Wednesday, 08 January 2020 00:00

የታገል ሠይፉ የፖለቲካ ስላቅ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(1 Vote)

   ደራሲና ገጣሚ ታገል ሰይፉ በያዝነው ዓመት “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር” በሚል ርእስ ልብ ወለድ ድርሰቱን አቅርቦልናል፡፡ ይህንን መጽሐፍ አነበብኩና አስተያየት ለመጻፍ አሰብኩ፡፡ ግን እንዴት ብዬ እንደምጀምር ሳስብ፣ ሳስብ ቆየሁና አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ 30 ዓመታት ያህል ወደ ኋላ ተመለስኩ፡፡
ታገል ሰይፉና እኔ ከተዋወቅን ሶስት አሰርት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ስንተዋወቅ እሱ የ9ኛ ክፍል እኔ የኮሜርስ ተማሪ ነበርን:: የመጀመሪያ መጽሐፉን ሲያሳትም፣ በጀርባ ሽፋኑ ላይ አስተያየት የጻፍኩት እኔ ነበርኩ፡፡ ገና መጽሐፉን ሳያሳትም የመጀመሪያ ቃለ ምልልስ ያደረግሁለትም እኔ ነበርኩ፡፡ “ታገል የነገው ሰው” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ቃለ ምልልስ፣ ቱሪዝም ኮሚሽን ያሳትመው በነበረው “ዜና ቱሪዝም” የተባለ ጋዜጣ ላይ ነበር የታተመው - በ1981 ዓ.ም፡፡ ያኔ ታገል የ15 ዓመት ታዳጊ ነበር፣ እኔ ደግሞ የ20 ዓመት ወጣት! የአሁኑን እኛ ለማወቅ 30 ዓመት መደመር ነው፡፡ አቤት አቤት አቤት… ጊዜው እንዴት ይበራል ጃል!
ከታገል የመጀመሪያ ቃለ ምልልስ…
በ1981 ዓ.ም ከታገል ጋር ያደረግኩትን ቃለ ምልልስ እንዲህ በማለት ነበር የጀመርኩት “እንግሊዛዊውን ባለቅኔና ጸሐፌ ተውኔት ዊልያም ሼክስፒርን ታውቁታላችሁ?… ፎቶግራፉን አይታችሁት ከሆነ [ታገል] በጥቂቱ እሱን ይመስላል፡፡ ምናልባት የደራሲነት ደም ተጋብቶበት እንደሆነም እንጃ፤ አንድ ሰሞን ሉጫ ፀጉሩን አሳድጎ፤ ከአናቱ ጀምሮ ወደ ፊት - ወደ ኋላ - ወደ ግራና ወደ ቀኝ ሞሽጦ፣ የተጠረጠረ የሐበሻ ቀሚስ አስመስሎ ያበጥረው ነበር…” በማለት ነበር፡፡ ይህንን ቃለ ምልልስ ካዘጋጀሁ በኋላ፣ እኔና ታገል ከሜክሲኮ አደባባይ ወደ አብዮት አደባባይ ዜና ቱሪዝም ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስንሄድ፣ ለገሀር ጉምሩክ አካባቢ ስንደርስ፣ ከየት እንደመጣ ያላወቅነው አሞራ፤ በታገል አናት ላይ ኩሱን ጥሎበት አለፈ፡፡ ታገል ምን ወደቀብኝ ብሎ ጭንቅላቱን ሲዳብስና ሲደናገጥ ያዩ በአካባቢው የነበሩ ሰዎች “ተወው ሲሳይ ነው፣ ሲሳይ ነው” ማለታቸውን እኔም ታገልም በጊዜ መርዘም፣ የምንዘነጋው አይደለም፡፡
አሁንም ያኔ ካደረግነው ቃለ ምልልስ ላይ ልጥቀስ፡፡ “ታገል በህጻንነቱ አስተዳደጉ እንዴት እንደነበር አጫውቶኛል፡፡ ቤተሰቦቹ የነገሩትን እንደነገረኝ ከሆነ፤ … ባህር ዳር እያሉ በተደጋጋሚ ይታመም ነበር፡፡ በየጊዜው ሀኪም ቤት እየሄደ ይመረመራል፡፡ ለውጥ ግን አልነበረውም:: ሊድን አልቻለም፡፡ [በወቅቱ በነበረው አስተሳሰብ መሰረት] የጎረቤት ሰዎች “ይህንን ልጅ ወደ አዋቂ ቤት ብትወስዱት ይሻላል” ብለው ወላጆቹን ይመክሯቸዋል፡፡ [የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ] አማራጭ አልነበራቸውም፣ ድኖ ነው! ጎረቤቶች ወሰዱት:: ጠንቋዩም፤ “አዬ… ይሄ ልጅ ዋጋ የለውም፡፡ አይተርፍም፡፡ እንዲያውም ከአሁን በኋላ የልጁ እድሜ 40 ቀን ብቻ ነው” አላቸው፡፡ ጎረቤቶች እናቱ ይህንን ጉድ እንዳይሰሙ አድርገው የታገል ሞት ይጠበቅ ጀመር…” ታገል ግን 40 ቀን ሳይሆን እነሆ 40 ዓመት አለፈው! እንዲያውም ከዚያን ጊዜ በኋላ እስከ አሁን ድረስ የከፋ ህመም ገጥሞት ወደ ሀኪም ቤት ሄዶ እንደማያውቅ ነግሮኛል፡፡
የታገል የመጀመሪያ ግጥም
ታገል የ12 ዓመት ታዳጊ ህፃን ሳለ የደረሰው የመጀመሪያ የስነ-ግጥም ሥራው ነው ከህዝብ ጋር ያስተዋወቀው፡፡ “ሠላም” በሚል ርእስ የጻፈው የመጀመሪያ ግጥሙ፣ ረዥም በመሆኑ በሦስት ቦታ ከፍሎ አንዱን ክፍል በለገዳዲ የትምህርት ስርጭት ሬዲዮ ጣቢያ፣ ሁለተኛውን ክፍል በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሑድ ፕሮግራም፣ ቀሪውን ሦስተኛ ክፍል በኢትዮጵያ ሬዲዮ የህፃናት ፕሮግራም ላይ አቅርቧል፡፡ ከዚያ ግጥም ላይ ጥቂት ስንኞች እንቀንጭብ፡-
“የሳይንስ የጥበብ፤ ፈጣሪና ሰሪው፣
በህዋ በራሪ፤ በጨረቃ ኗሪው፣
ዓለም ከተማውን፤ ህንፃ ያለበሳት፣
እሱ እንደገነባት፤ እሱው አፈረሳት፡፡
ብሎ ከመናገር፤ ተናግሮም ከማፈር፣
አፍሮም ከመጸጸት፤ አንጀት ከማሳረር፣
ጥበብ ፍልስፍናው፤ ምነው ቀልጦ ቢቀር፡፡
እንደ ጥንቱ ዘመን፤ ሆነን እንደ’ንስሳ፣
መኖር ይሻለናል፤ ከኒኩሌር አበሳ፡፡”
የታገል ገጠመኞች
ታገል እስከ 8ኛ ክፍል በጣም ጎበዝ ታማሪ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የኪነ-ጥበብ ዛር ሰፈረበትና በትምህርቱ እየቀነሰ፣ በድርሰቱ እየጨመረ ይሄድ ጀመር፡፡ 9ኛ ክፍል ሲገባ የድርሰት ስሜቱ ፈተና ሆነበት፡፡ መምህር ክፍል ገብቶ ሲያስረዳ ታገል የሚያስበው ስለሚጽፈው ግጥም ነው፡፡ አንዳንዴ እዚያው መሞነጫጨር ይጀምራል፡፡ “ለተንኮሉ አዳዲስ ሃሳቦች የሚመጡልኝና ልውጣ ልውጣ እያሉ የሚያስጨንቁኝ ክፍል ውስጥ ሆኜ አስተማሪ ማስረዳት ሲጀምር ነበር… ላጠና ደብተሬን ሳነሳማ የድርሰት ዛር ይሰፍርብኛል፡፡ ቀናተኛ ዛር!” ይላል ታገል፡፡
ታገል ቀልድ ይወዳል፡፡ ሁሉን ነገር ወደ ሳቅ መለወጥ ለታገል በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ ታገል ካለ ሳቅ አለ፡፡ አንዳንዴ በራሱም ላይ ይቀልዳል:: በ1979 ዓ.ም ታገል የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበር፡፡ ሰኔ 30 አካባቢ አገኘሁትና “ትምህርት እንዴት ነበር? አለፍክ?” አልኩት፡፡ “አዎ” አለኝ፡፡ ለማጣራት “ወደ ስንተኛ ክፍል?” አልኩት፡፡ “ከ10ኛ A ወደ 10ኛ B” አለና ረጅም ሳቅ አብረን ሳቅን፡፡
ከትምህርት ሁሉ የሂሳብ ትምህርት አይወድም ነበር ታገል፡፡ አንድ ጊዜ SOS ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ፣ የሂሳብ ፈተና ለመፈተን ወደ አዳራሽ ይገባል:: ፈታኟ ሴት መምህሩ ነበረች - ታውቀዋለች:: ፊት ነበር የተቀመጠው፡፡ የፈተና ወረቀት ታደለ፡፡ ፈተናው ተጀመረ፡፡ ታገል ጥያቄዎቹን ሲያያቸው የሚሰራቸው ዓይነት አልነበሩም - ከበዱት፡፡ የሚያውቃቸውን ጥያቄዎች ሰራ:: ቀሪዎቹን እንደነገሩ አጠቆረና ፈተናውን በጥቂት ደቂቃዎች አጠናቀቀ፡፡ ከዚያ በኋላ የጥያቄ ወረቀቱን በጀርባው ገለበጠና ይጽፋል - ይሰርዛል - ያስባል - ይጽፋል… ፈታኟ መምህርት ጥግ ላይ ቆማ ታገል የሚሰራውን ስታይ “ዛሬ እንዴት ጎበዝ ወጣው?” በማለት እየተገረመችና እየተጠራጠረች ወደ ታገል ዘንድ ሄደች፡፡ ቀረብ ብላ ስታይ ታገል የሚጽፈውና የሚሰርዘው ፈተናውን ሳይሆን ግጥም ነበር፡፡ ያን ወረቀት ቀማችውና ሌላ የፈተና ወረቀት ሰጠቺው፡፡ ያም ግጥም በዚያው ቀረ…
የዛሬ 31 ዓመት ስለ ታገል ያዘጋጀሁትን ቃለ ምልልስ የቋጨሁት ታገል ስለ ወደፊት ዓላማው የሰጠኝን መልስ በማስፈር ነበር፡፡ “የወደፊቱ ዓላማዬ፤ ከአበው ደራሲያን ሥራዎች በመማር የአጻጻፍ ስልቴን በማሻሻል ረጅም ልብ ወለድ ጽፌ፣ ለአንባብያን ለማቅረብና በትምህርቴም ገፍቼ፣ በእውቀት ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ለመድረስ ነው” ነበር ያለው ታገል፡፡ በርግጥም ይህንን ቃሉን ጠብቆ እስከ አሁን ድረስ ሰባት መጽሐፍትን  አሳትሟል፡፡ ከዚህ ሌላ በርካታ ግጥሞችን በተለያዩ መድረኮች አቅርቧል፡፡
አንዳንድ ነጥቦች በአዲሱ መጽሐፍ
በታገል አዲሱ የልብ ወለድ ድርሰቱ ዙሪያ ጥቂት ሃሳቦችን ለማቅረብ ወደድሁ፡፡ ታገል ሰይፉ በ1982 ዓ.ም የመጀመሪያ ድርሰቱን በ16 ዓመቱ “ፍቅር” በሚል ርእስ አሳትሞ፣ ከሀገራችን ደራሲያንና ገጣሚያን ዝርዝር (ሊስት) ውስጥ ስሙን አስመዘገበ፡፡ ከዚያ ወዲህ ስድስት መጽሐፍትን አሳትሟል፡፡ በነዚህ ድርሰቶቹ በርካታ ቁም ነገሮችን አስነብቦናል፡፡ የተለያዩ የአጻጻፍ ስልቶችንም አስተዋውቆናል፡፡  
አዲሱ የታገል ልብ ወለድ መጽሐፍ ርእስ “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሽ ቆር” የሚል ነው፡፡ ትርጉሙን በተመለከተ ወደ ኋላ ላይ እመለስበታለሁ፡፡ የዱሮ ደራሲዎች በመጽሐፎቻቸው መግቢያ ላይ “በዚህ ድርሰት ውስጥ ያሉ ገፀ ባህሪያትና ስሞቻቸው በገሀዱ ዓለም ያሉ ሰዎችን አይወክልም፡፡ ተመሳስሎ ቢገኝ ያጋጣሚ ጉዳይ ነው” የሚል ማሳሰቢያ ያስቀምጣሉ፡፡ ታገል ይህንን አላደረገም፡፡ ይሁን እንጂ የጻፈው “የፖለቲከ ስላቅ” በመሆኑ ከፖለቲከኞች ጋር ላለመጣላት በመጽሐፉ ውስጥ ላሉ ገፀ ባህሪያት በሙሉ ትርጉሙ የማይታወቅ፣ የተለየ ስም ሰጥቷቸዋል፡፡ ገፀ ባህሪያቱ ብቻ ሳይሆኑ የቦታ ስሞችም (መቼቱ) ከገሀዱ ዓለም የተለየ ስም ነው የተሰጣቸው:: ሌላው ቀርቶ መንግስታዊውን ጋዜጣ “ዘመን ጋዜጣ” ይላል እንጂ “አዲስ ዘመን ጋዜጣ” አይልም፡፡
ታገል ገፀ-ባህሪያቱን በምናባችን እንድንስላቸው አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡ ከሲታው ናኦሌ፣ ተቀምጦ የቆመ የሚመስለው ቀውላላው ጅማላ፣ እንቅልፋሟ እማማ ኩንዳሬ… በሰፈራችን የምናውቃቸው ዓይነት ናቸው፡፡ እማማ ኩንዳሬ ሌላም አይዘነጌ ባህሪ አላቸው:: እማማ ኩንዳሬ እንደ ስብሃት ገ/እግዚአብሔር አጋፋሪ እንደሻው ሞትን ይፈራሉ፡፡ አጋፋሪ ሞትን መፍራት ብቻ ሳይሆን ይሸሻሉ፡፡ እማማ ኩንዳሬ ግን አይሸሹም፡፡ ታገል አንድ ሰሞን ከእነ ጋሽ ስብሃት ጋር ይውል ነበር፡፡ እነ ጋሽ ስብሃት ስለ አጋፋሪ ሲያወሩ ብዙ ሰምቷል፡፡ አጋፋሪን በደንብ ያውቃቸዋል፡፡ እናም ለአጋፋሪ እንደሻው ተመሳሳይ ባህሪ ያላት “ውሽማ” ፈልጎላቸው እንዳይሆን ጠረጠርኩ - ሞት የሚፈሩ ሚስት!
ታገል በአዲሱ መጽሐፉ በርካታ ስላቆችን አስነብቦናል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ዩኒቨርስቲ ረብሻ መቀስቀሱን ይነግረናል፡፡ ያን ረብሻ የተቀሰቀሰው ደግሞ የአንድ ተማሪ የአንድ እግር ጫማ ከዶርሙ በመጥፋቱ ምክንያት ነው ይለናል፡፡ በዚህ ረብሻ ሰበብ 27 ተማሪዎች ይቆስላሉ፣ አራት ተማሪዎች ይሞታሉ፡፡ ለሳይንስና ምርምር ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎች፣ የአንድ እግር ጫማ ጠፋ ብለው ረብሻ መቀስቀሳቸው ትልቅ ፌዝ ነው፡፡ ታገል ሊነግረን የፈለገው ይህንን ይመስለኛል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶችን” በዩኔስኮ ማስመዝገብ እንደ ፋሽን የተያያዝነው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ያልተዋጠለት ታገል፤በዚሁ ድርሰቱ ውስጥ “የሙኢ ማህበረሰብ” ብሎ የሰየማቸው የቡድን ገፀ-ባህሪያት “ዓመታዊ ጭቃ የመብላት” ባህላቸው በዩኔስኮ “የማይዳሰሱ የባህል ቅርስ” ተደርጎ እንዲመዘገብ የሚያደርጉትን ጥረት በስላቅ ይነግረናል፡፡
ታገል “ስም አይጠሬው ፕሬዝዳንት” የሚላቸው ገፀ-ባህሪ አሉ፡፡ እኒህ ገፀ-ባህሪ በተሾሙበት እለት ባደረጉት ንግግር፤ “ሀገራችን ማርና ወተት ወደምታዘንብበት የብልጽግና ዘመን እስክትደርስ ድረስ ፈገግ አልልም” የሚል ቃል ገብተዋል፡፡ ከዓመታት በኋላ አንድ ነፃ ጋዜጣ፣ የስም አይጠሬውን ፕሬዚዳንት በሳቅና በፈገግታ የተሞላ ፎቶ ግራፍ በፊት ለፊት ገፁ ይዞ ይወጣል፡፡ ይህም ሁኔታ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ ንትርክ ይቀሰቅሳል:: የስም አይጠሬው ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች የሆኑ “ካድሬዎች” ይህንን ሁኔታ ለማስተባበል የሚያቀርቧቸው አስተያየቶች፤ ታዋቂው ደራሲ ጆርጅ ኦርዌል “የእንስሳት እድር” (Animal Farm) በሚለው መጽሐፉ ላይ ያቀረበው ዓይነት ቧልት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አንዱ ካድሬ “ስም አይጠሬው ፕሬዝዳንት ሀገራችን ማርና ወተት ወደምታዘንብበት የብልጽግና ዘመን እስክትደርስ ድረስ ፈገግ አልልም ቢሉም፤ ህዝብን ወክለው በማይገኙበት ስፍራ ግን ፈገግ የማለት መብት አላቸው” በማለት የመከራከሪያ ሀሳብ ማቅረቡን ያሳየናል ታገል፡፡ ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ መንግስታዊው ጋዜጣ በበኩሉ፤ “በሸፍጠኞች ውዥንብር የፕሬዝዳንቱ ግንባር አይፈታም” በሚል ርዕሰ አንቀጽ እስከ መጻፍ መድረሱን ያስነብበናል፡፡ ነፃ የግል ጋዜጣው ደግሞ በቀጣይ ሳምንት እትሙ “ፕሬዝዳንቱ አመኑ!” በማለት ርእሰ አንቀጽ ይጽፋል፡፡ ፓርቲው በጉዳዩ ላይ ለመምከር 37 ቀናት ጉባዔ ይቀመጣል… ይሄ ሁሉ ፌዝ ነው፣ ቧልት ነው፣ ምፀት ነው…
ዋነኛው የታገል ስላቅ የመጽሐፉ ርእስ ባደረገው ቃል ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ የአማርኛ ሶፍትዌር መምጣት በጀመረበት ሰሞን፣ በአማርኛ የተጻፈ ቃል ወደ ሌላ ፎንት ይቀየርና ታገል ለመጽሐፉ ርዕስነት የመረጠው ዓይነት “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሸ ቆር” የሚል ዓይነት ቃል ተደጋግሞ ይታይ ነበር፡፡ ይህም የኮምፒዩተር “error” ተደጋግሞ ይስተዋል ነበር፡፡ ታገል “ስም አይጠሬ” ያላቸው ፕሬዝዳንት ባደረጉት አንድ ንግግር፤ የጋዜጣ ህትመት ውስጥ “ብስጦሽ ቁዋጭ ቁዋጣሸ ቆር” የሚለው ቃል ገብቶ ይገኛል፡፡ በዚህም ቃል ምክንያት የአንድ መ/ቤት ሰራተኞች ስብሰባ ተቀምጠው ሲነታረኩና ጊዜያቸውን ሲያባክኑ ያሳየናል ታገል፡፡ ይህንን የኮምፒዩተር “error” አንዱ ካድሬ “ምስጢራዊ መልእክት ነው” ብሎ በሚፈልገው መልኩ ሲያብራራ፣ ሌላኛው ካድሬ ደግሞ ከአንድ ብሄር ቋንቋ ጋር በማመሳሰል የራሱን ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ሌላው ይነሳና፤ “የኮምፒዩተር ‘error’ ነው፡፡ ኮምፒዩተር ሰው ሰራሽ ነው፡፡ በተራ ሰውና በፕሬዝዳንት ንግግር መካከል ያለውን ልዩነት አያውቅም” በማለት ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ የሚሰማው የለም… በዚህ መልኩ ጭቅጭቁ ይቀጥላል፡፡
በታገል አዲሱ መጽሐፍ ውስጥ አልፎ አልፎ መዘናጋት የወለዳቸው ህፀፆችን አስተውያለሁ:: ለምሳሌ፡- ታገል የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ በ1997 አካባቢ እንደጻፈው፣ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ሲናገር የሰማሁ ይመስለኛል፡፡ ታገል “ባለ ራዕዩ መሪ” የሚለውንና “በቋንቋችሁ ካልተናገረ መልስ አትስጡ” የሚለውን ሃሳብ፣ በዚሁ መጽሐፍ ተጠቅሟል፡፡ ይሁን እንጂ “ባለ ራዕዩ መሪ” የሚለውን አነጋገር የሰማነው ግን አቶ መለስ ከሞቱ በኋላ ሲሆን፤ “በቋንቋችሁ ካልተናገረ መልስ አትስጡ” የሚለውን የአንድ ፖለቲከኛ ንግግር የሰማነው ደግሞ በቅርብ ዓመታት ነው፡፡ ታገል በ1997 ያዘጋጀውን ረቂቅ ሳያርም አሳትሞት ከሆነ፣ ጥሩ ትንቢት ይሆን ነበር፡፡ አርሞት ከሆነ ግን ይህንን ባያደርግ ጥሩ ነበር፡፡
የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና ሐያሲያን እንደሚሉት ከሆነ፣ የአንድ ደራሲ ሚና ታሪክን መንገር (story teller) እንጂ ሰባኪነት አይደለም:: ይህንን ገዢ ሃሳብ ይዘን ወደ ታገል መጽሐፍ ስንመለስ፤ በገጽ 71 ላይ ጅባካ የተባለውን ገፀ-ባህሪ “እንደ ጅባካ ያሉ የብሔር ልክፍተኞችን…” በማለት ፍርድ ይሰጣል ደራሲው፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ የተዘነጉ ነገሮች አሉ፡፡ በገፀ-ባህሪያቱ ተግባርም ሆነ ስነ-ምግባር ላይ መፍረድ የደራሲው ሳይሆን የአንባቢው ኃላፊነት ነው:: የደራሲው ኃላፊነት የእያንዳንዱን ገፀ-ባህሪ ድርጊት፣ አስተሳሰብ፣ አመለካከት፣… ማሳየት እንጂ ፍርድ መስጠት አይደለም፡፡ ይህንን ቢያየው መልካም ነው፡፡
በአጠቃላይ የታገልን መጽሐፍ ተራ አንባቢ የሚያነበው መስሎ አይታየኝም፡፡ ተራ አንባቢ ለማንበብ ከጀመረ ከ10 ገጽ በላይ መሄድ አይችልም የሚል ግምት አለኝ፡፡ ምክንያቱም ድርሰቱ ቧልታይ የሚመስል የፖለቲካ ስላቅ ነው፡፡ ከእንስሳት እድር (Animal Farm) እና ከዶን ኪሾት (Don Quixote) ጋር ተመሳሳይ ዘውግ ውስጥ የሚመደብ ድርሰት ነው፡፡ ለበሳል አንባቢ ግን ማንበብ ከተጀመረ የማይቀመጥ መጽሐፍ ነው፡፡ ብዕርህ ይባረክ፤ ወዳጄ ታገል!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 7803 times