብ የሚያጠናክርልን የፍልስፍና ፕሮፌሰሩ ሚለር “Questions that matter” በሚለው መጽሐፉ ያሰፈረው ሀሳብ ነው፡፡
“ The definition and the meaning of philosophy is itself one of the big issues in contemporary philosophy!” በግርድፍ ትርጉሙ፤ “በአሁኑ ጊዜ የፍልስፍናን ብያኔና ምንነት ለመረዳት ፍልስፍና በራሱ ትልቅ ጥያቄ ነው” እንደ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የስራ ብያኔ በማለት የሚያስቀምጡት “philosophy is the attempt to think rationally and critically about the most important questions.” (ፍልስፍና ማለት፤ መሰረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በጥልቀትና በምክንያት ማሰላሰልና ማሰብ ማለት ነው፡፡)
ጠቅለል ባለ መልኩ ስናየው፤ ፍልስፍና ማለት ለህይወት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ማለትም ስለ እውነት፣ እውቀት፣ ውበት፣ ተፈጥሮ፣ ትዕይንተ ዓለም፣ ሳይንስ እምነት፣ ስለ ፈጣሪ፣ ስለ ስነምግባር በመወሰን ሳይገደብ መጠየቅ፤ መመርመርና መደነቅ ነው፡፡ እውቀትና ጥበብን መፈለግ ነው፡፡ ፍልስፍና፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ካለማወቅ ወደ ማወቅ፣ከባርነት ወደ ነጻነት፣ ከስህተት ወደ እውነት የሚያሻግር ድልድይ ነው፡፡
አንድ ሀገር ፍልስፍና አለው ስንል፤ የሀገሩ ህዝብና መንግስት የሚመሩበት ገዢ ሀሳብ ማለታችን ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በመካከለኛው ዘመን የነበሩትን አውሮፓውያን (Medieval Europe) ስንመለከት፤ ስነ መለኮትን እንደ ገዢ ሀሳብ ወስደው ይከተሉትና ይመሩበት ነበር፡፡ የሮማን ግዛት ዘመን ደግሞ ህግ ነው፡፡ ማህበረሰቡ በህግ የበለጸገ ነበር፡፡ የአሁኑ ምዕራብ አውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ህዝብና መንግስት የሚከተሉት ፍልስፍና ደግሞ ሊበራሊዝም ነው፡፡ የጥንት ግሪኮች በተለይም አቴናውያንን ስናይ፤ ንግግር ማድረግ፣ መጠየቅና መመለስ (dialogue) መንፈሳቸው ነበር - ፍልስፍና! ይህን ሀሳብ እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ› በሚለው መጽሐፋቸው፣ በገጽ 56 ላይ፣ ‹‹አቴናውያን አዲስ ነገር ከመስማት ወይም ከመናገር በስተቀር ሌላ ምኞት አልነበራቸውም›› ካሉ በኋላ ቀጥለውም በገጽ 17 ላይ ‹‹አቴናውያን ወደ ፊት ለመራመድ የቻሉትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በማናቸውም የአውሮፓ ስልጣኔ ክፍሎች ዘንድ የእነሱን ማሕተም ያልተሸከመ ነገር አይገኝም፡፡ ጫፉን ለመጥቀስ ያህል በሳይንስ ረገድ እነ ዲሞክሪቶስ እስከ አቶም ፊዚክስ ድረስ የደረሱ ነበሩ፡፡በፖለቲካ ድርጅቶች ረገድ እስከ ዲሞክራሲ የደረሱ ነበሩ፡፡›› ብለዋል፡፡
አቴናውያን ለአዲስ ነገርና ለፈጠራ ከነበራቸው ውስጣዊ መሻት በመነሳት ግብረ ገብነትን ለዓለም ሰብከዋል፡፡ አስተምህሮታቸው አሁን ላለንበት ዘመን ብቻ ሳይወሰን ዘመን ተሻጋሪ ነው፡፡ በታሪክ ጽሁፍ፣ በስነ-ጥበብ፣ በኪነ- ህንጻና በሌሎችም የስልጣኔ ዘርፎች አርአያ የሚሆን ስራን ለዓለም ማበርከት ችለዋል፡፡ ‹ክላሲክ› የሚባለው ቅጽል፣ ዛሬ ለመላው የዚህ ዘመን ስልጣኔ ተሰጥቷል፡፡ ትርጓሜውም፤ ፍጹም ስራ ስለሆነ፣ ለተማሪዎች ለ ‹ክላስ› የሚቀርብ ማለት ነው፡፡
ከላይ ባነሳናቸው ሀሳቦች ላይ ተመስርተን፣ የሀገራችን ፍልስፍና ምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ መልሱ  መንፈሳዊነት ነው፡፡ መንፈሳዊነት ማለት የሆነ የአንድ ሃይማኖት ተከታይ ማለት አይደለም፡፡ የሃይማኖት ተከታይ መሆንና መንፈሳዊ መሆን የተለያዩ ናቸው፡፡ መንፈሳዊነት ማለት ሰው በተፈጥሮው የደግነትና የማስተዋል ጠባይ የተቸረው መሆኑን አምኖና ተቀብሎ፣ ይህን የተፈጥሮ መልካም ስጦታን በህይወቱ የሚፈጽም ማለት ነው፡፡
‹‹ሰው ልሙጥ ፍጥረት፣ ያልተጻፈበት ብራና አይደለም፡፡ የለባዊነት፣ የማሰብ፣ የሎጅክ ሕግጋት በህሊናው ውስጥ ተቀምጠው ይገኛሉ:: የበጎ አድራጎት፣ የስነ ምግባር፣ የሞራል ህግጋት በልቦናው ውስጥ በተፈጥሮ ተጽፈው ይገኛሉ::… ለማናቸውም ተግባሩ መሰረት ሊሆኑ የሚገባቸው እሊህ ህግጋት ናቸው:: ሰው ሰራሽ አይደሉም፡፡ አያረጁም፡፡ (እጓለ፣ 71)፡፡ ይህን የተፈጥሮ ህግ የተገነዘቡት ጥንታዊ አያቶቻችንና አባቶቻችን፣ በንጹህ ህሊናቸው በመመራት፣ ታላላቅ ገድሎችን ፈጽመዋል፡፡ ይህም ሳዊነታቸው ፍሬ ነበር፡፡
መንፈሳዊነት የኢትዮጵያውያን ልዩና ድንቅ ፍልስፍና ነው፡፡ ይህን ለማወቅና ለመረዳት ደግሞ የአኗኗር ይትባህላችንን፣ ተረቶቻችንን፣ ስነ ቃሎችችንን በጥልቀት መፈተሽና መመርመር የግድ ና፡፡ በተለይ በስነ ግጥምና በቅኔ ፍልስፍናችን ጎልቶ ይታያል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ ያልኳቸውን ፍሬ ነገሮች፣ በቻልኩት አቅም ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡
የአኗኗር ይትባህላችን
አኗኗራችንን ስንመለከት፣ በአብሮነት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የአኗኗር ይትባህላችን ከስነ- ምግባር ህግጋት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ‹ለ ሰው መድሃኒቱ ሰው ነው:: አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም፡፡ አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም ወዘተሰ፡፡”የሚሉት የሀገራችን ብሂሎች፣ ለአብሮነት ያለንን ዋጋ ከፍ አድርገው ያሳዩናል፡፡ የቀደሙት የሀገራችን ሰዎች ቤት ሲቀልሱ በደቦ ነው፡፡ አዝመራቸውን ሲሰበስቡና ሲወቁ በደቦ ነው፡፡ ሀዘንና ደስታ (ለቅሶና ሰርግ) በደቦ የሚከናወኑ ድንቅ ትዕውፊቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ከውስጣዊ መንፈሳቸው የመነጩ የመረዳዳት፣ የመተሳሰብና የመተባበር ተግባሮች ናቸው፡፡
በለቅሶ ጊዜ አብሮ በማልቀስ፣ አብረን እናዝናለን፡፡ ሀዘን የገጠማቸውን ሰዎች ‹ጽናቱን ይስጣችሁ! ሀዘናችሁን ያልልላችሁ ! ወዘተ› በማለት ከሀዘናቸው እንዲወጡ ብርታት እንሰጣለን፡፡ አንድ መንገደኛ በጉዞው ላይ የማያውቀው የለቅሶ ድንኳን ቢገጥመው ረግጦት አይሄድም፡፡ ከድንኳኑ ገብቶ ትንሽ ተቀምጦ ይቆይና፤‹ብርታቱን ይስጣችሁ› ብሎ ይወጣል እንጂ፡፡
በደስታ ጊዜም ‹ደስታችሁ ደስታችን ነው› በማለት በመዝፈን፣ በእስክስታ ፣ በማጨብጨብና በእልልታ የደስታቸው ተካፋይ የሚሆነው በርካታ ነው፡፡ በሀዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ እንዲሁም ድግስ ሲደገስ ተጋባዥ የሆኑ ሰዎች ምግብና የሚጠጣ ነገር ይዞ የመሄድ ልምድ አለ፡፡ ለችግራቸው ጊዜ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት ዘመናዊው ዓለም የሚጠቀምበት የባንክና ኢንሹራንስ ድርጅቶች ከመምጣታቸው በፊት ዕድር፣ ዕቁብና ማህበር በመመስረት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ይህ ሁኔታ ቢቀዘቅዝም ጨርሶ ግን አልጠፋም፡፡
እርስ በርስ የመተሳሰባችን ሌላው ማሳያ ሰላምታ አሰጣጣችን ነው፡፡ ሰላምታ አሰጣጣችን የሚጀምረው  የሰዎቹን ጤንነትና ደህንነት በመጠየቅ ነው፡፡ ‹‹ደህና ነህ/ ሽ፣  ደህና አደርክ/ሽ፣ ደህና አረፈድክ /ሽ/ ፣ ደህና ዋልክ /ሽ/፣ ደህና አመሸህ/ ሽ/፣ ደህና ሰነበትክ/ ደህና ከረምክ” በማለት የሰላምታ ልውውጡ  ይደረጋል፡፡ ይህ የሚሆነው በዙሪያችን ችግር ሲኖር ብቻ ሳይሆን በማናቸውም ሁኔታ ላይ ነው፡፡ በደጉም በክፉም ጊዜ፡፡ ከዚህ የምንረዳው፤ ጤንነት ለሰው ልጆች መሰረታዊ  ነገር መሆኑን ነው፡፡ ከእነ ብሂሉስ “ዋናው ጤና ነው!” አይደል የምንለው:: ሠላምታ የምንሰጠው ለምናውቃቸው ሰዎች ብቻ አይደለም፤ ሁለትና ሶስት ጊዜ ያየናቸውን፣ አለፍ ሲልም የማናውቃቸውንም ጭምር ሰላም እንላለን፡፡ ይህም ነው ባህላችንን ድንቅ የሚያደርገው፡፡
የእንግዳ ተቀባይነት መንፈሳችንና ለሰው ልጆች ያለን ክብር የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን:: ማንም ይሁን ማን ፣ ከየትኛውም አካባቢ ይምጣ፤ደጃችን ላይ ሆኖ ‹‹የመሸበት እንግዳ ነኝ፤ መጠጊያ የሌለኝ›› ካለን ‹ቤት የእግዚሃር ነው› በማለት ወደ ቤታችን አስገብተን እግሩን አጥበን፣ አብልተንና አጠጥተን እንኳን ስለማንረካ፤ ከአልጋችን ወይም ከመደባችን ወርደን፣ ለእንግዳው ቦታ ለቀን የምናሳድር መሆናችን አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሌላው የእንግዳ ተቀባይነታችንና ለሰው ልጆች ያለን አክብሮት መገለጫ የሚሆነው፤ የእስራኤል ህዝብ በተለያየ ዘመናት ችግር ውስጥ ሲገባ፣ በእንግድነት ተቀብለን፣ያስተናገድን  ህዝብ መሆናችን ነው:: ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ “ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያንና የኢትዮጵያውያን ታሪክ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ፣ ገጽ 177 ላይ፤ ይሄንኑ የሚያጠናክር ሃሳብ ያነሳሉ፡፡
‹‹የዛሬ 2500 ዓመት በእስራኤል ሊቀ-ነብያት በነበረበት ሰዓት የባቢሎን (የዛሬው ኢራቅ) ንጉስ ናቡ-ከነነጾር፣ እስራኤልን ወርሮ፣ የሰለሞንን ቤተ መቅደስ በማፈራረስ፣ መጽሐፍቱን አቃጥሎና ህዝቡን በሰንሰለት አስሮ ወደ ባቢሎን ባጋዘበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ፣ እነዚህን አይሁዳውያን ወደ ግዛታቸው በማስገባት፣ ጥገኝነት በመስጠት ሳይወሰኑ፣ መሬትና ስራ እየሰጡ አስተናግደዋል::››
የእንግዳ ተቀባይነታችን ጉዳይ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ባህል ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም ከተለያዩ የጎረቤት ሀገራት የመጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በሀገራችን ተቀብለን ማስተናገዳችንን ቀጥለንበታል፡፡ በዚህም “ራሳችን ተቸግረን ለምን ስደተኞችን እንቀበላለን?” ብሎ የጠየቀና የተቃወመ አንድም ኢትዮጵያዊ  የለም፡፡ በቅርቡ ከሶሪያ ተሰደው ሀገራችን የገቡ የሶሪያ ዜጎችን ተቀብሎ በማስተናገድ፣ ህዝባችን እንግዳ ተቀባይነቱን አስመስክሯል፡፡  
የጥንት ኢትዮጵያውያን፣ ሀይማኖትንና ባህልን ሳይቀር ተቀብለው የራሳቸው አድርገውታል፡፡ ለምሳሌ የኦሪት፣ የክርስትናና የእስልምና ሃይማኖቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጎይተኦም ታዲዮስ ‹‹ ሐበሻ ማን ነው ?›› በሚል ርዕስ ለሁለተኛ ጊዜ ባሳተመው መጽሐፍ፣ ገጽ 89 ላይ፣ ‹‹ሦስት ታላላቅ ሃይማኖቶችን በሰላማዊ መንገድ ወደ ሐበሻ ምድር በግለሰብና በመንግስት ደረጃ መግባታቸው፣ እኛ ሐበሾች ከፍ ያለ የስነ አመክንዮ ተፈጥሮ እንደነበረን ማስረጃ ነው፡፡›› በማለት ኢትዮጵያ ሁሉንም የዓለም ህዝብ፣ በንጹህ ልቦናዋ የምትቀበል የፍቅር ሀገር እንደሆነች ያስረዳል፡፡ በርካታ የሃይማኖትና የታሪክ ልሂቃን፤ ኢስላም በዓለም ላይ እስኪጠነክር ድረስ ለነብዩ መሐመድ ቤተሰቦች ጥገኝነት የሰጡና በተዘዋዋሪም እስልምና እንዲስፋፋ ያደረጉት ክርስቲያን ነገስታት እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
“በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች በሃይማኖት ልዩነቶች ካለመጋጨታቸውም በላይ ተፋቅረውና ተባብረው ቤተክርስቲያናትንና መስጊዶችን አንዱ ለሌላው በመገንባታቸው፤ አብረው በመጸለያቸውና ከተዋደዱ ያለ ብዙ ችግር መጋባት በመቻላቸው ልንኮራ ይገባል::” (ፍቅሬ፣231) ከዚህ ሀሳብ መገንዘብ ያለብን ፍሬ ጉዳይ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ፍቅር ከሁሉም ነገር በላይ መሆኑን ተረድተን፣ በህይወታችንም መተግበር ልማዳችን ማድረግ እንዳለብን  ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት የታማኝነት፣ የእኩልነት፣ የብርታት፣ የትዕግስት፣ የጽናት፣ የሰው አክባሪነትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ መሆኑን ለማረጋገጥ  ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ይህ ጠባይ የመንፈሳዊነት ምንጭና  የመንፈሳዊነት መንገዳችን መሆኑን ይጠቁማል፡፡
ለሰው ልጅ ካለን ክብር የተነሳ ቀደም ባለው ዘመን፤ ‹‹ሽሮ፣ በርበሬ፣ እንጀራ የሚሸጡ ሰዎች ምናልባት ሽሮው ወይም በርበሬው ቅመም አንሶበት ከሆነ (ሻጮቹ ካላመኑበት) ‹‹ይሄማ ለሰው አይሸጥም፡፡ ለኛ እናድርገውና ለሽያጭ ሌላ ይዘጋጅ›› በማለት ለደንበኛቸው ልዩ ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር፡፡ እንጀራቸውም ስስ መስሎ ከታያቸው እንደዚያው፡፡ ‹አንገት ከሚሰበር ባይበላስ ቢቀር › ማለት ታዲያ ይሄ አይደል!?
ለሰው ልጅ ለራሱ (ሰብአዊ ፍጡር እንደ ማለት) ይቅርና የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት ለሆነው ምግብ እንኳን ትልቅ አክብሮት ነበረን:: ምግብ በልተን ያተረፍነውን በንጹህ ዕቃ እናስቀምጣለን፡፡ ከመሬት የወደቀን እህል (እንጀራ ወይም ዳቦ) አንስተን ‹ እፍ እፍ› ብለን አቦራውን አራግፈን፣ ንጹህ ድንጋይ ላይ የማስቀመጥ ልማድ  ያለን ህዝብ ነን፡፡ ምርቃታችን እራሱ ‹ እህል ውሃ አያሳጣህ /ሽ! ብሩክ ሁኑ፣ መልካም ትዳር ይስጥህ፣ ዕድሜ ይስጥህ፣ ክፉ አይድረስብህ!…› የሚል ነው፡፡ ምርቃት ደግሞ የመልካም ስራ ሽልማት ነው፤ ማበረታቻ፡፡
የሰው ልጅ በህይወት እያለ ብቻ ሳይሆን ሲሞትም (ሲያርፍ) ክብር ይሰጣሉ፡፡ ‹ከሞቱ አሟሟቱ› የሚለው ብሂል ይህንኑ ያሳያል:: ስለ ህይወትና ሞት ያላቸውን ጥልቅ ግንዛቤ ያመለክታል፡፡ ሞት የማይቀር ዕጣ ፈንታ እንደሆነ አምነው መቀበላቸውን ያጸኸያል፡፡ የሰው ልጅ በህይወትና በሞት መካከል እንደሚመላለስ፣ በህይወት ዘመናቸው፣ ተፈጥሮን አስተውለውና መርምረው የደረሱበት ሀቅ ነው፡፡
ቀደምቶቹ አያቶቻችንና አባቶቻችን ተፈጥሮን የተረዱና የሚረዱ ነበሩ፡፡ “ያልተማረና ያልሰለጠነ” የሚባለው የገጠሩ ህዝብ፣ በድቅድቅ ጨለማ፣ ያለ ምንም ዘመናዊ የሰዓት መቁጠሪያ፣ ሰማዩንና ከዋክብቶችን በማስተዋል ብቻ፣ ሰዓቱን በትክክል  የመናገር ጥበብ አላቸው፡፡ ይህም አስደናቂ ነገር ነው፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እንድሪስ በወርሃ ህዳር 2012 ዓ.ም በሸገር ኤፍኤም 102.1 የጨዋታ ፕሮግራም ላይ ከጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ስለ ገበሬው የሀገራችን ህዝብ ንቃት ሲናገሩ፡- “ገበሬው በጣም አስተዋይ ነው:: አላህን የሚፈራውንና የማይፈራውን ሰው አስተውሎ በማየትና በንግግሩ ያውቁታል:: እንደ ከተማው ሰው፣ ተማረ እንደሚባለው፣ በሰማው ወሬ አይነዳም” ብለዋል፡፡
የሰው ልጅ በመማር ብቻ ሳይሆን በመኖር ይማራል፡፡ “የሰው አእምሮ እውነቱን ያውቃል:: ባይማርም እንኳን እውነትን ከመኖር ይማራል::” በማለት ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ፤ ‹አለመኖር› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ  ውስጥ ይገልጻሉ፡፡  ስለ ሰው ልጅ ሕይወትና አኗኗር ኮንፊሺየስን የሚጠቅሱት ዶ/ር ዳዊት፤ የሰው ልጅ ምን አይነት ኑሮ መኖር እንዳለበት ደግሞ የመምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር) “ምንትኑ ሰብኸ? ሰው ምንድነው? የማንነት ትርጉም ፍለጋ”  መጽሐፍን ይጠቁማሉ፡፡ “የሰው ልጅ ጥሩ ህይወት እንዲኖረው ከተፈለገ አራት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው፡፡ ቸርነት፣ ተገቢነት፣ እውነተኛነትና ጥበብ ናቸው፡፡
እነዚህ የጎደሉት ሠው የሌላ ሰውነትን ያጎድላል፡፡” ከዚህ ሐሳብ በመነሳት፣ የሀገራችን ገበሬዎች፣ በህሊናቸው በመመራትና በመኖር፣ ለሰው ልጅ አስፈላጊ የተባሉትን ጠባዮች ገንዘባቸው አድርገው መያዛቸውን መረዳት አያዳግትም፡፡
ከዚህ በታች የሀገራችን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በግጥሞቻቸው ከገለጹዋቸው ሃሳቦች ጥቂቶችን በየመሀሉ እየነቀስኩ  አቀርባለሁ፡፡ ደራሲና ገጣሚ በዕውቀቱ ስዩም ‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች› በሚል ርዕስ ባሳተመው የግጥም መድበሉ ውስጥ ‹አዳምና ጥበቡ› በሚል የከተበው ግጥሙ እንዲህ ይላል፡-
አዳምና ጥበቡ
በመጀመሪያ አዳም ሳተ
ከገነትም ተጎተተ፡፡
አዳም ከገነት ሲባረር
እነሆ እርቃኑን ነበር፡፡
ብርዱ ውርጩ አንዘፈዘፈው ዶፉ ጠሉ
ወረደበት
ያኝዠረገገውን አይተው አዕዋፍ አራዊት
ሳቁበት፡፡
ይሄነ አዳም ተማረረ
ተማረረና ተመራመረ፡፡
ተመራምሮም አልቀረ
ጋቢ መስራት ጀመረ፡፡
ጅማሬውን ወደደ
ተጀምሮ እስኪፈጸም የእድሜውን ግማሽ
ወሰደ
ያሳዝናል፤ ጋቢውን ጨርሶ ሲቋጭ ገላው
ብርዱን ለመደ፡፡
ገጣሚው፤ ልምድ ወሳኝ የእውቀት ምንጭ መሆኑን፣ ለልምድ መኖር እንጂ ሌላ አቋራጭ መንገድ እንደሌለው በቅኔ ያስረዳናል፡፡  ‹‹ወዳጄ ልቤና ሌሎችም›› በሚል ርዕስ ብላቴን ሕሩይ ወልደ ስላሴ ለንባብ ባበቁት መጽሐፍ፣ ገጽ 36 ላይ፣ እንዲህ የሚል ግጥም ሰፍሯል፡-
‹‹የተወለደ ካዳም፣
መሬት ያልገዛ የለም፤
ግብሩን መገበር አቅቷቸው፣
ገና ብዙ ዕዳ አለባቸው፡፡››
(ይቀጥላል)

Read 3747 times