Monday, 06 January 2020 00:00

የ4ቢ. ብር የዘይት ፋብሪካ በመዲናዋ ሊገነባ ነው

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(3 votes)

  • ኢትዮጵያ ለዘይት ከምታወጣው የውጭ ምንዛሬ 25 በመቶውን ያድናል
           • ፋብሪካው ስራ ሲጀምር ለ1ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል
                 
            በሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲ ድርጅት በ4ቢ ብር ወጪ በመዲናዋ እንደሚገነባ የተነገረለት “ሸገር” የዘይት ፋብሪካ አገሪቱ ለዘይት ግዢ ከምታወጣው የውጭ ምንዛሪ 25 በመቶውን ያድናል ተባለ፡፡ በቅርቡም ግንባታው እንደሚጀመር የሚድሮክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች ቢሮ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አብነት ገብረመስቀል ገለፁ፡፡ በ70ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈው የዘይት ፋብሪካው ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ አካባቢ ከፋርማኪዩር መድሃኒት ፋብሪካ ጐን በኩታ ገጠምነት በቅርቡ ግንባታው እንደሚጀመር ጠቁመዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናገረ የመጣውን የኑሮ ውድነትና የማህበረሰቡን ችግር የተገነዘቡት የሚድሮክ ኢትዮጵያ ሊቀመንበርና ባለሀብት ሼህ መሐመድ አሊ አላሙዲ የህብረተሰቡን ችግር ለመቅረፍ፣ ኢትዮጵያ ለዘይት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስና አገራችን እያስተዋወቀች ያለውን አገር በቀል የምጣኔ ሀብት ለውጥ ትግበራ ለመደገፍ ፋብሪካው እንዲገነባ መወሰናቸውን አቶ አብነት አብራርተዋል፡፡
ለአንድ ሺ ሰዎች ገደማ የስራ እድል ይፈጥራል የተባለው የዘይት ፋብሪካው፤ ኢትዮጵያ  በአማካይ በዓመት የምታወጣውን 600ሚ. የአሜሪካ ዶላር 25 በመቶ ያድናል ተብሏል፡፡
እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ከጣሊያን የሚመጡለት ሸገር የዘይት ፋብሪካ በአቶ ጀማል አህመድ መሪነት የሚሰራ ሲሆን ግንባታው አንድ አመት ተኩል ያህል እንደሚወስድና የማምረት አቅሙም ከፍተኛ እንደሆነ ያብራሩት አቶ አብነት፤ ለዚሁ ስራ የቴክኒክ እገዛና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርጉ የውጭ ኤክስፐርቶች አገር ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡ ሚድሮክ ኢትዮጵያ በተመሳሳይ የህዝቡን የዳቦ ፍላጐት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማርካት በቀን 1.6 ሚ ዳቦ ማምረት የሚችል የዳቦ ፋብሪካ ፕሮጀክት ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት የዳቦ ፋብሪካው የተለያዩ ማሽኖች ከውጭ እያስገባና ፋብሪካው እንዲሁም የፋብሪካው ስትራክቸር እየቆመ ስለመሆኑ የገለፁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከሁለት ወር በኋላ ማምረት እንደሚጀምርም ተናግረዋል፡፡
የዳቦውን አመራረት፣ ትክክለኛ ግራምና ጥራት የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች ከውጭ መምጣታቸውንና የእኛ አገር ባለሙያዎች በትክክለኛ ብቃት ላይ እስኪደርሱ ባለሙያዎቹ ለ1 ዓመት በስራ ላይ እንደሚቆዩ ዋና ስራ አስፈፃሚው ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Read 9988 times