Sunday, 05 January 2020 00:00

“ድፎ ዳቦ በትእዛዝ እንደፋለን”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  “ነጋ ጠባ…“የአምናን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው…” ከማለት የአምናን ለአምና ትተን “ለከርሞ የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል…” ብለን ለማሰብም፣ ተስፋ ለማድረግም፤ የማሰብና ተስፋ የማድረግ አቅሙ ያስፈልገናል፡፡--”
             
              እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
በነገራችን ላይ የበዓል አንዱ አሪፉ ነገር፣ ለአንዲትም ቀን ትሁን ለአንድ ቀን ተኩል፣ እንደምንም ሃያ አራት ሰዓት ካለችን ላይ አልንቀሳቀስ ያለውን ከባድ ደመና ያሳስበናል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ችግሮቻችን ላይ ጀርባችንን አዙረን የተወጠሩ ህዋሳቶቻችንን ፋታ ልንሰጣቸው፣  እኛም ዘና ለማለት እንሞክራለን:: ልክ ነዋ…ለተወሰነች ቀን ለመፍታታት የምንሞክረው እኮ…አለ አይደል…“ነገም ሌላ ቀን ነው፣” ለማለትም ነው፡፡ ነጋ ጠባ…“የአምናን ረገምኩት ለአፌ ለከት የለው…” ከማለት የአምናን ለአምና ትተን “ለከርሞ የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል…” ብለን ለማሰብም፣ ተስፋ ለማድረግም የማሰብና ተስፋ የማድረግ አቅሙ ያስፈልገናል፡፡
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…የ‘አምና’ን ነገር ካነሳን አይቀር፣ እንደው ከዚህ የኋላ ማርሽ ጉዞ የሚገላግለን ምን አይነት አጠፋሪስ ይሆን! ልክ ነዋ…ዛሬ ስንትና ስንት ጉድ እየታየ፣ ነገና ከነገ ወዲያ ላይ የኢዶኔዥያ ሱናሚ የሚመስል ነገር ‘መጣሁ፣ ቀረሁ’ እያለ፣ ምን የኋልዮሽ ንትርክ ነው! “ያኔ ከአለቅየው ጋር የተጣላሁ ጊዜ፣ ለእሱ አግዘህ ያደረግኸኝን የረሳሁ መሰለህ!” ይሄኔ መልሱ ምን ቢሆን አሪፍ ይሆናል መሰላችሁ…
“እና ምን ይጠበስ! ከፈለግህ እርሳው፤ ካልፈለግህ ደግሞ ክንድህ ላይ ተነቀሰው፡፡” በቃ፡፡ “የዛሬ አምስት ዓመት ለትዳር ብጠይቅሽ ‘ሞቼ ነው፣ ቆሜ! ሲያልፍም አይነካኝ’ ያልሽኝን የረሳሁ መሰለሽ?” አይነት ነገር እኮ የቅሽምና ፕሪሚየር ሊግ በሉት፡፡ እናማ… ይሄን ወሬ አሁን ምን አመጣው! የእሷዬዋ መልስ ምን ቢሆን ጥሩ ይሆን መሰላችሁ…
አንተም ባለትዳር፣ እኔም ባለትዳር
እረፍና ቁጭ በል፣ አትበለኝ ዳር፣ ዳር
በለው! በዚህ የግጥም እርፍናዬ፣ አንዲትም የግጥም ዝግጅት ላይ አቅራቢ አለመሆኔ ‘ፌይር’ ነው?! ቂ…ቂ…ቂ…  የምር ግን ከአንዳንድ የምንሰማቸው ‘ግጥሞች’…አለ አይደል…“አትበለኝ ዳር፣ ዳር” በስንት ጣእሟ!   
እናላችሁ…ነገና  ከነገ ወዲያ የሚያመጡልንን ወይም የሚያመጡብንን ነገሮች እሱ ይወቃቸው እንጂ…  ቢያንስ የበዓል እለት ዘና ለማለት መሞከር መልካም ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከሚያስደስቱን ነገሮች ይልቅ የሚያሳስቡን፣ የሚያስጨንቁን፣ እንቅልፍ የሚነሱን  ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ነገ “ሀገር ምን ትሆን ይሆን?” ብቻ ሳይሆን ነገ… “የእኔስ ግዴለም፣ እዳው ገብስ ነው፡፡ ቤተሰቤን ምን አብልቼ አሳድራለሁ?” የሚባልበት ጊዜ ነው፡፡ 
እኔ የምለው…ተደጋግሞ አንደሚወሳው አሁን ትልቁ ችግራችን የትኛው ‘…ኢስት’ ከየትኛው ‘…ኢስት’ ይሻላል የሚለው አይደለም፤ እንኳንስ ተንጠራርቶ ለመድረስ፣ ዘሎ ለመንካት አስቸጋሪ የሆነው የኑሮ ነገር ነው፡፡ እለት ተእለት ከአቅማችን በላይ የሆኑ የምግብ ፍጆታዎች እየጨመሩ ነው፡፡ እናላችሁ… የፖለቲካ ሰዎች የኑሮ መወደድ ለምን የእኛን ያህል እንደማያስጨንቃቸው ማስገረም ብቻ ሳይሆን ብዙ ጥያቄዎችም እየፈጠሩብን ነው፤፡  እኛ እኮ በየጓዳችን “አዳሜ በየሆቴሉ በግብዣ ስም ከርሷን እየሞላች፤ እኛ ምስኪኖቹን ማን ከሰው ይቁጠርን!” የምንለው የመለፍለፍ ጠባይ ኖሮብን ሳይሆን የኑሮ ሸክሙ በዝቶብን ነው፡፡  
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ትልቅ ችግር የሆነብን ነገር ምን መሰላችሁ… ተናጋሪው በዝቶ አድማጩ ያነሰባት ሀገር መሆኗ ነው፡፡ “እንደምን አደርክ?” የሚለው ሰላምታ አንድ መቶ አንድ ስፍራ ተሰነጣጥቆ፣ እንደ ፖለቲካ አቋም ሊወሰድ ምንም የማይቀርበት ዘመን ላይ ነን፡፡ “ሦስቴ እንዴት ዋላችሁ አንዱ ለነገር ነው” ይባል የነበረው ቀርቶ፣ አሁን ገና “እንዴት ዋላችሁ”… ሲባል…“ይህ ነገር ለእኛ ነው” አይነት ሊያስፎክር ሁሉ ይችላል፡፡
እናላችሁ…የበዓል ሰሞን ነው፡፡ በእንደዚህ አይነት ጊዜ ደግሞ…አለ አይደል… በተለይ በዓመት በዓል ገበያ ብንነጫነጭም፣ በተቻለ መጠን መልካሙን መስማት ነው የምንፈልገው:: አሁን ያለንበት ሁኔታ ደግሞ ብዙም ለዚህ አላመች ብሎናል፡፡   
‘ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ’ በአውሮፓውያኑ 2020 ግጭት ከሚያሰጋቸው አስር ሀገራት መካከል እኛን ወደ ላይ አስጠግቶ አስቀምጦናል፡፡ “ወሬ አድርጎ ያስቀርልን!” ከማለት ውጪ ምን ማድረግ ይቻላል! ክፋቱ ደግሞ ድርጅቱ፣ በጥናት እንጂ በወሬ መግለጫ የሚያወጣ አይነት አለመሆኑ ነው፡፡ 
ታዲያላችሁ…ከችግር ለመውጣት መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ አሁን ግን ምናልባት እየተናገርን ሊሆን ይችላል እንጂ እየተነጋገርን አይደለም:: ለመነጋገር በዚህ ወገን ያለው ተናጋሪ ብቻ ሳይሆን በዛኛው ወገን አድማጭ ያስፈልጋል:: አሁን ችግር የሆነው…“ቀይ” ብላችሁ ያወራችሁትን “ጥቁር” ብሎ የሚያዳምጥ እየበዛ መምጣቱ ነው፡፡ 
ይቺን ስሙኝማ…ዳቦ ቤት ነው፡፡ እናም… “ድፎ ዳቦ በትእዛዝ እንደፋለን፣” የሚል ማስታወቂያ አለ፡፡ እናላችሁ…መቼም ዘንድሮ የ‘ጉልቤ ዘመናዊነት’ በዝቶ የለ፣ አንዱ ዘመናዊ ነኝ ባይ፣ ማስታወቂያውን ያይና እንዲህ ሲል ይጠይቃል...“ዳቦ ብቻ ነው የምትደፉት?” ይሄኔ ሠራተኛው ብሽቅ ብሎ፣ ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው… “አይ ያስቸገረ ካለም በትእዛዝ እንደፋለን!” አለውና አረፈው፡፡ ምን ያድርግ! ዳቦ ቤት ሆኖ፣ በግልጽ “ድፎ ዳቦ በትእዛዝ እንደፋለን” ተብሎ ተለጥፎ “ዳቦ ብቻ ነው የምትደፉት?” ብሎ ጥያቄ፣ምን የሚሉት የሞንጎሊያ አራድነት ነው!
ታዲያላችሁ…ዘንድሮ እኮ እንዲህ አይነት ‘አሸር በአሸር ዘመናዊነት’ ነው አንድም እየበጠበጠን ያለው፡፡ እንበልና የሆነ ‘ቶይሌት’ የሚል የተጻፈበት በር ለመግባት በመክፈት ላይ ናችሁ፡፡ እና የሆነ ‘አሸር በአሸር ዘመናዊ’ ድንገት መጥቶ “ልትጸዳዳ ነው የምትገባው?!” ቢል ያታያችሁ፡፡ “አይ፤ የሆነ ሴሚናር ስላለብኝ ነው የምገባው” አትሉት ነገር!
ቢል ክሊንተን እንዲህ አሉ ይባላል… “ፕሬዝደንት መሆን ልክ የመቃብር ስፍራ እንደመጠበቅ ነው፡፡ እግርህ ስር ብዙ ሰዎች አሉ:: ግን ማንም አያዳምጥህም፡፡”
እግረ መንገድ… የሆነች ነገር ትዝ አለችኛማ…ሰውየው ጓደኛውን…
“ስማ፤ ይቺን ባርኔጣ ስታደርግ እድሜህ እኮ በአስራ አምስት ነው የሚቀንሰው” ይለዋል፡፡
“አትለኝም!”
“እውነቴን ነው፡፡ ግን አሁን እድሜህ ስንት ነው?
“ሠላሳ ሦስት፡፡”
“ባርኔጣዋን ሳታደርግ ማለቴ ነው፡፡”
የሚያዳምጥ ጠፋ! አፍ የሚናገረው አንድ ነገር፣ ጆሮ የሚሰማው ሌላ ነገር፡፡
የምር እኮ ህይወት፤ በበጨ/ጠቆረ አይነት የምትሄድ ነው የሚመስለው፡፡
ተናጋሪው በዝቷል፡፡
ሁሉንም ሰው ማመን መጥፎ ነው፡፡ ማንንም አለማመንም መጥፎ ነው፡፡ ክፋቱ ግን የሚነገረውና የሚደመጠው አልገጥም እያለን፣ ሁሉንም ወዳለማመን እየተገፋን ነው:: የሚባለውና የሚሆነው እየተዘበራረቀብን ነው፡፡ ሠዎች እንደ ኦሎምፒክ ጅምናስቲከኛ፣ ባህሪያቸውን በየቀኑና በየሦስት ቀኑ እየለዋወጡብን፣ ሁሉንም ወዳለማመን እየተገፋን ነው፡፡  
የሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት፣ ለገና በዓል አክባሪዎች የገበያ ቀናት ናቸው፡፡ መቼም ሁሉም  እንደየ አቅሙ እለቱን በደስታ ለማሳለፍ መሞከሩ አይቀርም፡፡ እናማ...ለገበያ ሲወጣ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ለማለት ነው፡፡ ይቺ ከተማ ጠንቀቅ ካላሉባት፣ አስቸጋሪ እየሆነች ነው፡፡ ጥንቃቄ! ጥንቃቄ!
እናማ… “ድፎ ዳቦ በትእዛዝ እንደፋለን” የሚለው ለጊዜውም ቢሆን በቀረበበት መልኩ ቢተረጎም አሪፍ ነው፡፡
በድጋሚ መልካም በዓል!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 1496 times