Sunday, 05 January 2020 00:00

የሰለጠነ ፖለቲካ እንዲህ ነው!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(1 Vote)

    በእኛ አገር ፖለቲካ መጠፋፋት የተለመደ ነው፡፡ የምንታወቅበት መለያችን ነው፡፡ ደርግና መኢሶን እጅና ጓንት ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከኢሕአፓ ጋር በሌላ ግንባር ቆመው፤ ‹‹የጠላቴ ጠላት›› በሚል እጃቸውን ሰንዝረዋል። በዚህ ፀብ ውስጥ ሃይሌ ፊዳ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የተሻለ አቋም እንደነበረው ተጽፏል፡፡ ሃይሌ፤ ለመንግሥቱ ኃ/ማርያም ሶሻሊዝምን አስጠንቷል፣ እንጭጩ ‹‹አብዮት›› እንዲበስል አግዟል። በኋላ ግን መንግሥቱ ኃ/ማርያም ‹‹አብዮት ልጆቿንም ትበላለች›› በሚል መርሃቸው፣ በ1979 ዓ.ም ከብዙ ስቃይ በኋላ አስወግደውታል፡፡ ማስወገድ የሶሻሊስቶች መርህ፣ የእነ ማኦም የትግል አቅጣጫ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ የዚያ ፍትፍት ጐራሽ ሆና፣ አሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ ልጆቿን ተራራ ስትቧጥጥ ኖራለች። የብዙ ሺህ ሰዎች ደም ያለ ፍርድ በከንቱ ፈስሷል። አላስፈላጊ ጦርነቶች ተደርገው በቢሊዮን  ብሮች የሚሰላ የአገር ሀብት ወድሟል። ምክንያቱም የእነርሱ መርህ ልዩነትን በውይይት መፍታት ሳይሆን በሀይል ማስወገድ ነው፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ሞት ምክንያት ተፈጥሮ የነበረውን የስልጣን ክፍተት ለመሙላት ልጅ ኢያሱ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ ሌላኛው አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ውስጥ ውስጡን ታግለው፣ ወጣቱን ልዑል ከሥልጣን ፈንግለውታል። በመጨረሻም በእስር ቤት ማቅቆ እንዲወገድ አድርገዋል፡፡ ለዚህም ነው መወጋገድ ለኢትዮጵያውያን ብርቃቸው አይደለም የምንለው፡፡ ተጀምሮ እስኪያልቅ ታሪካችን ይኸው ነው፡፡
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በተራቸው የአገሪቱን ታላቅ የጦር ሰው ጀኔራል አማን ሚካኤል አምዶንን በታንክ አስጨፍልቀዋል፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም፡፡ ጀኔራል ተፈሪ ባንተን፣ ኮሎኔል አጥናፉ አባተን በተመሳሳይ  መንገድ ከሥልጣን አስወግደዋል። ሁሌም ግን ጥፋተኛ የሚደረጉት የሚወገዱ ወገኖች ናቸው፡፡ ብዙዎችም መዓት ዲሪቶ ታሪካቸው ላይ ተለጥፎላቸው ወደ መቃብር ተልከዋል፡፡
እዚህ አገር በሥልጣን ተጋጭቶ ከሞት ማምለጥ ብዙም አልተለመደም፡፡ ምናልባት በቁም ቅጣት ብቻ ያመለጡት የሕወሃት ትልልቅ ባለሥልጣናት ሳይሆኑ አይቀርም፡፡ ሕወሃት ተሰንጥቃ አገር ሲናጥ፣ አቶ መለሰ ክፉኛ የተገዳደሯቸውን ውስጥ ውስጡን ሰርስረው በመጣል ዘብጥያ አወረዷቸው እንጂ እስከ መግደል ድረስ አልጨከኑባቸውም። የትግል አጋራቸውን ለአቶ ስዬ አብርሃ በአንድ ቀን ሕግ አውጥተው፣ ከእስር ቤት ወደ እስር ቤት ያስገቡት አቶ መለስ፤ ቢያንስ ቃታ አለመሳባቸው ትልቅ ለውጥ ነበር ብንል አልተጋነነም፡፡ እንግዲህ ለዘመናት የዘለቀ የአገራችን ታሪክ ይኸው ነው፡፡ የሀሳብ ልዩነት ሲኖር አሳድዶ መግደል፤ ከምድረ ገጽ ማጥፋት ከዚህ የተለየ መፍትሔ ወይም አማራጭ አናውቅም፡፡
 አሁን ለኢትዮጵያ አዲሱ ነገር ይህ ነው፡፡ ለውጡ ብዙ ሳንካዎች ቢኖሩትም፣ ተስፋ የሚሰጥና የሚያኮራ ስልጡን መንገድ ይዟል፡፡ በርግጥ ኢህአዴግ አግበስብሶ የያዛቸው ሆድ አደሮች ለውጡን ክፉኛ ተገዳድረውታል፡፡
ትልቁ ቁም ነገር የለውጡ ዘዋሪዎች በንፁህ ህሊና ማሰባቸውና የሰለጠነ መስመር መከተላቸው ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ ጐምቱ ባለስልጣናት ተጠራርገው ዘብጥያ አልተወረወሩም አልተገደሉም፡፡  
የኦሮሚያ ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ጀኔራል ከማል ገልቹ እንደ ልባቸው መንግሥትን ሲዘልፉ ሀይለ ቃል ሲናገሩ፣ በስም ማጥፋት ወይም በሌላ ተብሎ አልተከለሱም፡፡ አንዳንድ የህወሐሃት አመራሮችም እንዲሁ፡፡ ይሄ ደግሞ ወደ ሰለጠነ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየተጓዝን መሆኑን ያመላክታል፡፡
ዛሬ አገር ለማፍረስ የሚወዛወዙ ሕመምተኞችን የፈለፈለው ሃይማኖት ነው፡፡ ጣሊያን በጦርነት ሞክሮ ያቃተውን ህዝብን የመከፋፈል ስውር ደባ፤ በሃይማኖት ሰበብ ዘርቶ አብቅሏል፡፡ ዘረኝነት መርዝ ነው፡፡ ውስጡ ጥላቻ አለ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ‹‹ወንድሙን የጠላ ነፍስ ገዳይ ነው›› ይላል። እውነተኛ የፈጣሪ ተከታዮች ግን ሁሌ በፍቅርና በአንድነት ይቆማሉ፡፡  አገር ያድናሉ፣ ትውልድ ይታደጋሉ፡፡ በማስወገድ ሳይሆን በመነጋገር ያምናሉ፡፡
ዛሬ በእኛ ሕይወት የሚንፀባረቀው ነገር የእምነታችን፣ የባህላችንና የሥነ ልቡናዊ ዳራችን ውጤት ነው፡፡ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ሶሻሊስታዊ ጥንስስና እርሾም በልባችን አለው፡፡ ያ ደግሞ እርቅንና ይቅርታን ሳይሆን ጥላቻንና ማስወገድን ነው ያስተማረን፡፡  
ሰሞኑን በአገራችን በሁለቱ የለውጥ መሪዎች መካከል የተፈጠረው ሰላምና እርቅ ለአንዳንዶች ያልተዋጠላቸው ለዚህ ነው፡፡ አቶ ለማ መገርሳ፣ እንደ ስታሊንና እንደ ትሮቶስኪ፣ እንደ ኮሎኔል መንግሥቱና ኮሎኔል አጥናፉ ወይም እንደ መለስ ዜናዊና ስዬ አብርሃ እንዲሆኑ ነበር የተጠበቀው፡፡ በዚህም የተነሳ ስለዚህም ተስማሙ ሲባል ‹‹ቀድሞም አልተጣሉም ነበር›› የሚሉ ድምፆች በዙ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ለማ መገርሳን ከዷቸው›› የሚል ወሬ የተናፈሰው አሁን አይደለም፤ በጣም ቆይቷል፡፡
“መሪዎቹ ድራማ እየሰሩብን ነው” ያሉም አልጠፋም፡፡ እኛተቀበልነውም፣ አልተቀበልነውም ኦቦ ለማ መገርሳ ወደ ለውጡ መስመር ተቀላቅለዋል፤ ፍቅራቸው የማይነጥፈው ጠቅላይ ሚኒስትሩም፤ እጆቻቸውን ዘርግተው ተቀብለዋቸዋል፡፡ ግን እኒህ ሰው ለዚች አገር ባይመጡ፤ የማያልቅ ፍቅርና የማይነጥፍ ምህረት ባይኖራቸው፣ ይህንን ሁሉ መከራ እናልፈው ነበር? አይመስለኝም፡፡
የሰሞኑን ድንጋጤና ስጋት ወደ ሰላም ለመመለስ የደከሙትን አባገዳዎች፣ ተቋማትና  ማመስገን የሚገባ ይመስለኛል፡፡ የለውጡ ፊታውራሪዎችም በዚህ ሊመሰገኑ ይገባል፡። የሰለጠነ ሰው የሃሳብ ልዩነቱንና ችግሩን የሚፈታው በሰለጠነ መንገድ ነው፡፡ በመጠፋፋት ሳይሆን በውይይት አይደለም፡፡
ኦቦ ለማ መገርሳም የደከሙበትን እርሻ ጥለው ባለመቅረትዎ ምሥጋና ይገባዎታል። ለኮብላዩ ልጅ የተመረጠች የሰባውን ፊሪዳ፣ የእጅ ቀለበት፣ ደስታና ምስጋና ተመኝቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን በእሳት ውስጥ ብታልፍ አትቃጠልም። በውሃ ውስጥ ብትሄድ አትሰጥምም፤ ከሚገጥማት ፈተና ይልቅ የእግዚአብሔር ማዳን ያይላልና፡፡                          


Read 2327 times