Monday, 30 December 2019 00:00

ተስፋዋ የበዛ አገር!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

   ‹‹ተስፋ››፣ በባዶ ሜዳ አይመጣም፡፡ የመሻሻል አላማና ጥረት፣ የስኬት ጅምርና የስልጣኔ ታሪክ፣ እምቅ አቅምና የከፍታ ‹‹እድል›› … በእውን የሚታይ ከሆነ፣ በፈተና ጊዜም እንኳ፣ ተስፋ አይሞትም፡፡
በዚህ በዚህ፣ ኢትዮጵያ ከጥንት እስከ ዛሬ፣ ለበርካታ ሺ ዓመታት፣ ‹‹የተስፋ ምድር›› ሆና የዘለቀች አገር ናት ማለት ይቻላል፡፡
ከ2 ሺ ዓመታት በፊት፣ የግብፅ፣ የእስራኤልና የግሪክ ፀሐፊዎችና መሪዎች፣ ኢትዮጵያን በእጅጉ ከፍ አድርገው፣ ትልቅነቷን አክብረው ተርከዋል፡፡ የሃያልነትና የብልፅግና፣ የጤንነትና የጥንካሬ፣ የመልካምነትና የቅንነት አገር እንደሆነችም በየፊናቸው ጽፈዋል፡፡
ከ1500 ዓመታት በፊት፣ የወቅቱ የዓለም ሃያል ገዥ በነበረው በሮም መንግስት ዘንድ ሳይቀር፣ እንደ ዋና የሰላምና የፍትህ አለኝታ የተቆጠረችና፤ ተስፋ የተጣለባት አገር፣ ሌላ ሳትሆን ኢትዮጵያ ናት፡፡
በርካታ የሃይማኖት መሪዎች (የአይሁድና የክርስትና ሰባኪዎች)፣ ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር መሆኗን የመፃፋቸውን ያህል፣ ነብዩ መሐመድም፣ ኢትዮጵያ ከበደልና ከጥቃት የምትታደግ እንደሆነች መስክረዋል። ለፍትህ የቀናች፣ መጠጊያ ከለላ የምትሆን አገር መሆኗን በመጥቀስ ነው ተስፋ ያሳደሩባት፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የዛሬ 1000 ዓመት ገደማ በግብፅና በሌሎች የሰሜን አፍሪካ አካባቢዎች የነበሩ ታሪክ ፀሐፊዎችና የሀይማኖት መሪዎች፣ ኢትዮጵያ ‹‹ዋና ተስፋቸው›› እንደሆነች ገልፀዋል፡፡ ከመከራ ታድነናለች ብለዋል፡፡  
ኢትዮጵያ፣ ‹‹ህግና ስርዓት የተከበረባት››፣ ‹‹በጽኑ መሰረት ላይ የቆመችና የማትናወጥ አገር›› መሆኗን ምንኛ ያምኑ እንደነበር፣ በወቅቱ የተፃፉ ሰነዶች ይመሰክራሉ፡፡
ኢትዮጵያ፣ የሙሴ ህግ (የሙሴ ጽላትና ታቦት) ጠባቂ፣ የንጉስ ዳዊት መንበረ መንግስት ወራሽ፣ እንዲሁም የንጉስ ሰለሞን ቀለበት ባለቤት ናት ተብሎ የተመዘገበው፣ በግብጽና በሌሎች የሰሜን አፍሪካ ፀሐፊዎችና መሪዎች ነው (አንድ ሺ ዓመታትን ባስቆጠሩ ሰነዶች)፡፡
ከዚሁ ጐን ለጐን፣ ከስፔንና ከጣሊያን እስከ እንግሊዝና ጀርመን፣ በአውሮፓ ምድር ኢትዮጵያን አግንነውና አክብረው የሚያሳዩ ጽሑፎች ለበርካታ ምዕተ ዓመታት ሲናኙ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የትልቅና የክቡር ሚስጥር መገኛ፣ የጥንካሬና የብልጽግና ማህፀን፣ የፍትህና የስነምግባር ማዕከል፣ እንደ ሃያልነቷም፣ የዓለም ሰላም አለኝታ፣ እንደሆነች የሚገልፁ ታሪኮች፣ በአውሮፓ በብዛት ተሰራጭተዋል፡፡
ከቀዳሚዎቹ የስልጣን ፈር ቀዳጅ ፋናዎች መካከል አንዷ የነበረችው ኢትዮጵያ፣ ቀስ በቀስ ብርሃኗ እየደበዘዘ፣ እየወደቀችና እየተነሳች የኋሊት ከቀረች በኋላም እንኳ፣ በርካታ የውጭው አለም ፀሐፊዎችና የባህር ማዶ መሪዎች፣ በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው ተስፋ አልተዳፈነም፡፡
እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥም፣ በየዘመናቱ ወደ ስልጣኔ ለመመለስ የሚተጉ፣ ከውድቀት ተነስተው ወደ ከፍታ ለማቅናት የሚጣጣሩ፣ ተስፋ የማይቆርጡ ኢትዮጵያዊያን አልጠፉም፡፡ የዚያኑ ያህልም የስልጣኔና የስኬት ጅምሮችን፣ በእውን ሰርተው አሳይተዋል፡፡ የያኔ ስኬቶች፣ ዛሬም ድረስ፣ ምልከታቸው አልጠፋም፡፡ ከመውደቅና መነሳት፣ ከውጣ ውረድ፣ ከጦርነትና ከቃጠሎ ብዛት፣ በየመሃሉም የስልጣኔ ጅምር እየተዘነጋ፣ ብዙ ስኬቶች ቢወድሙም፣ በእድሜ ብዛት ቢፈራርሱና ቢጠፋም፣ ቀሪዎቹ ቅርሶች፣ ብዙ ነገር ይመሰክራሉ፡፡
ከየሐ እና ከአክሱም፣ ላሊበላና ጐንደርን አልፎ፣ እስከ ሐረር ድረስ…እልፍ የስልጣኔና የስኬት ቅርሶችን ማየትና ማስተዋል የቻለ ሰው፣ በኢትዮጵያ ላይ ተስፋ ባይቆርጥ አይገርምም፡፡
የገዳ ስርዓት፣ ክብረ ነገስት፣ ለፍትህ ትልቅ ክብር የመስጠት ቅንነት፣ “በህግ አምላክ” ብሎ በደልን የሚያስቆምና የሚክስ ህጋዊ ፍትህን የማግኘት ምኞት፣ እነዚህና ሌሎች በርካታ የስልጣኔ ጅምሮች እንዲሁ በዘፈቀደና በአጋጣሚ የሚከሰቱ ጉዳዮች አይደሉም፡፡
ስርዓት ያለው አስተዳደር፣ ህጋዊ ስልጣን ያለው መንግስት፣ ፍትህን የሚፈጽም ህግ… ያለእነዚህ መሰረታዊ ሃሳቦችና ጥረቶች፣ ‹‹አገር፣ ሰላም እና ሰርቶ መኖር›› የሚባል ነገር አይኖርም፡፡
እነዚህ ሃሳቦችና ጥረቶች ከሌሉ፣ የነፃነት፣ የብልጽግናና የስልጣኔ ተስፋ ሊኖር አይችልም፡፡
‹‹አገር፣ መንግስት እና ህግ›› የሚባል ነገር ከሌለ፣ ‹‹ነፃነት የሚከበርባት አገር፣›› ‹‹ነፃነትን የሚያስከብርና ፍትህን የሚፈጽም ህግ››፣ ይህንንም ‹‹በህጋዊ መንገድ የሚያስፈጽም ለህግ ተገዢ የሆነ መንግስት›› እንዲኖር መመኘት… እንዲሻሻልም መጣር አይቻልም፡፡ የሶማሊያን የቅርብ ዓመታት ታሪክ፣ የሊቢያን ሁኔታ፣ እንዲሁም የነየመንን ትርምስ ማየት በቂ ነው፡፡
‹‹አገር፣ መንግስትና ህግ›› ሲኖር ነው፣ በስልጣኔ ጐዳና እንዲሻሻሉ እየጣርን፣ ‹‹የነፃነት አገር፣ የፍትህ ህግ፣ እንዲሁም ለህግ የበላይነት የተገዛ መንግስት›› እንዲሆኑ ማድረግ የምንችለው፡፡
ኢትዮጵያ ለብዙ ምዕተ ዓመታት፣ ‹‹ከአስተዳደር ስርዓት፣ ከመንግስትና ከህግ›› ጋር ሳትራራቅ የዘለቀች አገር መሆኗ፣ ትልቅና ክቡር መንፈሳዊ ቅርስ ነው፡፡ ታዲያ፣ በዚህ አገር ላይ እንዴት ተስፋ ይቆረጣል?
በዓለም፣ በግዝፈቱ እስከ ዛሬ ተወዳዳሪ የሌለው፣ ከአለት ቆርጠው ውብ ሐውልት የቀረፁ ጥበበኛ ሰዎች የነበሩባት ድንቅ አገር እንደሆነች የምናውቀው፣ በጥንታዊ ሰነዶች ምስክርነት አይደለም፡፡ ዛሬም ድረስ በእውን መሬት ላይ ተጋድሞ ይታያል - ሃውልቱ፡፡
በአለም፣ በግዝፈቱ አቻ የሌለው ረዥም የሰው ሃውልት፣ ከብረት የቀረፁ ባለሙያዎች የነበሩባት አገር፣ ላሊበላና ጐንደርን፣ እንዲሁም ሐረርን፣ በየዘመኑ በጥረትና በጥበብ ድንቅ ስኬትን የተቀዳጁ በርካታ ጀግና ሰዎች የነበሩባት አገር እንደሆነች በግልጽ እየታየ፣ እንዴት በዚህች አገር ተስፋ ይቆረጣል?
ኢትዮጵያ የተስፋ ምድር የሆነችው፣ እውነትም ያለ ምክንያት አይደለም፡፡
ብዙ የውጭ መንግስታት፣ የባህር ማዶ አዋቂዎችና ፀሐፊዎችም፣ በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተስፋ የሚያድርባቸው፣ በባዶ ስሜት አይደለም፡፡
በጥበብና በትጋት የሚጥሩ ኢትዮጵያውያን እስካሉ ድረስ፣ መቼም ቢሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ ስልጣኔ፣ ወደ ብልጽግና፣ ወደ ከፍታ መገስገስ እንደምትችል፣ ከጥንት ጀምሮ በተደጋጋሚ ታይቷልና ነው፡፡
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ውስጥ እምቅ አቅም አለ፡፡ በመቶ ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ቢበዛ አስቡት፡፡ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ ከህንድና ከቻይና ጋር አፍሪካን የምታገናኝ ቁልፍ ድልድይ የመሆን ከፍተኛ እድል ያላት አገር፣ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የአለም አብዛኛው ህዝብና አብዛኛው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚገኝበትና እየተጧጧፈ በሚሄድበት አስገራሚ ቦታና ዘመን ላይ የምትገኝ ናት ኢትዮጵያ፡፡
ካወቅንበትና በጥበብ ከተጋን፣ የእስከዛሬ ፈጣን የስልጣኔና የብልጽግና ጉዞዎችን ሁሉ የሚያስንቅ፣ አስደናቂ የከፍታ ግስጋሴ፣ በአገራችን እውን እንዲሆን ማድረግ እንችላለን፡፡
በጥንትና በየዘመኑ በሕይወት የነበሩ በርካታ ጥበበኛና ታታሪ ኢትዮጵያውያን፣ ስልጣኔንን እውን አድርገው ከነበረ፣ ዛሬ እንዴት ያቅተናል? እንደማያቅተን ግልጽ ነው፡፡
ብዙ የውጭ አዋቂዎችና መሪዎችም፣ ይህንን ያውቃሉ፡፡ የስኬት ጅምሮችን በማየት እውቅና ይሰጣሉ፡፡
በተስፋም ሽልማትና ድጋፍ ያበረክታሉ፡፡ የኖቤል ሽልማት አንዱ ምሳሌ ነው  - የስኬትና የተስፋ ሽልማት፡፡
የIMF እና የአለም ባንክ፣ የነ አሜሪካና የነ አውሮፓ የብድርና የእርዳታ ድጋፍም ሌላው ምሳሌ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ያላቸውን ተስፋ ያሳያል፡፡ ደግሞም የተስፋ ምድር ናት፡፡
ተስፋን ወደ እውን ስኬት ለማድረስ በጥበብ መትጋት፣ የኛ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ነው፡፡

Read 9803 times