Print this page
Saturday, 28 December 2019 14:01

ዳሸን ባንክ የ100 ሚ.ብር ማህበራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

       በኢትዮጵያ ዘመናዊ የባንክ አሰራሮችን በመጀመር ግንባር ቀደም እንደሆነ የሚነገርለት ዳሽን ባንክ በ100 ሚ.ብር የሚተገበር የማህበራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ከትላንት በስቲያ ይፋ አደረገ።
‹‹የስራ ዕድል ፈጠራ፣ ድህነት ቅነሳና አካታች እድገት፡- የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በመንግሥት ለተቀየሰው የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅድ ትግበራ፣ የግሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚና›› በሚል ርዕስ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የግማሽ ቀን የፓናል ውይይትም አካሂዷል፡፡
ባንኩ ሐሙስ ረፋድ ይፋ ያደረገው ‹‹የኢትዮጵያ ታለንት ፓወር ሴሪስ›› የተሰኘ ይኸው ፕሮጀክት፤ ስራ ፈጠራን በማበረታትና ክህሎት ላላቸው ዜጎች የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠት፣  የስራ አጥነትን ለመቀነስ እንዲሁም ድህነትን ለማስወገድ የሚደረገውን አገራዊ እንቅስቃሴ በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለመወጣት ያስችለዋል ብለዋል - የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ፡፡
ባንኩ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳር፣ በመቀሌ፣ በድሬዳዋ፣ በሀዋሳና በአዳማ በሚተገብረው በዚህ ፕሮጀክት፤ በእያንዳንዱ ከተማ በመጀመሪያው ዙር አንድ አንድ ሺህ ሰልጣኞች ተጠቃሚ ይሆናሉ - ስልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የቢዝነስ ክለብ ይመሠርታሉ፣ ትልቅ ደረጃ እስኪደርስ የፋይናንስ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሏል፡፡  
ፕሮጀክቱ በስድስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ላይ የሚያጠነጥነው ሲሆን እነሱም፡- የሥራ ዕድል ፈጠራ ስልጠና፣ የጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አቅም ግንባታ፣ የከፍተኛ ትምህርት የፋይናንስ ድጋፍ መርሃ ግብር፣ የፋይናንስ ተደራሽነት መርሃ ግብር፣ የቢዝነስ ክለብ ምስረታ፣ የገበያ ትስስርና የእሴት ሰንሰለት የፋይናንስ ድጋፍ ናቸው፡፡
ባንኩ ከዚሁ ጎን ለጎን የስራ ፈጠራና ቢዝነስ ክህሎት ላይ የሚያጠነጥን ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም የስራ ፈጠራ ክህሎት ውድድር እየተደረገ ለአሸናፊዎች የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከትና ከተወዳዳሪዎች መካከል አሸናፊ ሀሳብ ላቀረቡ ስራ ፈጣሪዎች ደግሞ ወደፊት ሊጀምሩ ላሰቡት የንግድ ሥራ አስፈላጊው የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡
ለፕሮጀክቱ መተግበሪያ የሚሆን ፋይናንስ፣ የስልጠና ሞጁል፣ አማካሪ ድርጅትና አሰልጣኞችን አዘጋጅቶ ያጠናቀቀው ባንኩ፤ ፕሮጀክቱን ይፋ ባደረገ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከስድስቱ በአንዱ ከተማ የመጀመሪያውን ስልጠናና የቴሌቪዥን ፕሮግራሙን እንደሚጀምር የባንኩ ሃላፊዎች በኢንተር ኮንትኔንታል ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ዳሽን ባንክ በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረውን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድ ትግበራ ለመደገፍ በግሉ ተነሳሽነት የጀመረው ይህ ፕሮጀክት፤ በርካታ የስራ ፈጠራ ስልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎችን ማዳረስ ባይችልም ለሌሎች የግሉ የፋይናንስ ዘርፎች ምሳሌ በመሆን ተነሳሽነትን መፍጠር እንደሚችልም ገልጿል፡፡

Read 3429 times